Tuesday, 21 April 2020 19:39

አይባልም

Written by  አዛኤል
Rate this item
(0 votes)


               “--የመንፈስ ከተማ እንደተባሉት የሌሎች ሀገራት አብያተ ክርስቲያናት የኛም አፀድ እንዲያ እንዳይባል፣ እንዲያም እንዳይሆን ኪራላይሶን ያሻናል፡፡ የምንሳለመው ካህን ከእጁ ከመስቀሉ ተሰበሰበ፡፡ “እግዜር ይፍታህ” መባል ለካስ ከውሀም ይጠማል፡፡ ታዲያ ይሄን መሆን ከህማም ይለያል?! --”
            
             ከትንታኔ ራቅ እንበል ብንልም አልተቻለንም፡፡ ከቁጥር፣ ከመረጃ፣ ከትንቢት፣ ከፍርድ-- እንውጣ ብንባባልም አልተሳካልንም ፡፡
የሞታችን ሰአት መች እንደሆነ ባናውቀውም፣ አሁን ባይሆን ግን ምኞታችን ነው፡፡ እኔም ብሆን፡፡ ያናናቅናት ህይወት ዋጋዋ አልገባ ቢለን፣ በሞታችን እንማር ዘንድ ተወሰነብን፡፡
(የግል አተያይ መሆኑ ሳይረሳ:: ያው ያረጀ ሰው የግል አተያይ መያዝ ያበዛ የለ!)
ህዝቤ ሆይ ...
መተንፈስ ...መራመድ ...መጨባበጥ ...ወጥቶ መግባት ....አብሮ መቀመጥ.....ማስቀደስ ....ጁመአ ማድረግ .... ተራ ናቸው ስንል፣ ክቡራን ክቡዳን መሆናቸውን፣ በመከልከል አወቅን፡፡  አቢሲንያ የሰሞነ ህማማትን ያህል የጭንቅ ሰሞን ከተያያዘች ሰነበተች፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ፅሁፍ ቆምጣጣነቱ የተስፋ መቁረጥ ወይም  ነጮቹ  suicide note እንደሚሉትም  አይነት አይደለም፡፡
መሬት ስናወርደው.....
የመኖር ትርጉም ከመሞት ይቀዳል፡፡ መኖር ከመሞት እንደሚከብድ ፈላስፎቹ ይነግሩናል፡፡ የሚከብደው መኖር ግን የራሱ አቅላይ ደስታም እንዳለው አልሸሸጉም:: የዚህ እውነት ምንነት ግጭት ሲያስነሳ ቢኖርም፣ ዛሬ ግን ከግጭት አልፈናል፡፡ ለመጋጨትም ለካ መኖር የግድ ነው፡፡ ምን አልባት አሁን ከታመሙት ሰዎች ይልቅ ያልታመምነው ህይወትን “ስለረገምኩሽ ይቅር በይኝ” የምንል ይመስለኛል፡፡(አያድርስ እንጂ እኛም... አንዳችን ....አንባቢውም ወይም ፀሀፊውም ይህንን ደዌ ልንቀላቀለው እንችላለን)
* ወገኖቼ፤ ሟርትና የመሆን ሁኔታን መገመት ይለይልኝ፡፡
ሰው የሌለው ፋሲካ እንድናከብር ስለ ምን ሆነ? መመርመር ከመጠርጠር ያሳርፋል:: እየተጠነቀቅን እንመርምር፡፡ ስቅለትን ቤተ መቅደሱ ብቻውን አሰበው:: መስገድ ብርቅ ሆነብን፡፡ መከራው በየቤታችን መጣ፡፡ ንዋየ ቅድሳቱ ሰውን ናፈቁ፡፡ የመቅደስ እጣን የሚያጎነብስ የሚያሸት የሚባረክ ነፍስ ራቀው፡፡ የመንፈስ ከተማ እንደተባሉት የሌሎች ሀገራት አብያተ ክርስቲያናት የኛም አፀድ እንዲያ እንዳይባል፣ እንዲያም እንዳይሆን ኪራላይሶን ያሻናል:: የምንሳለመው ካህን ከእጁ ከመስቀሉ ተሰበሰበ፡፡ “እግዜር ይፍታህ” መባል ለካስ ከውሀም ይጠማል፡፡ ታዲያ ይሄን መሆን ከህማም ይለያል! ከክርስቶስ ህማም ተካፈልን፡፡
“ተጨነቀ ተሰቃየ አፉንም አልከፈተም:: ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡”
ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ ፶፫ ቁጥር ፯
ተጨነቅን ...ተሰቃየን... አፋችንን እንዲሁ መክፈት እንዳንችል በትንፋሻችን መዐት መጣ፡፡ አብረነው እንዳልነበርን እንድናውቅ አብሮን ሆነ፡፡ ትህትና ቢያሳርድም ከሞት የሚያስነሳን እምነት አውርሶናል፡፡
በሞኝነታችን....አቅም ያለን መስሎን የምናየውን ኒኩሌር ቦንብ ስንፈራ በማናየው አይነ ልቡናችን እንዲበራ እንደ ኤማሁስ መንገደኞች ተገለጠልን፡፡
ሌላ መሬት ስናወርደው......
ይቺን ሶስት አስርት አመታት የወሎ መጀን ትንቢተኛው ሼህ ሁሴን ጅብሪል ከዘንድሮ ሁኔታ አመጣጥ ጋር የምትሄድ የሚመስል ስንኝ ይቀኛሉ፡፡
በነገራችን ላይ....
(ሼህ ሁሴን ጂብሪል ከ1811-1908 የኖሩ ከአባታቸው ከሼህ ጅብሪል በወሎ ክፍለ ሀገር በወረሄመኖ አውራጃ በባዙራ ምክትል በባሆች ቀበሌ ልዩ ስሙ እንበለ ሴዳ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ተወልደው፣ በ97 አመታቸው እንዳረፉ፣ ቦጋለ ተፈሪን ዋቢ አድርገው ዶ/ር ጌቴ ገላዬ፣ ነሐሴ 1996 ዓ.ም ባሳተሙት ጥናት ይነግሩናል፡፡)
በነገራችን ላይ ....(ዶ/ር ጌቴ ገላዬ በጀርመን ሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ፣ የአፍሪቃና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል፣ የአማርኛ ቋንቋና የአፍሪቃ ፎክሎር መምህር ናቸው፡፡)
* በዛውም አማርኛ ጀርመን ሀገር ትምህርት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ.....
“ድንጋይ ዱቄት አርገው መንገድ የሚያበጁ
ገመድን ዘርግተው መብራት የሚያበጁ
አህያ የሚያርዱ አሞራ የሚፈጁ
መጡ የተማሩ ሀበሻን ሊያበጁ
ማማሩን አማረች ግን ብዙ ሰው ፈጁ::”
(ሼህ ሁሴን ጅብሪል)
የነዚህን ቃላት ትርጉም ማብራራት ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብናል፡፡ ከ200 አመት በፊት የተፈጠሩት ሼህ ሁሴን ትንቢተኛ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ፣ የግጥም ቃል አቅማቸው ከቃል ሀገር ወሎ መፍለቃቸውን ያስመሰክራል፡፡ በዚህ ትንቢት ውስጥ ግርም የሚለኝ፡-
“.....አህያ የሚያርዱ አሞራ የሚፈጁ
መጡ የተማሩ ሀበሻን ሊያበጁ
ማማሩን አማረች ግን ብዙ ሰው ፈጁ::”
ወገን...ሰው እንደዚህ ይተነብያል፡፡ (ወይ እኛም አገናኝተነው ይሆናል) ብቻ የብዙ ፍጅት በምን መልኩ እንደሆነ ባይታወቅም አይቀሬ ክስተት መሆኑን ግን የምናየው ሀቅ ነው፡፡ ሀበሻ መፈጀት ብርቁ እንዴ የሚል ሰው አይጠፋም፡፡ ትክክል ነው፡፡ ብቻ ፍጅቱን እናስቀረው ዘንድ ይህ ደመና ይገፈፍ ዘንድ የናቅነውን ወደ ማክበር፣ የረሳነውን በወርቅ ፅላት ወደ መፃፍ መመለስ ግድ ነው፡፡ ከታላቁ መፅሐፍ ከሚደንቀኝ፣ ከሚያስፈራራኝ ጥቅስ ጋር ልተዋችሁ ነው፡፡
“የተናቀ በሰውም የተጠላ የህማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፡፡ ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት ነው፡፡ እኛም አላከበርነውም፡፡” (ትንቢት ኢሳይያስ፡ ፶፫-፫)
አጃኢብ አይደለም ታዲያ፡፡
ያላከበርነው ፈጣሪ ያክብረን አይባልም፡፡
         መልካም የትንሳኤ በአል!!


Read 563 times