Saturday, 18 April 2020 14:48

ዓለም በሩንም ደብሩንም ዘግቶ ያከበረው ትንሳኤ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

   “የዘንድሮን ትንሳኤ በዓል ስናከብር፣ መጪውን በጎ ዘመን እያሰብን መሆን አለበት”

             የጸሎተ ሐሙስ የካህናት ተምሳሌታዊ እግር አጠባና ቅዳሴ፣ ብዙዎችን የሚያሰባስበው አስደማሚው የዕለተ ስቅለት ስግደት፣ ማራኪው የቅዳሜ ሌሊት የቤተ ክርስቲያን ስነ ስርዓት፣ ደማቁ የትንሳኤ በዓል፣ የዓውደ አመት ሰሞን ሃይማኖታዊ ስርዓትና በሽር ጉድ የታጀበ የበዓል አከባበር ዘንድሮ፣ ለአብዛኛው የአለም ህዝበ ክርስቲያን የሚታሰብ አልነበረም፡፡
ኢትዮጵያውን ነገ የምናከብረውን የትንሳኤ በዓል፤ በአብዛኞቹ የዓለም አገራት የሚገኙ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ባለፈው እሁድ 12 ነበር፣ ከወትሮው በተለየ መልኩ በየቤታቸው ተዘግተው በተቀዛቀዘ ስሜት ያከበሩት፡፡
አለምን ክፉኛ እየፈተነ በሚገኘው የኮሮና ቫይረሰ ወረርሽኝ ሳቢያ በተለያዩ አገራት የሚገኙ እጅግ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች፣ የዘንድሮውን ትንሳኤ በዓል፣ በአብያተ ክርስቲያናት ታድመው በድምቀት ያከብሩት ዘንድ አልታደሉም፡፡ ካህናትና ቀሳውስት ያለ ወትሯቸው አንድም ሁለትም ሆነው የሚፈጽሙትን ስርዓተ ቅዳሴና ስብከት፣ በየቤታቸው ሆነው በቴሌቪዥን መስኮት እየተከታተሉ፣ ከመጣው የጥፋት ማዕበል እንዲያተርፋቸው፣ ለፈጣሪያቸው ጸሎታቸውን ከማድረስ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡
ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ፣ ከእስያ እስከ አፍሪካ በበርካታ የአለማችን አገራት በትንሳኤ ሳምንት በተለየ ሁኔታ በምዕመናን ይጥለቀለቁና ድምቀትን ይጎናጸፉ የነበሩ እጅግ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት፣ ዘንድሮ ግን በሮቻቸው ተዘግተው አልያም ባልተለመደ መልኩ ጭው ጭር ብለው ነው ሳምንቱን ያሳለፉት፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአለም አገራት መንግስታት፣ ዜጎች ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ ከቤታቸው እንዳይወጡ ወይም መሰል ሃይማኖታዊ ስነስርዓቶችን በጋራ እንዳይከውኑ አስገዳጅ ህግ በማውጣታቸው፣ በአብዛኞቹ አገራት አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋል፤ ምዕመናንም አምልኳቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲፈጽሙ ተገድደዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በአገራችን የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮችም ዘንድ ተመሳሳይ ተጽዕኖ ነው የፈጠረው፡፡ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በወሰዳቸው እርምጃዎች፣ ቤተ ዕምነቶች ተዘግተው፣ ምዕመኑ፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በቤቱ ተቀምጦ በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት መከወን ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡
ነገር ግን በትንሳኤ በዓል ሰሞን የቤተ እምነቶች ደጃፍ ተዘግተው የሚያወቁበትን ጊዜ ከቶ ማንም አያስታውስም፡፡ በዚህ በ"ዘመነ ኮሮና" ጊዜ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፣ ቤተ ክርስትያናት ተዘግተው ምዕመኑ ቤት ሆኖ በዓሉን የሚያከብረው፡፡መጋቢ ሠላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ፣ የቤተ ክርስትያን ደጃፎች፣ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በትንሳኤ በዓል፣ በራቸው መዘጋታቸውን አስመልክቶ ሲናገር፤ "ከቤተ ክርስትያን ጋር ትውውቄ ከ4 እና 5 ዓመት ዕድሜዬ ጀምሮ ነው፤ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ደጆች የተዘጉበት ጊዜ ገጥሞኝ አያውቅም፤የዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤በእውነቱ በሆነው ልቤ በጣም ነው የተሰበረው፡፡"ብሏል፡፡
"በፖሊስ ገመድ ዙሪያው ታጥሮ፣ ማንም እንዳይገባ ተከልክሎ ሲታይ ልብ ይነካል፡፡ መንግሥት፤ እርግጥ ነው ለዜጎቹ ደህንነት የመጨነቅ ሃላፊነት አለበት፡፡ ይሄን ካላደረገ ነገ በትውልድም በታሪክም ይጠየቃል። ከዚህ አንፃር መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ትክክል ናቸው፡፡" ይላል፤ቀሲስ ሰሎሞን፡፡
የበሽታው መድሃኒት አልተገኘም፡፡ስለዚህ መፍትሄ ሆኖ የተገኘው ከቤት አለመውጣት፣ አለመሰባሰብ፣ ንጽህናን መጠበቅ፣አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ነው፤ እነዚህን ማድረግ ነው ለጊዜው መድሃኒቱ፡፡" ሲል ይመክራል፡፡
ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው፤ "የዘንድሮን ትንሳኤ በዓል ስናከብር፣ መጪውን በጎ ዘመን እያሰብን መሆን አለበት፡፡" ይላሉ፡፡ ሁለቱም የሃይማኖት መሪዎች በኮሮና ቫይረስ፣ በትንሳኤ በዓልና በቤተእምነቶች ደጃፍ መዘጋት ዙሪያ የሰጡትን ሙሉ ቃለ ምልልስ በገጽ-- ያገኙታል፡፡


Read 11123 times