Saturday, 25 April 2020 12:53

የአንበጣ መንጋ 1 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ለምግብ እጥረት ያጋልጣል - (ፋኦ)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በድጋሚ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ በጠቅላላው 1 ሚሊዮን ህዝብ ለምግብ እጥረትና ረሃብ ሊዳርግ እንደሚችል የአለም የእርሻ ድርጅት አመልክቷል፡፡
በአንበጣ መንጋው ወረራ ምክንያት ለምግብ እጥረትና ረሃብ ይጋለጣሉ የተባሉት በ5 ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎች መሆናቸውን የድርጅቱ ሪፖርት ይገልፃል፡፡
በሶማሌ ክልል 390 ሺህ፣ በኦሮሚያና ድሬዳዋ 360 ሺህ፣ በአፋር 100 ሺህ፣ በአማራ 72 ሺህ፣ በትግራይ 43 ሺህ፣ በደቡብ 13 ሺህ ያህል ዜጎች በምግብ እጥረት ይጠቃሉ ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
የአንበጣ መንጋ ሊያደርስ ይችላል የተባለው የጉዳት መጠን ጥናት የተሰራው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅንጅት መሆኑን የገለፀው የፋኦ፤ በተለያዩ ክልሎች የደረሰው ውድመትም ተሰልቷል ብሏል፡፡
በአጠቃላይ የበረሃ አንበጣ መንጋው 2 መቶ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ 356 ሺህ ሜትሪክ ቶን ሰብል ማውደሙን የገለፀው ሪፖርቱ፤ በኦሮሚያ ክልል 123 ሺ ሜትሪክ ቶን፣ በሶማሌ 100 ሺህ ሜትሪክ ቶን፣ በትግራይ 84 ሺህ ሜትሪክ ቶን ሰብል እንደወደመባቸው ተመልክቷል፡፡
የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ካደረሰው ጉዳት በተጨማሪ 1.3 ሚሊዮን ሄክታር የግጦሽ መሬትም ባድማ አድርጓል ተብሏል፡፡
በዚህም በሶማሌ ክልል 61 በመቶ የግጦሽ መሬት፣ በአፋር 59 በመቶ፣ በድሬዳዋና ደቡብ 35 በመቶ እንዲሁም በኦሮሚያ 31 በመቶ የግጦሽ መሬት በአንበጣ መንጋው ወድሟል፡፡ 

Read 11573 times