Sunday, 19 April 2020 00:00

የትንሣኤ በአልና ኮሮና ቫይረስ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ምን ይመክራሉ?

           ምዕመናን በቤተክርስቲያን ባልተሰባሰቡበት ሁኔታ የሚከበረው የዘንድሮ የትንሣኤ በዓል ምን ገጽታ ይኖረዋል? ምዕመናን እንዴት ባለ ሁኔታ በአሉን ሊያከብሩ ይገባል? በእግዚብሔር ማመንና ከኮረና መጠንቀቅ እንዴት ይታረቃሉ በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዶን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የስብከተ ወንጌልና ሃዋሪያዊ ተልዕኮ ኃላፊ መጋቢ ሠላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻን አነጋግሮ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

           ከፀሎት ጐን ለጐን የህክምና “መጪውን በጎ ዘመን እያሰብን በዓሉን እናክብር” ባለሙያዎች የሚመክሩትን መተግበር ያስፈልጋል
              እግዚአብሔር ለሃኪሞች ጥበብን፣ ለምድር ፈውስን እንዲያመጣ መለመን አለብን
                            መጋቢ ሠላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ
                               በኢ/ኦ/ተ/ቤተ/የስ/ወ/ሃ/ተ/መ/ሃ
              
    የአምልኮ ቤቶች ትንሳኤን እንዲህ ያለ ምዕመናን ያሳለፉበት የታሪክ አጋጣሚ ተከስቶ ያውቃል?
ሰሞኑን ለአንድ ጉዳይ ማለዳ ተነስቼ ስጓዝ፣ በቤተ ክርስቲያናት ደጃፍ ያልተለመደ ነገር በማየቴ ጥልቅ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ እኔ አሁን ዕድሜዬ 50 አመት ነው። ቤተ ክርስቲያንን ያወቅሁት ከ4 እና 5 ዓመት ዕድሜዬ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን እሄዳለሁ፡፡ በታሪክ እንዲህ ያለ የክርስቲያኖች ቤተክርስትን ቤታቸውም ጭምር ነው፡፡ ስሜቴን የሚጎዳ ጊዜ አላየሁም፡፡ እውነት ልቤ በጣም ነው የተሰበረው፡፡ ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያን ደጆች የተዘጉበት ጊዜ ነው ያጋጠመን፡፡ እርግጥ ሁሉም ቤተ እምነቶች ተዘግተዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ለየት የሚያደርጋት አማኙ ሁሉም ነገሩ የተሳሰረው ከቤተ ክርስቲያኒቷ ግቢ ጋር ነው፡፡ ጠዋትም ማታም ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ይፀልያል፡፡ በክርስትና፣ በፍትሃት፣ በክርስትና አባትና ልጅ ግንኙነት፣ በኪዳን፣ በሰዓታት፣ በቅዳሴ፣ በፀበል በሁሉ ነገር ከቤተ ክርስቲያን ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ለምሳሌ አራዳ ጊዮርጊስን ብንመለከት በዕለተ እሁድ ሰንበት በርካቶች የእምነት ሥርዓታቸውን ከቅፅር ግቢው ተገኝተው ከመተግበራቸው ባለፈ ብዙ የተጣሉ፣ የተቃቃሩ፣ በማህበር የሚወዳጁ ሰዎች ተሰብስበው የሚታረቁበት፣ ማህበራዊ ጉዳያቸውን የሚፈጽሙበት ነው፡፡ ዛሬ ግን ይሄ የለም፡፡ ይሄን ማየት ልብ ይነካል፡፡ እኔ ይሄን ሳይ ጊዮርጊስ በር ላይ መኪና አቁሜ፣ አዝኜ አልቅሼ ነው የሄድኩት፡፡ በፖሊስ ገመድ ዙሪያው ታጥሮ፣ ማንም እንዳይገባ ተከልክሎ ሲታይ ልብ ይነካል፡፡ መንግሥት፤ እርግጥ ነው ለዜጎቹ ደህንነት የመጨነቅ ሃላፊነት አለበት፡፡ ይሄን ካላደረገ ነገ በትውልድም በታሪክም ይጠየቃል። ከዚህ አንፃር መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ትክክል ናቸው፡፡ የበሽታው መድሃኒት አልተገኘም፡፡ ስለዚህ መፍትሄ ሆኖ የተገኘው ከቤት አለመውጣት፣ አለመሰባሰብ፣ ንጽህናን መጠበቅ፣ ማህበራዊ ርቀት መጠበቅ… የሚለው እንኳ አተረጓጎሙ ላይ ችግር አለበት፤ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ነው መባል ያለበት፡፡ እነዚህን ማድረግ ነው ለጊዜው መድሃኒቱ፡፡ እግዚአብሄር ፊቱን ወደኛ መልሶ በምህረት አይኑ እንዲያየን ከመፀለይ ጎን ለጎን፣ እነዚህን መተግበር ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ከልብ የሆነ የእንባ ፀሎት ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ይሄን ጭንቀታችንን አይቶ፣ ለህክምና ባለሙያዎች ጥበብን፣ ለምድር ፈውስን እንዲያመጣ መለመን አለብን፡፡ መንግሥትም እነዚህን ክልከላዎች ሲያደርግ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው ያለው፡፡ ቤተ እምነቶችም ተጠሪነታቸው ለፈጣሪያቸው ነው፡፡ ስለዚህ ለመንፈሳዊ ልጆቻቸው ጥበቃ ማድረግ አለባቸው፡፡ ህብረተሰቡ አሁን አማራጭ አለው፡፡ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እስከ ጥቂት ጊዜ ቤቱ ሆኖ፣ አማኙ ፀሎቱን እምነቱን መፈፀም አለበት፡፡ የክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ቤታቸውም ጭምር ነው። የፀሎት ቤት አላቸው፤ በዚያም እየፀለዩ እግዚአብሄር ምህረቱን እንዲያወርድ መለመን አለብን፡፡
እኛም እውነት ለመናገር ፈተና ውስጥ ነው የገባነው፡፡ መስቀል አናሳልምም ስንል፣ “ግዴለም እኛ እናምንበታለን አሳልሙን” የሚሉ አሉ “መስቀሉን ስመነው እንሙት” የሚሉ የመንፈስ ልጆቻችን ስላሉ በእውነት ለኛ ለአገልጋዮቻቸው ፈተና ሆኗል፡፡ ግን በትዕግስት በማስተማር ነገሩን ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍ ሲራክ “ከመታመምህ በፊት ዳን” ይላል፡፡ ይሄንን ቃል መከተል አለብን፡፡ አንደኛ ንስሃ ገብቶ ድኖ ከዚህ አለም መለየት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ደግሞ በስጋ ከመታመማችን በፊትም ሐኪሞች ጠቢባን የሚሉንን ሰምተን መጠበቅ አለብን፡፡ በዚህ በኩል አገልጋዮችም ሆነ የእምነት አመራሮች የህሊና ጥንካሬ ያስፈልገናል፡፡
“ኮሮና ከእግዚአብሔር አይበልጥም” በሚል አንዳንዶች የተለመደ ተግባርን ማከናወን ያስፈልጋል ሲሉ ይደመጣል፡፡ በዚህ ላይ የእምነቱ አስተምህሮ ምን ይላል?
ይሄ እግዚአብሔርን መፈታተን ነው፡፡ የእግዚአብሔር ክብርና አምላክነት በዚህ አይገልጽም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም የሚያስተምረን ይሄንኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ሄሮድስ ጌታን ሊገድለው ባሰበ ሰዓት፤ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በህልም ተገልጦ “ይህ ክፉ ሰው ተነስቷልና እናቱንና ህፃኑን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ” ነው ያለው፡፡ እግዚብሔር እኮ አምላክ ነው፡፡ ሁሉን ማድረግ የሚችል ነው፡፡ ታዲያ ለምን ወደ ግብፅ ሽሽ? አለ ሄሮድስን እኮ ድምጥማጡን ማጥፋት ይችል ነበር ግን የቁጣና የመከራ ጊዜያትን በትዕግስት ማስፈን ነው ያስተማረን፡፡ ስደትን ለሃዋርያት አስተምሯል፡፡ ያው መልአክ እኮ ቁጣው ሲያልፍ ለዮሴፍ ምን አለው? ጌታንና እናቱን የሚፈልገው ሄሮድስ ሞቷልና ወደ ሀገር ግባ ነው ያለው፡፡ “ይሄም በሽታ አልፏልና ወደ መደበኛ አገልግሎታችሁ፤ ዝማሬያችሁ ተመለሱ” ይለናል እኛንም፡፡ ደግሞ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ማን ያውቃል? ምናልባት እግዚአብሔር ክብሩን ሊገልጽ ቢሆንስ? ያላወቁትን ሊያንበረክክ ከሆነስ? ከኛ በላይ ላሳር ያሉትን ሊያስተምር ከሆነስ? ማን ያውቃል? የጣሊያኑ ማስወረር እኮ የምድሩን ጨርሰናል መልስ የምንጠብቀው ከሰማይ ነው ማለታቸውስ… ጌታ ይሄን ሊያሰማን ይሆን? ከቶ የእግዚአብሔርን ፍቃድና ሐሳብ የሚያውቀውስ ማን ነው? እግዚአብሔር እኮ አዋቂ ነው፡፡ እኛ ምን እናውቃለን? ስለዚህ ይሄን ጊዜ በትዕግስት በጥበብ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርን መፈታተን አያስፈልግም፡፡ ጣሊያን ውስጥ እኮ ብዙ ሺዎች ሞተዋል፡፡ እነሱ እግዚአብሔርን አያውቁትም ማለት ነው? እኛ ግብዘኞች ልንሆን አይገባንም፡፡ መደማመጥ ያስፈልገናል፡፡ መታዘዝ ይገባናል፡፡ “ሃያል ነኝ፤ ለሁሉም ዜጐቼ እጠነቀቃለሁ” የምትለው አሜሪካ እኮ አልቻለችውም፡፡ እውቀት ቴክኖሎጂ፣ ገንዘብ አልመለሰላትም፤ ስለዚህ አሁን ፍጥረታት በሙሉ ተስፋቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ከዚህ ክፉ ይሰውራል፡፡ እንፀልይ እንለምነው ይሰውራል፡፡ እምነት ጋሻ ነው ይከልላል፤ ከፀለይን ከለመንን ያልፋል፤ እንሻገረዋለን፡፡ ንስሃ ብንገባ ከዘላለም ሞትም እናመልጣለን፡፡ ሁሉም እግዚአብሔር ሲፈቅድ ነው የሚሆነው፡፡ በዚያው ልክ እግዚብሔር ጥበቡን የገለፀላቸው ሐኪሞች የሚመክሩንን መስማት አለብን፡፡
ምዕመኑ በዓሉን እንዴት ነው ማክበር ያለበት?
አሁን አብዛኛው ቴክኖሎጂ እጅ ላይ አለ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ በተለይ በከተማ ያለው፣ በዚህ መንገድ የእምነት ሥርዓቱን ለጊዜው በቤቱ ሆኖ መከወን የሚችልበት ዕድል ተመቻችቶለታል፡፡ ገጠር ላሉ ደግሞ ከተማ ያለው በተለያየ መንገድ ግንዛቤ ቢሰጥ ጥሩ ነው፡፡ ሰው በዓሉን በየቤቱ በሚተላለፉ ሃይማኖታዊ የቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት እየተከታተለ እንዲያከብር እንመክራለን፡፡ የእርድ ክንውኖችን በጤና ጥበቃ መመሪያ መሠረት እንዲያደርግ እንመክራለን፡፡ ሌላው ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፆም ፀሎት ለአንድ ወር ማወጇን ተከትሎ፣ ፆም ይቀጥላል የሚለው ነገር ነው፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡ ፆም የለም፤ ፀሎትና ምህላው ግን ይቀጥላል፡፡

_________________


               “መጪውን በጎ ዘመን እያሰብን በዓሉን እናክብር”
                       ፓስተር ፃድቁ አብዶ


                የዘንድሮ የትንሳኤ በዓል፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እየደቆሳት በሚገኝበት ክፉ ጊዜ ላይ ነው የሚከበረው፡፡ ምዕመናን እንደተለመደው ቤተ ክርስትያን በመሄድ እምነታቸውን መፈፀም አልቻሉም:: ይልቁንም የቅዳሴ ሥርዓትም ሆነ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ እንዲሁም ፀሎትና ምህላ በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ከቤታቸው ሆነው መከታተል ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ፈረንጆቹም ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ሁኔታ ነው በዓሉን ያከበሩት፤ ቤተ - አምልኮ ሳይሄዱና ራሳቸውን ለወረርሽኙ ሳያጋልጡ ተጠንቅቀው፡፡ ለመሆኑ ከዚህ ቀደም ቤተ - አምልኮዎች ተዘግተው ትንሳኤ የተከበረበት አጋጣሚ ይኖር ይሆን? ቤተ ክርስትያን ከመሄድ መቆጠባቸው የበሽታው ስርጭት ከመግታት አንፃር አስተዋጽኦው ኢትዮጵያውያን በዓሉን እንዴት ነው ማክበር ያለባቸው? ‹‹እግዚአብሔር ከኮሮና ይበልጣል›› በሚል ራስንና ሌሎችን ለቫይረሱ ማጋለጥ በሃይማኖት አስተምህሮ እንዴት ይታያል? የክርስትና ሃይማኖት መሪዎች ስለኮሮና ቫይረስና ስለፈጠረው ተፅዕኖ፣ ምዕመናን ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ሃሳባቸውንና ምክራቸውን ለግሰውናል፡፡
የዘንድሮ የትንሳኤ በዓል ባልተለመደ ሁኔታ የአምልኮ ቤቶች በተዘጉበት ድባብ ነው የሚከበረው፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ አጋጣሚ ተከስቶ ያውቃል?
በአሁኑ ወቅት መሬት በምትባል ፕላኔት ላይ የምንኖረው ሁሉ በአንድ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ከዚህ በፊት በዓለም ላይ እንዲህ ያለ አጋጣሚ ታይቶ ያውቃል ወይ ከተባለ፣ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ አልነበረም ማለቱ ይቀላል፡፡ ነገር ግን በዓለም ላይ ሶሻሊዝም  የሚባል ርዕዮተ ዓለም በተንሰራፋበት ዘመን፣ በምሥራቅ ከሩሲያ ጀምሮ በተለያዩ አገራት የነበሩ የወንጌል አማኞችም ሆኑ ሌሎች ክርስትያኖች በይፋ አምልኮ ተከልክለው ነበር:: በወቅቱ እንደዚህ አይነት በዓላትን አያከብሩም ነበር:: ተደብቀው አነስ ባለ ቁጥር ተሰብስበው ነበር ለማምለክ የሚሞክሩት፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ በተለይ ከ1968 በኋላ ደርግ ‹‹ሶሻሊዝምን ነው የምከተለው›› ብሎ በተነሳ ጊዜ፣ አብዛኞቹ በተለይ እኛ ወንጌላውያን የምንባለው፣ በይፋ ቤተ አምልኮቶቻችን ተዘግተው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ በየቤታችን ነበር የምናከብረው፡፡ ምናልባት ጎረቤት እየተጠራራን ነበር በመጠኑ ሰብሰብ ብለን የምናከብረው፡፡ ግን በአለማቀፍ ደረጃ ከቤተ እምነቶች ውጪ ትንሳኤ ሲከበር፣ ያሁኑ የመጀመሪያው ይሆናል ብዬ አስባለሁ::
“ኮሮና ከእግዚአብሄር አይበልጥም፤ ፋሲካን ተሰባስበን ከማክበርም አያግደንም” የሚሉ አመለካከቶች ከአንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች አድምጠናል፡፡ ይሄ ምዕመኑን ለአደጋ ማጋለጥ አይሆንም? በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
በጣም አስገራሚ ነገር ነው፡፡ መረጃውን በኒውዮርክ ፖስት ላይ ነው ያነበብኩት:: አንድ ፓስተር የአሜሪካ መንግሥት ያስቀመጠውን ክልከላ ወደ ጎን በመተው፣ “መንግሥት እኔን እስኪያስረኝ ድረስ በጭራሽ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አላቆምም፤ እግዚአብሄር ከዚህ በላይ ስለሆነ አገልግሎቴን አላቆምም” ብሎ ነበር፡፡ ያ ሰውዬ ግን በኋላ በኮሮና ሞተ፡፡ ከዚህ ብዙ መማር አለብን፡፡ እርግጥ ነው፤ ይሄ ቫይረስ ከእግዚአብሄር አይበልጥም፡፡ እንደውም የእግዚአብሄርን ሃይልና ሰው ምን ያህል ውሱን መሆኑን እንድናይ ያስገደደን ክስተት ነው:: ሆኖም ግን ቅዱሳት መጽሐፍት ምን ያዛሉ የሚለውን ማየት አለብን፡፡
እኛ አገር ሶስት ተገቢ ያልሆኑ አመለካከቶች እንዳሉ እረዳለሁ፡፡ አንደኛው አጉል የሆነ ትምክህት ነው፡፡ አንዳንዴ ከእምነት ጋር፣ አንዳንዴ ከማንነታችን ጋር እናያይዝና “እኛን አይነካንም፤ እኛ የቃል ኪዳን ሕዝቦች ነን” ብለን ልክ ራሳችንን ከሰው ሁሉ የተለየን አድርገን እንታበያለን:: ኤችአይቪ በመጣ ጊዜም ትምክህት ነበር:: ‹‹እኛን አይነካንም›› ይባል ነበር። እንዲህ የሚሉ ሰዎች፣ የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 13ን በደንብ ቢያነቡት ጥሩ ነው፡፡ ሌላው ምንም እንዳልተፈጠረ የሚሆኑ ቸልተኛ ሰዎች ደግሞ አሉ፡፡ “በቃ አንዴ መጥቷል፤ ምን ያህል ራሴን ጠብቄ እችላለሁ? የሆነው ይሁን” የሚሉም አሉ፡፡ ሶስተኞቹ ደግሞ በጣም ይሸበራሉ፡፡ ይሄም ተገቢ አይደለም:: ታዲያ የትኛው ነው ትክክለኛው? ከተባለ፣ በእግዚአብሄር መታመን ከጥንቃቄ ጋር አይጣረስም፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‹‹ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፤ ማስተዋልም ይጋርድሃል›› ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ መጠንቀቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዘን ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሄር ያድነኛል ብሎ መርዝ መጠጣት እንዴት ይቻላል? ጥንቃቄ አድርግ ሲባል እምቢ ያለው የአሜሪካው ፓስተርም፣ እግዚአብሄርን እየተፈታተነው ነበር፡፡ እግዚአብሄር ይጠብቀኛል ብሎ መተማመን ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን መፈታተን የለብንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም የሚያስተምረን ይሄንን ነው፡፡ ለምሳሌ “እጄን አልታጠብም፤ ምንም አላደርግም፤ እሳትም ቢሆን ሮጬ እገባለሁ” ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት አንድ ኢትዮጵያዊ ለንደን ይሄድና አንድ ዘመድ ቤት ያርፋል፡፡ ዘመዱ ቤቷን ስትቆልፈው የመጀመሪያው በር የብረት ፍርግርግ ነው:: ሌላ ሁለተኛ በር ደግሞ አለው፡፡ ሰውየው ከገባ በኋላ እነዚህን በሮች ተራ በተራ ቆለፈች፡፡ ይሄን ጊዜ ሰውየው ገረመውና፤ “እናንተ እዚህ አገር ያላችሁ ሰዎች በእግዚአብሄር አታምኑም እንዴ? ‹‹የማይተኛው የማያንቀላፋው ጌታ እንደሚጠብቅ አታምኑም ማለት ነው?›› ይላታል፤ እሷም ምን መለሰችለት፡- ‹‹በእግዚአብሄርም አምናለሁ፤ በሬንም እዘጋለሁ›› አለችው:: ስለዚህ በእግዚአብሄር አምናለሁ ተብሎ በርን ለሌባ ክፍት ተድርጎ አይተኛም፡፡ የእግዚአብሄርን ለእግዚአብሄር ትቼ፣ የኔን ሃላፊነት ታዲያ ለምንድን ነው የማልወጣው:: እግዚአብሄር ሉአላዊ ነው፤ እውነት ነው፡፡ እግዚአብሄር ፈጽሞ ፈቅዶ የሚያመጣቸው ነገሮች አሉ፡፡ እሱ ፈቅዶ የሚያመጣቸው ነገሮች በአብዛኛው መልካም ናቸው፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ግን አይከለክልም:: እግዚአብሄር ይፈቅዳል አይከለክልም፡፡ የእግዚአብሄር ፈቃድ በሚሆንበት ጊዜ እኛ  “ከልክልልን” ብለን በንስሃ ወደ እርሱ ማልቀስ መጮህ አለብን፡፡ ስንፀልይ “ፍቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁም በምድር ትሁን” እንላለን፡፡ የእግዚአብሄር ፍቃድ በምድር ላይም አለ፡፡ ስለዚህ ያኔ ወረርሽኝ በሰው ጥፋትም የመጣ ስለሚሆንና እግዚአብሄር ስላልከለከለው በአጭሩ እንዲያስቀርልን መፀለያችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እኛም እንደ ነነዌ ሰዎች በምላሳችን ሳይሆን በልባችን በእውነት እንድንመለስ ነው የሚያስፈልገው:: እግዚአብሄር ምላሳቸውን ሳይሆን ስራቸውን ነው ያየው፡፡ እኛንም ፈጣሪ ምላሳችንን ሳይሆን ስራችንን ልባችንን ነው የሚመረምረው፡፡ ስለዚህ አሁንም አክቲቪስቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፖለቲከኞች… በምላሳቸው ሳይሆን በተግባራቸው ነው ወደ በጎ ነገር መመለስ ያለባቸው፡፡ እኛ እኮ ምርጫ ለማካሄድ ስንዘጋጅ ነበር፡፡ እግዚአብሄር ግን ሉዓላዊ ስለሆነ በአንድ ጊዜ ነገሩን ሁሉ የሚገለብጥ ነገርን ፈቀደ፡፡ ስለዚህ እኛ እንደ ሰውነታችን አቅም እንደሌለን ማወቅ አለብን፡፡ አቅም ወደ ሚሰጠን መመለስ ይገባናል:: እግዚአብሄር ደግሞ ምላሳችንን ሳይሆን ልባችንን ነው የሚመረምረው፤ ተግባራችንን ነው የሚያየው፡፡
ምዕመኑ በነገው ዕለት የትንሳኤ በዓልን እንዴት እንዲያከብር ይመክራሉ?
የዘንድሮ ትንሳኤ በዓልን ስናከብር፣ መጪውን በጎ ዘመን እያሰብን መሆን አለበት:: ህመም ሁልጊዜ የለም፤ ሞትም ሁልጊዜ የለም፤ ለቅሶ ማታ ነው፤ ጠዋት ደስታ ይሆናል… ይላልና መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳው፣ እኛም ይሄን ችግር ድል አድርገን እንደምናልፈው በማሰብ፣ በደስታ እንድናከብርና በቤታችን ሕጉ በሚፈቅደው መጠን እንድንሆን ነው የምመክረው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ በአቅም ማነስ በዓሉን ማክበር የማይችሉትን ሰዎች የምንረዳበትና የምንደግፍበት እንዲሆን መልዕክት አስተላልፋለሁ፡፡ የብዙዎቹ ቤተ እምነቶች የአምልኮና የበዓል አከባበር በመንፈሳዊ ጣቢያዎቻቸው ስለሚተላለፍ፣ ሰዎች ቤታቸው ሆነው ማክበር ይገባቸዋል:: መጽሐፍ ቅዱስ “ሁለትም ሶስትም ሆናችሁ በስሜ ከተሰበሰባችሁ በመካከላችሁ”… ስለሚል፤ ሁለትም ሶስትም ብንሆን፣ እግዚአብሄር ከኛ ጋር ነው፤ ስለዚህ ትንሳኤን በደስታ እንድናከብር ነው የሚያስፈልገው:: መነሳቱን እንዳወጁት፣ እኛም የክርስቶስን ትንሳኤ በደስታ እንድናከብር ነው መልዕክቴን የማስተላልፈው፡፡     


Read 1170 times