Saturday, 18 April 2020 15:05

"ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጥፋ"

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፣ የቅዳሜ ሹር ዕለት ሌሊት፣ ቤተሰብ በሙሉ የሌሊት መፈሰኪያውን ዶሮ አቁላልቶ፣ ትርክክ ባለ ፍም ከሰል ላይ ጥዶ፣ የመፈሰኪያውን ሰዓት ይጠባበቃል፡፡ አባት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ስነ ሥርዓት አብቅቶ ሰው ሁሉ ወደየ ቤቱ  ይመጣል፡፡
የመፈሰኪያውን ሰዓት ለማብሰር በሚመስል መልኩ መኪኖች ጥሩምባ እየነፉ መንገዱን ሞልተውታል፡፡
አንድ ቤተሰብ ትሪ ከቦ፣ አባት ማዕዱን ባርከው ሊመገቡ እየተዘጋጁ ሳለ፣ አንድ እንግዳ ከውጪ በር ያንኳኳል፡፡ በሩን ሲከፍቱ ለረጅም ጊዜ ተለይቷቸው የነበረ ዘመድ፣ ወደ ቤቱም እንዳይሄድ ቤቱ ርቆበት፤ በቤተ ክርስቲያን አቅራቢያም የመሸበት እንግዳ እንዳይል ጨንቆት፣ እነዚህ ዘመዶቹ ቤት መጥቶ ኖሯል፡፡
ዘመዶቹ በደስታ ስሜት እጁን አስታጥበው ወደ ማዕዱ እንዲቀርብ አደረጉ፡፡
ቤተሰቡ እንደ ወትሮው ልማዳቸው አባላቱ ሙሉ ትሪ ከበው ነው የሚበሉት፡፡ ልጆቹም አብረው ቀርበዋል፡፡ ከልጆቹ መካከል አንድ አመለኛ ልጅ አለ፡፡ ገበታ ላይ ከሰው ፊት እየተሻማ ያስቸግራል፡፡ ዛሬ ማታ በተለይ እንግዳ ባለበት ወደ ማዕዱ መቅረቡን አባትየው ስላልወደዱት፣ ልጁን ቆጥ ላይ አውጥተው አስረውታል፡፡
ምግብ መብላት ሲጀመር ልጁ ማልቀስ ይጀምራል፡፡
ከትሪው ምግብ እንቁላሉን አንዱ የቤተሰብ አባል ያነሳል፡፡
ልጁ… ‹‹ኧ… ኧ… ኧ…ኧ!›› እያለ ድምፁን ያሰማል፤ በለቅሶ፡፡
አባት - ‹‹ዝም በል አንተ! ዛሬ እንግዳ ስላለ ነው በኋላ ትበላለህ!››
ልጅ ለጊዜው ዝም ይላል፡። አባት መላላጫውን አንስተው እንግዳው ፊት ያስቀምጣሉ፡፡ ልጁ ከቆጥ ላይ ሆኖ ‹‹ኧ…ኧ…ኧ" እያለ ማልቀሱን ይቀጥላል፡፡
ይሄኔ እንግዳው ያፍርና፤
‹‹ኧረ ነውር ነው፤ ልጅን እንዲህ ማሳቀቅ አይገባም፡፡ የበላነውን ይበላል፡፡ ድርሻው ይሰጠዋል፡፡ ፍቱና ከቆጡ ይውረድና አብሮን ይብላ፡፡ ይሄንን ፈጣሪ አይወደውም፡፡ እኔም አይዋጥልኝም!›› ይላል፡፡
አባትም ያፍርና ልጁን ከቆጡ ያወርደውና ወደ ገበታው እንዲቀርብ ያደርገዋል፡፡
ልጁ እውነትም አመለኛ ነው፡፡ በመጀመሪያ ፈረሰኛውን ከአባቱ ፊት አፈፍ ያደርጋል፡፡
አባት - ‹‹አላልኋችሁም?!›› ይላል፡፡
እንግዳው - ‹‹ተውት ይብላ›› ልጅ አይደለም እንዴ? ይላል የምንተ እፍረቱን፡፡
ለእንግዳው ሌላ የዶሮ እግር ይወጣለታል፡፡ ልጁ ላፍ ያደርጋል። እንግዳው አሁን ብልት ሳይበላ ሊቀር መሆኑ ገባውና ወደ አባትየው ዞሮ፤
‹‹እንግዲህ፣ ሸ - ብ!›› አለ፡፡
***
ልጅን ዓመት በዓል ስለመጣ፣ አሊያም እንግዳ ስለመጣ ሳይሆን፣ ገና ከሕጻንነቱ ጀምሮ መክሮ፣ መስመር አስይዞ ማሳደግ እንጂ አድጎ ፈር ከለቀቀ በኋላ መፍትሄ እሻለታለሁ ማለት ከንቱ ነው፡፡ ሳይሳካ ሲቀርም መቆጣት፣ መግረፍ ወይም ማሰር ክንቱ ጥረት ነው፤ ‹‹ውሃን ከምንጩ ነገርን ከሥሩ›› የሚባለው ይሄንኑ የአስተዳደግ ችግርም ከመሰረቱ የሚያመላክተን ነው ‹‹ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ›› ይሆናል የሚባለውም ሳናውቀው ሥር እየሰደደ፣ ኋላ መጣፊያው እንዳያጥር፣ መመለሻው እንዳይቸግር፤ ቀደም ብሎ እንዲስተዋል የሚያሳስብ ደወል ነው፡፡
የቀደመ ልማዳችንን መመርመር፣ በተለይ በአሁኑ ‹‹በዘመነ - ኮሮና›› ወቅት ተገቢ ነው፡፡ በህይወት ለመኖር ጽዳትን መጠበቅና ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ሆኗል፡፡ ሁሉ በተግባር የሚፈተንበት፣ ጉዳቱ በሞት የሚፈረድበት አስጊ ዘመን በመምጣቱ፣ ከእንግዲህ ‹‹ዋዛ ፈዛዛ ልብ አያስገዛ›› የሚለው በቅጡ የሚሰመርበት ዘመን ነው! ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ነው ምላሹ መሆን ያለበት፡፡ ሁለተኛውና አስከፊው ገጽታው ደግሞ በኮሮና ቫይረስ የተያዘው ሰው ብቻውን አለመሄዱ ነው! ተያይዞ ማለቅ ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ነው፡፡
ባለፈው እንዳልነውም፡-
‹‹ወንድም የሞተ እንደሁ በአገር ይለቀሳል፡፡
  እህትም ብትሞት ባገር ይለቀሳል፡፡
  እናት ሞታም እንደሁ ባገር ይለቀሳል፡፡
   አባት የሞተ እንደሁ ባገር ይለቀሳል፡፡
    አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?
የተባለው ‹‹አድጎ››፤ ‹‹ዓለም የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል!››
በሚል ተለውጧል፡፡
የበሽታው መድሐኒት ተገኝቶ የዓለም ፈውስ እልባት እስኪያገኝ፣ ዛሬም የሐኪምን ምክር መስማት ተቀራርበን እናስበው የነበርነውን፣ ተራርቀን ማሰብ፤ ቢሰለችም፤ ቢታክትም፤ መፍትሄው እስኪበጅ ቤት መቀመጥና በትዕግሥት መጠበቅ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡ እንጠንቀቅ፣ ቤት እንቀመጥ፣ ፅዳታችንን እንጠብቅ!!
የአበሻ ገጣሚ፡-
‹‹ገዴ ዞራ ዞራ በእንቁላል ላይ
  ጊዜ እሚጠብቅ ሰው ጅል ሊባል ነውይ!›› ይለናል፡፡
ጊዜ እንጠብቅ!
በመተሳሰባችን፣ በመረዳዳትና በመተጋገዛችን፤ እንደ ቤታችንም፤ እንደ ጎረቤታችንም በመኖራችን፤ የነገ መንገዳችንን ዛሬ የመጀመራችን አንድ እርምጃ ነው፤
‹‹ወርቁ ቢጠፋ
ሚዛኑ አይጥፋ!!›› ነው፡፡
መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንልን!


Read 12849 times