Saturday, 25 April 2020 13:06

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሾተላይ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

    የኢትዮጵያ ታሪክ በቅኝ ግዛት ግፍ የጨቀየ ባይሆንም፣ ሃገሪቱ አንድ ትሆን ዘንድ ብዙ መስዋዕትነት መከፈሉ ለዘመናት ሲወሳ የኖረ ሃቅ ነው፡፡ ሁሉም በየአካባቢው ነግሶ የፈቀደውን ከሚያደርግበት የመሳፍንት አገዛዝ፣ የንግስና ዘር የሌላቸው ዐጼ ቴዎድሮስ፤ በአንድነት መንፈስ ሁኔታውን እስኪቀይሩ ድረስ ሃገሪቱ በአሳዛኝ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡
ዐጼ ቴዎድሮስ ሸፍተው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ባደረጉት ፍልሚያ፣ በለስ ቀንቷቸው ብዙዎችን እያስገበሩ የሰለጠነች አንድ ጠንካራ ሃገር ለመገንባት፣ ያለ የሌለ ሃይላቸውን ተጠቅመው ብዙ ቢጓዙም፣ በዘመኑ የነበሩት መሳፍንትና መኳንንት አድመው፣ ቤተ ክህነትም ‹‹ስልጣኔና ርስቴ ተነካ›› ብላ ተቆጥታ፣ የኋላ ኋላ ስልጣናቸው እየተዳከመ፣ የሰራዊታቸው ብዛት እየቀነሰ ሄዶ፣ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር በተፈጠረው ግጭት ጦርነት ገጥመው፣ መቅደላ ላይ ለጠላት እጅ ላለመስጠት ራሳቸውን ሰውተዋል፡፡
በጀኔራል ናፔር የሚመራውን የእንግሊዝ ጦር ተባብረው ያስገቡት፣ አኩራፊው፣ በኋላም በቂ የጦር መሳሪያ ያገኙት ዐጼ ዮሃንስም ስልጣን ከጨበጡ በኋላ ጠላቶቻቸውን ድል የሚያደርጉበት መሳሪያ ቢታጠቁም ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑላቸውም፡፡ በዐጼ ቴዎድሮስ ዘመን ተማርከው ከነበሩበት አምልጠው ወደ ሸዋ የገቡት የሃይለመለኮት ልጅ ምኒልክ፣ ሸዋ ላይ መንገሳቸው ራስ ምታት ሆኖባቸው ነበር፡፡ በአንድ ሃገር ሁለት ንጉስ መኖሩ ብዙዎችን እያነጋገረ ከቆየ በኋላ፣ ዐጼ ምኒልክ በብዙ ፍጭት ለዐጼ ዮሃንስ እንዲገብሩ ሰላሌ ላይ ተስማምተው ስልጣናቸው ቀጥሎ ነበር፡፡
ይሁንና በጎጃሙ ንጉስ ዐጼ ተክለሓይማኖትና በምኒልክ በኩል ግዛት የማስፋፋት ፉክክር ስለነበረ ጦርነት መፈጠሩ አልቀረም ፡፡
ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ዐጼ ዮሃንስ የተረጋጋ ሃገር አልነበራቸውም፤ ትግራይ ውስጥ ሽፍታ፤ ጎጃም ውስጥ ሽፍታ፣ ሸዋም ውስጥ ሽፍታ አለ፡፡ ሀገር ውስጥ ሽፍታ፣ ከሀገር ውጭም ጠላት አለ፡፡ መሬት ለመቁረስ፣ ድንበር ለማስፋት፣ ሃገሪቱን ቅኝ ለመግዛት የሚፋለሙት አውሮፓውያንና፣ ጎረቤት ሆነው፣ በቱርክ መንግስት እየተረዱ ግዛት መስፋፋት የጠማቸው ግብጾች ፋታ ከልክለዋቸዋል፡፡
ዮሃንስ ዐጼ ቴዎድሮስን መቅደላ ድረስ መጥተው ጦር የገጠሟቸው እንግሊዛውያን የሰጧቸው መሳሪያ ቢኖርም፣ የጎጃሙን ንጉስ  በማሸነፍ ብቻ ነገር አልተጠናቀቀም:: ግብጽን ሁለት ጊዜ በጦር ሜዳ አፈር አስግጠው መልሰዋታል፡፡
በኋላም ወዳጄ ናት ያሏት እንግሊዝ፣ በሱዳን አጣብቂኝ ውስጥ የገባውን የግብጽና የቱርክ ሰራዊት፣ ከመህዲ ሰራዊት ከበባ አድነው፣ ወደ ምጽዋ እንዲሸኙ ካደረጉ በኋላ የምጽዋን ወደብና ሌሎች ቦታዎች አገኛለሁ ብለው፤ በብዙ ዋጋ ከደርቡሾች ጋር ተዋግተው ጦራቸውን አሳጅበው፣ እስከ ምጽዋ ቢሸኙም እንግሊዝ ለባዕድዋ ለኢትዮጵያ ከመስጠት ይልቅ ለወዳጅዋና ለነጭዋ ለኢጣልያ ወደቡን በመስጠትዋ ህልማቸውን ከንቱ አድርጋባቸዋለች:: ኢጣልያም በዘዴ ሱልጣን ኢብራሂም ከተባለ የአውሳ ባላባት ጥቂት መሬት በግል ኩባንያ ስም ገዝተው ድንበር እያሰፉ መጥተው፣ ወደ ደጋማው ክፍል ሲስፋፉ፣ ዐጼ ዮሃንስ ታላቅ ፈተና ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡
ስለዚህም በጊዜው በተደጋጋሚ ከኢጣልያና ከእንግሊዝ መንግስታት ጋር ችግሩን በውይይት ሊፈቱ ሞክረዋል፤ ይሁን እንጂ ሃገሪቱ በተለያዩ መሪዎችና መኳንንት በስልጣን ምክንያት በተራራቀ ልብ ስለምትመራ፣ የሃገሪቱ ጠላቶች በገዛ ወገኖቻችን እየተጠቀሙ፣ ዐጼ ዮሃንስን ድል ማድረግ እንደሚችሉ በማሰብ የትኛውንም የዲፕሎማሲ መንገድ መቀበል አልፈለጉም:: ከዮሃንስ ጋር ከመወያየት ይልቅ ያኮረፉ የሃገር ሰዎችን ጠመንጃ በማስታጠቅ ሌላ ችግር እየፈጠሩ ንጉሱን ያዋክቡ ነበር፡፡
ዐጼ ዮሃንስ አንዴ ወደ ምጽዋ፣ አንዴ ወደ ጎንደር፣ አንዴ ወደ ጎጃም ሲሉ፤ ሌሎቹ የየአውራጃው ገዢዎችና መኳንንት በየጊዜው ጥቅማችን ተነካ በማለት ከባዕድ ጋር በማበር መንግስታቸውን ይወጋሉ፡፡ እነርሱ ወደዚያ በገቡ ቁጥር የሃገር ድንበርና ግዛት መጠቃት ምንም አይመስላቸውም ነበር፡፡
ዐጼ ዮሃንስ የተዋህዶን ሃይማኖት እጅግ በማጥበቃቸውና በዘመኑ በነበረው አስተሳሰብ የተነሳ በተለይ ቦሩ ሜዳ ላይ በወሰኑት ውሳኔ፣ በህዝብ ላይ የፈጠሩት ቅሬታ ቢኖርም፣ ዋና ዐላማቸው የሃገሪቱን አንድነት ማስጠበቅና ዳር ድንበር ማስከበር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይተርኩልናል፡፡
በዘመነ መሳፍንት የነበረው የባለስልጣናት እርስ በርስ መበላላት፣ የኢትዮጵያውያን በሽታ ሆኖ ለጠላት በር በመክፈቱ ንጎሶቻችን ዘመናቸው አሳዛኝና አንድ ጋት እንኳ ወደፊት ፈቅ የማይል ሩጫ እንዲሆንባቸው አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ከዐጼ ቴዎድሮስ ሞት በኋላ በስልጣን ዘመናቸው ባላምበራስ የሚለው ማዕረግ በቂ አይደለም በሚል አኩርፈው የሸፈቱት የተምቤኑ በዝብዝ ካሳ (ኋላ ዐጼ ዮሃንስ)፤ከዛጉዬ ዘር የወረዱት የላስታው  ዋግሹም ጎበዜ፣ ሸዋንና ወሎን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው የነበሩት ዐጼ ምኒልክ ዋነኞቹ ተፋላሚዎች ነበሩ፡፡
ሶስቱ በተለያየ ሰበብና ሁኔታ ሲፈላለጉ፣ አንዳንዴም ሲዋጉ ጠላት ዙሪያቸውን ገመድ ገምዶ፣ የግል የሥልጣን ጥማታቸውን ጋብ አድርገው፣ በጋራ ለጋራ ጉዳይ ስላልቆሙ እስከ ዛሬ ድረስ ወደብ አልባ የሆንበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ጣልያን ምኒልክና ዮሃንስ ተክለሃይማኖትን ጨምረው ጠላትን በጋራ ቢወጉ የምጽዋና የአሰብ ወደብ፣ የመተማውም ሽንፈት አይፈጠርም ነበር:: የኛ ሰዎች ችግራቸውን አቻችለው በጋራ ከመቆም ይልቅ ተከፋፍለው ለጠላት በር በመክፈትና በመበላላት እስከ ዛሬ የሚዘልቅ ቁስልና ችግር ለሃገር አቆይተዋል፡፡
የዚህ ዐይነቱ ችግር በእነ ምኒልክ ዘመን ብቻ ኣላበቃም፡፡ በንጉስ ኃይለስላሴና በልጅ ኢያሱም ዘመን ቀጥሎ፣ እርስ በርስ ሲበላሉ፣ ጠንካራ መንግስትና መከላከያ ባለመገንባታቸው፣ ጣልያን የዐድዋ ሽንፈትዋን ለመበቀል ስትመጣ እኛ ይዘን የጠበቅናት፣ ከአርባ ዐመታት በፊት የተማረኩ የጦር መሳሪያዎችን ነበር፡፡
በኃይለስላሴና በልጅ ኢያሱ ግጭት ምክንያት ከወሎ የመጣውና በራስ ሚካኤል የሚመራው ጦር፤ ከሸዋው ጦር ጋር ባደረገው ውጊያ ያለቀው የሰው ብዛት ምናልባት የማይጨውን ጦርነት ውጤት ሊቀይረው ይችል ነበር፡፡ ጥሎብል እርምጃችን የሚበላሸው፣ ዕድገታችን የሚቀጨው በራሳችን ሰዎች ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ጠላቶቻችን እንደ መሳሪያ የሚጠቀሙትም ይህንኑ ደካማ ጎናችንን ነው፡፡ እርስ በርስ መጠፋፋትና መበላላት የኢትዮጵያውያን የተለመደ መንገድ ነው፡፡ መጠላለፍ ባይሆንና ለመገዳደል ጠመንጃ ፍለጋ በፈረንጆች እግር ስር ባንወድቅ፣ ይሄኔ የት እንደርስ ነበር ብሎ የተሻለ ነገር ማሰብ መሳሳት አይመስለኝም፡፡ ይህ ችግር በንጉሱ ዘመን ቢቆምና ቢደመደም ደግ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፤ተማሪ በጥይት ተቆልቶ ባመጣው ለውጥ፣ ድንገት ስልጣን ላይ ፊጥ ያለው ደርግና በርሱ ዘመን የነበሩ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ስህተት ፈጽመዋል፡፡
የዚህኛውን መጠፋፋት ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገው፣ ከቀድሞዎቹ ይልቅ ፊደል የቀመሱና በተለያዩ ሃገራት የተማሩ ሰዎች፣ ቀድሞ ባለማወቅና ባለመማር ከተሳሳቱት፣ ምንም ያህል ያልተሻሉ መሆናቸው ነው:: ደርግ ከኢሕአፓ፣ ኢሕአፓ ከመኢሶን፣ አንዱ ከአንዱ የተሻለ ነገር ሲያደርጉ አለመታየታቸው ያሳዝናል፡፡ ያ ሁሉ የተማረ ሰው በውይይት ችግሩን ቢፈታ፣ ያ ሁሉ ምሁር በየቦታው ተሰማርቶ ቢያስተምርና የጥናትና ምርምር ስራ ቢሰራ፣ ውጤቱ ምን ይሆን እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡
ልዩነቱ የተለያዩ ፓርቲዎች ብቻም አልነበረም፤ ደርግ የራሱን ሰዎች ለስልጣን ሲል በልቷል፡፡ ኮሎኔል መንግስቱ፣ ጀነራል ተፈሪ በንቲንና ሻለቃ አጥናፉን በሞት አስወግደዋል፡፡ እርስ በርስ ተጫርሰዋል:: ታዲያ ምን ያደርጋል? ይህ ሁሉ የሃገር ሾተላይ ሆኗል፡፡ ወልዳ መቅበር፣ አሳድጋ መብላት ለምዶባታል፤ ሱሰኛ የሆነች ይመስላል፡፡
ኢሕአፓም በሚዘገነን ሁኔታ እርስ በርሱ ተጨራርሷል፡፡ ጌታቸው ማሩ፣ዘሩ ክህሽን፣ ተስፋዬ ደበሳይ… ሁሉ ለየብቻ ሆነው ሞተዋል፡፡ ከፊሉ በደርግ ሌሎቹ እርስ በርስ፡፡ ተስፋዬ ደበሳይን የመሰለ በሞቱ እንኳ ለሌሎች ጥንቃቄ የሚያደርግ ጀግና፤ በዚያ ፒኤች ዲ ብርቅ በነበረበት ዘመን፤ ለነፍሱ ሳይሳሳ የሞተ፣ ሲሞት ፊቱ እንዳይታይና የትግል ጓዶቹ እርሱን አይተው ሞራል እንዳያጡ ከፎቅ ሲወድቅ ማንነቱ እንዳይታይ ያደረገው ወጣት ባይሞት ኖሮ፣ ሃገራችንን ምን ያህል ይጠቅም ነበር ይሆን የሚል ሃሳብ ያጭርብናል፡፡
ኢትዮጵያ ሾተላይ ያለባት እስኪመስል እርስ በርስ መበላላቱ አሁንም አለ:: ወያኔ ከበረሃ ሲመጣ አብሮት የታገለና የተጋደለውን ጓዱን ከተማ ከገባ በኋላ ማሳደዱን አይተናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ መከላከያ የነበሩትን ስዬ አብርሃን ከስልጣን አባርረው ዘብጥያ መጣላቸው፣ የዚያ የመጠፋፋት ባህላችን አካል ነው፡፡ ዋነኞቹን አልኩ እንጂ እነ አቶ ገብሩ አስራት፣ እነ ዐለምሰገድና ሌሎችም በዚሁ ግጭት መራራ ጽዋ ቀምሰዋል፡፡
በግሌ መጠፋፋቱን ከጥይት ወደ እንጀራ ነጠቃና እስር ቤት የቀየረው ወያኔ የተሻለ ነው፡፡ በመግደል ከማስወገድ አስሮ መልቀቅም ምናልባት ስር ሰድዶ የመጣውን አሰራር ይቀንሰው ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የደርግ አባላቱን በጥይት አለመቁላቱ ወያኔን ትንሽ ፈቅ ያለ ሃሳብ ያለው ያስመስለዋል፡፡
ዋነኛው ትርምስ ሁልጊዜ መንግስት በተቀየረ እንደ መሆኑ መጠን፣ ወያኔ ገለል ካለ በኋላ የተፈጠረው ትርምስና የመጠፋፋት ሙከራ ሳይሳካ ቢቀርም፣ ከዐያቶቻችን የባሰ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከመነጋገርና ከይቅርታ ይልቅ መገዳደልና መጨራረስ የናፈቀው የወያኔ ቡድን.፤ ከስልጣን ገሸሽ ማለቱ ያሳበደው እስኪመስል በየክልሉ ሊጭር የሞከረው እሳት ሲታይ፣ ስልጣንና ጥቅም ምን ያህል ቀልብ እንደሚያሳጣ ያሳያል፡፡
በቅርቡ ያየነው ለስልጣን የመስገብገብ አባዜ፣ ከ50 ዐመታት በላይ በዱር ቆይቶ አንዳች ነጻ መሬት ሳይኖረው በለውጡ መንግስት ዕድል የተሰጠው ኦነግ፤ ማምሻ ያስጎመዠውን ወንበር ለመንጠቅ ምርጫ መጠበቅ አቅቶት በርካታ ሙከራ ማድረጉ፣ ይህ በሽታ አልላቀቅ እንዳለን ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የለውጡ መንግስት ጠብመንጃ ላይ ቀልቡን ባለመጣሉ፣ የጀመረው ሰላማዊና የእርቅ መንገድ በርካቶች እንደ ድክመት ስላሰቡት ብዙ የጥፋት ጉድጓዶችን ሲቆፍሩ ከርመው ነበር፡፡ ጎን ለጎንም ሕግ ማስከበር አልቻለም በሚል ለፍፈው ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ ከመሪው ፓርቲ በቀር ሁሉም በሚባል ሁኔታ የጎጣቸውን መዝሙር የሚዘምሩና በግርግሩ ሰፈራቸውንና ቤታቸውን ለመጥቀም የሚሰገበገቡ ናቸው፡፡ ስለዚህም ሃገር ከሌሎች ሃገራት ጋር የሚገጥማትን አለመግባባት፣ ለፖለቲካ ገበያቸው ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ ታይቷል፡፡
አንዳንዶቹማ ዐይናቸውን በጨው አጥበው ለኮሮና ቫይረስ የሚደረገውን ጥንቃቄ ለመንግስት መቃወሚያነት ሊጠቀሙበት  ሲሞከሩ ተስቆባቸዋል፡፡‹‹የሌባ ዐይነደረቅ፣ መልሶ ልብ አድርቅ›› ተብለዋል፡፡ ሌሎቹ የምርጫው ጊዜ በምርጫ ቦርድ ሲለወጥ፣ ‹‹እኛ ሳንስማማ›› በማለት እንመራዋለን ለሚሉት ሕዝብ፤ ቅንጣት ታህል ግድ እንደሌላቸው በአደባባይ  አረጋግጠዋል፡፡
አሁን አሁንማ የምኒልክና የዮሃንስን  መንግስት ዐይነት ፉክክሮች እየተፈጠሩ ይመስላል፡፡ አንዱ አንድ ቦታ የራሱን ሰዎች በሃይልም ሆነ በሰበብ አሰልፎ አረ ጎራው እያሉ ይመስላል፡፡ እውነት ለመናገር፣ የሸዋው ንጉስ ዐጼ ምኒልክ፣ ዐጼ ዮሃንስን አልታዘዝም አይሉም፤የታሪክ ጸሐፍት እንደሚጠቅሱት፤ እቴጌ ጣይቱና የተወሰኑ መኳንንት፣ ምኒልክ ዮሃንስን እንዲረዷቸው ይጎተጉቱ ነበር፡፡ የአሁኖቹ ቡድንተኞች ግን የሀገሪቱን በጎ ነገር ሁሉ በማጥላላት ተጠምደዋል፡፡
ልክ እንደ ቀድሞዎቹ መኳንንት ስልጣን ጠምቷቸው፣ በማህበራዊ ሚዲያ ነገር የሚያጣምሙ ሞልተዋል፤ አማኞች በበዙባት ሃገር፣ ዕርቅና ጸሎትን እንደ አቅም ማጣት ያዩት አልጠፉም፡፡ ይሁንና ሁላችንም በጸሎቱ ተስማምተናል፤ ጠንቋይ ከሚያጠያይቅ ገዢ፣ ጸሎት ወደ ሚጸልይ መሪ መሸጋገራችን የተሻለ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ሆነን፣ ዛሬም እንደ”ማይሞቹ” አባቶቻችን በስልጣን ሽኩቻ ለጠላት በር የምንከፍት ከሆነ፣ የእኛ ‹‹ተማርን›› ትውልድ ወሬ ጥቅሙ ምንድነው?!... ተለያይቶ ሃገር ከማፍረስ ይልቅ አንድ ሆኖ፣ ወደ ብልጽግና መገስገስና ከዘመናቱ የጥፋት ሾተላይ መውጣት አይሻልም?


Read 1433 times