Sunday, 19 April 2020 00:00

በስቅለቱ ቀን

Written by  ድርሰት፡- ሊዬኒድ አንድሬዬቭ ትርጉም፡- ዐቢይ ጣሰው
Rate this item
(2 votes)

 በዚያ አሰቃቂ ቀን፣ ሁሉን አቀፍ ኢ-ፍትሃዊነት በተፈጸመበት… ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ወንበዴዎች መሃል በጎለጎታ በተሰቀለበት…በዛች ዕለት የእየሩሳሌሙ ነጋዴ ቤን-ቶቪት፣ ከጠዋት ጀምሮ እጅግ ከባድ የጥርስ ህመም አሞት ነበር፡፡ ህመሙ በዚያች ቀን ዋዜማ፣ አመሻሹ ላይ ነበር የጀመረው፤ የቀኝ መንጋጋው፣ ከክራንቻው ቀጥሎ ያለችው ጥርስ ትመስለዋለች፡፡
ምላሱ ጥርሷን ስትነካት ትንሽ ነበር ያመመው፡፡ ከእራት በኋላ ግን ሲሰማው የነበረው ህመም አልፎለት ስለነበር ጭራሽኑ ረስቶታል፡፡ በዕለቱ ያረጀ አህያውን በጠንካራ ወጣት አህያ ለውጦት ስለነበር፣ በደስታ ተውጦ፣ ለጥቃቅን ነገሮች እምብዛም ዋጋ አልሰጠም፡፡
እናም ማታ ሲተኛ ጥሩ እንቅልፍ ነበር የወሰደው፡፡ ሊነጋጋ ሲል ግን የሆነ ነገር ይረብሸው ጀመር፣ የሆነ ሰው ለአስቸኳይ ጉዳይ እየነዘነዘ እንደሚጠራው አይነት፡፡ ቤን-ቶቪት በንዴት ጦፎ ከእንቅልፉ ሲነሳ፣ ጥርሱን እየመዘመዘው ነበር፡፡ ምዝመዛው ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በመቦርቦሪያ እንደሚፈለፈል ያህል ክፉኛ ያመው ጀመር:: የትንላቷ ጥርስ ትሁን ወይም ከእርሷ ጋር ሌሎች ጥርሶች አብረው ይመሙት እርግጠኛ መሆን አልቻለም፡፡ ብቻ አሁን ቤን-ቶቪት መላ አፉን ጨምሮ ጭንቅላቱ ሳይቀር በከፍተኛ ህመም እየተወቀረ ነው፤ አንድ ሺ የጋሉ ምስማሮች አያኘከ ነው የመሰለው፡፡ ከማሰሮው እፍኝ ውሃ ጠጣ፤ ህመሙ ትንሽ ጋብ አለለት፡፡ ጥርሶቹ እንደ ማዕበል ይንገጫገጫሉ፣ ከበፊቱ አንጻር ህመሙ አስደሳች ሆኖለታል፡፡
ቤን-ቶቪት ጋደም አለ፤ ወጣቱን አህያ አስታወሰ፡፡ ጥርሱን ባያመው ኖሮ ምን ያህል ደስተኛ እንደሚሆን አሰበ፤ መተኛት ፈለገ:: የጠጣው ውሃ ሞቅ ያለ ነበር፡፡ ከአምስት ደቂቃ በኋላ የጥርስ ህመሙ እጥፍ ድርብ ሆኖ ዳግም ተቀሰቀሰ፡፡ ቤን-ቶቪት ቁጭ ብሎ እንደ ፔንዱለም ደፋ ቀና እያለ መናጥ ጀመረ፡፡ ፊቱ ተጨረማመተ፤ እንደ ጨረጨሰ ሽማግሌ የተሸበሸበም መሰለው:: ከአፍንጫው ጫፍ ላይ አንዲት ዘለላ ላብ ተንጠለጠለች፡፡ ፊቱ ገርጥቷል፡፡
በማሰሮ ውስጥ እንደሚናጥ ወተት ከንበል ቀና እያለ፣ ጉሎጎታንና በእርሷ የተሰቀሉትን ሶስቱን ልታይ፣ ከዚያም በታላቅ ፍርሃትና ሃዘን መልሳ ልትጨልም የተፈረደባትን ፀሀይ ቀደምት ጨረር ተቀበለ፡፡
ቤን-ቶቪት ጥሩ እና መልካም ሰው ነበር፣ ኢ-ፍትሃዊነትን አምርሮ የሚጠላ:: ባለቤቱ ከእንቅልፏ ስትነሳ ግን አስደሳች ያልሆነ ነገር ተናገራት፡፡ እንደ ምንም አፉን ከፍቶ፣ በህመም እያጓራ እንዲሰቃይ እንደተፈረደበት ቁስለኛ ቀበሮ ብቻውን እንደተተወ ወቀሰ፡፡ ባለቤቱ ተገቢ ያልሆነውን ወቀሳ በትዕግስት አሳለፈችው፤ ከክፉ ልብ የመነጨ አይደለምና፡፡ በርካታ ማስታገሻዎች ሰጠችው፡፡ በአፉ እንዲይዘው ቁርንፉድ፣ ጊንጥ የተዘፈዘፈበት ጠንካራ መጠጥ፣ ሙሴም ከሰበረው የፅላት ስባሪ:: ቁርንፉዱን ሲይዝበት ትንሽ ቢሻለውም ብዙም አልቆየም፡፡ ውሃውም፣ የፅላቱም ስባሪ ጨርሶ አላሻሉትም፡፡ ህመሙ ዳግም ሲመጣ ብርቱ ሆኖ  ነበር፡፡
ከህመሙ እፎይታ ባገኘባቸው ጊዜያት ቤን-ቶቪት በወጣቱ አህያ ትውስታ ይጽናናል፤ ስለ አህያው ያልማል:: ህመሙ ዳግም ሲቀሰቀስበት ያጓራል፣ ባለቤቱን ይሰድባል፣ ህመሙ በዚህ ከቀጠለ ጭንቅላቱን ከአለት ጋር አጋጭቶ እንደሚያፈርሰው ይዝታል፡፡
ከቤቱ ጣሪያ ላይ ወጥቶ ከአንድ ጥግ ወደ ሌላ ጥግ መንጎራደድ ጀምሯል፡፡ ሰው እንዳያየው ወደ መንገዱ በኩል ወዳለው ጣሪያው መጠጋት አፍሯል፤ እንደ ሴት ጭንቅላቱን በሻሽ ግጥም ተደርጎ ታስሯል:: ልጆች ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ በተደጋጋሚ እየመጡ ነግረውታል፡፡ ቤን-ቶቪት ለአፍታ ዝም ብሎ ፊቱን አጨማዶ ያዳምጣቸዋል:: ብዙም ሳይቆይ በንዴት መሬቱን በእግሩ እየደበደበ ያባርራቸዋል፡፡ መልካም ሰው ነው፤ ልጆችም ይወዳል፡፡ ነገር ግን በማይረባ ነገር እየረበሹት አበሳጭተውታል፡፡
ከመንገዱ ዳርና ከጎረቤት ጣሪያ ላይ በርካታ ሰዎች ተሰባስበው፣ እንደ ሴት ሻሽ የለበሰውን ቤን-ቶቪትን በግርምት ማየታቸው ረብሾት ከጣሪያው ላይ ሊወርድ ሲል ባለቤቱ፤
“ተመልከት፣ ወንበዴዎቹን እየወሰዷቸው ነው፡፡ ምናልባት ሃሳብን ከህመሙ ላይ ሊወስዱት ይችላሉ” አለችው፡፡
“ባክሽ ተዪኝ፡፡ ስቃይ ውስጥ እንዳለሁ አይታይሽም?” ቤን-ቶቪት በንዴት ለባለቤቱ መለሰላት፡፡
ነገር ግን በባለቤቱ ንግግር ውስጥ ትንሽ እውነት ቢገኝ፣ ለጥርስ ህመሙ ማስታገሻ ከሆነኝ ብሎ ወደ ታጠረው መንገድ ሳያስበው አመራ፡፡ ጭንቅላቱን ወደ አንድ ጎን ጥሎ፣ አንድ ዐይኑን ጨፍኖ፣ በአንድ እጁ ጉንጩን ደግፎ፣ ሊያለቅስ ቋፍ ላይ እንዳለ ሰው፣ ሊገረፍ እንደተዘጋጀ ልጅ ፊቱ በፍርሃት ተወሮ መንገድ መንገዱን አቀርቅሮ እያየ ነበር የሚራመደው፡፡
በጠባቡ መንገድ እጅግ በርካታ ሰው ስርአት የለሽ በሆነ ሁኔታ ዳገቱን እየወጣ ነበር፤ አቧሯ ለብሰው ያለማቋረጥ ይጮሃሉ:: ከመሃከላቸው በተሸከሙት መስቀል የጎበጡ ወንበዴዎች አሉ፤ ከላያቸው ላይ የሮማውያን ወታደሮች አለንጋዎች እንደ ጥቁር  እባብ ይወናጨፋሉ፡፡ ከወንበዴዎቹ መሃከል አንደኛው፤ ነጣ ያለ ጸጉር ያለው፣ በደም የተጨማለቀና የተበጣጠሰ ካባ የለበሰው ድንጋይ አደናቅፎት ይወድቃል፡፡ ይሄኔ ጨኸታቸው በረታ፤ ህዝቡ እንደ ቀለም ባህር የወደቀውን ሰው ሊያፍነው ጎረፈ:: ቤን-ቶቪን ድንገት በህመሙ ተርገፈገፈ፤ የሆነ ሰው የጋለ መርፌ ጥርሱ ውስጥ ሸቅሽቆ ያዟዟረበት መሰለው፡፡ አጓርቶ ከመንገዱ አጥር ወጣ፤ ተናዷል፣ በፍርሃት ተርበድብዷል፡፡
“እንዴ አባታቸው ነው የሚጮኹት!” አለ በቅናት፤ ጤነኛ ጥርሶች ያጀቧቸውን አፋቸውን እያሰበ፡፡ እርሱ ጤነኛ ቢሆን ምን ያህል ከእነርሱ በበለጠ አፉን ከፍቶ እንዴት እንደሚጮህ ባሳያቸው፡፡ ይህ ሃሳቡ ህመሙን ይበልጥ ስላባባሰው፣ የተጀቦነ ጭንቅላቱን እያርገፈገፈ ጮኸ “ኡኡኡ…ኡኡኡ…”
“የታወረ ይፈወሳል ይላሉ” አለች ከአጥሩ መልስ የቀረችው ባለቤቱ፡፡ በሮማውያን አለንጋ ከወደቀበት ተነስቶ በዝግታ እየተጓዘ ወዳለው ኢየሱስ፣ አነስተኛ የኮብል ድንጋይ አንስታ ወርውራበታለች፡፡
“በርግጥ…ታዲያ የጥርስ ህመሜን መፈወስ ነበረበት” ሲል በምጸት መለሰላት:: ብስጭትጭት እያለው “አቧራውን እንዴት ነው ያነሱት ጃል! እንደ ከብት መንጋ! በዱላ መባረር ነበረባቸው! ከዚህ ውሰጅኝ ሳራ!”
***
ሚስትየዋ ትክክል ነበረች፤ ትዕይንቱ ቤን-ቶቪትን በትንሹም ቢሆን አሽሎታል፡፡ ወይም ቅሩንፉዱም ሊሆን ይችላል ያሻለው:: መጨረሻ ላይ ግን እንቅልፍ ወስዶታል:: ከእንቅልፉ ሲነቃ የጥርስ ህመሙ ሙሉ በሙሉ ለቆታል፡፡ በቀኝ መንጋጋው በኩል ብቻ ትንሽ ትንሽ ይጠዘጥዘዋል፡፡ ሚስቱ ህመሙ ምንም ማለት እንዳልሆነ ነገረችው፡፡ ቤን-ቶቪት በደስታ ፈገግ አለ፡፡ ሚስቱ ምን ያህል ገራገር ልብ እንዳላትና ለእርሱ መልካም ነገሮችን መንገር ምን ያህል እንደምትወድ ያውቃል፡፡
ቆዳ ፋቂው የቤን-ቶቪት ጎረቤት ሳሙኤል መጥቶ፣ አዲሱን አህያ ሊያዩ ከቤት ወጡ:: ሳሙኤል ጎረቤቱ ስለ ራሱና ስለ አህያው በኩራት የሚነግረውን እያዳመጠ ነበር፡፡
ከዚያ በጉጉዋ ሳራ ጠያቂነት ሶስቱ የተሰቀሉትን ለማየት ተያይዘው ወደ ጎለጎታ ወጡ፡፡ በመንገዳቸው ላይ ቤን-ቶቪት ለሳሙኤል ትላንት ስላመመው የቀኝ መንጋጋው ጥርስ ህመምና እንዴት ህመሙ ሌሊት እንደቀሰቀሰው በዝርዝር ነገረው፡፡ ህመሙ እንዴት እንደነበር ለማሳየት ፊቱን የሰማዕት አስመስሎ፣ አይኖቹን ጨፍኖ፣ ጭንቅላቱን ነቀነቀ፡፡ ቤን-ቶቪት ማጓራቱን ሲጨምር፣ ሳሙኤል ጭንቅላቱን በሃዘኔታ ነቅንቆ “እህ፣ እንዴት ያለ ከባድ ህመም ነው ባክህ!” አለው፡፡
ቤን-ቶቪት በሳሙኤል ምላሽ ተደሰተ፡፡ ታሪኩን ደገመለት፡፡ በዚህም ሳያበቃ ወደ ኋላ ተመልሶ ቆየት ብሎ በግራ መንጋጋው በኩል አሞት ስለነበረው ጥርስ መተረክ ጀመረ፡፡ ሞቅ ባለው ንግግር እንደተመሰጡ ጎለጎታ ደረሱ፡፡ በዚያ አሰቃቂ ቀን እንድትወጣ የተፈረደባት ፀሃይ ራቅ ካሉት ጋራዎች ጀርባ ከጠለቀች ቆይታለች፡፡ በምዕራቡ የሰማይ ግርጌ ቀይ ሃምራዊ መስመር እየተንቀለቀለ ነበር፤ ልክ መሬት ላይ እንደፈሰሰ ደም:: መስቀሎቹ ከዚህ ትዕይንት ዳራ ጨለማ ውስጥ በድንግዝግዙ ቆመው ይታያሉ፡፡ በመሃከለኛው መስቀል ስር ነጭ የተንበረከኩ ምስሎች፣ እዚህም እዚያም ተሰባጥረው ይታያሉ፡፡
ተሰባስቦ የነበረው ህዝብ ከተበተነ ቆይቷል፡፡ ቅዝቃዜ እየጀመረ ነበር፡፡ የተሰቀሉትን ሰዎች ለአፍታ አየት አድርገው፣ ቤን-ቶቪት ሳሙኤል ይዞት በቀስታ ወደ ቤቱ አቅጣጫ አዞረው፡፡ ወደዚህ ሲመጡ በተለየ መልኩ ንግግር አዋቂነት ተሰምቶታል፡፡ እናም የጀመረውን የጥርስ ህመሙን ታሪክ መጨረስ ፈልጓል፡፡  እናም ጉዞ ላይ ናቸው፡፡ ቤን-ቶቪት ደግሞ ፊቱን የሰማዕት አስመስሎ፣ ጭንቅላቱን እየነቀነቀ ድራማዊ በሆነ መልኩ ያቃትት፣ ሳሙኤልም በሃዘኔታ ጭንቅላቱን ይነቀንቅ፣ አሁንም አሁንም፣ የሃዘኔታ ድምጽ ያሰማ ነበር፡፡ ከጥልቁ፣ ከረከሰው ሸለቆ፣ እጅግ ርቆ በቁጣ ከሚንቀለቀለው አምባ ጭለማ፣ ምሽት ወጣ፡፡ የምድርን ታላቁን ወንጀል ከሰማይ ዕይታ ለመሸፈን የፈለገ ይመስላል፡፡   

Read 644 times