Tuesday, 21 April 2020 00:00

የዛሬ መራራቅ ነገ ያቀራርበናል!

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(1 Vote)

        የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታትና ራስን ከበሽታው ለመከላከል መወሰድ ከሚገባቸው ጥቂት ጥንቃቄዎች ውስጥ በቀላሉ ለመተግበር ያልተቻለውና ለኛም ሆነ ለአብዛኞቹ የዓለም አገራት ፈታኝ የሆነው አካላዊ ርቀትን መጠበቅ (Social distancing) ይመስለኛል:: በአገራችን በተግባርም እያየነው ነው፤ ፈታኝነቱን፡፡ በመዲናችን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚታየው የሰዎች መጨናነቅና ትርምስ፣ ኮሮና ወደ አገራችን ጨርሶ የገባ አይመስልም፡፡ ይሰቀጥጣል፡፡
እጅን መታጠብና የመሳሰሉትን የመከላከያ ዘዴዎች ተግብረን፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ከተሳነን ድካማችን ሁሉ ከንቱ ሆኖ እንደሚቀር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ (ዓላማችን ራሳችንን ከበሽታው መከላከል እስከሆነ ድረስ ማለቴ ነው)
እነ ጣልያን፣ ስፔንና አሜሪካ በወረርሽኙ ብዙ ሺ ዜጎቻቸውን በየዕለቱ እያጡ ያሉት የተለየ ሃጢአት ሰርተው ወይም የፈጣሪ ቁጣ ወርዶባቸው አይደለም፡፡ በፍጥነት የጥንቃቄ እርምጃን፣ በተለይም አካላዊ ርቀትን በፍጥነት መተግበር ባለመቻላቸው እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ (ልብ በሉ፤ በአሜሪካ፡- 26 ሺ 064፣ በጣልያን፡- 21 ሺ 067፣ በስፔን፡-  18 ሺ 255 ሰዎች በኮሮና ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡)የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በቀላሉ መተግበር ያልተቻለበት ምክንያት፣ የባህሪ ለውጥ ከማምጣት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡ (ከእነ አካቴው አይቻልም ማለት ግን አይደለም) የባህሪ ለውጥ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማምጣት ያስቸግራል:: ክፋቱ ደግሞ እኛ ጊዜ የለንም:: ወረርሽኙ እንደ ሰደድ እሳት ይሰራጫል፡፡ ከእጃችን ያመልጠናል፡፡ ከቁጥጥራችን ውጭ ይሆናል::  
ከዚህ አንጻር ሕብረተሰቡ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው አካላዊ ርቀትን ጠብቆ፣ ራሱን ከበሽታው መከላከል ይችል ዘንድ፣ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን ጨምሮ፣ ቅጣት መጣልን የመሳሰሉ ህጋዊ እርምጃዎችን መተግበር የግድ ይላል፡፡ በነጻነት ጉዳይ በማትደራደረው አሜሪካ አንዳንድ ግዛቶች ሳይቀር ማህበራዊ ርቀት መጠበቅን ተፈጻሚ ለማድረግ፣ የቅጣት ድንጋጌዎች ከሰሞኑ የወጡ ሲሆን መመሪያውን የተላለፉ በርካታ ሺ ዜጎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን እየሰማን ነው፡፡  ጉዳዩ ህይወትን የማዳን ጉዳይ ነዋ! የአገርን ህልውና የማረጋገጥ እርምጃም ነው፡፡ አሜሪካውያን ይህን እርምጃ መጀመሪያውኑ ባለመውሰዳቸው አሁን ብዙ ዋጋ እያስከፈላቸው ነው፤ በህይወትም በኢኮኖሚ ኪሳራም፡፡  
እኛ ግን በቸልተኝነትና በመዘግየት የሚመጣውን አደጋ ለመቋቋም በቂ አቅም የለንም፤ብዙ ሰው ያልቅብናል፤ኢኮኖሚያችን ለማገገም በሚያዳግት ሁኔታ ሊንኮታኮትብን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከረር ገረር ማለት ይጠበቅብናል፡፡ የከፋ ጉዳት ከመከሰቱ  በፊት፡፡  
 በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ መስተዳደር፣ የአትክልት ተራን የሰዎች ትፍግፍግና ትንቅንቅ ለማስወገድ፣ የግብይት ሥፍራውን ወደ ጃንሜዳ ፈጥኖ ማዛወሩ የሚደነቅ እርምጃ ነው፡፡ (እዚያም ግን ችግሩ ቀጥሏል መባሉ ሌሎችም እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉ አመላካች ነው) አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፤ የሕይወትና ሞት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም በቀላሉ ተስፋ ቆርጠን እጅ ልንሰጥ አንችልም፡፡ ከህብረተሰባችን አኗኗርና ባህል ጋር የሚጣጣሙ አዳዲስ መላዎች መዘየድ ከሁላችንም ይጠበቃል:: ለመንግስት አካላት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ግን ለነገ አይደለም፤ ለዛሬ ነው፤ ለአሁን፡፡  
ምናልባት ከኮሮና ቫይረስ መከላከልና ጥንቃቄዎች ላይ በበጎ ፈቃደኝነት እየሰሩ የሚገኙ ወገኖች፤ሃይልና ትኩረታቸውን አጠናክረው ሰዎች በሚበዙባቸው ሥፍራዎች፣ ሕብረተሰቡ አካላዊ ርቀቱን እንዲጠብቅ ከሥር ከሥር ቢያስታውሱትና ቢጎተጉቱት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን አሻፈረኝ በሚሉት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድም ይገባል፡፡
ወገኖቼ፤የምንተርፈውም የምንጠፋውም ተያይዘን ነው፡፡ ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፤ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል›› የሚለው አገራዊ ብሂል፣ ለኮሮና ቫይረስ አይሰራም፡፡ ካልጣፈጥን ሁላችንም ነን ተያይዘን የምንጣለው፡፡ (ልብ በሉ፤ እስካሁን በመላው ዓለም ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ120 ሺ በላይም በበሽታው ህይወታቸው አልፏል፡፡)
እና ምን ይሻላል? በፍጥነት ከዝንጋታ እንውጣ፡፡ ከእንቅልፋችን እንንቃ!! ለምንወዳቸው ቤተሰቦቻችን ስንል አካላዊ ርቀት መጠበቅን ጨምሮ ሁሉንም የመከላከያ ጥንቃቄዎች ሳንዘነጋ እናድርግ፡፡ ነገ ከመጸጸት ዛሬን በአስተውሎት እንጓዝ፡፡ ለሞት ከሚዳርግ ክፉ ወረርሽኝ ጋር ጦርነት መግጠማችንን ተገንዝበን፣ በቆራጥነትና በጀግንነት ውጊያችንን እናፋፍም፡፡ ከኛ የሚጠበቀው ጥንቃቄ ብቻ ነው፡፡
ልብ በሉ፤  የዛሬ መራራቅ ነገ ያቀራርበናል:: የዛሬ አለመጨባበጥ ነገ ያስተቃቅፈናል፡፡
መልካም የትንሳኤ በዓል!  ፈጣሪ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ያፍጥንላት!  Read 7721 times