Saturday, 11 April 2020 14:41

ወርኀ መጋቢትና ወቅታዊ ትኩሳቶቿ

Written by  አዲሱ ዘገየ (ዲላ ዩኒቨርስቲ፣ የሀገረሰብ ጥናት ተቋም)
Rate this item
(2 votes)

 “አስቦስ እንደሆን ሰይጣኑ ለበጎ
ያቃጠለው ቤትህን ሊያሞቅህ ፈልጎ?!” (ሰ. ሣ.)
ወርኀ መጋቢት የራሱ/ሷ የባህርይ ግብር አለው/አላት፤ ከጎረቤቱ/ቷ የካቲትና ከሌሎች አዝማዶቹ/ቿ (ለምሳሌ ከኅዳር) የሚወርሰው/የምትወርሰው የዝምድና መልክ ባለቤት ነው/ናት፡፡ መጽሐፍ እንዲል፣ ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤ ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ያስተላልፋል፡፡ በውርርስ ሂደቱ ለሰው የሚሰማ ንግግርና ቃላት የሉም፤ ነገር ግን መልእክቱ ግብ መቺ ነውና ምድርን ሁሉ ያዳርሳል፡፡ በዚህም ዕለተ እሁድ ውሎና አዳሩን ለሰኞ፣ ሰኞ ለማክሰኞ፣ ማክሰኞ ለቀጣዩ ይናገራሉ፤ ሌሊትም ለቀጣዩ ሌት፣ ወራትና ዓመታትም እንዲሁ፡፡ እንኳን ከቅርብ ጎረቤት ይቅርና ከሩቆች ሳይቀር የሚያዛምድ ሂደት አይጠፋም፡፡ መጋቢት ከመስከረም አቻው ጋር ሰዓተ መዓልትና ሌሊታቸው እኩል መሆኑ እኩያና አምሳያ ያደርጋቸዋል፡፡ አስራ ሶስቱ የኢትዮጵያ ወራት እርስ በርሳቸው የሚዛወጉበት የአንድነት መልክ አላቸው፡፡ መጋቢት ማዶ ካለው የኅዳር ወር የሚያዛምደውን በረከተ-መርገም ተመሳሳይነት ለማስረዳት አንዱ ምሳሌ የሚሆነው የኅዳር መባቻ በዋለበት ዕለት ማግስት፣ የመጋቢት መባቻ መዋሉ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ መጋቢት የኅዳርና የየካቲት ማግስታቸው ሲሆን፣ የተጠቀሱ ወራት ለመጋቢት ዋዜማዎቹ ናቸው፡፡ ከላይ በቀረበው የዕውቀት ሽግግር መሠረት፣ ዕለት ከቀዳሚውና ካለፈው ዕለት፣ ወር ከቀዳሚውና ካለፈው ወር እየተነገራቸውና እየተማሩ ራሳቸውን ከወቅታዊው ድባብ ጋር የሚያስማማ ቅድመ ዝግጅት ያደርጋሉ::
መጋቢት ከኅዳር ትላንትናዋ ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ በወረሰችው የመተንፈሻ አካል ሕመም ብዙኀኑን ወደ አፈር ስትመልሰው ታይቷል፡፡ ኅዳር ያመጣባቸውን ዕልቂት ለመታደግ ኅዳርን ሲያጥኑ የነበሩ ንዋያተ ቅድሳት ዳግም ላገልግሎት ሲበቁ ታይቷል፡፡ ቀድሞ ያልተማሩና ያልሰለጠኑ ዜጎች በኅዳር በሽታ እንዳለቁት ሁሉ፣ ያሁኑ ትውልድ ተምሮና ሠልጥኖ ራሱን ከዕልቂት ማዳን አልተቻለውም፡፡ ባንዲት ሀገር ላይ የአዋቂ መምህራን መበራከት ለሕዝቦቿ መድኃኒትና ፈውስን እንደሚያስገኝ ቢታመንም፣ ይህ ሁሉ ምሩቅ በተጥለቀለቀባት ሀገር ግን የመምህራንና የአዋቂዎችን ምክር ወስዶ መተግበር ዘበት ሆኖ ታየ፡፡ የመምህራንና የሊቃውንት አንደበትና ዕውቀት አዋቂውን ማዳን ሲሳነው ትምህርቱ፣ ጥበቡ፣ ዕውቀቱ፣ የኑሮ መልኩ ወዘተ የተኳለ፣ የተለሰነ፣ የተቀጠለ፣ ተፈጥሯዊ ቃና እና መዓዛው የተነሣው መሆኑን አለመጠርጠር አይቻልም፡፡ ወረርሽኙ ዓለምን አዳርሶ፣ ወደ ሀገራችን ከገባ ቀናትን አስቆጠረ፡፡
ሰው ግን የዕለታትና የጊዜያት ጌታ ሲሆን፣ ከሚገዛቸው ንብረቶቹ አለመማሩ እንዳለ ሆኖ፣ የቀዳሚ የበኩር አባቶቹን ታሪክ እንዳሻው እየፈተፈተ ካጠገቡ የቆመ ወንድሙን ለማጥመጃ የሚሆን መረብ መጎንጎንን ትምርት አድርጎ ይታያል፡፡ ካለፈው አምሳያው፣ እንዲሁም ከሚገዛቸው ፍጥረታት ሕይወት በጎ በጎውን ከመቅሰሙ ይልቅ ታሪክን በማማረር መሠልጠንና መማርን መረጠ፡፡ ካለፈው የመማር ዕድል በመመናመኑ የተነሳም አድማስን እያቆራረጠ የሚገሰግሰውን መልአከ ሞት የሚያቆም/የሚያዘገይ ሥልጣኔው የማዳን ሥልጣኑ ተሽሮበት ታየ፡፡ ይህም በአንድ ወገን ሰው እንዲህ ዓይነቶችን ታሪካዊ ክስተቶች የሚገምትበትና የሚቆጣጠርበት ልቦናው እንደተለየው የሚያሳይ፣ እንዲሁም ዕውቀትና ጥበቡ ከሀሳብና ቃል/ጽሑፍ ባለፈ ለተግባር ፍሬነት የማይበቃ መሆኑን ጠቋሚ ማሳያ ነው፡፡
“ሰው ከሰው ቢለዩ ዓመትም አይቆዩ!” ከሚለው የሀገሬው ልማድ ጋር መፋታትን የማይመርጠው ወረርሽኝ፤ “እገሌን ብቻ በምን ዕዳዋ!” ብሎ ከሀገር ሀገር እንደ ልቡ ሲናኝ፣ ጥፋቱን እያካበዱ ደረት ከመደለቅ ይልቅ፣ ከተቀጣጠለው ሰደድ ጋር የተቃየጡ መልካም አጋጣሚዎችን ማነፍነፍ ተገቢ ነው፡፡ ይህ የዓለም ቀውስ አለመማርን ወለል አድርጎ ከማሳየት ባለፈ፣ ሰው ዓለማቀፍ ፍጡር ነውና የቦታና ጊዜ ወሰን ሳይወስነው የዓለምን በረከትና መርገም እኩል የመካፈል ዕጣ እንዳለው ያረጋገጠ ነው፡፡ በሥነ ዐዳር/መንግሥት የሙያ ዘርፍ ተግዳሮቶችን ወደ መልካም ዕድል/አጋጣሚ መቀየር የልማት ሁነኛ ፈርን ለመቀየስ እንደሚረዳ ይተረካል፤ ቢያንስ በቲዎሪ ደረጃ ይነገራል፡፡
ይህ የጥፋት ሰደድ ከሩቅ ምሥራቅ ሀገራት (በነገራችን ላይ ምሥራቅን መነሻ ምንጩ የሚያደርግ ነፋስ፣ ለቅጣትና ለጥፋት መሾሙን ልብ ማለት ተገቢ ነው) መነሻውን ቢያደርግም፣ ዓለምን ለማዳረስ ግን ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ዓለም በደረሰችበት ገናና ሥልጣኔ፣ ዘመነኛ የአኗኗር ዘይቤ፣ የካበተ ቁሳዊ ሀብት፣ አእምሯዊ ዕውቀት፣ የደረጀ የጦር ሠራዊት የማይበገር ክንድ ያለው መልአከ ሞት ክቡሩን የሰው ልጅ ወደመጣባት ምድር ከማጋዝ አንዳቸውም አላገዱትም፡፡ ይህ በመሆኑም ዘመኑን እንደሚያሻግርና ትውልድን እንደሚቤዥ የታመነበት ጥበብ ሥልጣኑን ሲነጠቅ፣ ባለቤቶቹ የተማመኑበትና የተመኩበት ዓለማዊ ጥበብ ማርጀትና መድከሙን የሚያሳይ፣ በምትኩ አዲስ ወደሆነ የጥበባት ዓለም የሚያሸጋግር ተስፋ መፈንጠቁን የሚያሳይ መከራን ይዞ በየበራችን ተደቀነ:: ወርኀ መጋቢት ከሚያቃጥለው ሐሩራማ የበጋ ወቅት መውጣትንና ወደ በልግ/ጸደይ ልምላሜ መሸጋገርን የሚያውጅ ወር መሆኑ ለሽግግሩ አብነት ይሆናል፡፡
በሌላ ወገን ደግሞ መዋያና ማደሪያውን ስቶ የሚዋልለውን የሰው ቀልብ ምድር እንዲይዝ፣ በርጋታና ተመስጦ ወደ ማንነቱ ጠልቆ ገብቶ መዳኛ/ማምለጫ መላን እንዲዘይድ የታወጀበት ወር ሆነ፡፡ ባለንበት የመረጃና የዕውቀት ዘመን ላይ ኖሮ ከአዳኝ ዕውቀት የተራቆተውን የልማድ ባሪያ ነጻ የሚያወጣና የሠለጠነበትን ኋላ ቀር ልማድ ጥቅም አልባ ማድረጉን መገመት አትራፊ ባይመስልም፣ ኪሳራ ግን የሌለው አተያይ ነው፡፡ የመጋቢት ፍቺ አንዱ በራሱ ዙሪያ ቅጥር አበጅቶ፣ ከብቦ ራሱንና አምሳያውን ከደራሽ የጥፋት ሰደድ እንዲጠብቅ ያደረገ የጤና ጥበቃ አዋጅ ተሰምቷል፡፡ ይህም በቤትና በግቢው የሚወሰነው ሰው አንደኛ በዓለም ውስጥ በልማድ ከሚዘወተረው መድረሻና መዳረሻው ከማይታወቅ የማያልቅ ጉዞ ለአፍታም ያህል በመገታትና ቆሞ በማሰብ የሚበጀውን መሻገሪያ እንዲያስብ አነሳሽ በር መክፈቱ ይበል ያሰኘዋል፡፡ ሰው የእጁን በማያጣበት ዓለም፣ በእጁ ሞትን እንደሚጋብዝ ሁሉ፣ እጁን ለፈውስ እንዲያውል የታወጀበት ወር ነው፡፡ ለጥፋት የተዘረጋ እጅ፣ ለልማት መዋል እንደሚችል የታየበት መልካም አጋጣሚ የመጋቢት በረከት ነው፡፡  
ዕውቀትና ጥበብ ለሰው የሚበጁ ሰዋዊ ችሮታዎች ሆነው ሳለ ዕውቀትና ጥበብ ለጥፋት መንስዔ ሆነው ለኢ-ሰብዓዊ ዓላማ መዋላቸውን በመቃወም ከፈጣሪ የታዘዘ መቅሰፍት እንደሆነም ምንጭ ጠቅሰው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ከሰው ራስን ማብለጥ፣ ሰውን ለፖለቲካዊ ፍጆታ መሣሪያ ከማድረግ ውጪ የተሻለ አማራጭ በማይታሰብበት ዐውድ ላይ የተከሰተ ዱብ ዕዳ ነው፡፡ የዓለሙ ዘመነኛ ሰው በቦታና ጊዜ ራሱን አጥሮ፣ አንዱ ከሌላው የሚለይበትን ማኅበረ-ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ተፈጥሯዊና ሥልጣኔያዊ ጀብዱዎች መንዝሮና ቸርችሮ ማደርን መርጧል፤ አንዱ ያለሙያውና ያለዝንባሌው ተነስቶ በዘመናት ሂደት የተወሳሰበውን የዘር ተኮር ፖለቲካ ድውር እንዳሻው ተልትሎ፣ በጣጥሶና ቆራርጦ ሲቀጥል ውሉ እንዳይጨበጥ የድርሻውን ማወሳሰብ ግዴታው ያደረገ ይመስላል፡፡ አዳሜ ከራሱ ተጣልቶ ሌላውን ለማባላት ሰውነቱን አዋርዶና ወርዶ በሚታትርበት የጉልምስና ዘመኑ ለሌላው እየደገሰለት ካለው ድግስ ራሱ እንዲቀምስ ወረርሽኙ እኩል ሊያደርግ ይሰራል፡፡ በወሬ መፍታት፣ በወሬ ዘርና ማንዘርን ማጥፋት መተዳደሪያቸው ያደረጉ አጥፍቶ ጠፊዎች፣ የያዙትን የጥፋት ርዕስ አስገድዶ አስቀይሯልና መልካምነቱን በዚህ በኩል አለማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ሀገርና ሕዝብን (አጥፊና ጠፊውን ለጊዜውም ቢሆን) ላንድ ዓላማ ሲያቆም “ለካንስ ቤቴን ያቃጠለው እኔን ሊያሞቀኝ አስቦልኝ ኖሯል!” አያስብልም? በጎዎች በሌሉበት ቀዬ፣ በጎነት ሕልም በሆነበት ቀውጢ ሰዓት ላይ ሰው ራሱን አድምጦ በጎ እንዲሆን አጋጣሚው አያስገድደው ይሆን?
መጋቢትም እንዲሁ ለዕለት ሲሣይ የሚውሉ የምግብ ዓይነቶችን አሰናድቶ መመገብ፣ ማብላት፣ ማጠጣት፣ መቀለብ የሚከወንባት መሆኗ ይህም በቃሉ ፍቺ የሚተረጎም የግብር መለያዋ ነው:: በሌላ ወገን ደግሞ፣ ነባር ልማዶችና ዕውቀቶች ጥቅመ ቢስነታቸው በመከራው በመፈተናቸውም አዳዲስ ግብና ዓላማን ለማሳካት፣ ራስን በመጠበቅ ሌላንም ለማዳን ክተት ተጠርቶባታል፡፡
በትረ መንግሥትን ለመጨበጥ በመጋቢት ወር የሚደረግ እንቅስቃሴ ቢኖር ያለጥርጥር መሳካቱን እንዲያምኑባት የሚያስችል ቤተመንግሥታዊ በረከት ይዛለች፡፡ ወርኀ መጋቢት ለመመገብ ተግባር የተሰማራ መጋቢን፣ ለጥበቃ ተግባር የተሰማራ ጠባቂን ማለትም ሹምን/ሹማምትን አስገኝ/ወላጅ ወር ናት፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ለውጥን ተከትሎ የተካሄደው ሹም ሽር ወርኀ መጋቢትን ተገን አድርጎ መከናወኑ ይህ ወር የታጨበትንና የሠለጠነበትን ሙያዊ በረከት ያስመሰከረ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው፡፡ አዲሱ ጠባቂ፣ አዛዥ፣ መሪ፣ እንደራሴ፣ ምስለኔ፣ የሕዝብ ወኪል፣ መሪም ቢሉ አስተማሪ መንበረ መንግሥቱ ላይ እንዲወጡ ወሩ ይረዳል፣ ብቻ ሳይሆን ያበቃል ቢባል ሐሰት አይደለም፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውጥን እንዲዘል ካደረጉ መልካም አጋጣሚዎች አንዱ ምስረታው በወርኀ መጋቢት መሆኑ አንዱ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም በመጋቢት ወር ላይ የበታችና የበላይ፣ ታላቅና ታናሽ፣ ዝቅተኛና ከፍተኛ፣ መሪና ተመሪ፣ ተማሪና መምር ወዘተ ባሉበት የልዩነት ማዕረግ እንዲሠለጥኑ አትመክርም:: ይልቁንም የማዕረጋት ልዩነቶች ጠፍተው አንዱ ከሌላው ጋር በእኩያነት ደረጃ እንዲቆሙ መደላድል ትፈጥራለች፡፡ ዓባይ ምግቤ፣ ቀለቤ፣ ዋስትናዬ፣ ጠበቃዬ፣ የደህንነቴ መከታ ብለው የሞት ሽረት ትግል የሚያደርጉ ሀገራት የዓባይን ውለታ ዘርዝረው መቁጠር ቢሳናቸውም ሀገራችንም የእኩል ተጠቃሚነት መብትን ተገን አድርጋ መዝለቋ እኩል የበረከቱ ተካፋይ እንደሚያደርጋት እማኝ መቁጠር ቢያሻን መጋቢትን ብቻ መጥራቱ በቂ ነው:: የመጋቢትን በረከት የሚካፈሉ ሀገራትና ሕዝቦች፣ አንዱ ከሌላው የሚበልጥና የሚያይል ሥልጣኔውን፣ የቀደመ ታሪኩን፣ የጉልበት አቅሙን፣ የጦር ሠራዊቱንና ሌሎችን ቢያሰማራም ያሰበውን ሉዓላዊ ማዕረግ እንዲያገኝ ጊዜው አይፈቅድለትም:: በወርኀ መጋቢት አያትም ሆነ አባት፣ ከልጁና ከልጅ ልጁ ተካክሎ፣ ጠላትም ሆነ ወዳጅ በአንድነት፣ በእኩያነት ማዕረግ ቆሞ፣ የሀብታምና የደሀ ሀገራት ሕዝቦች እንደ ሀብታቸው መጠን ተለያይተው የሚቆሙበትን የከፍታና የዝቅታ ማዕረግ ማስተካከልና መቀራረብ ግድ ይላል፡፡ በዚህም ባለጸጋው በሀብቱ ሳይኩራራ፣ ደሃው ድኅነቱን ሰበብ አድርጎ ሳያንስ ለእኩልነት ሲባል ከቆሙበት የልዕልና/የትህትና ማዕረግ ወርደውና ወጥተው ተስተካክለው መቆም እንዲገባቸው መጋቢት በጥበቡ ይመራል፤ ያስተምራልም፡፡
መጋቢት ወርኀ ዕሪና ይከወንባታል:: ይህ ማለት፣ አንዱ ከሌላው ለምሳሌ አጥፊው ከጠፊው፣ ተማሪው ከመምሩ፣ አባት ከልጁ፣ ወዘተ ጋር የሚተካከልበት፣ አንድነቱን እኩልነቱን የሚገልጥባት፤ አንዱ ከሌላው አለመብለጡ፣ አለመበላለጡ የሚመዘንባት አደላዳይ ወር ናትና፡፡ ለዚህ ይመስላል ዓለምን ባዳረሰው ወረርሽኝ እንኳ የዓለም ሀገራትን ስንመዝናቸው አሜሪካ ከኢራን፣ ጣልያን ከስጳኝ፣ ቻይና ከአንዱ የአፍሪካ ሀገር ወይም ከአሜሪካ፣ ጀርመን ከእንግሊዝና ከፈረንሳይ ወዘተ በእኩል እንዲዳኙ እንዲተካከሉና መልአከ ሞትም ሀብታቸውንና ጦራቸውን ሳይሰቀቅ እንዳሻው ሲያረግፍ የምናየው:: በነገራችን መቋጫ ላይ በሀገራችን የባሪያ ንግድ እንዲቆም የሚያስችል አዋጅ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የተደነገገው በመጋቢት ወር ላይ ነበር፡፡ በሀገረ አሜሪካም ለጥቁሮች መብት የሚታገለው ማርቲን ሉተር ኪንግ የእኩልነት ድምጹን ከሚያሰማባቸው መድረኮች መካከል ባንዱ ላይ በጥይት ተመትቶ የወደቀበት ወርኀ ዲሞክራሲ ናት ቢባል ሐሰት አይሆንም፡፡

Read 794 times