Saturday, 18 April 2020 14:49

(COVD--19) ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከል፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

       በአለም አቀፍ ዙሪያ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የያዘው እና ከ70/ሺህ በላይ ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት የሆነው የኮሮና ቫይረስ በእርጉዝ ሴቶች እና ጨቅላዎቻቸው ላይ ሊያስከትለው የሚችለው የተለየ ችግር ይኖር ይሆን? ለሚለው ጥርጣሬ መልስ የሚሆን የባለ ሙያዎችን ግኝት ማስነበብ ከጀመርን እነሆ ሶስተኛው እትም ላይ ደርሰናል፡፡
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በእርግዝና ወቅት ተፈጥሮአዊ የሆነ የሰውነት ለውጥ ስለሚኖር ለበሽታ የመጋለጥ እድሉ እርጉዝ ካልሆኑት የበለጠ ሊጨምር ይችላል፡፡ ስለዚህም በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች በቫይረሱ ከተያዙ በከፍተኛ ሁኔታ ሊታመሙ ይችላሉ የሚለውን ግምት አስቀድሞ በመውሰድ ጥንቃቄውን መውሰድ ይገባል፡፡ ለምሳሌም ቀደም ሲል ጉንፋንን በሚመለከት በአገራችን እርጉዝ ሴት ጉንፋን ከያዛት ቶሎ አይለቃትም የሚል የተለምዶ አባባል እንደነበር አይዘነጋም:: ስለዚህም በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች አካባቢ እራሳቸውን ማራቅ እንዲሁም በአጠቃላይ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የጥንቃቄ መልእክቶች ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ባለፈው እትም የኢትዮፐጵያ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ማህበር ከኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስ ቴርና ከሚድዋይፍ ማህበር ጋር በመተባበር አዘጋጅቶ ያወጣውን እርጉዝ ሴቶች ሊያደርጉዋ ቸው የሚገቡትን ጥንቃቄዎች ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ከ1-9 ተራ ቁጥር ያሉትን ነጥቦች እንዳነበባችሁ በማመን በዚህ እትም ደግሞ ከ10-16 ያሉትን ምክሮች እነሆ ለንባብ ብለናል፡፡
የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ኢንፌክሽንና እርግዝና ፤በኢትዮጲያ የማህጸንና ፅንስ ሐኪሞች ማህበር የተዘጋጀ፡፡  
10. በኮሮና ቫይረስ የተያዘች ወይንም የኮሮና ቫይረስ ምልክትን ያሳየች ነፍሰጡር ሴት የት መውለድ አለባት?
ለጥንቃቄ ሲባል በኮሮና ቫይረስ የተጠቃች ወይንም ምልክቶቹን ያሳየች ነፍሰጡር ሴት ምጧ በመጣ ጊዜ ለእርሷም ሆነ ለጽንሱ አስፈላጊውን ህክምና ለመስጠት በተዘጋጁ የህክምና ማእከላት ውስጥ መውለድ ይኖርባታል፡፡ አዲስ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳብ እስኪመጣ ድረስም ይህ እንዲሆን ይመከራል፡፡
11. በኮሮና ቫይረስ የተያዘች ወይንም የኮሮና ቫይረስ ምልክትን ያሳየች ነፍሰጡር ሴት በምጥ መውለድ ትችላለች?
በአሁን ሰአት በኮሮና ቫይረስ የተያዘች ወይንም የኮሮና ቫይረስ ምልክትን ያሳየች ነፍሰጡር ሴት በምጥ እንዳትወልድ የሚከለክል ምንም አይነት ሳይንሳዊ መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን ከህመሙ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የመተንፈስ ችግር ካላት፤ በኦፕሬሽን መውለድ አስፈላጊ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡
12. ኮሮና ቫይረስ ወደ ህፃን ልጅ ይተላለፋል?
ይህ በሽታ አዲስ እንደመሆኑ መጠን በቂ ጥናቶች ባይኖሩም እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት የኮሮና ቫይረስ በሽርት ዉሃም ሆነ በእትብት ደም ውስጥ አልተገኘም፡፡ እንደሌሎች የመተንፈሻ አካላት የቫይረስ በሽታዎች ሁሉ በእርግዝና ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ አይተላለፍም ተብሎ ይገመታል፡፡
13. የተወለደው ጨቅላ ህፃን ለኮሮና ቫይረስ ምርመራ ይደረግለታል?
አዎ ይደረግለታል። በኮሮና ቫይረስ ከተያዘች ወይንም የኮሮና ቫይረስ  ምልክቶች ካላት እናት የተወለደ ህፃን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲደረግለት ይመከራል፡፡
14. የበሽታውን ምልክቶች ካሳየች ወይንም በኮሮና ቫይረስ ከተያዘች እናት ለተወለደ ልጅ ምን አይነት ጥንቃቄ ይደረጋል?
ህፃኑ በደህና ሁኔታ እስከተገኘና በጨቅላ ህፃናት ማቆያ ክፍል ክትትልና ህክምና የሚያስፈል ገው እስካልሆነ ድረስ ህፃኑ ከእናትየው ጋር እንዲቆይ ይመከራል፡፡  
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በምርመራ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ያለባት እናት ከወለደች በኋላ ህፃኑን ለ14 ቀናት ያህል ከእናትየው ተለይቶ እንዲቀመጥ ይመክራሉ፡፡ ነገር ግን ልጅን ከእናት መለየት በህፃኑ አመጋገብና ጡት ማጥባት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል፡፡ በመሆኑም እንደዚህ አይነት ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ከሃኪም ምክር መጠየቅ ይገባል፡፡
15. የኮሮና ቫይረስ በሽታ የተገኘባት እናት ወይም የበሽታውን ምልክቶች ያሳየች እናት ጡት ማጥባት ትችላለች?
እስካሁን ባሉ መረጃዎች የ ኮሮና ቫይረስ በጡት ወተት ውስጥ አልተገኘም፡፡ የጡት ወተት የህጻንን የሰውነት ከበሽታ የመከላከል አቅምን ይጨምራል፡፡  በመሆኑም በአጠቃላይ ጡት ማጥባትይመከራል፡፡
ጡት በሚጠባበትም ጊዜም የሚከተሉት ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ ይመከራል፦
ከማጥባት በፊት እጇን በአግባቡ መታጠብ፤
በህጻንኑ/ዋ ላይ በቀጥታ ከማስነጠስና ከማሳል መቆጠብ፤
ከህጻኑ/ዋ ጋር በምትሆንባቸው ጊዜዎች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ፤
በተለያይ ምክንያት ጡት ማጥባት ከተከለከለ የጡት ወተትን በማለብ ህጻኑን/ዋን መመገብ ይቻላል፡፡ የጡት ወተት በሚታለብበት ጌዜ የሚከተሉት ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ ይመከራል፦
የጡት ወተት ከማለብ በፊት እጅን በአግባቡ መታጠብ፤
የጡት ወተት ለማለብ የተጠቀምንበትን ቁስ/መሳሪያ ካለ በደንብ ማጠብ፤
የታለበውንም ወተት ለህጻኑ/ኗ ለማጥባት ከኮሮና ቫይረስ ነጻ የሆነ ሰው ቢሆን ይመከራል።  
16. ነፍሰ ጡር የሆነች የጤና ባለሙያ ማድረግ የሚገባት ጥንቃቄ ምንድነው?
በጤና ተቋም በስራ  ላይ ያለች እርጉዝ የጤና ባለሞያ  በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንደምትሆን ይታወቃል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት እርጉዝ የሆኑ የጤና ባለሞያዎች እርጉዝ ካልሆኑ የጤና ባለሞያዎች ጋር ሲነፃፀሩ ለቫይረሱ የተለየ ተጋላጭነትም ሆነ ለከፋ ህመም የመጋለጥ እድል የላቸውም፣ ሆኖም በኮሮና ቫይረስ ከተጠቃ ወይንም ከተጠረጠረ ህመምተኛ ጋር ያላትን ቅርበት መቀነስ ይኖርባታል፡፡
በአጠቃላይ
የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ኢንፌክሽንና እርግዝናን በተመለከተ አዳዲስ መረጃዎች በየጊዜው ይወጣሉ። ስለሆነም የኢትዮጲያ የማህጸንና ፅንስ ሐኪሞች ማህበር ወቅታዊ የሆኑ ሳይንሳዊ መረጃዎችንና መመሪያዎችን ለህብረተሰቡና ለጤና ባለሙያዎች በየጊዜው ያሳውቃል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት መመሪያዎች ተጨማሪ የጥናት ግኝቶች ሲኖሩ ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይችላል።
COVID-19 የኮሮና ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ ስለመተላለፉ ከላይ ካነበባችሁት በተጨማሪ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት እስከአሁን በታየው መረጃ መሰረት ቫይረሱ በእርግዝና ወቅት ሊተላለፍ አይችልም የሚል እሳቤ ቢኖርም ህጻኑ ከተወለደ በሁዋላ ግን ልክ ሌሎች ሰዎች ሲነካኩ ቫይረሱ ሊተላለፍ እንደሚችል ሁሉ እናት ለልጅዋም ወይንም ቤተሰብ በንክኪ ቫይረሱን ለተወለደው ልጅ ሊያስተላልፉ የሚችሉ መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል የሚለውን ማሳሰቢያ የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ለአንባቢ በድጋሚ ማስታወስ ይፈልጋል፡፡  

Read 11429 times