Monday, 13 April 2020 00:00

እውነቱን የማይናገር መንግስትና የማይሰማ ህዝብ ካለ ውጤቱ በኮሮና ማለቅ ነው

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(4 votes)

 በዚህ ሳምንት በማቀርበው መጣጥፍ “ጋዜጠኞች ሙያችሁን ለማስከበር በራሳችሁ ላይ ዝመቱ” ያልኩበትን ምክንያት፤ እንዲሁም ስለ ሀገራችን ሚዲያዎችና ስለ ዘመኑ የሀገራችን ጋዜጠኞች ያለኝን አስተያየት ለማቅረብ ቀጠሮ መያዜ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ቀጠሮዬን እንዳፈርስ ያስገደደኝ አንድ ጉዳይ ገጠመኝ - ኮሮና! እናም የጀመርኩትን ርእሰ ጉዳይ አቆምኩና ስለ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ - 19) ይህቺን ማስታወሻ ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡ ይህቺ መጣጥፍ ምናልባትም “የኮሮና ሰለባ ከመሆኔ በፊት” ያዘጋጀኋት ማስታወሻ ልትሆን ትችላለች፡፡
ኮሮና ከጉንፋን ዘር የመጣ ወረርሺኝ በሽታ ነው፡፡ አያቱ የህዳር በሽታ (Spanish Flu) ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ እናም ስለ ኮሮና ከማንሳታችን በፊት በአገራችን የተከሰቱትን ወረርሺኝ በሽታዎች ታሪክ በአጭሩ እንይ፡፡ ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት፤ የኢትዮጵያን የወረርሺኝ ታሪክ በስፋት ጽፈዋል፡፡ እርሳቸው በጻፉት መሰረት፤ በሀገራችን በመሀከለኛው ዘመን ለበርካታ ምዕት ዓመታት በርካታ የወረርሺኝ በሽታዎች ተከስተው ነበር፡፡ የበሽታው ዓይነትና የተከሰተበት ዘመን ግን በበቂ ሁኔታ በዝርዝር ሊገኝ አለመቻሉንም ገልጸዋል፡፡ በ9ኛው ክፍለ ዘመን በመጽሐፈ ስንክሳር ሁለት ወረርሺኞች ተጠቅሰዋል፡፡
የመጀመሪያው እ.ኤ.አ ከ831 እስከ 849 ባለው ጊዜ ሲሆን፤ ሁለተኛው በ12ኛውና በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (ከ1131 እስከ 1145) የተከሰተ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ዘመን (ለምሳሌ፡- ከ1261-1262) በሐረር አካባቢ ድርቅና ቸነፈርን መሰረት ያደረገ ወረርሺኝ መከሰቱ በታሪክ ሰነዶች ተመዝግቧል፡፡ ከ12ኛው እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደግሞ በርካታ ጅምላ ጨራሽ በሽታዎች መከሰታቸውን የቅዱሳን ታሪኮች ከተጻፉባቸው ሰነዶች ላይ መገኘታቸውን የታሪክ ተመራማሪው በትንታኔያቸው አስረድተዋል፡፡ ለምሳሌ በቅዱስ ተ/ሃይማኖት ዜና መዋዕል ውስጥ እንደተገለጸው፤ በገዳማትና በቅዱሳን ስፍራዎች ይኖሩ በነበሩ መነኩሴዎችና መናንያን ላይ ጭምር የከፋ ጉዳት መድረሱ ተጠቅሷል፡፡
በአፄ አምደጽዮን ዘመነ መንግስት (እ.ኤ.አ 1314 - 1344) ነጭ ዝንቦች ተሰራጭተው ሰዎችንና ፈረሶችን በመንከስ ጉዳት ማድረሳቸው፣ በርካታ ሰዎችና እንስሳት ለሞትና ለስደት መዳረጋቸው ተጠቅሷል፡፡ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ዘርኣ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት (እ.ኤ.አ 1434 - 1468) የተከሰቱ የበሽታና የቸነፈር ጊዜያት ቀደም ሲል ከነበረው ዘመን በተሻለ ሁኔታ በሰነዶች ላይ ሰፍሮ መገኘቱን ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ጽፈዋል፡፡ በአፄ ዘርኣ ያዕቆብ ዜና መዋዕል ውስጥ በሰፈረው መሰረት፤ በተነሳው ወረርሺኝ ራሱ ንጉሱ መታመሙም ተጠቅሷል፡፡ በዋና ከተማው በደብረ ብርሃን አካባቢ በርካታ እልቂት መድረሱም ተጽፏል፡፡ ሰዎችን መቅበር አስቸጋሪ በመሆኑ ንጉሱ ሁሉም ሰው ለቀብር እንዲወጣ በማድረግ በሃይማኖት አባቶች የጥምቀት ስርዓት ማከናወኑም ይነገራል፡፡
ከአፄ ዘርኣ ያዕቆብ እስከ ጎንደር ዘመነ መንግስት ድረስ በነበሩት ዓመታት በርካታ ድርቅና ርሃብን ተከትሎ የተከሰቱ ወረርሺኝ በሽታዎች ነበሩ፡፡ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፍራንሴስኮ አልቫሬዝ በጻፈው መሰረት፤ በደብረ ቢዘን ገዳም በነበሩበት ወቅት በወረርሺኝ ያልተለከፈ ሰው እንዳልነበረ ጽፏል፡፡ በዚያ ወቅት በደብ ሊባኖስ ገዳም ብቻ በአንድ ዓመት ውስጥ 400 መነኮሳት መቀበራቸው ተገልጿል፡፡ በዚሁ ዘመን በሐረር አካባቢ ተመሳሳይ ወረርሺኝ ተነስቶ ታዋቂው የሐረሩ አሚር ኑር መሞቱ ተዘግቧል፡፡
በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት “መናን ትታ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ወረርሺኝ ተከስቶ ነበር፡፡ በተለይም በጎንደር፣ ደንቢያ በተባለ አካባቢ የነበረውን ሁኔታ በተመለከተ በወቅቱ የነበሩ ጸሐፍት “የደረሰውን ጉዳት ለመግለጽ ይዘገንናል” በሚል መንፈስ ገልጸውታል:: ከንቲባ ዘጊዮርጊስ የተባሉ የደንቢያ ገዢ በዚሁ ወረርሺኝ ሞተዋል፡፡ ሚሲዮናዊው አሉሲየስ ዴ አዝቬዶ በበኩሉ፤ “ታላቅ እልቂት” ብሎታል፡፡ በጎርጎራም አካባቢ በርካታ መኳንንት መሞታቸው ተዘግቧል፡፡
ፈንጣጣ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዋና ገዳይ ወረርሺኝ በሽታ ነበር፡፡ ጄምስ ብሩስ የተባለ ስኮቲሻዊ ተጓዥ (እ.ኤ.አ ከ1682 - 1706) በነበረው ጊዜ በአሁኑ በኦሮሚያ ውስጥ በሚገኙ አካባቢ “የክፍለ ሀገሩ ህዝብ ግማሽ ያህሉ አልቋል” በማለት ዘግቧል፡፡ ዛሬ በአንድ ክትባት የሚድነው ኩፍኝም በህዝብ ላይ ተመሳሳይ ጥፋት አድርሷል፡፡ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተለይም እ.ኤ.አ ከ1811 - 1812፣ በ1838/39፣ በ1854፣ በ1878፣ በ1880 እና ከ1889 - 1890 ባሉት ዓመታት በአማካይ በየትውልዱ ህዝብ ጨራሽ ወረርሺኝ መከሰቱን ሪቻርድ ፓንክረስት ጽፈዋል፡፡
ታላቁ ርሃብ የሚባለው በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት (እ.ኤ.አ 1888 - 1892) የተከሰተው ነው፡፡ አልፍሬድ ኢልግ የተባለው ስዊድናዊ የምኒልክ አማካሪ እንደዘገበው፤ እ.ኤ.አ በ1890 ከአድዋ ጦርነት የተመለሰው የምኒልክ ሰራዊት 15% ያህሉ በወቅቱ በትግራይ በተቀሰቀሰው የፈንጣጣ በሽታ አልቋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1904 - 1905 እንዲሁም ከ1911 - 1913 ባሉት ዓመታት የፈንጣጣ ወረርሺኝ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተስፋፍቶ በርካታ ዜጎችን እንደ ቅጠል አርግፏል፡፡ በዚህ ወቅት ትግራይ፣ ሀረር፣ ድሬ ዳዋ፣ ደሴና ደምቢዶሎ በዚህ ወረርሺኝ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በሀገራችን ኩፍኝ፣ ኮሌራ፣ የተስቦ በሽታ (የካምፕ/የወታደር በሽታ)፣ ኢንፍሉዌንዛን የመሳሰሉ በርካታ ወረርሺኝ በሽታዎች ተከስተው ነበር፡፡ የወረርሺኝ ታሪካዊ አመጣጥን የምናሳርገው እ.ኤ.አ 1918 ላይ ይሆናል፡፡ በዚያ ወቅት የተከሰተው ወረርሺኝ አሁን ከተከሰተው “ኮሮና” ጋር ታሪካዊ ግጥምጥሞሽና ተያያዥ ታሪክ አለው፡፡ በዚያ ወቅት የተከሰተውን ወረርሺኝ አንዳንዶች “ስፓኒሽ ጉንፋን” ይሉታል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ሌላ ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ ስያሜው ታሪካዊ መነሻ አለው፡፡ ይኸውም፤ እ.ኤ.አ በ1917 የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ለገሀር ደረሰ፡፡ በዓመቱ (በ1918) በሽታው ወደ ኢትዮጵያ ገባ:: እናም ኢትዮጵያውያን “የባቡር በሽታ” የሚል ስያሜ ሰጥተውት እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ “የህዳር በሽታ” ይሉታል፡፡ ይህ ወረርሺኝ እንደ ኮሮና ዓለምን ያመሰ በሽታ ነው፡፡
በዚህ በሽታ ንግስት ዘውዲቱ ምኒልክና ራስ ተፈሪ መኮንን (በኋላ አፄ ኃ/ስላሴ) በበሽታው ተለክፈው በአልጋ ቁራኛ፣ በደዌ ዳኛ ተይዘው ነበር፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ አራተኛው ከንቲባ የነበሩት ደጃዝማች ወሰኔ ዘአማኑኤል በዚሁ ወረርሺኝ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ በትውልድ ግብፃዊ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት አቡነ ማቴዎስ ወደ ዝቋላ በማፈገፈግ ከወረርሺኙ መዳናቸው ይነገራል፡፡
የኮሮና ቅድመ አያት የሆነው ስፓኒሽ ፍሉ (የህዳር በሽታ)፤ አንድ ሦስተኛውን የአውሮፓ ህዝብ ፈጅቷል፡፡ በኢትዮጵያም 40 ሺህ ያህል ህዝብ አልቋል ተብሎ ይነገራል፡፡ ያ ወቅት ሰው በተቀመጠበትና በተኛበት ሞቶ የሚቀርበት፣ ቀባሪ አጥቶ በጅብ የተበላበት ወቅት ነበር፡፡ አያቶቻችን ይህንን በሽታ የተከላከሉት በ“ሳኒታይዘር” አልነበረም፡፡ በመታጠብ አልነበረም:: እቤታቸው በመቀመጥም አልነበረም፡፡ በነጭ ሽንኩርትም፣ በዝንጅብልም፣ በሀበሻ አረቄም፣… ነበር እንጂ! ቫይረሱ ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ እነሆ ዛሬ ራሱን ቀይሮ መጥቷል፡፡ ገጽታው በመሣሪያ ሲታይ ዘውድ (በእንግሊዝኛ crown) ቅርጽ ያለው በመሆኑ “corona” የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ይነገራል፡፡ እስከ አሁን ዳቦ ተቆርሶ የሀበሻ የዳቦ ስም አልወጣለትም፡፡
አንድ ነገር ሲከሰት ክፉም በጎም ነገር ጥሎ ማለፉ ይታወቃል፡፡ የህዳር በሽታ ለአንድ መቶ ዓመታት ያህል በየዓመቱ ህዳር 12 ቀን በመላ ሀገሪቱ ቁሻሻን የማቃጠል የጽዳት ሥራ እንዲከናወን አሻራውን ጥሎ አልፏል:: ኮሮና አሁን ጭቀት ቢፈጥርብንም ከቀናት፣ ምናልባትም ከወራት በኋላ ክትባት መድኃኒት እንደሚገኝለት ይጠበቃል፡፡ እናም አሁን የጀመርነው መታጠብና በመኖሪያ አካባቢ የመወሰን ሁኔታ ባህል ሆኖ ቢቀጥል የበሽታው መታሰቢያ ከመሆን ባለፈ ለቀሪ ለህይወታችን አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በዚህ ወቅት ስለ ኮሮና የተለያዩ ነገሮች በተለያዩ ሚዲያዎች ሲተላለፉ እናያለን፣ እንሰማለን፣ እናነባለን፡፡ የምናያቸው፣ የምንሰማቸውና የምናነባቸው መረጃዎች ብዙዎቹ አስጠንቃቂ፣ አስጊ፣ አስደንጋጭ፣… መሆናቸውን በግሌ አስተውያለሁ:: የቫይረሱ ሦስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዓለምን ማጥለቅለቁና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ፣ ከፍተኛ ሽብርና ድንጋጤ ይፈጥራል፡፡
ደራሲ በእውቀቱ ስዩም “የተሸበረ ህዝብና በጅምላ የሚሸሽ ሰራዊት መንገድ አይመርጥም - መውጫ ብሎ ያሰበው ላይ ሁሉ ይረባረባል” ይላል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ለመትረፍ እጅን መታጠብ፣ በቤታችን መታቀብ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም:: ራስን በቫይረስ ከመለከፍ አድኖ ሌሎችን ከማዳን አንፃር ከመዘንነው እጃችንን መታጠቡም ሆነ በቤት ውስጥ መመሸጉ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ ለተጨማሪ ዓመታት በህይወት እንድንኖር ያደርገናል:: ለሌላውም ጠንቅ ከመሆን ያድነናል፡፡ ጀግንነት ማለት የእሳት ራት መሆን ማለት አይደለም፡፡ ጀግንነት ማለት ከጠላትህ ጋር መጋፈጥ በሚገባህ ሰአት መጋፈጥ፤ መሸሽ በሚያዋጣህ ሰአት መሸሽ ማለት ነው፡፡
እንዲህ ያለ ወረርሺኝ ሲመጣ ዓለማዊ እውነትንና መንፈሳዊ እምነትን መሰረት በማድረግ ግለሰባዊና ማህበረሰባዊ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ራስን መጠበቅና ቤተሰብን ብሎም ማህበረሰብን ከጉዳት መከላከል ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ስለ ቫይረሱ መረጃ ማግኘት ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ በመንግስት በኩል ስለ ቫይረሱ ምንነት እና ሊያደርስ የሚችለውን የጉዳት መጠን በግልጽ ቋንቋ ለህዝቡ መንገር፣ ማስተማር፣ ደጋግሞ ማስረዳት የግድ ነው፡፡ እውነቱን የማይናገር መንግስትና የማይሰማ ህዝብ ካለ ግን ውጤቱ እልቂት፣ መዳረሻው ሞት መሆኑ እሙን ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 989 times