Saturday, 18 April 2020 14:54

የኢትዮጵያ የሺ ዓመታት አይበገሬነትን እናስከብር

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

  • ኢትዮጵያ፣ የጥንት ስልጣኔን የሚያስታውሱና መንፈስን ለሚያነቁ የስልጣኔ “ቅርሶች”ን በብዛት የታደለች አገር ናት። ልናከብራቸውና ልንጠቀምባቸው         ይገባል።
    • በአድናቆትና በክብር ሊወደሱ የሚገባቸው የዘመናዊ ስልጣኔ አርአያዎችም አሏት - አገራችን። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
    • ብዙ የስልጣኔ ገጽታዎችን በማሟላት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚስተካከል፣ የስልጣኔ አርአያ በአገራችን አለ?
    • በኢትዮጵያ እጅግ የላቀ ብቃት የሚታይበት ሙያ የትኛው ነው ብላችሁ ጠይቁ። የሕክምና ሙያን የሚስተካከል አለ?
              
              ለእውነተኛ መረጃ፣ ለሳይንሳዊ ዘዴና ለእውቀት፣ ቀዳሚ ክብር የሚሰጥ ስልጡን ባህል፤ ትልቁ የ“መኖሪያ ሃይል” ብቻ ሳይሆን፣ ትልቁ የአገር ስንቅም ነው።
“ስልጡን ባህል”፣ የማይጨበጥ ጉም አይደለም። በሀሳቦች ተዘርዝሮ፤ በተግባር ይመነዘራል። ግን፣ ተበትኖ አይቀርም። በእያንዳንዱ ሰው ጥረት፤ ዝርዝር ሃሳቦች በቅጡ እየተዋሃዱ፣ የዕለት ተዕለት ተግባራትም እየተደመሩ፣ በእውን የሚታይ ውጤት ያስገኛሉ። በእውቀትና በሙያ፣ በስኬትና በኑሮ መሻሻልን፣ ወደ ብልጽግና መራመድን ያመጣሉ። ይህም ብቻ አይደለም። መልካም ባህርይንና ብቁ ሰብዕናን የሚቀዳጁ ሰዎች ይበራከታሉ።
ይሄ ሁሉ፣ ለዘወትር ኑሮ የሚያገለግል ዋና የሕይወት ኃይል ነው። በአደጋ ጊዜ ደግሞ፣ ትልቅ ስንቅ ይሆናል። ድሃ አገራት፣ ለእንዲህ አይነት ስልጡን ባህል ሩቅ ናቸው።
በርካታ መረጃዎችን፣ የእውቀትና የሙያ ዓይነቶችን፣ ብዙ ሰዎችንና መሳሪያዎችን፣ በርካታ ስራዎችንና ግብአቶችን፣ እንደየባህርያቸው በፈርጅ ጠቅልሎ፣ በዝርዝርም ተንትኖ፣ ዋና ዋና አስኳሎችን ጨብጦ፣ ተጓዳኞችንም አሟልቶ፣ በአጠቃላይ፣ አቀናጅቶና አቀናብሮ፣ ‹‹በነቢብና በገቢር›› የመጓዝ ተቋማዊ ብቃት፤ አንደኛው የስልጡን ባህል ስንቅ ነው።
በዚህም ምክንያት፤ እንደ  ሜርሰድስ ኩባንያ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ሆስፒታሎችን በቴክኖሎጂና በሙያ ሊያግዝ እንደሚችል ጥርጣሬ አልነበረኝም። የመተንፈሻ መሳሪያዎችን በሚመለከት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በስተቀር፣ ብቃት ያለው ሌላ ተቋም በአገራችን የለም። ይሄ የእውቀትና የሙያ ስልጣኔ ነው።
“ምን? ወይም ምንን?” ብሎ መጠየቅ በቂ አይደለም። ዝርዝራቸውን ብቻ ሳይሆን ትስስራቸውንም፣ ማገናዘብ ያስፈልጋል። ምንና ምን? ምንን ከምን? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ከነትስስራቸው አሟልቶ የመገንዘብና የመስራት ብቃት፣ የስልጣኔ ደረጃን ያመለክታል።
ከዕለት ተዕለት ባሻገር፣ የሳምንትና የወር፣ ከዚያም አልፎ የአመትና የረዥም ጊዜ ጉዳዮችን አሰናስሎ፣ በቅድመ ዝግጅትና በቅድመ ተከተል፣ በስራ ድርሻና በጊዜ ሰሌዳ አሰናድሎ፣ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን አሟልቶ፣ ሥራን ጠንቅቆና አስተካክሎ ለማሳለጥ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት፣ ሁለተኛው የስልጡን ባህል ስንቅ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድን አሰራር የሚያውቅ ሰው፣ የዚህ ትርጉም ይገባዋል።
 እንዴት? በምን? ከሚሉ… የአሰራር፣ የመንገድ፣ የሥነ ሥርዓት ጉዳዮች አንፃር፣ ከዋና የስነምግባር መርህ ጀምሮ እስከ እለታዊ የሥራ ሰዓት ክትትል ድረስ፣ ሁሉንም ነገር አዋድዶ የሚያሳልጥ ሥርዓት፣ የስልጣኔ ደረጃን ይመሰክራል።
ዋና አላማና ንዑስ ግቦችን፣ ቅድመ ሁኔታዎችንና ጊዜያዊ መሸጋገሪያዎችን፣ የእለት ተእለት ውጤቶችንና የረዥም ጊዜ እቅዶችን በአግባቡ አስተሳስሮና አመጋግቦ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ደረጃ በደረጃ ወደ ላቀ ስኬት ለመገስገስ አነጣጥሮ፣ ሃላፊነትን የመውሰድና በጽናት የመምራት ብቃት፣ ሦስተኛው የስልጡን ባህል ስንቅ ነው።
‹‹ወዴት ለመጓዝ? ለምን አላማ?›› በሚሉ ጥያቄዎች አማካኝነት፤ ሁሉንም ነገር አቀናብሮ (ደምሮ)፣ በምልዓት ራስን ወይም ተቋምን የመምራት ብቃት፣ የስልጣኔ ደረጃን ያሳያል።
ደሃና ኋላቀር አገር መሆን ማለት፣ የስልጡን ባህል እጥረትና የስንቅ እጦት ማለት ነው። ወደ ስልጡን ባሕል ያልገሰገሰና ብዙ የሚቀረው ማለት ነው - ኋላቀር አገር ማለት። ችግሩ ደግሞ ስልጡን ባሕል በአንድ ጀንበር የሚበቅል አይደለም፤ በአመት በሁለት ዓመትም አይታነጽም። ረዥም ጊዜ ይፈጃል።
እንዲያም ሆኖ፤ ደሀና ኋላቀር አገራት፣ ቅንጣት የስልጡን ባሕል ገጽታ የላቸውም ማለት አይደለም። አላቸው። ሌላው ቢቀር፤ አገርና መንግሥት፣ ሕግና ሥርዓት የሚባሉ ነገሮች፤ አነሰም አጠረ፣ የስልጣኔ ምልክቶችና ውጤቶች ናቸው።
የመረጃ መቀባበያ አውታሮችና የትምህርት ማዕከላት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የምርትና የገበያ ተቋማት፣ የአካልና የአእምሮ ጤና፣ የነፍስና የመንፈስ ማደሻ ኪነጥበብ፣ መዝናኛ የስፖርት ውድድር፣… የተሰኙ ነገሮች በየአገሩ አሉ። በአፍሪካና በአረብ አገራት፣ ገና ደካማ ቢሆኑም እንኳ፤ እነዚህ ነገሮች ፋይዳ አላቸው። የስልጣኔ ፍንጮች ናቸው።
ኢትዮጵያ ደግሞ፣ ከእነዚህም በላይ ሌሎች እጅግ ውድ የስልጣኔ ገጽታዎች አሏት።
የስልጣኔ “ቅሪት”፣ የስልጣኔ “ቅርስ”።
ከቀዳሚዎቹ ‹‹የስልጣኔ ፋና ወጊ›› አገራት መካከል አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ለሺ ዓመታት የኋሊት ብትንሸራተትም፤ ጠፍታ አልጠፋችም።
ለምን? ሙሉ ለሙሉ ለመራቆትና የስልጣኔ ታሪክን እስከናካቴው ለመርሳት ፈቃደኛ ያልሆኑ በርካታ አዋቂዎች፣ ብልሆችና ጀግኖች በየዘመኑ የአቅማቸውን ያህል ጥረዋል። የምኞታቸው ያህል ወደ ስልጣኔ ለመገስገስ ባይሳካላቸውም፤ ጥረታቸው መና አልቀረም። ቢያንስ ቢያንስ፣ ለሁለት ሺህ ዓመታትና ከዚያ በላይ በሕልውና ከዘለቁ ጥቂት አገራት መካከል፣… በጣት ከሚቆጠሩ አይበገሬ አገራት መካከል አንዷ ናት - ኢትዮጵያ።
ወደ ስልጣኔ ጐዳና የመመለስ ተስፋዋም ጨርሶ አልጨለመም። ዋናውን ስልጣኔ ብታጣም፣ እስክታገግም ድረስ፣ መንፈስን ከሚያነቁ ውርሶች፣… ከስልጣኔ ምልክቶችና ከቅርሶች ጋር አልተቆራረጠችም። አዎ፤ ቅርሶቹ፣ የቀድሞ ስልጣኔ “ቅሪቶች” ናቸው። ግን ለስልጣኔ የሚያነቁ የዘወትር ህያው አስታዋሽ ናቸው - እንደ ምክር እንደ ተግሳጽ።
ኢትዮጵያ፣ ከእውቀት ጋር ብትራራቅም፤ ለእውቀትና ለትምህርት አንዳች የአክብሮት ስሜት የማሳየት አዝማሚያ፣ ዛሬም ድረስ ከአገራችን አልጠፋም። በጠንካራና በትክክለኛ መሰረት ላይ በቅጡ የተዋቀረ የመልካም ስነምግባር መርህና ባሕርይ ቢሸረሸርም፤ በጥቅሉ ‹‹የጨዋነት›› ቅርስ ግን፣ ዛሬም ድረስ ዘልቋል።
ከዚህም በተጨማሪ፤ “ለራስና ለቤተሰብ ኑሮ”፣ የግል ኃላፊነትን የመውሰድ አኗኗር፣ በተወሰነ ደረጃ ጥሩ ልማድ ሆኗል። በእርግጥ የግል ኃላፊነትን መውሰድ፣ ትክክለኛ የክብር ምንጭ እንደሆነ በግልጽ አይታወቅም፤ የሚገባው ያህል አድናቆት አይሰጠውም። ቢሆንም ግን፣ የማሳውን ወሰን ሳይሻገር በራሱ ጥረት አርሶ በሚያመርት አንድ የገበሬ ቤተሰብ ውስጥ የምናየው አኗኗር፣ “የግል ኃላፊነት”ን የሚያሳይ የአኗኗር ልማድ ነው።
የሰው ማሳ ላይ ሳይደርስ፣ የራሱንም በንቃት ይዞ፣ የአቅሙን ያህል በጥረቱ አምርቶ፣ ለገበያም አቅርቦ፣ እንደ አቅሚቲ በጐተራ ቆጥቦ አመቱን የሚዘልቅ ገበሬ፣… ለራሱ ቤተሰብ የግል ኃላፊነትን ወስዷል ማለት ይቻላል። ለቀጣይ ዓመት እርሻውም፣ ዘር መርጦ ያዘጋጃል። ከጐረቤት ሳይቆራረጥ፣ ግን ደግሞ የራሱን ጐጆ ቀልሶ፣ እንደወጉም አጥር ሰርቶ፣ ራሱንና ቤተሰቡን የሚያስተዳደር ሰው፣ ‹‹የግል ኃላፊነትን የመውሰድ›› መልካም የስልጣኔ ገጽታን ያሳየናል።
ለራስና ለቤተሰብ ኑሮ፣ የግል ኃላፊነትን ወስዶ መስራት፣ ትልቅ የስነምግባር መርህና የክብር ምንጭ እንደሆነ በግልጽ አለመታወቁ ነው የጐዳን። ከስልጣኔ ባህል ያራራቀን። እንዲያም ሆኖ እንደ ልማድ እንደውርስ፣ ያ የስልጣኔ ገጽታ ዛሬም አለ። የስልጣኔ ቅርስ ነው።
በደል ሲደርስበት፣ አቤቱታ ያቀርባል፤ በሕግ አምላክ፤ ፍረዱኝ ብሎ ይከራከራል። ፍትህ ባያገኝ እንኳ፣ “የፍትህ መንገድ”፣ “የህግ መንገድ” እንደሆነ፤ በጥቅሉ ይሰማዋል። ጐረቤቶቼና የወንዜ ልጆች ለኔ ይወግናሉ ብሎ፤ እንዳሻው ወንጀል ለመፈፀም የሚደፍር ኢትዮጵያዊ ጥቂት ነው - በአመጽና በግርግር ወቅት ካልሆነ በቀር። ይሄም የግል ማንነትንና የግል ሃላፊነትን የሚያሳይ የስልጣኔ ቅርስና ጭላንጭል ነው።
ለእውነት፣ ለእውቀትና ለትምህርት፣ …ለጨዋነት፣ ለሰው ማሳና ለግቢ አጥር፣…ለህግና ለፍትህ፣ ለግል ማንነትና ለግል ኃላፊነት በተወሰነ ደረጃ ወይም በዘልማድ ክብር መስጠት፣  የተወሰነ ያህል ቦታ መስጠት፣ የተሟላ ስልጣኔ አይደለም። ነገር ግን፣ የስልጣኔ ገጽታ ነው። የድሮ የስልጣኔ ታሪክን የሚያስታውሱ፣ የወደፊት የስልጣኔ እድልን የሚያመላክቱ እንዲህ ዓይነት የስልጣኔ ቅርሶች በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ።
እነዚህን ቅርሶችና ጭላንጭሎችን ከሚያዳፍኑ ፀረ ስልጣኔ “የጭፍንነት፣ የምቀኝነትና የመንጋ አስተሳሰቦች” መቆጠብ እንችላለን። የዚህና የዚያ ሃይማኖት ተከታይ፣ ሃብታምና ድሃ፣ የእገሌና የእከሌ ብሔረሰብ ተወላጅ እያሉ የሚሰብኩ፣ የሚቀሰቅሱና የሚያቧድኑ ክፉ ተግባራትን ለመከላከልም እንጣር። ይሄም ይቻላል።
ከዚህ ጐን ለጐን፣ የስልጣኔ ጭላንጭሎችንና ቅርሶችን፣… ዛሬ፣ መልካም ተግባራትን ለማበረታታት ልንጠቀምባቸው እንችላለን። በረዥሙም፣ ለወደፊት ወደ ስልጣኔ ለመገስገስ፣ መሸጋገሪያ መንደርደሪያ ይሆኑልናል።
ሕያው የስልጣኔ ዘመናዊ አርአያዎችስ?
ኢትዮጵያ፣ ምንም እንኳ በድህነትና በኋላ ቀርነት የተጎዳች ብትሆንም፤ የጥንት ስልጣኔን የሚያስታውሱና መንፈስን ለማነቃቃት የሚያግዙ የስልጣኔ “ቅርሶች” በብዛት የታደለች አገር ናት። ልናከብራቸውና ልንጠቀምባቸው ይገባል።
ይህም ብቻ አይደለም። በአድናቆትና በክብር ሊወደሱ የሚገባቸው የዘመናዊ ስልጣኔ አርአያዎችም አሏት - አገራችን። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ሌሎችም አሉ።
በኢትዮጵያ እጅግ የላቀ ብቃት የሚታይበት የሙያ መስክ የትኛው ነው ብላችሁ ጠይቁ። የሕክምና ሙያን የሚስተካከል አለ? ቁጥራቸው ጥቂት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ ድረስ፣ በአለማቀፍ ስልጡን የሙያ ደረጃ በብቃት የሚሰሩ ሃኪሞች ተፈጥረዋል - በኢትዮጵያ።
ዘርፈ ብዙ የስልጣኔ ገጽታዎችን በማሟላትስ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሚስተካከል፣ አስገራሚ የስልጣኔ አርአያ በአገራችን አለ? አዎ፣ ብዙዎች በአድናቆትና በአክብሮት ነው የሚያዩት። ነገር ግን፣ ለሁሉም የስራ መስኮች እንደ መማሪያ የሚያገለግል ትልቁ የአገራችን የስልጣኔ አርአያ እንደሆነ የተገነዘቡ ሰዎች ብዙ አይደሉም።
የውጭ ወረራን የመከላከል የኢትዮጵያ ህያው የስልጣኔ ገጽታን ጨምረን፣ የህክምና ሙያን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና የአትሌቶችንም አለማቀፋዊ ብቃት ከነስኬታቸው አካትተን፣ “ሚስጥራቸው ምን እንደሆነ” መመርመር ይገባናል።   


Read 1273 times