Saturday, 18 April 2020 14:43

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሳይንሳዊ መረጃን ያገናዘቡ እንዲሆኑ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ኮሮናን ለመከላከል የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተንተርሶ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን መሰረት ያደረጉ ብቻ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
ኮሚሽኑ “ይድረስ ለመንግሥት” ሲል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአተገባበር በኩል ጥንቃቄ ያሻዋል ሲል ምክረ ሀሳቦችን በዝርዝር ባቀረበበት መግለጫው፤ በዋናነት በአዋጁ መነሻ የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደየ አካባቢው ሁኔታ ተመጣጣኝና ሳይንሳዊ እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡ አዋጁ ለታለመለት አላማ ብቻ መዋል እንዳለበትም ገልጿል - ኮሚሽኑ፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚደረግ የመብት እገዳም ሆነ ማናቸውም ሌላ እርምጃ በዘር በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በቋንቋ ወይም በመሰል ሁኔታ ምንም አይነት አድሎዎና ልዩነት እንዳይደረግም አሳስቧል - ኮሚሽኑ፡፡
መንግሥት አዋጁን ሲያስፈጽም አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ደረጃን የጠበቀ መሆን ይገባዋል ያለው ኮሚሽኑ፤ በዚህ መሰረትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት ገደብ የተጣለባቸውን መብቶች ዝርዝር ከነምክንያቱ እንዲሁም ገደቡ የሚያልቅበትን ጊዜ ጭምር በግልጽ በተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አማካኝነት ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቅ ግዴታ አለበት ብሏል፡፡ ይህም በአፋጣኝ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡ አዋጁ በሚቆይባቸው ጊዜያት ምንም እንኳ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በጊዜያዊነት ተገድበው የሚቆዩ ቢሆንም መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት የሆኑት ግን ፈጽሞ ገደብ ሊደረግባቸውም ሊጣሱም አይገባም ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ ገደብም ሆነ ጥሰት ሊፈጸምባቸው አይገባም ብሎ  የዘረዘራቸው መብቶችም በሕይወት የመኖር መብት፣ ኢ - ሰብዓዊ አያያዝ ክልክል መሆኑ፣ የእኩልነትና የሕግ ጠበቃ የማግኘት መብት፣ የሃይማኖት፣ የማሰብና የሕሊና ነፃነት መብቶች፣ የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ የማያሰራ የመሆኑ ጉዳይ እንዲሁም የፍትሃ ብሄር የውል ግዴታን ባለመፈፀም ምክንያት ያለመታሰር መብት ናቸው፡፡
አዋጁን የሚያስፈጽሙ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ተግባራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት በከፍተኛ ሃላፊነት የሃይል እርምጃ ከመውሰድ በመቆጠብ፣ ከቀጪነት ይልቅ በአስተማሪነት መንፈስ መመራት እንደሚገባቸውም ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል፡፡ የዳኝነቱ አካልም በነፃና ገለልተኝነት እንዲንቀሳቀሱና ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ሊቆሙ ይገባል ብሏል - ኮሚሽኑ፡፡   

Read 9904 times