Print this page
Saturday, 25 April 2020 12:51

የኢዜማ አመራሮችና አባላት ደም እየለገሱ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ድጋፍ የማሰባሰብ ተግባራትንም እያከናወነ ነው

            “ደም እንለግስ! ወገን እንታደግ!” በሚል መርህ የኢዜማ አመራሮችና አባላቱ የሚሳተፉበት የአንድ ሣምንት የደም ልገሳ መርሃ ግብር ትናንት መጀመሩ ታውቋል፡፡
ለአንድ ሣምንት በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራሮችና አባላት የሚያደርጉት የደም ልገሳ፣ ፓርቲው በኮቪድ 19 መከላከል ላይ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች፣ ማህበራዊ ግዴታውን ለመወጣት ከያዛቸው እቅዶች አንዱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ብሔራዊ የደም ባንክ፣ በኮሮና ምክንያት የደም ለጋሾች ቁጥር ቀንሷል፣ የደም እጥረት ሊገጥመኝ ይችላል ማለቱን ተከትሎ፣ ኢዜማ ለዚህ ብሔራዊ ጥሪ ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው እስከ ወረዳዎች በሚዘልቀው አደረጃጀቱ፣ የፀረ ኮቪድ 19 መከላከል ግብረ ሃይል አቋቁሞ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን የግብረ ሃይሉ ዋና ፀሐፊ ፅዮን እንግዳዬ ለአዲስ አድማስ ያብራሩ ሲሆን፤ ፓርቲው በዋናነት ለህብረተሰቡ በቫይረሱ ጉዳይ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ትናንት የተጀመረውና ለአንድ ሣምንት ይቆያል የተባለው የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ፤ በአዲስ አበባና በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የፓርቲው አባላት ደጋፊዎች እና አመራሮች የሚሳተፉበት እንደሚሆን ዋና ፀሐፊዋ አስረድተዋል፡፡
ይህ የደም ልገሳ መርሃ ግብርም የፓርቲው አባልና ደጋፊ በሆኑ የህክምና ባለሙያዎች የሚመራ መሆኑም ታውቋል፡፡
መንግስት ካቋቋመው ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጋር በመቀናጀትም፣ የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታዎችን የማሰባሰብ ተግባራትን ኢዜማ እያከናወነ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ባለቤታቸው ሰሞኑን የደም ልገሳ ሲያደርጉ በኢቢሲ መታየታቸው አይዘነጋም፡፡


Read 11388 times