Wednesday, 15 April 2020 20:06

"እናቴን በእናቶች ቀን አጣሁ"

Written by 
Rate this item
(4 votes)


እ.ኤ.አ ሜይ 10 የሚከበረው የእናቶች ቀን ሳምንታት ሲቀረው የ33 ዓመቷ አያ (ስሟ ለዚህ ዘገባ የተለወጠ) ለእናቷ ምን ዓይነት ስጦታ እንደምትሰጣቸው በማሰብ ተወጥራ ነበር፡፡ እናቷን እንደምትቀብር ግን በህልሟም ሆነ በእውኗ ፈጽሞ አላሰበችውም፡፡
የአያ እናት በግብጽ፣ በኮሮናቫይረስ ከሞቱት የመጀመሪያዎቹ አስር ሰዎች አንዷ ሆነዋል፡፡  
ግብጽ በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ መከሰቱን በየካቲት መጀመሪያ ላይ ይፋ ብታደርግም ቅሉ፣ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በመደበኛነት ማየት የጀመረችው ግን በየካቲት መጨረሻ ሳምንት ላይ ነበር፡፡
እስካሁን በግብጽ ከ2ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ቢያንስ 160 ሰዎች በበሽታው ሞተዋል፡፡  
እናቷ ለሳምንት ያህል በአስከፊ የጤና ይዞታ ላይ የቆዩ ቢሆንም፣ ይሄ የመጨረሻቸው ይሆናል ብላ ፈጽሞ አላሰበችም  ነበር፡፡ ድንገተኛ መርዶውን ስትሰማም፣ ራሷን መሳቷን ታስታውሳለች፤ አያ፡፡
"ወንድሜን እየዋሸኸኝ ነው ብዬው ነበር፤ቀደም ብሎ እየተሻላት እንደሆነ ነግሮኝ  ነበር፡፡" ትላለች አያ፡፡
"የእናቶች ቀን ጥቂት ቀናት ሲቀረው ሆስፒታል ስለገባች፣ አፕሪል ላይ ለልደቷ ወደ ቤት ትመለሳለች ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ሁለቱንም በዓላት (ልደትና የእናቶች ቀን) አጣምረን  ልናከብር ነበር፡፡"
የአያ እናት በደቡብ ካይሮ የሄልዋን ግዛት ወደ ሚገኝ የለይቶ ማቆያ ሆስፒታል የገቡት ከመሞታቸው አንድ ቀን በፊት የኮቪድ - 19 ምርመራ አድርገው ፖዘቲቭ መሆናቸው ከታወቀ በኋላ ነበር፡፡
"ለመጨረሻ ጊዜ ያወራኋት ማክሰኞ ዕለት ነበር---እሁድ አባቴ የጠበቡ የደም ስሮችን የማስፋት ህክምና ላይ ስለነበር ለአፍታም አልተለየሁትም፡፡" ስትል ታስረዳለች አያ፡፡
ለአያ ፈተና የሆነባት እናቷን ለመጨረሻ ጊዜ መሰናበት አለመቻሏ ብቻ አይደለም፡፡
እናቷ የሞቱ ዕለት በመላ አገሪቷ ሁሉም ጸሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ  ታግደው ነበር፡፡ መስጊዶች በሙሉ እንዲዘጉም ትዕዛዝ ተላልፎ  ነበር፡፡
ስለዚህም በቀብር ወቅት  የሚከናወነውን ጸሎት በሆስፒታሉ የአስከሬን ክፍል ውስጥ ለማድረግ መገደዷን አያ ትገልጻለች፡፡
የእናቷን አስከሬን ከሆስፒታል የማውጣት ሂደት ብዙ ሰዓት በመፍጀቱ የተነሳም፣ ቀብሩን ያከናወኑት በምሽት እንደነበር ነው የተናገረችው፡፡  
"በጣም ጥቂት የቤተሰብ አባላት ነበር የመጡት፡፡ ሁላችንም የፊት ጭምብልና ጓንት አድርገን ነበር፡፡ የወንድሜ ሚስት እጄን ይዛ 'አቅፌ ባጽናናሽ እወዳለሁ፤ ግን አልችልም ' አለችኝ በሹክሹክታ፡፡ የወንድሜ ሚስት እናት ክፉኛ አዝነው ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳችን ሌላኛችንን ማጽናናት አልቻልንም፡፡"
"አባቴም እናቴን ሊሰናበታት አልቻለም፤በቀብሩ ላይ ቢገኝም ለሳምንት ያህል አላያትም ነበር፡፡"
ከእናቷ ሞት በኋላ አባቷም ቫይረሱ ስለተገኘባቸው በተመሳሳይ የለይቶ ማቆያ ሆስፒታል ውስጥ ገብተው ነበር፡፡
እሳቸው ግን ከበሽታው አገግመው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ለቤታቸው በቅተዋል፡፡
አያም ሆነች ወንድሟ ፖዘቲቭ ባይሆኑም፣ ሁለቱም ራሳቸውን ነጥለው መቆየት ነበረባቸው፡፡
"እንደ አንድ ቤተሰብ፣ አንዳችን ለሌላችን ልንሆን እንኳን አልቻልንም" ብላለች፤አያ በሃዘን ተሞልታ፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ

Read 5308 times