Monday, 13 April 2020 00:00

አይባልም

Written by  አዛኤል
Rate this item
(2 votes)

 በዘመኔ ካነበብኳቸውና ዘወትር ሳስባቸው ከሚያስገርሙኝ መጻህፍት መካከል “ወዳጄ ልቤ” አንዱ ነው፡፡ ይህ መፅሐፍ  ገና ከርዕሱ ጀምሮ ነው ግርምትን የሚያጭረው፡፡ መፅሐፉ  በ1915 ዓ.ም  ለመጀመሪያ ጊዜ እንደታተመ ተጠቁሟል፡፡ ደራሲው፤ “በ18 አመቴ ከዘመዶቼ ተለይቼ ወዳጄ  ልቤን አስከትዬ ከቤቴ ተነሳሁ” በሚል ነው ድርሰታቸውን የሚጀምሩት፡፡
በነገራችን ላይ…… በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተነሱት የአማርኛ ስነፅሁፍ ኮከብ ደራሲያን መካከል ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴ አንዱ ናቸው፡፡ ብላቴን የፖለቲካ ሰው፣ ዲፕሎማት ናቸው፤ በምክር መፃህፍቶቻቸው፣ በማህበራዊ ህፀፅ ነቃፊ ፅሁፎቻቸው በስፋት  ይታወቃሉ፤ በተለይም “ወዳጄ ልቤ” የሚለው መጽሐፋቸው ተወዳጅነትን ያተረፈ ነው፡፡
፠ የዚህ ፅሁፍ አላማ መፅሐፉን መዳሰስ አይደለም፤ እንዲያው የመፅሐፉን ጭብጥ  ከኛ ዘመን ጋር ማስተሳሰር ነው እንጂ፡፡
አንድ ሰው ጉዞ ሲያደርግ የምናውቀው በአካለ ስጋ ከአንድ ግዘፍ አለም ወደ ሌላኛው ግዘፍ አለም ቢሆንም ብላቴን ጌታ ኅሩይ ግን ወደ መልክአ ልቡና (inner landscape) የሚደረግ ጥልቅ ፍለጋን በፈጠሩት ገፀ ባህሪ ውስጥ እንደሚተርኩልን  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ፅሑፍ ትምህርት ክፍል መምህሩ ቴዎድሮስ ገብሬ  አስረግጦ ይነግረናል፡፡ ሰው ከተፈጠረበት ሶስት ባህሪያተ ነፍስ  መካከል አንዱ ለባዊነት ነው (ነባቢነትና ህያውነት ሁለቱ ናቸው)፡፡
ለባዊነት ፦ አዋቂነት፣ አስተዋይነት፣ አሳቢነት የሚል ትርጓሜ አለው፡፡
ሰው በዘመን መሄድ መምጣት ውስጥ የሚኖር ፍጡር ነው፤ አለም ከተፈጠረ ኋላ የተፈጠረ ሁሉ ለርሱ የተዘጋጀለት ድንቅ ስራ እንደሆነ ይታመናል፤ ድንቅ ሰው ድንቅነቱን ይዞት ሲከርም ብዙ ድንቅ ሃሳቦችን ፈጠራዎችን  ጥበቦችን ቀምሞ አለምን አለም አድርጓታል፤ በዛው መጠን የሚተካከልም ስግብግብነት ባለቤት ሆኖ ሰንብቷል ….ሰው፣  ራስ ወዳድነቱ  ራሱ ለፈጠረው  ግኝት  የበታች ባሪያ በመሆን ለእልቂትም ደርሷል…ሰው፤ በገዛ ክፋቱ  በርካታ ክፉ ጊዜዎችን ተቀራምቷል፤ የሀያላን አለም ለመፍጠር  በሚያደርገው የጅል ትግል እራሱ ሲሸነፍም ማየት የተለመደ ነው፤ አንዴ በጦርነት አንዴ በቅኝ ግዛት፣ አንዴ በእርዳታ፣ አንዴ በበሽታ ….ራሱ ሰው::
እንግዲህ …የዚህ አይነቱ ክፉ ጊዜ ለማለፍ እውቀትና ሳይንስ ከሚያደርጉት መፍትሄ ሰጪነት በላይ የሃይማኖት ትምህርት ትልቅ ድህነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሳይንስ አለምን ወደ ተሻለ አለም አሻግራለሁ ብሎ መልህቁን አንስቶ ጉዞ ቢጀምርም የባህሩ መሃል ላይ አስቀርቷታል፤ ያውም አንዴ እያጋጨ አንዴም እያፋጨ፡፡ ሳይንስ ለዘመናት እያጣጣላት የኖረው “ትሁቷ” ሃይማኖት፤ የችግር ጊዜ መሸሸጊያ የክፉ ዘመን መዋጊያ ሆና ለብዙዎች ልብ  ማረፊያ ሆናለች፤ የዚሁም እምነት አካል ነው ሃገረ ኢትዮጵያ የፀሎትና የእንባ ጊዜ  ለአንድ ወር ያወጀቸው፡፡
“..ጉልበት ያልህ በጉልበትህ፣ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለምሽትህ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ….” ሲሉ፤ ንጉሰ ነገስት ምኒልክ የዚሁ አይነት አዋጅ አውጀው እንደነበር ታሪክ  ይነግረናል፤ ንጉሱ ትልቁ እምነታቸው በአቅማቸው ላይ ሳይሆን በአምላካቸው ላይ ነበር፤ እውነተኛው ወኔያቸው በሰይፋቸው ላይ ሳይሆን በልባቸው ላይ አድሮ ነበር፤ ልብ ያለው ህዝብ ጠላቱን መመለስ ያውቅበታል፤ ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን ጦርነቱን በልባቸው ሲደርጉት፣ ጣልያንያውያን ግን የመድፍ ያደረጉት፡፡ የድል ዕድሉ ልብ ላይ ይወሰናል፡፡
ይሄን ክፉ ዘመን በልባችን፣ ከልባችን ከተፋለምነው እናልፈዋልን፡፡  
ኢትዮጵያም አለምም ወደ ቀልቡ ይመለስ ዘንድ፤ በብላቴን ኅሩይ ርዕስ መሰረት ሰው ሁሉ ወዳጁ የሆነን ልቡን ያፈላልግ ዘንድ፤ ይሄንን ክፉ ጊዜ በደግ ልቦች ይተካ ዘንድ ፀሎት ግድ ነው፤ ሃይማኖት የፀሎት አጥሩ ነውና፤ …እንኳንም ሃይማኖት  ያላት ሃገር ኖረችን ያስብላል፡፡
እስከ ዛሬም እንደ ማህበረሰብ አማኝ ነን ያልነውን የምናሳይበት የፈተና ጊዜ ነው፤ “እምነትህ በምትኖረው ህይወት ላይ ይሁን፤ እሱንም ለመኖር እንጂ ለማውራት አይሁን” እንደሚሉን ዜኖቹ፤ የእውነትም አንደበታችን ላይ ያለው ማንነታችን ወደ ልቡናችን ወርዶ፣ የወረደብንን መቅስፈት የሚመልስ መሆን አለበት፡፡
ሃይማኖትና ሳይንስ እልፍ ጊዜ ለጦርነት ተፋጠዋል፤ ይሄም ዘመን አንዱ ነው፤ ይሄንን ፍጥጫ ለየት የሚያደርገው ግን የማንኛቸውም አሸናፊነታቸው የሚለካው ሰውን በማኖርና በማኖር ብቻ መሆኑ ነው፤ ሳይንስም ለሰው ሃይማኖትም ለሰው አለሁ የሚልበት ጊዜ ነው፡፡ …..
ትልቁ ግብግብ  ከገዛ ለባችን ከገዛ ነፍሳችን ጋር ነው፤ ፈጣሪም ኢትዮጵያን ያድናት ዘንድ ልባችንን እንጂ ልብሳችንን መቅደድ እናቁም፤በደህና ጊዜ የረሳነው አምላክ በክፉ ጊዜ እንዳናስታውሰው ከሆነስ፤ ገብተንበት የማናውቀውን ደብርና መስጊድ  መልስን እናክብራቸው ዘንድ ታቅዶ ቢሆንስ? የእውነተኛ ሰውነት መለኪያ፣ የመንፈስ ሰላም ማንቂያ ቢሆንስ ይሄን መከራ ያመጣብን? (ማን ያውቃል?)
ብቻ እኛ …ባለቅኔው እንዳለን ሰርክ መቀኘት ያስፈልገናል፤
አስምኣኒ  
አስምአኒ ነገረ ፅድቅ
ዘያስተፈስህ ህሊና
አስምአኒ ከጌታ ሰማኒ
      ዕዝነ ልቡናዬን ክፈትልኝ
      ዓይነ ህሊዬን አብራልኝ
  የጠጠረው እንዲላላ ….ውስብስቡ እንዲገራልኝ፤
፠ ባለቅኔ ሙሉጌታ ተስፋዬ     
እኛም እጃችንን ለአሚን እንዘርጋው እስቲ……
አሜን….የጠጠረው ይላላን
አሜን…..ውስብስቡ ይገራልን
አሜን…..ቤታችን ይታደስ
አሜን ….ልባችን ይመለስ፤
አሜን…
ልባችንን እንኑር እንጂ እንደ ልባችን እንኑር አይባልም!Read 617 times