Print this page
Saturday, 11 April 2020 14:30

የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ኢንፌክሽንና እርግዝና፤

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

             በኢትዮጲያ የማህጸንና ፅንስ ሐኪሞች ማህበር የተዘጋጀ

               የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ከኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ጋር በመተባበር ኮቪድ-19 የተሰኘው ወረርሽኝ በተለይም በእርግዝና ላይ ባሉ እናቶች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ሕመም በተለየ የሚመለከት መረጃ አዘጋጅቶ ለንባ ብሎአል፡፡ ይህ እትም በበራሪ ወረቀቱ ላይ የሰፈረውን ቁም ነገር ለአንባቢ ይድረስ በሚል አጠር አጠር አድርጎ ለንባብ አቅርቦታል፡፡ ይህ መረጃ በVERSION 01/ESOG March 27, 2020/ ለንባብ ይፋ የሆነ ነው፡፡
1. የኮሮና ቫይረስ በነፍሰ ጡር እናቶች ላይ ምን ያስከትላል?
እስከ አሁን ባለው መረጃ መሰረት የነፍሰ ጡር እናቶች ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በተለየ ሁኔታ ከባድ የሆነ የጤና እክል አልታየባቸውም። ሆኖም አዲስ ቫይረስ ስለሆነ በሽታው እንዴት የነፍሰ ጡር  ጤንነትን እንደሚያውክ ገና በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። አብዛኛው የነፍሰ ጡር እናቶች ግን ቀላል ወይም መለስተኛ የሆነ የጉንፋን በሽታን የሚመስል ምልክት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በቫይረሱ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክል የሚታይባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አዛውንቶች፣ የተዳከመ የበሽታ መከላከል አቅም ያላቸው ወይም የሰነበተና የታወቀ በሽታ ያላቸው ናቸው።
በእርግዝና ጊዜ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም ስለሚቀንስ ፤ አንድ ነፍሰ ጡር ሴት በትንፋሽ ለሚተላለፉ የበሽታ አምጪ ቫይረስ  ያላት ተጋላጭነት እጅግ ከፍ ያለ ነው። ነፍሰ ጡሯ የሰነበተና የታወቀ በሽታ ለምሳሌ የአስም ወይም የስኳር ህመምተኛ ከሆነች፤ ኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክል ሊያስከትልባት ይችላል።
2. የነፍሰ ጡር እናት በምርመራ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ህመምተኛ ከሆነች፤ ጽንሱ ላይ ምን ሊከሰት ይችላል?
የኮሮና ቫይረስ አዲስ የበሽታ አምጪ ህዋስ በመሆኑ ባህሪው ገና ያልታወቀ ፤ ከፍተኛ ምርምር  እየተደረገበት ያለ ቫይረስ ነው። እስከ አሁን ያሉት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ግን፤ ቫይረሱ ውርጃን ስለማስከሰቱ ወይም እድገት ላይ ወዳለው ሽል ስለመተላለፉ የሚያሳይ መረጃ የለም። ስለዚህ ተጨማሪ መረጃ እስኪገኝ ድረስ የነፍሰ ጡር ሴት የኮሮና ቫይረስ ህመምተኛ ከሆነች ፤ ልጇ ላይ የአፈጣጠር ችግር የመኖሩ እድል ዝቅተኛ ነው ማለት ይቻላል።
3. የነፍሰ ጡር እናት የኮሮና ቫይረስ ህመምተኛ ከሆነች የመውለጃ ጊዜዋ ሳይደርስ ምጥ ሊጀምራት ይችላል?
ከዚህ በፊት የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በቫይረስ የሚመጡ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክ ሽኖች ነፍሰጡር ሴትን ጊዜው ላልደረሰ ምጥ ተጋላጭ ያደርጓታል፡፡  ነገር ግን ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ስለሚችል ጊዜውን ያልጠበቀ ምጥ የሚያሳይ አስተማማኝ የሆነ ሳይንሳዊ መረጃን መጠበቅ አስፈላጊ ነው።
4. የኮሮና ቫይረስ መድሐኒት አለውን?
በአሁኑ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ምንም አይነት የተረጋገጠ ህክምና የለውም። እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስ የሚከላከል ክትባት አልተገኘም። ሆኖም  የኮሮና ቫይረስ መድሐኒት ወይም ክትባት ለማግኘት የሚሰሩ ጥናቶች በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።  
5. የነፍሰ ጡር እናት የኮሮና ቫይረስ እንዳይዛት ምን ማድረግ አለባት?
እጅን በሳሙናና በውሀ(ቢያንስ ለሃያ ሰኮንድ ያህል) ደጋግሞ መታጠብ።  በተለይ ወደ ስራ ቦታ ወይም ወደ ቤት በሚገባበት ጊዜ እጅን በሳሙና መታጠብ ዋነኛው የ ኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴ ነው።
ሳሙናና ውሀ በማይኖርበት ጊዜ ከአልኮሆል በተዘጋጀ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር) መጠቀም፤
ንጹህ ባልሆነ እጅ አይን፣ አፍንጫና አፍን አለመንካት፤
በምታስልበት ወይም በምታስነጥስበት ጊዜ አፍና አፍንጫን በ ክንድ ወይም በመሐረብ መሸፈን፤ በሳል ወይም በማስነጠስ ጊዜ በእጅ አለመሸፈን።
ጥቅም ላይ የዋለ የሶፍት ወረቀት ክዳን ባለው የቆሻሻ መጣያ ውስጥ በመጣል እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ፤
የኮሮና ቫይረስ ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች በሁለት የአዋቂ እርምጃ ውስጥ አለመሆን፤
ከተቻለ ስራን ቤት ውስጥ ሆኖ መስራት፤
ማህበረሰባዊ ግንኙነቶችን መቀነስ፤ ለምሳሌ ከጎረቤቶች ጋር ቡና መጠጣት፣ ወደ ምግብ ቤቶችና ቲያትር ቤቶች ከመሄድ መቆጠብ፤
ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች አለመሆን፤
ወደ ቤት የሚመጡ እንግዶችን፣ ጓደኞችንና ቤተዘመዶችን መቀነስ፤
6. የነፍሰ ጡር እናት መጓጓዣ (ትራንስፖርት) ስትጠቀም እንዴት መሆን አለበት?
በጣም አስፈላጊ  ካልሆነ በስተቀር ማንኛውንም አይነት ጉዞ ማድረግ ለኮሮና ቫይረስ ያለውን ተጋላጭነትን ይጨምራል።
ከአገር ውጭ ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ነፍሰ ጡር ሴቶች ለ14 ቀን በተለየ ሆቴሎች ተለይተው የሚቆዩ ሲሆን፤ በቆይታቸው ጊዜ ለዚህ ተብሎ በተዘጋጁ የህክምና ቦታዎች የእርግዝና ክትትል እና የወሊድ አገልግሎት ያገኛሉ።
በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር በቤት ውስጥ በመሆን፤ በህዝብ ትራንስፖርት መንቀሳቀስን መቀነስ ተገቢ ነው።
7. አንድ ነፍሰ ጡር እናት የኮሮና ቫይረስ ምልክቶችን ካሳየች ወይም ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ ከሆነች ምን ማድረግ አለባት?
አንድ ነፍሰ ጡር ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን(ትኩሳት)፣ አዲስ የተከሰተ የማያቋርጥ ሳል ወይም የመተንፈስ ችግር ካላት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ወደተዘጋጁት ስልክ ቁጥሮች ማለትም ወደ 8335 ወይም 952 በመደወል የጤና ባለሙያዎችን ምክርና ህክምና አገልግሎት ማግኘት ትችላለች።
ካልሆነም የአፍ እና የአፍንጫ ጭንብል በማድረግ አቅራቢያዋ ወዳለው የጤና ተቋም የግል በሆነ የመጓጓዣ መኪና ወይንም ሌላ ከህብረተሰቡ ጋር ንክኪ በሚቀንስ የማጓጓዣ መንገድ በመጠቀም እንድትመጣ ይመከራል። ጤና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲደረግላት ከመከሩ፤ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ይደረግላታል።
8. አንድ ነፍሰጡር የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዴት ማድረግ ትችላልች?
የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማድረጊያ መስፈርቶች በፍጥነት እየተቀየሩ ይገኛሉ።
ጤና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲደረግላት ከመከሩ፤ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ይደረግላታል። የምርመራውም ሂደት እንደማንኛውም ነፍሰጡር ያልሆነ ግለሰብ ነው። ምርመራውንም ለማድረግ ናሙና ከአፍና አፍንጫ ይወሰዳል። እንደአስፈላጊነቱም በማሳል የአክታ ናሙና እንድትሰጥ ልትጠየቅ ትችላልች።  
9. ከኮሮና ቫይረስ ያገገመች ነፍሰጡር  ምን አይነት ህክምና/ ክትትል ይደረግላታል?
አንዲት ነፍሰጡር ሴት ከኮሮና ቫይረስ ህመም ካገገመች 14 ቀን በኋላ ለጥንቃቄ ሲባል የአልትራሳውንድ ምርመራ ይደረግላታል፡፡ ይህም የጽንሱን ጤንነት ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡
ነገር ግን ወደፊት የሚወጡ ተጨማሪ ሳይንሳዊ መረጃዎች በማገገሚያ ወቅት በጽንሱ ላይ የሚኖር ጉዳት የሚያሳዩ ከሆነ ከ 14 ቀን ባነሰ ቀጠሮ የጽንሱን ጤንነት ማረጋገጥ የተሻለ ይሆናል፡፡
አንድ ነፍሰጡር ሴት ምጥ ከመምጣቱ በፊት ባሉት ጊዜያት ከህመሟ ካገገመችና ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆኗ በምርመራ ከተረጋገጠ፤ እንደማንኛውም ነፍሰጡር ሴት በፈለገችው የጤና ተቋም ውስጥ አምጣ መውለድ ትችላለች፡፡
ይቀጥላል


Read 1689 times