Print this page
Saturday, 25 April 2020 12:55

ሶማሌ፣ አፋርና ድሬዳዋ ከኮሮና ጋር ተያይዞ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ለጅቡቲና ለሶማሊያ ተጎራባች በሆኑት አፋር፣ ሶማሌና ድሬዳዋ የኮሮና ወረርሽኝ ከፍተኛ ስጋት  መደቀኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁት ነዋሪዎች፤ መንግሥት ለአካባቢዎቹ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ክትትል እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ቀጥሎ በኮሮና የተያዙ ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገበው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፤ የወረርሽኙ ስጋት እየከፋ ከመጣ በእንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ ሊጥል እንደሚችል ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡ በከተማዋ በተለይ በመዝናኛ አካባቢዎችና በትራንስፖርት አጠቃቀም ላይ አሁንም ርቀትን የመጠበቅ ሕጎች እየተተገበሩ አለመሆናቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፤ በሕገ ወጥ መንገድ ከጅቡቲ የሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ ለከተማዋ ሕብረተሰብ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን ገልጸዋል፡፡
ከጅቡቲ ወደ ድሬዳዋ እየተመለሱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን የሚጠቁመው ምንጮች፤ እስካሁን በከተማዋ 6 ግለሰቦች በቫይረሱ ከተጠቁ 4ቱ ከጅቡቲ የተመለሱ መሆናቸው ስጋቱን አስረጅ ነው ብለዋል፡፡
የድሬዳዋን ጉዳይ አስጊ የሚያደርገው ከጅቡቲ፣ በየብስ፣ በተሽከርካሪና በባቡር የሰዎች ዝውውር መኖሩ ነው ይላሉ - ነዋሪዎች፡፡
የሶማሌ ክልል ሁኔታ ምን ይመስላል ስንል ያነጋገርናቸው የክልሉ የሚዲያ ባለሙያዎችና ሌሎች ነዋሪዎች በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት የምርመራ ላብራቶሪ ስራ በማስጀመር ጭምር ወረርሽኙን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ ጥንቃቄዎችን እያደረገ ቢሆንም፤ በተለይ በድንበር አካባቢ የሰዎች ዝውውር ያለ መገታቱ እንዲሁም  ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን ተግባራዊ ሲያደርጉ ያለመታየታቸው ክልሉን የስጋት ቀጠና አድርጎታል ብለዋል፡፡
በክልሉ የድንበር አካባቢ ሰሞኑን ተዘዋውሮ ምልከታ ማድረጉን ለአዲስ አድማስ የገለፀው የክልሉ የሚዲያ ባለሙያ፤ በዋናነት ክልሉ የኮሮና ወረርሽኝ በየቀኑ እየጨመረ ከመጣው ከሶማሊያ ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ድንበር አካባቢ ባሉ ዋና ዋና ኬላዎችና መተላለፊያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ቢሆንም፣ ሰዎች ከሶማሊያ ወደ ክልሉ በእግራቸው ድንበር ጥሰው እየገቡ መሆኑ አስጊ ነው ብሏል፡፡
በአፋር በኩል ወደ ድሬዳዋ የሚገቡ ዜጎችም የሶማሌ ክልል ሲቲ ዞንን አቋርጠው የሚገቡ እንደመሆኑ ለክልሉም ለአካባቢውም በሕገወጥ መንገድ እየተከናወነ ያለው የሰዎች እንቅስቃሴ ስጋት መደቀኑን አስታውቋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴን በጥብቅ እየተቆጣጠረ ቢሆንም ሰዎች በእግራቸው ተደብቀው በብዛት እየገቡ ነው ተብሏል፡፡ የሶማሌ ክልል ከሶማልያ፣ ኬንያና ጅቡቲ ጋር የሚዋሰን ሲሆን በእነዚህ አገራት ደግሞ ከፍተኛ የኮሮና ተጠቂዎች እየተመዘገበ ከዚህ አንፃር በሶማሊያ ክልል ላይ ያንዣበበውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ከሚደርሰው የከፋ ጉዳት እንዲታደገው ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ለሶስት አገራት ተዋሳኝ ከመሆኑ ጋር ተደማምሮ የቫይረሱ ስርጭትን ለመግታት ያግዛሉ የተባሉ የመከላከያ መንገዶችን የወረርሽኙን አደጋ ከሌላው አካባቢ የከፋ ያደርገዋል የሚሉት ምንጮች፤ የፌደራል መንግሥትና ጤና ሚኒስቴር ለአካባቢው ልዩ ትኩረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
በተለይ በድሬዳዋ በጅግጅጋና ጅቡቲ መካከል ያለው ሕገ ወጥ የሰዎች እንቅስቃሴ ሁኔታውን በከፋ ደረጃ አስጊ ያደርገዋል ብለዋል ምንጮቻችን፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ለክልሎቹ ያለውን ሁኔታ ያገናዘበ ተግባር እየሰሩ አለመሆኑንም ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ ከጅቡቲ ጋር ድንበር የለሽ መጎራበትና የሰዎች እንቅስቃሴ ባህል ያለው የአፋር ክልልም፤ በቫይረሱ ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ መሆኑን ከክልሉ ነዋሪዎች አዲስ አድማስ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የክልሉ መንግሥት የድንበር አካባቢዎች ላይ የሙቀት ልኬት ምርመራ እያደረገ መሆኑን ነገር ግን እስካሁን በጅቡቲና በአፋር ክልል መካከል ያለው የሰዎች ዝውውር ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ ባለመሆኑ አካባቢው በከፍተኛ ወረርሽኝ ስጋት ስር መውደቁን ይናገራሉ፡፡
ክልሉ ከጅቡቲ ጋር ከሚዋሰንባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ኤልዳሃር በኩል የለይቶ ማቆያ ጣቢያ ተቋቁሞ ክትትል እየተደረገ መሆኑን  የገለፁልን ምንጮች፤ ሆኖም በሕገወጥ መንገድ በእግር ድንበር ጥሰው የሚገቡ ሰዎች ከፍተኛ አደጋ መጋረጡን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ እስካሁን የሙቀት ልኬት ምርመራ በማድረግ ብቻ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት ሲሆን የነበረ ሲሆን በቅርቡ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የላብራቶሪ ምርመራ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪ፣ ሾፌሮችና ረዳቶቻቸው በሶስት የተለያዩ ኬላዎች ላይ የሙቀት ልኬት ምርመራ እየተደረገላቸው እንዲያልፉ እየተደረገ መሆኑን ነገር ግን በዋናነት እረፍት በሚያደርጉባቸው የአፋር ከተሞች አካባቢ ተገቢው ጥንቃቄዎች እየተደረጉ አለመሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡


Read 12100 times