Saturday, 07 July 2012 10:33

ስፔን በቲኪ ታካ የምንግዜም ምርጥ ቡድን ሆናለች!?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ላ ፉርያ ሮጃ ወይም ቀዮቹ ጦረኞች በሚል ስያሜያቸው የሚጠሩት ስፓንያርዶች 14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በሻምፒዮናነት ከደመደሙ በኋላ ቲኪ ታካ በተባለው የጨዋታ ስልታቸው የምንግዜም ምርጥ ቡድን መሆናቸው እያነጋገረ ነው፡፡ የስፔን ብሄራዊ ቡድን ከ4 ዓመት በፊት በዓለም እግር ኳስ የማይሳካለት ቡድን ሲባል የቆየ ነው፡፡ በ2008 እኤአ ላይ 13ኛውን አውሮፓ ዋንጫ ፤በ2010 እኤአ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ  ዘንድሮ ደግሞ 14ኛውን የአውሮፓ ዋንጫ በሻምፒዮናነት ሲያስገብር በዓለም እግር ኳስ ከታዩ ምርጥ ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ መፈረጅ ጀምሯል፡፡ በሁለት ተከታታይ የአውሮፓ ዋንጫ ውድድሮች ሻምፒዮናነቱን በማስጠበቅ ብቸኛ ታሪክ ያስመዘገበው ቡድኑ ከዓለም ዋንጫ ድሉ ጋር በታላላቅ የውድድር መድረኮች ሶስት ዋንጫዎችን አከታትሎ በመውሰድ የምንግዜም ምርጥ ብሄራዊ ቡድን ተብሏል፡፡

በ14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የውድድሩን ኮከብ ተጨዋች አንደሬየስ ኢኒዬስታ እንዲሁም በኮከብ ግብ አግቢነት ፈርናዶ ቶሬስን ያስመረጠው የስፔን ቡድን በአውሮፓ ዋንጫው ምርጥ ቡድን  1 በረኛ፤ 3 ተከላካዮች፤ 3 አማካዮችና 2 አጥቂዎችን በማስመልመል ብቸኛው ነው፡፡

የስፔን ብሄራዊ ቡድን ባለፉት 4 ዓመታት በዓለም እግር ኳስ ላሳየው የበላይነት ቲኪ ታካ የተባለ የጨዋታ ታክቲክ ዋናው ምክንያት ነው ፡፡ ይሄው አጨዋወት ለከፍተኛ ትችት ቢጋለጥም በባለጋራዎቹ አንድ ጎል ብቻ ተቆጥሮበት፤ ከሁሉም ቡድኖች የተሻለ 12 ጎሎችን አግብቶና ብዙ ኢላማቸውን የጠበቁ የጎል ሙከራዎች አድርጎ፤ በኳስ ቁጥጥር ከየትኛው ብሄራዊ ቡድን የተሻለ ብልጫ አሳይቶና እስከዋንጫው ድል ለእያንዳንዱ ተጋጣሚ አስጨናቂ ብቃት አሳይቶ የስፔን ብሄራዊ ቡድን ዋንጫውን ማንሳቱ አሳማኝ ሆኗል ፡፡

አንዳንድ መረጃዎች ቲኪ ታካ ወደ እግር ኳስ አስደናቂ ውበትን አምጥቷል፤ በስፖርቱ ከጉልበትና ፍጥነት ባሻገር ሌሎች የላቁ ቴክኒኮች መኖራቸውን አመልክቷል ይላሉ ፡፡የእንግሊዝ ፤የጣሊያንና የሩስያ ሚዲያዎች እንዲሁም የዩክሬን ስፖርት አፍቃሪዎች ደግሞ አጨዋወቱን የሚያሰለች፤ ዓለማ ቢስ እንቅስቃሴ እና የእግር ኳስን የፉክክር ደረጃ ያደበዘዘ ብለው አውግዘውታል፡፡ የስፔን ቲኪ ታካ የጨዋታ ስልት የጣሊያንን የመከላከል አደረጃጀት፤ የጀርመንን ታታሪ አጨዋወት እንዲሁም የሆላንድን ሁሉንም ተጨዋች የሚያሳትፍ የቶታል ፉትቦል አዋህዶ የያዘ ነው በሚልም ተወድሷል፡፡

የስፔን ብሄራዊ ቡድን ከሁለት ዓመት በኋላ ብራዚል በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የበላይነቱን ማስጠበቁ አይቀርም የሚለው ግምትም የተለያያዩ የመከራከርያ አጀንዳዎችን እየፈጠረ ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች ለስፔን ብሄራዊ ቡድን አጨዋወት በአውሮፓ የጀርመን፤ የጣሊያንና የሆላንድ ብሄራዊ ቡድኖች ምላሽ እንደሚኖራቸው ቢተነብዩም ብዙዎች ማርከሻውን ብራዚል ታመጣለች ብለው ተስፋ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በ1970ዎቹ ከነበረው የብራዚል ብሄራዊ ቡድን የአሁኑ የስፔን ብሄራዊ ቡድን እንዴት እንደሚያነፃፅር የተጠየቀው የእግር ኳሱ ንጉስ ፔሌ በሰጠው ምላሽ እሱ የነበረበትና ሳምባ ፉትቦል የተባለውን የጨዋታ ስልት ያሳየው የብራዚል ቡድን የላቀ ተሰጥኦ ባላቸው ተጨዋቾች ብዛት መሻሉን በልበሙሉነት ተናግሯል፡፡

በ1970ዎቹ ፔሌን ጨምሮ እነ ጌርሰን፤ ቶስታዎ፤ ሬቬሊኖ፤ ካርሎስ አልቤርቶ የነበሩበት የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ሜክሲኮ ያስተናገደችውን ዓለም ዋንጫ ያሸነፈው በፍፃሜ ጨዋታ ጣሊያንን 4ለ1 በማሸነፍ ነበር፡፡ ፔሌ እኔ ያለሁበት የያኔው የብራዚል ቡድን ከዛሬው የስፔን ቡድን ጋር ቢጫወት ማሸነፉን አልጠራጠርም ብሏል፡፡

 

 

 

Read 1618 times Last modified on Saturday, 07 July 2012 11:06