Sunday, 12 April 2020 15:02

ኮሮናን ለመከላከል የተሰራው መካኒካል የእጅ መታጠቢያ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 - ለኮሮና የሰራሁትና ለአተት የሰራሁት ብዙ ልዩነት አላቸው
    - በ3ሺ 500 ብር ይሸጣል ተብሏል
    - ኮሮና ቫይረስ ሲቆምም የመሳሪያው ጥቅም የሚቆም አይደለም
    - ግለሰቦች መሳሪያውን እንድሰራላቸው ትዕዛዝ ሰጥተዋል


           ተወልደው ያደጉት እዚህ አዲስ አበባ፣ ቀበና ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው፡፡ በሙያቸው ሜካኒክ ናቸው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ ያገኙትን ብረት እየሰበሰቡ በማጠራቀም፣ አንዱን ካንዱ እያገናኙ መቀጥቀጥ ይወዱ ስለነበር ሰፈር ውስጥ “ቆራሊዮ” የሚል ስያሜ እንደተሰጣቸው ያስታውሳሉ፡፡ አቶ አብርሃም መንገሻ (ጆሞ) በስደት ሱዳን በቆዩባቸው ዓመታትም በሜካኒክነት ሙያ በተለይም ሞደፊኮችን በመስራት ሙያቸውን ማዳበራቸውን ይገልፃሉ፡፡ የኮቪድ ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ይረዳል ያሉትን አንድ ፈጠራ ሰሞኑን ይፋ አድርገዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከቴክኒክ ባለሙያው ጆሞ ጋር ከዚህ ቀደም በአዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ስላስመዘገቡትና አሁን ይፋ ስላደረጉት አዲስ የፈጠራ ሥራና  በሽታውን በመከላከል ረገድ ስላለው ፋይዳ አነጋግራቸዋለች፡-


           አሁን በዋናነት ሥራዎ ምንድን ነው?
እኔ በዋናነት የጋራዥ ሰራተኛ ነኝ፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ወደ ንግድ ሥራም ገብቻለሁ፡፡ ይበልጥ ነፍሴ የምትሳበው ግን ወደ ቴክኒክ ሥራ ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ከብረት እየቀጠጥኩ ስሰራ ቤተሰቦቼ ሁኔታዬን ተረድተው፣ ይሄ ልጅ ጋራዥ ገብቶ መስራት አለበት ብለው ጋራዥ አስገቡኝ፡፡ ለስራው ፍቅር እንዳለኝ ያወቅኩት በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ጥሩ የሚባል የጋራዥ ባለሙያ መሆን ስችል ነው፡፡ በሁለት ወራት ውስጥ የተዋጣልኝ ባለሙያ ሆኜ ሥራዬን ቀጠልኩ፡፡ ደሞዝም ቢሆን በአጭር ጊዜ ጥሩ ክፍያ ማግኘት ችያለሁ፡፡ በተለይ ሞደፊክ መስራት ነው የሚያስደስተኝ፡፡ በሙያው እስከቆየሁበት ጊዜ ድረስ ታታሪና ተወዳጅ ሰራተኛ ነበርኩ:: በዚህ ሙያ አገር ውስጥ ከ10 ዓመት በላይ፣ በሱዳን በስደት ላይ እያለሁም ከ6 ዓመት በላይ ሰርቻለሁ፡፡
አሁን ወደ እርስዎ ጋ የመጣነው ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳና ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ሰርተዋል መባሉን ሰምተን ነው፡፡ እስኪ ስለሱ በስፋት ያብራሩልኝ?
ጥሩ፡፡ ወደ ስራዎቹ ከመሄዴ በፊት ልነግርሽ የምፈልገው ነገር ምን መሰለሽ… ለቴክኒክ ባደረብኝ ፍቅር ብዙ ነገሮችን እሞክራለሁ፡፡ በአገር ደረጃም ችግር ሲከሰት አዕምሮዬ የሚያውጠነጥነው በሙያዬ ምን ሰርቼ የበኩሌን ላበርክት የሚለው ላይ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ችግር ሲከሰት ሀኪም፣ ተመራማሪ የሚያስፈልገውን ያክል የቴክኒክ ስራም እኩል አስፈላጊ ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ እዚህ አገር ግን ለቴክኒክ ስራ ብዙ ትኩረት የተሰጠው አልመሰለኝም፡፡ ይህን የምለው ያለምክንያት አይደለም፡፡
እስኪ ምክንያትዋን ያስረዱኝ?
ለምሳሌ ያ መጀመሪያ የሰራሁትን መታጠቢያ ነው አሁን የሰራሁት፡፡ አገራችን ላይ ከአመታት በፊት ተከስቶ የነበረውን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ለመከላከል ነበር የሰራሁት፡፡ በሽታው ከንፅህና ጉድለት እንደ መምጣቱ፤ ሰው በተለይ ብዙ ነገር ሲነካካ የሚውለውን እጁን በደንብ መታጠብ እንዳለበት ያኔም ይነገር ነበር፡፡ እንደውም ያኔ ወደ ወርክሾፕ እየሄድኩ ሳለሁ ነበር “እንዲህ አይነት በሽታ ተከስቷልና እጃችሁን ታጠቡ” የሚል በራሪ ወረቀት ይሰጥ የነበረው፡፡ እኔም እንዳጋጣሚ ያ ወረቀት ደረሰኝ፡፡ ወደ ወርክሾፕ ለመሄድ የ5 ደቂቃ መንገድ ይወስድብኝ ስለነበር እየሄድኩ ስለ እጅ መታጠብና ጥንቃቄ ማሰብ ጀመርኩኝ፡፡ መጀመሪያ ቧንቧ ከፍቼ እጄን ታጠብኩ፡፡ ከዚያ መልሼ ቧንቧውን ስነካ መጀመሪያ ሳልታጠብ የነካሁትን ቧንቧ ነው የምነካው፡፡ “ታዲያ ምኑን ተጠነቀቅኩት” አልኩኝ ለራሴ፡፡ ከዚያ አድርስ የተባልኩትን ትዕዛዝ ትቼ፣ ያንን ሜካኒካል የሆነና ከንክኪ ነፃ  የእጅ መታጠቢያ ሰራሁ፡፡ በጣም ደስተኛ ሆኜ ተጣድፌ ወረዳ ሄድኩና ነገርኳቸው፡፡ “ይሄንን ነገር ተጠቀሙበት፤ ለጤና ጣቢያም ስጡት መፍትሔ ይሆናል” አልኳቸው፡፡ እነሱም መጀመሪያ እንዳይሰረቅ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤትና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሄደህ አስመዝግብ፤ ከዚያ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሂድ” አሉኝ፡፡ “እዚህ ሰው እያለቀ እንዴት እንደዚህ ትላላችሁ? “መጀመሪያ ሰው ይዳን፤ ከዚያ ይሰረቅ ግዴለም” አልኳቸው፡፡ እነሱ ግን ነገሬም አላሉት፡፡ ገረመኝ፡፡ እኔ እኮ ት/ቤት፣ ጤና ጣቢያ፣ ክሊኒክ ይወስዱና ይጠቀሙበታል ብዬ ነበር የጓጓሁት፡፡ ብዙም አልተረዱትም፡፡ እኔ ለማንኛውም አልኩና ከቤተሰቤ ተማክሬ፣ የፈጠራ ባለቤትነቴን አስመዝግቤ ዝም አልኩኝ፡፡ ለሁሉም ቀን አለው ብዬ ተውኩት፡፡
አሁን ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ይረዳል ያሉት የፈጠራ ስራ የተለየ ነው? ለአተት ከሰሩት የእጅ መታጠቢያስ በምን ይለያል?
ይሄ መጥፎ አለም አቀፍ ወረርሽኝ ሲመጣ “ኧረ ይሄን ለመከላከል የሚረዳ መሳሪያ አለኝ” ብዬ መጀመሪያ ለአተት ያወጣሁትን ሳወጣ፣ ህዝቡም የመንግስት አካላትም  ነው የተደሰተበት፡፡ ያው ለሁሉም ጊዜ አለው ይባል የለ፡፡ ግን ለኮሮና የሰራሁትና ለአተት የሰራሁት ብዙ ልዩነት አላቸው:: አንደኛውና መሰረታዊው ልዩነት በአተት ጊዜ የተሰራው እጅሽን ለመታጠብ ቧንቧ በእጅሽ ባትነኪም፣ ሳሙና የመንካት ግዴታ አለብሽ፡፡ አሁን የሰራሁት ግን ሳሙናም ቧንቧም በእጅ አትነኪም፤ በእግርሽ ብቻ ሁለቱንም በመጫን ሳሙና ከወሰድሽ በኋላ እንደገና ውሃውን ተጭነሽ መታጠብ ነው፤ ንክኪ የሚባል ነገር የለውም፡፡ ሁለተኛ፤ አዲሱ ታንከር ከቧንቧ ጋር የተገናኘ ሲሆን፤ ታንከሩ ሲሞላ ቧንቧው ራሱ ይቆማል:: ሌላው ታንከሩ ከበፊቱ ትልቅ ነው፤ 150 ሊትር ውሃ ይይዛል፡፡  ኮቪድ 19 በሽታ ቶሎ ቶሎ እጅን መታጠብ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ በዛ ያለ ውሃ የግድ ያስፈልጋል፡፡ የመካኒካል ስራው የተሰራበት ብረት፣ አቀማመጡ ሁሉ ጠንካራና ለአይንም ማራኪ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ስትታጠቢ ወይም እጅሽን እስክታሺ ድረስ ውሃ ዝም ብሎ አይፈስስም፡፡ ልክ ከፔዳሉ ላይ እግርሽ ሲነሳ ውሃው መፍሰሱን ያቆማል፡፡ አሽተሽ ስትጨርሺ ፔዳሉን ረገጥ ስታደርጊው፤ ውሃው እጅሽ ላይ መፍሰስ ይጀምራል፡፡ የእጅ መታጠቢያው ሲንክ ነው፤ ብረት ከሚሆን ሲንክ (ሴራሚክስ) ለማጽዳትም ቀላል ነው፤ ለአይንም ማራኪ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ ኮሮና ቫይረስ ብረት ላይ የመቆየት አቅሙ ትልቅ ስለሆነ ብረት አልተጠቀምኩም፡፡
ይሄ መሳሪያ ለሆስፒታሎች፤ ለጤና ጣቢያዎች ሌላው ቀርቶ ለመኖሪያ ቤቶች ሁሉ ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣል:: ውሃም ከመቆጠብ አንፃርም በጣም ውጤታማ ነው:: ለምሳሌ ቤት ውስጥ ባኞ ቤት ፊታችንን ስንታጠብ፣ ጥርሳችንን ስንቦርሽ፣ የጥርስ ቡርሽ ተጠቅመን እስክንጨርስ ወይም ፊታችንን በሳሙና አሽተን እስክናጠናቅቅ፣ ቧንቧውን ከፍተን እንተወውና ውሃው በከንቱ እየፈሰሰ ይቆያል፡፡ ይሄ ግን እየተንጐራደድኩ ጥርሴን ልቦርሽ ብትይ፣ ልክ እግርሽ ከፔዳሉ ላይ እንደተነሳ ውሃው መፍሰሱን ያቆማል፡፡ በአገራችን ሴንሰር በትልልቅ ሆቴሎች ብቻ ነው ያለው፡፡ ሁላችንም ሴንሰር የመጠቀም አቅም እስክናዳብር በየሆቴሉ፣ በየመኖሪያ ቤቱ፣ በየሆስፒታሉ፣ በየክሊኒኩ፣ በየት/ቤቱና መሰል ተቋማት ሥራ ላይ ቢውል ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ኮሮና ቫይረስ ቢቆም እንኳን የመሳሪያው ጥቅም የሚቆም አይደለም፡፡
ለመሆኑ ይህንን ስራ ለመስራት ምን ያህል ወጪ ይጠይቃል? እስካሁን ከመንግስት አካል ያገኙት ማበረታቻስ አለ? በድርጅትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ እቃውን የገዛ ወይም እንዲሰራለት ያዘዘስ ይኖራል?
አሁን ስራው የሰውን ህይወት ለማዳን በፍጥነት የተሰራ ስለሆነ ከ2500 ብር በላይ ወጥቶበታል፡፡ ግለሰቦችም እንድሰራ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ተፈላጊነቱ እየጨመረ ሲመጣና ወደ ቢዝነስ ሲቀየር፣ ጥናቶች ተጨምረውበት ጥራቱ አድጐና ተሻሽሎ መስራት ይችላል፡፡ ለምሳሌ መጠኑ ከዚህ በላይ የሆነ ወይም ያነሰ የሚፈልግ ይኖራል፡፡ ያኔ አጠቃላይ ጥናት ተደርጐ፣ ቢዝነስ ፕላን ተሰርቶለት የሚመረት ይሆናል፡፡ አሁን ግን አጣዳፊ ችግር ስለገጠመን የሚሰማ ካለ፣ ቶሎ ለችግር እንዲደርስ ነው የተሰራው፡፡
ሰዎች እንዲሰራላቸው ትዕዛዝ መስጠታቸውን ነግረውኛል፡፡ በስንት ብር ይሸጣል?
እስካሁን በዚህ እሸጠዋለሁ ብዬ አልተመንኩም፤ ነገር ግን ፈጠራው፣ የመስሪያ ቁሳቁሱ፣ ጉልበትና ጊዜው ግምት ውስጥ ገብቶ ይተመናል፡፡ እንደዛም ሆኖ አሁን ችግር ላይ ስለሆንን እስከ 3500 ብር ቢሸጥ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ በሞተር ሳይክል የፍሬን ሲስተም የሚሰራ፣ ቀላል፣ በተለይ አሁን ለመጣብን አደጋ ምላሽ የሚሰጥ ነው ባይ ነኝ፡፡ ከዚህ አንፃር ዋጋው የሚከብድ አይደለም፡፡ ከመንግስት ያገኘኸው ነገር ምላሽ አለ ወይ ብለሽኝ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ስለ እኔ በተለይ የመንግስት የጤናው  ዘርፍ የሚያውቀው ነገር አለ፡፡ ባዛርና የፈጠራ ውድድር ሲኖር ይጋብዙኛል:: ከዚህ ቀደም ባዛር ላይ ካንዴም ሁለት ጊዜ ተጋብዣለሁ:: ወረዳውም ያውቃል፡፡ ወረዳው እንደውም ይህን ስራ በይበልጥ እንደሚፈልግ ተነግሮኛል፡፡
ለአዲሱ ስራህ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ጠይቀሃል ወይስ?
ለዚህኛው አልጠየቅኩም፡፡ ለምን ብትይኝ… አሁን ጊዜው ይህን ለማሰብ አይመችም፡፡ የእኔ አላማ፤ መንግስትና ማህበረሰቡ የዚህን መሳሪያ ጠቀሜታ አውቆ፣ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውልና ከመጣብን ችግር እንድንድንበት ነው፤ ምክንያቱም ከማከም መከላከል በእጅጉ የተሻለ መሆኑን እረዳለሁ፡፡
አሁን ይሄ መሳሪያ በስፋት ቢፈለግ የማቅረብ አቅምዎ ምን ያህል ነው?
እኔ ይህንኑ አስቤ ስለሰራሁት ዝግጁ ነኝ፡፡ ወርክሾፑ መሳሪያው እውቀቱ በእጄ ነው፡፡ በጣም ተፈላጊ ከሆነ፣ የሰው ሃይል በመጨመር በደንብ ማቅረብ ይቻላል፡፡
ከእጅ መታጠቢያው ውጭም ሌሎች የፈጠራ ስራዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ?
አንዱ የሰራሁት ቬንትሌተር ነው:: በሌላው ዓለም ቬንትሌተር ንፁህ አየር ለማግኘት በየስብሰባ ቦታው ሁሉ ይገጠማል፡፡ እኔ እዚህ አገር አንድ ስብስባ ላይ ተጋብዤ ባጋጠመኝ ነገር ነው ልሰራ የቻልኩት፡፡ ቬንትሌተር በተለይ በህክምና ተቋማት ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ነገር ነው፤ የተበከለ አየርን ለማደስ ይረዳል፡፡ እኔ አንድ ጊዜ ስብሰባ ላይ ተጋብዤ ተገኘሁ፤ አዳራሹ በሙቀት ተጨነቀ፤  ህዝቡ ስብሰባውን ትቶ ማንቀላፋት ጀመረ፡፡ አዳራሹ በዱሮው የአየር ፀባይ ነው የተሰራው፤ ቬንትሌተር አያስፈልገውም ነበር፤ አሁን አየሩ ተቀይሯል፤ እና በዚያ ስብሰባ ሁሉም ተጨነቀ፡፡
ይህንን ነገር በስብሰባ፣ በህክምና ተቋማት፣ በት/ቤት፣ በቤተ መጽሐፍት ሁሉ በማስገባት ሰው ያለ ጭንቀት እንዲያክምና እንዲታከም እንዲያስተምርና እንዲማር፣ እንዲያነብና በጥሩ ስሜት እንዲሰበሰብ ማድረግ ይቻላል በሚል ራሴ ሰራሁት፡፡ ቬንትሌተሩ አየርን ከማቀዝቀዝ በተጨማሪ ብናኝ አቧራን ወደ ውስጥ በመሳብና በመሰብሰብ ውስጡ ባለው ውሃ ይዞ ወደ ስር ያስቀራቸዋል፡፡ አየርን ማቀዝቀዝ ብቻ ሳይሆን ማጽዳትም ይችላል ማለት ነው፡፡ ስራው በጥራት ሲሰራ ከፋይበርግላስ ሊሰራ ይችላል፡፡ እኔ አሁን የሰራሁት በዙሪያዬ ካለ ከወዳደቀ ነገር ነው:: እጅግ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡
ሌላው ከዚህ ቀደም ከስር የዳቦ መጋገሪያ ቀጥሎ እንደ መሳቢያ የሚወጣና የሚገባ የእንጀራ ምጣድ፤ ከምጣዱ በላይ ስቶቭ፣ ከስቶቩ ቀጥሎ መጠነኛ ኪችን ካቢኔት በአንድ ላይ ሰርቻለሁ፡፡ በኦቭን ቅርጽ ሆኖ ሁሉን በአንድ የያዘ፣ በእግር ፔዳል ራሱ ሊጥ ማቡካትና ሊጥ መቅዳት የሚችል ድካምን የሚቀንስ ምጣድ ሰርቼ ነበር፡፡ ይሄ አሰራር በተለይ ጠባብ ቤት ለሚኖሩ ቦታ በመቆጠብ መፍትሔ የሚሰጥ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ የእንጀራ ጋጋሪውን ድካም የሚቀንስ ነው፡፡ ሶስተኛ፤ ሁሉንም በተመሳሳይ ጊዜና ቦታ በመስራት ጊዜን ይቆጥባል፡፡ በአገር ውስጥ ጥሬ እቃ የሚሰራ ስለሆነ የውጭ ምንዛሬን ያስቀራልና ይሄንን በፋብሪካ ደረጃ በስፋት የመስራት ህልም አለኝ፡፡
እነዚህን የፈጠራ ሥራዎች ለገበየ ማቅረብ ያልቻሉበት ምክንያት ምንድን ነው?
እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረኝን ህልም እዚህ ድረስ አሳድጌዋለሁ፡፡ በትምህርት የተደገፈ ስልጠና ሳይኖረኝ በወንድሜ እገዛና ድጋፍ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ አሁን ይህንን ህልም እውን ለማድረግና በኢንዱስትሪ ደረጃ ለማሳደግ ያለብኝ ችግር የፋይናንስ አቅም እጥረት ነው:: በዚህ ሥራ የሚያምን፣ ይህ ስራ ቢያድግ አገርና ወገንን ይጠቅማል የሚል ባለሀብት አብሮኝ ለመስራት ቢፈቅድ እመኝኝ ትልቅ ሥራ ይሰራል፡፡
በሌላ በኩል፤ አሁንም በአጽንኦት የምናገረው መንግስት የቴክኒክ ባለሙያዎች ላይ ትኩረት ያድርግ፤ ብዙ ይጠቀማል፡፡ በተረፈ ራሳችንን በመጠበቅ፤ ሃላፊነታችን በመወጣት፣ ርቀታችንን በመጠበቅና እጀችንን በመታጠብ ኮሮና ቫይረስን በአጭር ጊዜ እንቅጨው እላለሁ፡

Read 1230 times