Saturday, 18 April 2020 14:45

ለትንሣኤ በዓል ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን እንዲገኙ ፓትሪያሪኩ ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ለትንሣኤ በዓል ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ተገኝተው፣ በልዩ ጥንቃቄ ያከብሩ ዘንድ በልዩ ሁኔታ እንዲፈቀድ ፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ አቀረቡ፡፡
ፓትሪያሪክ አቡነ ማትያስ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፃፉት ደብዳቤ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱና ምዕመኖቿ፣ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ ያወጣውን አዋጅ አክብረው እየተንቀሳቀሱ መሆኑንና ቤተ ክርስቲያኒቱም የመንግስትን ሀገር የማዳን እንቅስቃሴ በጽኑ ደግፋ ኮሚቴና ግብረ ሃይል አዋቅራ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ምዕመናንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሄድ በመታቀብ፣ በየቤታቸው በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ የፀሎት ስነ ስርዓቶች ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ ያስታወሱት ፓትሪያሪኩ፤ ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና የሚያዛቸውን ተግባራት መፈፀም ይችሉ ዘንድ በልዩ ሁኔታ ምዕመናን በቤተክርስትያን የሚገኙበት ሁኔታ እንዲፈቀድ ጠይቀዋል፡፡
ምዕመናን በፆሙ ማጠቃለያ ሊፈጽሙት ከሚገባ ሃይማኖታዊ ቀኖና አንዱና ዋነኛው የሆነው የቁርባን መቀበል መሆኑን ያመለከቱት ፓትሪያሪኩ ይህም በአካል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ሊፈጽሙት የሚገባ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ይህን ተግባር ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምዕመኖቹ ጋር ተገቢውን የጤና ዋስትና፣ ምክርና ጥንቃቄ በተከተለ መልኩ እንድትፈጽም ይፈቀድላት ዘንድ በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከመንፈሳዊ አገልግሎት ይልቅ ቫይረሱን የመከላከል ስራን ጥያቄ ውስጥ የከተተው በተጨናነቀ ሁኔታ የሚካሄዱ ግብይቶች፣ አውራ ጐዳና የሞሉ መንገደኞችና የመጓጓዣ ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች እንደሆኑ አቡነ ማቲያስ በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል፡፡
ምዕመናን በቤተእምነቶች ተገኝተው አምልኳቸውን ከመፈፀም እንዲታቀቡ የተደረገው ሰዎች በብዛት ተሰባስበው ስለሚገኙና የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ያስፋፋዋል ተብሎ በመስጋቱ እንደሆነ አይዘነጋም፡፡  

Read 9913 times