Print this page
Sunday, 26 April 2020 00:00

“ክልሉና ህዝቡ፤ ህወሓትና ጄኔራሎች በሞግዚትነት የሚያስተዳድሩት፣ የሚዘርፉት፣ የሚገድሉትና የሚያስሩት ነበር”

Written by 
Rate this item
(3 votes)


          መቀመጫውን በእንግሊዝ ሀገር ያደረገው “ዩኒቨርሳል ቲቪ” በሶማልኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ዘንድ ሰፊ ተመልካች ያለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። ጣቢያው በርካታ ፕሮግራሞች ሲኖሩት፤ ጋዜጠኛ አብዱልሃፊዝ ሙሐመድ የሚያዘጋጀው የቃለ መጠይቅ ፕሮግራም በሞጋችነቱና ጎላ ያሉ ጉዳዮችን አንስቶ በማፋጠጥ አቀራረቡ ዝናን ያተረፈ፣ በርካታ ታዋቂ የፖለቲካ ተክለ ሰብዕና ያላቸው እንግዶች የሚቀርቡበት “ሀርድ ቶክ” አይነት ፕሮግራም ነው። የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ሙሐመድ ኦማር በዚህ ሞጋች ጋዜጠኛ ፕሮግራም ላይ እንደሚቀርቡ ከተነገረበት ዕለት ጀምሮ በርካቶች በጉጉት ጠብቀውታል። እንደተገመተው የሞቀ፣ ዱላ ቀረሽ፣ በስሜት የተሞላና በመጨረሻም በመከባበር መንፈስ የተቋጨ ቆይታ አድርገዋል።
ቃለ ምልልሱን ሙክታር ዑስማን ከሶማልኛ ወደ አማርኛ መልሶታል:: ተርጓሚው በቃለ ምልልሱ የተነሱትን ጥያቄዎች ሁሉ አላቀረበም። ሆኖም አንኳር አንኳር ጉዳዮችን ለመሸፈን ጥረት አድርጓል። “ብታነቡት እንደምታተርፉበት ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም” ይላል ተርጓሚው ሙክታር ዑስማን። እነሆ፡-


            ክቡር ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፋ ኦማር፤ ለቃለ መጠይቅ ፍቃደኛ ስለሆኑ ከልብ አመሰግናለሁ። በርካቶች በተለይ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በፕሮግራሜ ላይ ስጋብዛቸው እሺ አይሉኝም። እርስዎ ፍቃደኛ በመሆንዎ ለድፍረትዎና የራስ መተማመንዎ ሳላመሰግን አላልፍም። ወደ መጀመሪያ ጥያቄዬ ልግባና… ክልሉን እርስዎ ከመምራትዎ በፊት የነበረበትን አጠቃላይ ሁኔታ እስቲ ለተመልካቾቻችን ጠቅለል ያለ ምስል ይስጡልን።
መልሴን በአላህ ስም እጅግ ሩህሩህ፣ እጅግ አዛኝ በሆነው እጀምራለሁ። እኔም በዚህ በርካታ የተከበሩ ሰዎች ሲቀርቡበት በነበረው ዝግጅትህ ላይ እንድቀርብ ስለተጋበዝኩ አመሰግናለሁ። ፍቃደኛ የሆንኩትም በአንተ ሚዛናዊና ሞያዊ ስነ ምግባር አድናቆት ስላለኝና ዩኒቨርሳል ቲቪ የክልላችንን ጉዳይ በዋነኝነት ሲዘግብ ስለነበረ፣ አሁን ያለውን የሽግግርና የለውጥ ሁኔታ ለህዝባችን መረጃ ለመስጠት የእናንተን ፕሮግራም ምርጫዬ ስላደረግሁ ነው። ወደ ጥያቄህ ስመጣ፤ ክልሉን እኔ ከመረከቤ በፊት የነበረበት ሁኔታ እጅግ ለመናገር በሚከብድ ደረጃ የሶማሌ ክልል ህዝብ የተዋረደበት፣ እንደ ማህበረሰብ ቅስሙ የተሰበረበት፣ የሰው ልጅ መሆኑ የተካደበትና ከፍተኛ እንግልት የደረሰበት፣ ከአውሬ ጋር የታሰረበት፣ አካላዊና መንፈሳዊ ማሰቃየቶች የተፈፀመበት፣ ያለ ፍርድ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉበት፣ ሴቶች የተደፈሩበት፣ እንዲሁም ሰዎች በጅምላ እየተረሸኑ በአንድ መቃብር የሚቀበሩበት ክልል ነበር። ይህም የአለም ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ሪፖርት፣ የተቀረፁ ምስሎችን ጭምር በማየት ማረጋገጥ ማንም ሰው የሚችለው ነው።  ክልሉን ስንረከብ እንደ መንግስታዊ ተቋም የሚሰሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በአጠቃላይ አልነበሩም:: መዋቅራቸው ፈርሷል። አጠቃላይ የክልሉ ቢሮክራሲን ሊያቀላጥፉ የሚችሉ መንግስታዊ ድርጅቶች ወድመዋል። በጣም በሚያሳዝን ደረጃ የነበረ ክልልንና ቅስሙ የተሰበረ ህዝብን ነው ስንመጣ ያገኘነው። ችግሩ እንዲሁ በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
እርግጥ ነው የገለፁት ሁሉ እውነት ስለመሆኑ፣ ክልሉን በቅርበት ስለምከታተል ልክ ነዎት። ለውጥ መጥቶ፣ እርስዎ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ያሳኳቸው ቁልፍ ተግባራትን ሊዘረዝሩልኝ ይችላሉ?
በርካታ ተግባሮችንና ስኬቶችን በተጨባጭ አስመዝግበናል። ዝርዝሩ ብዙ ነው። ምናልባት ኋላ በሚነሱ ጥያቄዎች ዘርዘር አድርጌ እመለስበታለሁ። ጠቅለል አድርጎ ለማስቀመጥ ያህል፤ የክልሉ ህዝብን አጠቃላይ ክብር ነው ወደ ቀድሞ ቦታው፣ ወደ የተከበረ እና ይገባው የነበረ ስፍራ የመለስነው። የወጣቶችን ምናብና መንፈስን ነው አድሰን በሀገራቸው ተስፋ እንዲያደርጉ፣ የራስ መተማመን እንዲኖራቸው፣ ማለም እንዲችሉ የተገፈፉትን ሰብአዊ ክብር መልሰን፣ ሞራላቸውን ለሀገር ልማት እንዲተጉ ወደሚያስችል ቁመና ከፍ አድርገናል። የሶማሌን ህዝብ ክብር በኢትዮጵያ ከፍ እንዲል፣ ሀገራችን ሰላሟ የተጠበቀ እንዲሆን፣ የሶማሌ ህዝብ ሰላም ወዳድ ህዝብ መሆኑን የቀጠናውን ሰላም በማስከበር ምሳሌ እንዲሆን አድርገናል። በርግጥም የሶማሌ ህዝብ ሀይማኖተኛ፣ ሰው አክባሪ፣ ሰላም ወዳድ፣ ሀገር ወዳድ እንደሆነ እንዲያረጋግጥ እድሉን አመቻችተንለት ለኢትዮጵያም፣ ለምስራቅ አፍሪካም መልካም እሴቱን አሳይተናል። ስርዓት ሲስተካከል ህዝብ የዘመናት የሰላም ጥማቱን በተግባር አሳይቷል። ይህ እኛ በሀላፊነትና በቅንነት በሰራነው የተቀናጀ ስራ የመጣ ውጤት ነው።
የሴቶቻችንን ክብር አስጠብቀናል። ከሁሉ በላይ በነፃነት መኖርን፣ ያለ ፍራቻ ወጥቶ መግባትን በክልሉ አስፍነናል። እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ የተማሩ የክልሉ ተወላጆች በመማራቸውና በማወቃቸው መከበር ሲገባቸው የሚሸማቀቁበትን ስርዓት ለውጠን እውቀታቸውን ለማህበረሰባቸው እንዲያውሉ አስችለናል። ወደ ህዝብ አገልግሎት ስንጠራቸውም መስፈርቱን ችሎታ ብቻ በማድረግ፣ አካታች የሆነ የሲቪል ሰርቪስ ስራን ተግብረናል፡፡ ከፈቀድክልኝ ትንሽ የማክለው ደግሞ… ከዚህ ቀደም በአብዲሌ የዘረፋ ቡድን የተዘረፉ መሬቶችና ያለ ህግ የተዘረፉ ንብረቶችን ለህዝብ አስመልሰናል። የህዝቡን ንብረት መዝረፍ የሚባል ነገር ተወግዷል። በጥቅም ትስስርና በሞኖፖሊ የመንግስትን ስልጣን በመጠቀም ይደረግ የነበረውን የኢኮኖሚ የበላይነት ለአንድ ወገን ማመቻቸትን አስቀርተናል።
በተለይም የሰራነው ቁልፍ ተግባር፣ የሶማሌን ህዝብ ጥያቄ ወደ መሀል ሀገር ወስደን ከሀገሩ ሀብት በፍትሃዊነት የሚገባውን እንዲጠይቅ ወክለነው የሚያኮራ ስራ ሰርተናል። የሶማሌ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄን ወደ መሀል የሀገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካ አምጥተን በመሞገት፣ ከተፈጥሮ ሀብቱ የሚጠቀምበትን መንገድ በእስትራቴጂና በእውቀት ታግዘን በኩራት አቅርበናል። በዚህም የኢትዮጵያውያንን ክብርና ፍቅር አረጋግጠናል። የሶማሌ ህዝብ የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ፣ የፖለቲካው የዳር ተመልካች ሳይሆን የመሀል ተጫዋችና በሚወሰኑ ውሳኔዎች ድምፅ ሆነዋል። በመሰረተ ልማት ደረጃም በርካታ ተግባሮች ጀምረናል። የተጠናቀቁና በጅምር ላይ ያሉ በርካታ ናቸው። የክልላችን ህዝብ ዋነኛ ችግር መንገድ እንደሆነ ግልፅ ነው። በህጋዊ መንገድ ስርአታቸውን ጠብቀው ሰባት ረጃጅም ደረጃ አስፋልት ተጀምረዋል። እንግዲህ እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የምንመሰገንበት እንደሚሆን አምናለሁ። አየህ፣ መሰረተ ልማት ጊዜ ይወስዳል። ፍሬው ለመታየት ጥቂት ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ለፖለቲካ ትርፍ አያገለግልም። ለሀገር ለወገን የሚሰራ ነው።
ወደ ሰላሳ ለሚሆኑ ከተሞች የሃያ አራት ሰዓት መብራት አስገብተናል። የጤና ሴክተሩንም ለማሻሻል ከዚህ ቀደም ከፌደራል የሚላክልንን ብቻ የምንጠብቀው፣ አሁን 150 አምቡላንሶችን በራሳችን ወጪ ገዝተን ራቅ ራቅ ላሉ ወረዳዎች አስረክበናል። ወደ 450 ት/ቤቶችን፣ አስሩ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሶስት የቴክኒክ ኮሌጆች ሰርተናል። ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኝ መንገድ፣ የከተሞች የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን አሰርተናል። አዲስ ሆስፒታሎችና እየታደሱ ያሉ ሆስፒታሎች፣ የደም ባንኮች፣ የፓርላማ ህንፃና የዞን አስተዳደሮችን ህንፃዎች በአመት ከስምንት ወር ቆይታችን ውስጥ እያሰራን ነው። እውነት ለመናገር በአስራ ስምንት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ስራዎችን አከናውነናል። ፖለቲካውን ካረጋጋንና ሰላም ካሰፈንን በኋላ የሰራነው  ዝርዝሩ ብዙ ነው። ከሁሉ በላይ ለልማት አመቺ የሆነውን ሰላም፣ በክልሉ እውን ማድረጋችን ትልቁ ስኬታችን ነው።
በዘረዘሩልኝ ስኬቶች ላይ የማነሳቸው ጥያቄዎች አሉኝ። ከዚያ በፊት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር ያላችሁ ግንኙነት እንዴት ነው?
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መልካም ግንኙነት ነው ያለን። በሀገሪቱ ህገ መንግስት፣ የፌደራልና የክልል የአሰራርና የግንኙነት ስርዓትና ደንብ መሠረት፤ ነፃነታችን ተጠብቆልን ነው የምንሰራው። አሁን ደግሞ በአንድ ፓርቲ፣ ብልፅግና፣ ስር በፓርቲ ደረጃ ስለምንሰራ መልካም የሆነ ገንቢ ግንኙነት ነው ያለን።
ካነሱት አይቀር ይህ የብልፅግና ፓርቲ ነገር፣ በርካቶች ጥያቄ ያነሱበታል። የሶማሌ ህዝብን መብት ያስጨፈልቃል እያሉ አስተያየት የሚሰጡ አሉ። ክቡር ፕሬዚዳንት፣ ብልፅግና ስትባሉ፣ የተባለው ብልፅግና እውነትም ብልፅግና ስለመሆኑ በምን አረጋግጠው አመኑ? በፓርቲዎ ውስጥም ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ሽኩቻና እስር ተካሂዷል፤ ከምዕራብ ሶማሌ ህዝብ ፓርቲ ጋርም ግጭት ውስጥ ገብታችኋል---
አንድ በአንድ ዘርዘር አድርጌ እንድመልስልህ፣ ጥያቄዎችህን በቅደም ተከተል አስቀምጥልኝ።
እሺ ከብልፅግና ፓርቲ እንጀምር… ክቡር ፕሬዝዳንት የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ህዝብ እራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትን መብት ይገፋል። የሶማሌ ህዝብ ማንነቱንና ባህሉን በነፃነት እንዳያራምድ እንቅፋት ይሆናል ብለው ቅሬታቸውን የሚያሰሙ አካላት አሉ። ብልፅግና ፓርቲ የተባለው እውነትም እንደተባለው ብልፅግና ለሶማሌ ህዝብ እንደሚያመጣ በምን አረጋግጣችሁ ነው የተቀላቀላችሁት?
ብልፅግና ፓርቲ በምን መልኩ፣ እንዴት የሶማሌን ህዝብ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደሚገፋ፣ እንዴት የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብት እንደሚነጥቅ ዘርዘር አድርገው ማስረዳት ያለባቸው ብልፅግናን የሚቃወሙት ሰዎች ናቸው። ይህን ማስረዳት ያለባቸው እነሱ ናቸው። እንግዲህ ተነጠቀ የሚባለው አንድ ነገር ቀድሞ በእጅህ ያለ ነገር ሲሆን ነው። አነሰ ተቀነሰ የሚባለው ቀድሞ ሙሉ የነበረ ነገር ነው። ሊሄድብን ነው የሚባለው ቀድሞ የነበረ ነገር ነው። የሶማሌ ህዝብ በ28 አመት ውስጥ በሀቀኛ ዴሞክራሲና ነፃነት እራሱን አስተዳድሮ አያውቅም። ዴሞክራሲያዊ መንግስት አልነበረውም። እውነተኛ ፌዴራሊዝም ኖሮን አያውቅም። በህወሃት ባለስልጣናት የበላይ አዛዥነት የሚመራ የሞግዚት አስተዳደር ነው የነበረው። አጋር ተብሎ የተገፋ፣ ከመሀል ሀገር የፖለቲካ ውሳኔ ውጪ ሆኖ የበይ ተመልካች እንዲሆን የተደረገ ክልል ነው። ጄኔራሎች የሚያስተዳድሩት፣ ሁሉ እየመጣ የሚዘርፈው፣ የሚገድለውና የሚያስረው ህዝብ ነበረ በክልሉ። በርዕዮተ-ዓለም ሳይቀር በይፋ የአርብቶ አደርነት የኑሮ ዘይቤ፣ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ የማይመጥን ኋላ ቀር ስለሆነ የሶማሌ ህዝብን የሚወክል የፖለቲካ ድርጅት ወደ ኢህአዴግ ፓርቲዎች መቀላቀል አይችልም ነው በመለስ ዜናዊ የተባልነው። ይህን ውርደት ነው እራስን በራስ ማስተዳደር ነበር የሚባለው? ይህ ነው ፌዴራሊዝም? ይህ ነው እኩልነት? ይህ ነው ዴሞክራሲ?
እኛ እንደምናምነው፤ የሶማሌ ህዝብ የነበረውና የሚወሰድበት መብት የለም። ያልነበረ ነገር አይቀማም። ሀቀኛ ሆኖ በፌዴራሊዝም መርህ ላይ የተመሰረተ አስተዳደር፣ የሶማሌ ህዝብ አይቶ አያውቅም። ያላየው ስርዓት ደግሞ አይናፍቀውም፣ ተቀማሁ ብሎም አያዝንም። አሁን በብልፅግና ፓርቲ መንገድ፣ ትክክለኛውን የራስን በራስ ማስተዳደር ሀቀኛ ፌዴራሊዝም እየጀመርን ነው።
እንደ እርስዎ እምነት የሶማሌ ህዝብን መብት ብልፅግና ፓርቲ ያስከብራል ነው እያሉን ያለው?
በእርግጠኝነት! አሁን በያዝነው መንገድ የሶማሌን ህዝብ ወደ መካከለኛ የሀገሪቱ ፖለቲካ አምጥተን መብቱን እናስከብራለን። በፍትሃዊነት የድርሻችንን እንጠይቃለን። ብልፅግናን የተቀላቀልነው ሶማሌ ሆነን ነው። ባህላችንን፣ እምነታችንን፣ እሴታችንን ይዘን ነው ወደ ብልፅግና የገባነው። ከዚህ ቀደም ወደ መሀል ፖለቲካ መግባት አለብን፣ ተገልለናል፣ ወደ ዳር ተገፍተናል እያልን ስናኮርፍ ነበረ። አሁን እድሉን ስናገኝ ወደ ኋላ ማለት የለብንም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ መንገድ ተዋውቋል። ይህን መንገድ እንሞክረዋለን። ተቃዋሚዎቻችን ግን ለምን ብልፅግና የህዝቡን መብት ይገፋል እንደሚሉ እነሱን መጠየቅ ነው። ስትጠይቃቸውም፣ ለህዝቡ የሚያስቀምጡለትን አማራጭም አብረህ ጠይቃቸው። አማራጫቸው ትናንት ሲገላቸው፣ ሲያሳድዳቸውና በፌክ ፌዴራሊዝም ሲያታልላቸው የነበረውን የህወሓት መንገድ አይነት እንደማይሆን እምነት አለኝ። ብልፅግና መብትን ይገፋል የሚሉት አንዳንዶቹ፤ ከዚህ ቀደም መብትን በመግፈፍ የሚታወቁ፣ እንደተነቃባቸው እንኳን አውቀው ትንሽም የማያፍሩት ናቸው።
እንግዲህ ይህን ጉዳይ ህዝቡ፣ እንዲሁም ብልፅግናን የሚቃወሙት ሰዎች ቅሬታቸው ከምን እንደሆነ ለእነሱ የምተወው ይሆናል። ወደ ሌላ ጥያቄ ልለፍ። በክልሉ ቅድም እርስዎም እንደጠቀሱት ከፍተኛ ወንጀሎች ተፈፅመዋል። ህዝቡ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። በዚህ በኩል የእርስዎ አስተዳደር ዳግም የህዝቡ ጉዳትና ጉዳት ባደረሱት አካላት መካከል እርቅና መግባባት እንዲኖር አስፈላጊ ነው። ለተፈፀሙት ወንጀሎች ፍትህ የሚፈልግ ህብረተሰብም አለ። እንዲሁም ይህ ግፍ ለደረሰባቸው ግለሰቦች ከጉዳታቸው እንዲያገግሙም ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የተሳካላችሁ ጉዳይ ካለ እና እክል የገጠማችሁ ነገር ካለም እባክዎ ይንገሩን--
አንተም እንደምታውቀው የደረሰው ግፍና መከራ በጣም ከሚታሰበው በላይ ሰፊና በተወሳሰበ ደረጃ የተተገበረ፣ በመንግስት ደረጃ በጣም በጥንቃቄ ታቅዶበት የተፈፀመ ወንጀል ነው። ለረጅም ጊዜ የተካሄደም እንደሆነ መረሳት የለበትም። ሁሉንም ጉዳይ ከስር መሰረቱ አጥርቶ ለማወቅና መረጃ ለመሰብሰብ በዚህ በአጭር ጊዜ ሊያልቅ የሚችል አይደለም። ፍትህ የማስገኘቱ ስራ አሁንም እየተሰራ ያለ ነው። ማስረጃዎችን በዶክሜንት ደረጃ የማጥራት ስራ ጊዜ የሚፈልግ ነው። ምክንያቱም ፍትህን ከበቀል መለየት አለብን። በጥድፊያ የሚሰራ ነገር ስህተት ሊኖረው ይችላል። በሌላ በኩል ግን የዚህ ግፍና ወንጀል ሰለባ የሆኑትን ለመደገፍ ጥረት አድርገናል። ማህበር መስርተው እንዲንቀሳቀሱ፣ በኢኮኖሚ በምንችለው ደረጃ ደግፈናል። የጤና መቃወስ የገጠማቸውን አሳክመናል። ሆኖም የደረሰው ጉዳት በጣም አሰቃቂ ስለነበረ እውነት ለመናገር ሁሉን ነገር ብናደርግ እንኳ ጠባሳውን ማሻር አንችልም። ከባድ ስቃይ ነው የተፈፀመባቸው። በርካታ ነገሮችን ሞክረናል። ሆኖም አጥጋቢ እንዳልሆነ ግን አምናለሁ።
መልካም። ይህን ግፍ ሲቃወሙ ለዚህም ሲታገሉ የነበሩ ድርጅቶች ነበሩ። ስርዓቱ በርካታ በደል አድርሶባቸው የነበረ ለህዝባቸው የታገሉ አሉ። ከነዚህም ውስጥ ነፃ አውጪ ግንባር የነበረውና የምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጪ ግንባር በመባል በሚታወቀው ድርጅትና በእርስዎ አስተዳደር መካከል አለመግባባት እንዳለ ይነገራል። የፀባችሁ መንስዔ ምንድነው?
በእኛ እና “የምዕራብ ሶማሊ ነፃ አውጪ ግንባር” በሚባል ድርጅት መካከል የተፈጠረ ችግር የለም። ምክንያቱም በዚህ ስም እኛ የምናውቀው ድርጅት የለም። ከሌለ ድርጅት ጋር ደግሞ ልንጋጭ አንችልም።
በሌላ መንገድ ላስቀምጠው ጥያቄዬን። ከአማፂ ግንባርነት ወደ ፖለቲካዊ ፓርቲነት የተሸጋገረ አካል ጋር ስምምነት አድርጋችሁ ወደ ሀገር ገብቷል። ስምምነታችሁ ምን ነበረ?
ከማን ጋር ነው ስምምነት የፈጠርነው? አንተ ስሙን ከጠቀስከው ድርጅት ጋር ስምምነት አልፈጠርንም። በዚህ ስም የተደራደርነው አካል የለም እያልኩህ ነው።
ኤርትራ ላይ ተደራድራችሁ ስምምነት ፈፅማችሁ ወደ ሀገር የገባ ድርጅት እኮ አለ፤ ክብር ፕሬዚዳንት--
አንተ በገለጽከው ስም የሚጠራ አካል አይደለማ! ከማን ጋር እንደተደራደርን በትክክለኛ ስሙ ጠርተህ ጠይቀኝ እመልሳለሁ።
ከግንባሩ ጋር አልተደራደርንም እያሉኝ ነው?
የትኛው ግንባር?
ONLF የሚባለው ግንባር
ፊደሎቹ የሚወክሉትን ቃላት ዘርዝርልኝ እስቲ…
ምኑን ነው የምዘረዝረው ገለፅኩት እኮ…
እኔ እኮ አንተን ለመጠየቅ የፈለኩት… ይህ በምህፃረ ቃል ያቀረብክልኝ ድርጅት ስሙ ማን ይባላል? ሙሉ ስሙን ጥቀስልኝና መልሱን ልስጥህ።
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ እያወራሁ ያለሁት በስፋት ስለሚታወቅ ግንባር ነው። በዚህ ጊዜዎን ማባከን አልፈልግም። ግንባሩ ስሙ ምንም ይባል ምን፣ ከመንግስት ጋር ስምምነት ፈፅሞ ወደ ፖለቲካ የገባ ድርጅት አለ። እኔም እርስዎም እናውቀዋለን። የተስማማችሁት በምን ላይ ነው። አሁንስ ምን ችግር ተከሰተ? እንደሚሰማው ስልጣንዎን ሊወስድ እንደሚችል ሰግተው፣ ያልፈፀሙትን ወንጀል ፈፅመዋል እያሉ በሀሰት እንደሚከሷቸው ይነገራል። ስለዚህ ጉዳይ ሊመልሱልኝ ይችላሉ?
አንተ በምህፃረ ቃል ብቻ የጠቀስከውን ድርጅት ሙሉ ስሙን መጥቀስ ካልፈለክ እኔ ልንገርህ። “Ogaden National Libration Front” በመባል የሚጠራ ድርጅት ነው። ጥያቄህን የድርጅቱን ስም ጠቅሰህ ነው መጠየቅ ያለብህ። ጥያቄህን የጀመርከው “የምዕራብ ሶማሊያ ነፃ አውጪ ግንባር” ብለህ ነው። በዚህ ስም የሚታወቅ የፖለቲካ ድርጅት ደግሞ የለም። በሌለ ድርጅት ላይ ደግሞ አስተያየት መስጠት የለብኝም:: ለማለት የፈለከው እንደመሰለኝ WSLF በመባል ይታወቅ የነበረ ድርጅት ነው። West Somalia Liberation Front ይባል የነበረው ድርጅት ህልውናው በ1980ዎቹ ያከተመ ነው። ስለዚህ ድርጅት የታሪክ ሰዎችን መጠየቅ እንጂ እኔን ስምምነት ፈፅመሀል ብለህ መጠየቅ የለብህም። ይህን ዝግጅት በርካታ ሰው ያየዋል። እኔ እና አንተ ብናውቀውም ሌላውን ሊያደናግር ስለሚችል መጠንቀቅ አለብን።
ተቀብያለሁ፡፡
የሶማሌ ህዝብ እያዳመጠን ያለ በመሆኑ እውነቱን አፍረጥርጠን መነጋገር አለብን። “ምዕራብ ሶማሌ” በሚል የሚታወቅ ድርጅት ሳይሆን “የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ድርጅት” ተብሎ ከሚታወቅ ድርጅት ጋር ተደራድረን በብዙ ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰናል።
ይህ የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ የሚለውን ስያሜያቸውን ወደ አጠቃላይ የክልሉ የሶማሌ ህዝብ ሊወክል በሚችል ስም በመተካት ለክልሉ ህዝብ ሁሉ ወካይ ስም በራሳቸው ምርጫ እንዲሰይሙ አጠቃላይ መግባባት ነበረን። ዘርዘር ለማድረግ … በመጀመሪያ ደረጃ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ፓርቲ ሆነው እንዲታገሉና አሁን የተገኘውን እድል በሰላማዊ መንገድ እንዲጠቀሙበት፣ የታጣቂ ወታደሮቻቸው ጉዳይን የምንፈታበትና በትጥቅ ትግል ላይ ከመኖራቸው አንፃር የእነሱን ጉዳይ ማኔጅ የሚደረግበት መንገድን በእኛና በእነሱ መካከል የፖለቲካ ውድድር የሚካሄድ በመሆኑ ስለዚህ ጉዳይ የተግባባንባቸው ነጥቦችም አሉ:: እኛ ቃል የገባነውን አድርገናል። በሞቀና በደመቀ ሁኔታ ተቀብለናቸዋል። ለአቀባበሉና ለወታደሮቹ መቋቋሚያ 500 ሚሊየን ብር ያህል አውጥተን፣ መልካም አቀባበል አሳይተናል። ይህ ሁሉም ህዝብ የሚያስታውሰው ነው። እንግዲህ ወደ ፖለቲካው ውድድር ሀሳብን ወደ መሸጥ ነው የተገባው። በዚህም አንዱ የሌላውን ሀሳብ ፍሬ ያለው ነው ወይስ የለውም፣ ያስኬዳል ወይስ አያስኬድም ወደሚል ትችት መግባት ያው የፖለቲካው አንድ አካል ነው የሚሆነው። ይህ የሀሳብ ትግል ነው። ከተከፉም በዚህ ነው እንጂ በምንም ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም።
እርስዎ ድርጅቱ ወንጀለኛ እንደሆነ፣ ደም ሲያፈስ እንደነበረ አንስተው የተናገሩበት አጋጣሚ የለም?
እንደዚያ ብዬ አላውቅም።
ይህ ድርጅት የፖለቲካ ስልጣን ሊይዝ ነው ከእርስዎ ጋር የሚወዳደረው። ያለ እስርና ወከባ እንዲወዳደር ፍቃደኛ ነዎት?
መፍቀድ ብቻ አይደለም extra mile ሄደን በፖለቲካ ነፃ ውድድር እስከፈቀደልን ድረስ ፍቃደኝነታችንን አሳይተናል። ለዚህም ሽማግሌዎች ምስክር ናቸው። ውድድሩንም የሀገር ሽማግሌዎች እንዲታዘቡት የሚያስችል አሰራር ሁሉ ለመዘርጋት ተስማምተናል። በውድድር ለማሸነፍ ነው እቅዳችን።
ቅድም ስለ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፣ የህግ የበላይነትና ስለ ሰብዓዊ መብት ብዙ ነግረውኛል። ሆኖም በክልሉ አሁንም በፖለቲካ ሳቢያ የሚታሰሩ ሰዎች አሉ። በቅርቡ የታሰሩ አካላት ለምን እንደታሰሩ ሊነግሩኝ ይችላሉ?
በጥቅሉ አትጠይቀኝ። የታሰረ ሰው አለ የምትለው ማን ነው? በስም ጠቅሰህ የታሰረን ሰው ጥቀስልኝ…
በርካታ ልጠቅስ እችላለሁ። ክቡር ፕሬዚዳንት፤ በክልሉ በቅርቡ የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ እስር ተካሂዷል። በክልሉ ስለተፈጠረው ጉዳይ ሊነግሩን ይችላሉ? በተለይ የእርስዎ የፕሮቶኮል ሀላፊ የነበሩት አቶ አብዱል ቃድርን አስረውታል? ምክንያቱ ምንድነው?
እኔ በግል ፀብ አላሰርኩትም። የታሰረው በህግ ጥሰት ምክንያት ነው። ሀገር ነው የምንመራው። ሀገር በህግ እያስተዳደርን ነው። ህግ ሲጣስ ህጉ እኛንም እንድናስር ያስገድደናል። ሆኖም.....
ምን ጥፋት አገኛችሁበት? የትኛውን ህግ እንደጣሰ ይህን ፕሮግራም በቀጥታ እየተከታተሉ ላሉት የተከበሩ ተመልካቾቻችን ሊነግሩ ይችላሉ?
አይ አልናገርም፡፡
ክቡር ፕሬዚዳንት ለምን አይነግሩንም?
የማልናገረው ለተከሳሹ መብት ስል ነው። እኔ መሪ ሆኜ የተከሳሹን የህግ ጥሰት በአደባባይ ከተናገርኩ፣ የፍትህ ስርዓቱ ላይ አላስፈላጊ ጫና እናም አድሎ እንዳያመጣ ስጋት አለኝ። ማንም ሰው በህግ ፊት ንፁህ እንደሆነ የህግ ግምት አለ። በህገ መንግስታችን የተቀመጠ ነው። እዚህ ያጠፋውን ብዘረዝር እራሱን ለመከላከል ከፍተኛ ጫና ሊኖርበት ነው። ህግ እየጣስኩ ህግ አስከብራለሁ የማለት ሞራል አጣለሁ። ስለዚህ የማልናገረው ለተከሳሹ መብት፣ ፍትህና ደህንነት ስል ነው።
ምንም ጥፋት ሳይኖርበት አስረውት ቢሆንስ…?
በፍርድ ቤት ስራ ጣልቃ መግባት ስለሌለብኝ ነው የህግ ጥሰቱን የማልነግርህ። ጠቅለል አድርጌ የምነግርህ፤ እኛ ህግ ጥሷል ብለን በህግ ጥሰት ጠይቀነዋል። ህግ መጣስ አለመጣሱን ማጣራት ያለበት ፍርድ ቤት ነው። ያሻውን ያህል ምርጥ ምርጥ ጠበቆችን አሰልፎ የመሟገት መብት አለው። እኛም አቃቤ ህግ መድበን እንሟገታለን። አስፈላጊ መስሎ ከታየን የችሎቱን ሂደት ለህዝብ በቀጥታ ልናስተላልፍም እንችላለን። ጋዜጠኛም ፍርድ ቤት ገብቶ ሊመለከት፣ በነፃነት ሊዘግብ ይችላል።
ህግ ያልጣሰ ከሆነስ…?
ህግማ ጥሷል አልኩህ እኮ…
የቱን ህግ?
በቅርቡ ከተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ፣ አሁን እዚህ በገለፅኩልህ ምክንያት የማልዘረዝረውን የህግ ጥሰት ፈፅሟል ብለን እናምናለን። ፍርድ ቤት ደግሞ የራሱን ፍርድ ይሰጣል። የችሎቱን ሂደት ቤተሰቡም ሆነ ፍላጎት ያለው ሰው መታደም ይችላል። በእስር ቤት በህግ ለተጠየቁ ሰዎች በህገ መንግስቱ የተረጋገጡለት መብቶች እንዳይነኩበት፣ እኔው እራሴ ነኝ፣ ትዕዛዝ ያስተላለፍኩት። ትዕዛዜ ተግባራዊ ስለመሆኑም ተከታትዬ እያጣራሁ ነው። እንደ መሪ ማድረግ ያለብኝ ይህን ነው።
የተፈጠረው እና እሱ በግል ተሳትፎበታል ያሉት ጉዳይ ምንድነው?
የፖለቲካ አለመረጋጋት አልያም የፖለቲካ ክራይስስ ልንለው እንችላለን፡፡
እንዴት ያለ የፖለቲካ ክራይሲስ?
(ፈገግ እያሉ) የፖለቲካ ክራይሲስ ብዬ ብጠቅሰው ነው እኔ የምመርጠው፡፡
የፖለቲካ ክራይሲስ ሲባል እንግዲህ መንግስት ለመገልበጥ ማሴር ሊሆን ይችላል። የፓርላማውን ስራ በህገወጥ መልኩ ማደናቀፍ እና ለህገወጥ ተግባር መመሳጠር ሊሆን ይችላል፣ አማፂ ማደራጀት ሊሆን ይችላል፣ እነዚህን የመሳሰሉት ሊሆኑ ይችላል። ከጠቀስኩት አንዱን መቼም ፈፅሞ ሊሆን ይችላል ብላችሁ ነው የምታምኑት። አይደለም እንዴ ክቡር ፕሬዚዳንት? እስቲ አሁን ከጠቀስኳቸው የትኛው ሊሆን ይችላል?
አንተ የመገመት መብት አለህ። እኔ ግን የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም ፖለቲካል ክራይሲስ በሚለው አገላለፅ እፀናለሁ፡፡
በክልሉ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግስት ማለትዎ ነው?
የፖለቲካ ክራይሲስ ለመፍጠር የታሰበ ሴራ ነው ብዬ የማስቀምጠው፡፡
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አልነበረም እያሉኝ ነው?
የፖለቲካ አለመረጋጋትና ነውጥ ለመፍጠር አይነት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
ምንም ጥፋት ሳይኖርበት አስረውት ቢሆንስ…?
በፍርድ ቤት ስራ ጣልቃ መግባት ስለሌለብኝ ነው የህግ ጥሰቱን የማልነግርህ። ጠቅለል አድርጌ የምነግርህ፤እኛ ህግ ጥሷል ብለን በህግ ጥሰት ጠይቀነዋል። ቀሪው የፍትህ ስርአታችን ስራ ነው። ፍትሀዊ እንዲሆን የሚቻለውን ብቻ ሳይሆን በህግ የተቀመጠውን መብቱን ሁሉ እናስጠብቃለን።
መልካም። ሌሎች የታሰሩም አሉ። እነ ማህዲ ሀሰን ገፍዲድ የሚባል ሰው። ከድር ኦላድ የሚባል ሰው። እነዚህስ ምን አድርገው ነው? ኧረ ብዙ ነገር የማነሳልዎት አለ። ለምሳሌ እርስዎ ያቀረቡትን የደም ባንክ ተጠናቅቋል እወጃ፣ የጤና ሚኒስትሩ አለመጠናቀቁን አስታውቀዋል፣ ተናብባችሁ አትሰሩም ማለት ነው? የጂግጂጋ ከተማ ለህይወት መሰረታዊ የሆነውን ውሃ የተነፈገች ከተማ ናት። ውሃ የለም። የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊውን ለምን በሌላ ተኩ? ብዙ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። እንደውም እርስዎ አክቲቪስት እንጂ ሀገር መምራት አይችሉም ይባላሉ። ክቡር ፕሬዚደንት፤ እውነቱን ለሶማሌ ህዝብ እንዲያሳውቁ እጠይቅዎታለሁ። ይመልሱልኝ!
ሙስጠፋ፡- (አየር ስቦ አስወጣ። ፈገግ አለ። በማዘን ጭንቅላቱን ከወዘወዘ በኋላ) ስማ ማነህ አብዱልሀፊዝ፣ እንዲህ ተብሎ አይጠየቅም… (ሙስጠፌ፣ የተቆጣ ይመስላል…)
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ሁለት ሰዎች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ያሉ አሉ። አንዱ ሪፖርተር፣ አንዱ ደግሞ የቀድሞ አማካሪዎ መሆናቸው ይታወቃል። ለምን ታሰሩ?
በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ አይደሉም። ቀድሞ ታስሮ የነበረው ገፍዲድ ነው። ከድር ቀድሞም አልታሰረም፣ አሁንም አልታሰረም። በነገራችን ላይ የተሳሳተ መረጃ ደርሶሃል። ገፍዲድ የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንጂ ጋዜጠኛ አይደለም። ከድር ኦላድም የእኔ አማካሪ የነበረ ሰው ነው። በነፃነት እየተንቀሳቀሱ ነው በአሁኑ ወቅት። ደውለህ ልታገኛቸው ትችላለህ።
ቀድሞስ ገፍዲድ በማስረጃ ምን ተገኝቶበት ነው የታሰረው?
እንደ ቅድሙ በህግ የተያዘ ጉዳይ ነው። ሆኖም ደጋግመህ እንዳትጠይቀኝ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ሳይገባ ጠቅለል አድርጌ ልንገር። ገፍዲድ ፖለቲከኛ ነው። የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር ማዕከላዊ ኮሚቴ ነው እንደነገርኩህ። ለረጅም ጊዜ በሀገሪቱ በወንጀል ሊያስከስሰው የሚችልን ተግባር በማህበራዊ ሜዲያ ሲቀሰቅስ ነበረ። እንግዲህ ከፓርቲው ጋር ስምምነት ነበረን፤ በሰላማዊ ፖለቲካ ለመጓዝ። እሱ ግን በእኔ ላይ የግድያ እርምጃ እንዲካሄድ ሲቀሰቅስ፣ ሀይማኖታቸው ከሶማሌ ህዝብ ሀይማኖት የተለየውን እንዲገደሉ ሲቀሰቅስ በኦዲዮ ቪዡዋል ማስረጃ አለን። ወንድሜ በጩቤ እንደተወጋ ታስታውሳለህ። ይህን አሳዛኝ ጉዳይ በተመለከተ አደገኛ አስተያየቶችን ሲናገር ነበረ። ጎሳን ከጎሳ የሚያጋጭ ቅስቀሳ ውስጥ ሲገባ፣ እንግዲህ ከዚህ በላይ አንታገስም ብለን አስረነው፣ በዋስ ተፈቷል። ባለፈው በክልላችን የደረሰ ከባድ አደጋ የሶማሌን ህዝብ ምስል አበላሽቶብን ነበረ። ይህ እንዲደገም ስላልፈቀድን ይዘነው፣ በዋስ ተፈቶ አሁን ነፃ ነው፡፡
ፍትሃዊ ፍርድ እንደሚያገኝ ቃል ይገባሉ?
ሰውዬው ከእስር ቤት ውጪ ነው አልኩህ እኮ። ፍርዱ ቅድም እንዳልኩህ፣ በህጉ ያለው መብት ሁሉ ተጠብቆለት ይዳኛል።
መልካም ወደ ሌላ ጥያቄ ልለፍ። እርስዎ አሁን የሚገኙበት ጂግጂጋ ከባድ የውሃ ችግር አለ። የመጠጥ ውሃ ችግር አለ። ቅድም ብዙ ስኬት እንዳስመዘገባችሁ ነግረውናል። ታዲያ የጂጂጋ ከተማ ውሃ ችግር ከየት የመጣ ነው። ከዚህ ቀደም ያልነበረ እና የማይነገር ችግር አሁን እንዴት መጣ? ለምንስ አልተቀረፈም?
የጂጂጋ የውሃ ችግር ቀድሞ ከኔ በፊትም የነበረ ነው። አሁን ድንገት የመጣ አድርገህ ማቅረብ የለብህም። ከዚህ ቀደም በአብዲሌ ቆይታ ጊዜ አምስት ቢሊየን ያህል ገንዘብ የተበላበት ችግር ነው። ሌቦች እየተፈራረቁ የሚበሉበት ጉዳይ ነው። እኛ ስንመጣ ይህን ችግር ለመቅረፍ እየተንቀሳቀስን ነው። አሁን የውሃ ሽፋኑ እየተሻሻለ መልካም በሚባል ደረጃ ነው ያለው። ልዩነቱ የቀድሞ መንግስት ያልተሰራን በፕሮፓጋንዳ ያሳያል። እኛ በውሸት ፖለቲካ መነገድ አንፈልግም። በቀድሞ ስርዓት ስለ ችግር መተንፈስ አትችልም። እኛ ግን የሰውን ቅሬታ የማቅረብ መብት ሰጥተናል። ለዚህ ነው ችግሩ የተጋነነ የመሰለህ።
ሌላው ባሳካነው ሰላም ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ክልሉን ምርጫ አድርገው ለኑሮም፣ ለንግድም እና ለተለያየ አላማ እየመጡ ነው። ይህ ደግሞ በውሃ አቅርቦት ላይ ጫና ማምጣቱ የሚጠበቅ ነው። በፌስቡክ የሚለቀቁ፣ እውነታውን የማያንፀባርቁ ፎቶዎችን ሳይሆን ከፈለክ እኔ ከክልሉ ውሃ አገልግሎት ባለስልጣን ጋር አገናኝቼህ ዝርዝር መረጃ እንዲሰጥህ ለማድረግ እችላለሁ።
ቅድም ብዙ ስኬቶችን እንዳስመዘገቡ ተናግረዋል። ሆኖም እኛ የተለያዩ ሰዎችን ጠይቀን መረጃ ሰብስበን በርካታ ችግሮች እንዳሉ ለማወቅ ችለናል። መንገድ የለም። የመሰረተ ልማት ችግሮች አሉ። የፈራረሱ መንገዶች በየቦታው አሉ። በኢኮኖሚም በኩል ችግር አለ። እንዳልክዎት የውሃ ችግር አለ--
ስላሳካነው ጉዳይ ዶክመንት ስላደረግነው ላቀርብልህና በፕሮግራምህ አሳይተህ ህዝቡ መመልከት ይችላል።
አሃ በእናንተ የተዘጋጀውን ነው እኛ የምናስተላልፈው? እውነታ የሌለው ነገር አዘጋጅታችሁ ቢሆንስ?
ከፈለክ መጥተህ በአካል ማየት ከፈለክም እንደዚያው። በዋይፋይ ከቻልንም እንዳሁኑ ቃለ መጠይቅ አይነት በማዘጋጀት ማስጎብኘት እንችላለን።
የፈራረሱ መንገዶች፣ የውሃ ችግሩ እኮ ፈጦ ያለ ነው ክቡር ፕሬዚዳንት…
(ፈገግ አሉ፤ በቅሬታ አይነት) አብዱልሀፊዝ፤ እባክህ እንዲህ አይጠየቅም። ለተመልካቾቻችን ክብር ስንል እንዲህ አይጠየቅም…
ለምን አይጠየቅም?
የሚጠየቀው ባላችሁ ሀብት ምን አቅዳችሁ ምን አሳካችሁ ነው። ለምሳሌ ጥናት አድርገን የዚህ ክልልን በአንድ አመት የተሻለ ልማት ልናመጣ የምንችለው በምን ያህል ገንዘብ ነው ብለን ስናሰላው፤ ወደ አስር ቢሊየን ዶላር ያህል ይሆናል። እኛ በወቅቱ በእጃችን የነበረው አምስት ቢሊየን ዶላር ነው። በዚህ በያዝነው ብር ምን ቅድሚያ በመስጠት ሰራን፣ ብሩ የት ገባ? ባቀዳችሁት መሰረት ምን አሳካችሁ? ብለህ መጠየቅ ጥሩ ነው። በአንተ መንገድ ግን ጥያቄ አይጠየቅም።
እንዴ ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ጥያቄ የመጠየቁ አማራጭ መንገድ እኮ የኔ ምርጫ ነው። እንደፈለኩት ብጠይቅ ምን ችግር አለው?
እሱማ መብትህ ነው መጠየቅ፣ ሰው ይታዘበኛል የማትል ከሆነ። ለምሳሌ እኔ ልጠይቅህ?
እሺ፡፡
ሞቃዲሾ እንደ ኒውዮርክ ለምን ፎቅ በፎቅ አልሆነችም ብዬ ብጠይቅህስ? (ጋዜጠኛው አልመለሰም) … አየህ አንድ ነገር ስረ መሰረቱን የሚገነዘብ ጥያቄ ነው መጠየቅ ያለብህ። facts on the ground and reality የሚባል ነገር አለ። ይህን መሳት የለብህም። በዚህ መንገድ መጠየቅ የምንችለውንና የማንችለውን፣ የተሳካና ያልተሳካውን ለመለየትና ለመሞገት ይቻላል። ለምን የተፈረካከሰ መንገድ ይኖራል? ብሎ ጥያቄ፣ ለኔ ጥያቄ አይደለም።
ደሃ ሀገር ነው ያለነው። በርካታ ያልተሟሉ ነገሮች አሉ። ፍላጎት አለ። እንኳን እዚህ አንተ ያለህበት የለንደን ነዋሪን ስለ መሰረተ ልማት ብትጠይቀው በርካታ ችግር ሊነግርህ ይችላል።
(ጋዜጠኛው ፈዞ ቀረ። ፕሬዚዳንቱ  ፈገግ አሉ። … ጋዜጠኛው ወደ ሌላ ጥያቄ ለመሻገር ጉሮሮውን ጠረገ።)
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ሙስና እንደሚታይ ይነገራል። የስልጣን ክፍፍል ላይም የአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ እንደተሰባሰባችሁ መረጃው ደርሶኛል። በኋላ በሰፊው ዘርዝሬ እጠይቅዎታለሁ። አሁን ግን አንድ ሳልዘነጋው መጠየቅ የምፈልገው የተፈናቃዮች ጉዳይን ነው። ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ አስከፊ ነው። ምነው በልማት እቅዳችሁ ዘነጋችኋቸው? አቅም አጥሯችሁ ነው ወይስ አንዳንዶች እንደሚወቅሷችሁ ስላልፈለጋችሁ?
ተፈናቃዮችን በተመለከተ የሰራነውና እየተሰራ ያለ ስራ አለ። በተለይም ቀጥታ ከኑሮአቸው ጋር የተያያዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው። የትምህርት፣ የጤና እና የመሳሰሉ አስፈላጊና አንገብጋቢ ጉዳዮችን እየሰራን ነው። አንዳንድ ጉዳዮችን ከሩቅ ከመተቸት ይልቅ ስራውን ቀረብ ብሎ ውስብስብነቱን ተረድቶ ፌር የሆነ ምልከታ ሊኖረን ይገባል። እኛ ስልጣን ከያዝን በኋላ በሰላም ላይ በሰራነው እልህ አስጨራሽ ስራ፤ በኢትዮጵያ መፈናቀል ያልታየበት ክልል እኔ የማስተዳድረው ክልል አንዱና ምሳሌም ሊሆን የበቃም ነው። በዚህም ተፈናቅለው የነበሩና አሁን የተረጋጋ ሰላማዊ ኑሮ የጀመሩ በርካቶች ናቸው። ይህም በተግባር በሚሰራ ስራ የሚገኝ ውጤት ነው።
እኔ እንግዲህ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከተፈናቃይና የስደት ጉዳዮች ጋር የመስራት ልምድ አለኝ። በበርካታ ሀገራት የስራ ልምዴ፣ በአመት ከስድስት ወር፣የተፈናቃይ ጉዳዮች ሁሉ ተፈትቶ፣ ምቹ የሚሆንበት አለም የለም። ጊዜ ይፈልጋል። ፖለቲካውን ማረጋጋት ያስፈልጋል። እንደውም እኛ ጋ ያሉት ተፈናቃዮች በዓለም አቀፍ ኢንዲኬተር ልኬት መሰረት ስናየው የተሻለ የሚባል ነው። ወደ ቀያቸው መመለስ፣ ግጭት መፍታት፣ ባሉበት ቦታ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች እንዲሟሉላቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን ደግሞ ክልሉ ብቻውን ለመስራት የአቅም ችግር አለብን። የፌደራል መንግስት፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርዳታ ያስፈልጋል። ተባብረን የሰራናቸው ስራዎች አሉ። መስራት ሲገባን ያልሰራናቸውም አሉ።
መልካም። አንዳንዶች የስልጣን ክፍፍልን በተመለከተ፣ የርስዎ አስተዳደር የሚቀርብዎትን ሰዎች ብቻ፣ ከአንድ አካባቢ፣ ማለትም እርስዎ ከተወለዱበት አካባቢ ብቻ ስልጣን ላይ እንዳስቀመጡ በምሬት ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?
(ሳቅ ብለው) ይህ አስተያየት አዲስ ነው ለእኔ። ካልክ አይቀር እኔ እንደውም የምከሰሰው ለተወለድክበት አካባቢ ሰው፣ ለሚቀርብህ ሰው ስልጣን አትሰጥም በሚል ነው። እኔ እስከማውቀው የስልጣን ክፍፍል፣ ከሁሉ አካባቢ የተውጣጣ፣ ፍትሃዊና ሚዛናዊ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው፣ እኔ ጎጥና ቀበሌ አልመለከትም፤ የማምነው በችሎታ  ነው። ችሎታ ደግሞ አላህ የሰጠው በሁሉም አካባቢ ላሉ ሰዎች ስለሆነ ሚዛኑን መጠበቁ ተፈጥሮአዊ ነው። ሆኖም ሚዛኑን እንዳይስት ከሁሉም አካባቢ ሰዎች እንዲኖሩ ጥረት እናደርጋለን። ለምሳሌ ዋና ዋና የስልጣን ቦታ ከሚባሉት አምስቱን ብዘረዝርልህ፣ ምክትል ፕሬዚዳንታችን ከሲቲ ዞን ነው (ከድሬዳዋ ዙሪያ እስከ አፋር አካባቢ ያለ ዞን ነው) የፓርቲያችን ዋና ፀሀፊ ከአፍዴር ዞን ነው (ክልሉ ወደ ደቡብ ምስራቅ) የክልሉ አፈ-ጉባዔ ከሞያሌ አካባቢ ነው። የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቶግ ወጃሌ አካባቢ ነው። የክልሉ ጄኔራል ኦዲተር ፋፈን ዞን (ጂግጂጋ አካባቢ) ነው። እንዲህ እየዘረዘርኩ ላስረዳ እችላለሁ። ለህዝቡ ምን ሰራችሁ በሚለው ብንመዘን ይሻላል። ማን ስልጣን ያዘ። ከየት አካባቢ። ከየትኛው ጎሳ፣ ከየትኛው ጎሳ ንዑስ ጎሳ እያልን ነው የማናድገው። በዚህ በኩል ችግር አለ እንባላለን። በዚህ በኩል ደግሞ ስልጣንና የጠበበ ጎሰኝነትን እናራምዳለን። በየት በኩል እንደግ?
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ በእርስዎ ላይ ወቀሳ የሚሰነዝሩ ወገኖች እኮ “የማናድገው በከፍተኛ ደረጃ የህዝብ ገንዘብ እየተበላ ስለሆነ ነው” እያሉ ነው። ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የእርስዎ አስተዳደር በሙስና ተጨማልቋል ይባላል። መልስ አለዎት?
እኔ እኮ የሚገርመኝ እንዲህ መሰረተ ቢስ ወሬ የሚነዙ ሰዎች ናቸው። ማን እንደሆኑ ደግሞ አውቃለሁ። እነዚህ ሰዎች ከአብዲሌ ጋር አይን ባወጣ ሙስና የተጨማለቁ፣ የሶማሌን ህዝብ ስጋና አጥንት ሳይቀር ግጠው የጨረሱ፣ የለመዱትን ሌብነት በእኔ አስተዳደር ጊዜ እየተከታተልኩ ቀድሞ የሚበሉትን ሙስና ስላስቀረሁባቸው ነው የሚያላዝኑት። ይገርማል። ለለውጡ ከበጀ ይሁን እስቲ ብለን ዝም ብንላቸውም፣ ሊያርፉ አለመቻላቸው ያሳፍራል። በነፃነት እየሰሩ ነው። ዘርፈው በገነቡበት ትልልቅ ሆቴልና ቤቶቻቸው ዘና ብለው እየኖሩ ነው። ግዴለም ይስሩ። ይኑሩ። ሆኖም ትናንት የለመዱትን የህዝብ ሀብት ዘርፎ መብላት እንደ መንግስታዊ የተለመደ ስራ ስለሚቆጥሩት፣ እነሱ ካልዘረፉ “ሌላው እየዘረፈ ነው ማለት ነው” እያሉ ያለ ማስረጃ ዝም ብለው ያወራሉ። በአማርኛ “ሌባ እናት ልጇን አታምንም” እንደሚባለው ነው። እየውልህ የነውራቸውን መጠን ልንገርህ። እኛ በዚህ በአንድ ዓመት ከስምንት ወር የሰራነውን እነሱ በአስር አመት አልሰሩትም። ሰባት ደረጃ አንድ የአስፋልት መንገድ ስራ አስጀምረናል። አምስት ሆስፒታል ሰርተን፣ ሶስት ወደ ሆስፒታልነት ደረጃ ከፍ አድርገን፣ ሁለት አጠቃላይ ጥገና አድርገናል። ሰላም የፈጠርነው ከሰላሳ ሺህ በላይ ወጣቶችን ተገቢውን ስልጠና ሰጥተን፣ ትጥቅና ስንቃቸውን አሟልተን ነው። በየገጠሩ ከአስር በላይ የገጠር ድልድይና ጥርጊያ መንገድ ሰርተናል። ከዚህ ቀደም የደም ባንክ ነበረ? የለም። አሁን ሶስት አለ። የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች በርካታ ናቸው። እኔ “ገና እንሰራለን፣ በዚህ አንኩራራ” ስለምል በቴሌቪዥን ከበሮ አላስደልቅም። ይህ ርካሽ ፖለቲካ ስለሆነ ነው።
እኔ ሀገር እየመራሁ ነው። ስራ አለብኝ። ለአሉባልታ እየመለስኩ ጊዜ አላባክንም። በርግጠኝነት እኔን ከአዲሳባ መጥቶ በገንዘብ የምመልሰው ሰው የለብኝም። ፈርቼ ገንዘብ እየሰጠሁት የማባብለው ባለስልጣንም ሆነ የጦር ጄኔራል የለም። ያስቆምኩት በሞኖፖል የተያዘውን፣ በአብዲሌ የቅርብ ሰዎች የመንግስትን ስልጣን ተጠቅመው የዘረጉትን የንግድ መረብ ነው። ይህ የሚያንገበግበው ብዙ ሰው አለ። በርካታ ትግል አድርገናል ሙስና ላይ። አሁንም እያደረግን ነው። ለምሳሌ ልንገርህ፣ የሾምኩት አንድ ባለስልጣን ነበረ። ስሙ ይለፈን። ለትምህርት ቤት ያስመጣው ወንበርና ቁሳቁስ በጣም የወረደ ነበር። አስመረመርኩት። ሙስና አገኘሁበት። አሰርኩት። በፌስቡክ “ሙስጠፋ እንደ አብዲሌ እስር ጀመረ” ተብሎ ዘመቻ ተከፈተብኝ። ሙስና ላይ ቁርጠኛ ነኝ። እየሰራን ነው።
ከርስዎ ጋር ስላልተግባባ ስልጣን ላይ የነበረ ሰውን አንስተው ሌላ ሰው ተክተዋል...
ሀገር እየመራሁ ነው። መንግስታዊ ስራ ነው የምሰራው፡፡ ከስራው አንዱ መንግስት የያዘውን እቅድ የሚያስፈፅምለትን ትክክለኛ ሰው፣ በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ ነው። አንተ ስለ የትኛው ሰውና ቦታ ነው እየጠየቅኸኝ ያለኸው?
በቅርቡ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎትን አንስተውታል። ለምን አነሱት?
ለኔ ምክንያት አለኝ። የፀጥታ ስራው በምፈልገው ደረጃ በእስትራቴጂና በእቅድ ሊመራልኝ አልቻለም። ከቀን ወደ ቀን የፀጥታ ስራ እየተበላሸ ሲመጣ ታወቀኝ። የተቀናጀ እቅድና ሪፖርት አያመጣልኝም። የእሱ ስራ በአጠቃላይ እኔ ላይ ወደቀ። እኔ ደግሞ የሚያግዘኝ ሰው እፈልጋለሁ። ቦታው የሚፈልገውን ግዴታዎች ሳይወጣልኝ ሲቀር ቀየርኩት። ሰላም ከተረበሸ በኋላ መጣደፍ ሳይሆን ሰላም እንዳይረበሽ በእቅድና በእስትራቴጂ መስራት ያስፈልጋል። ሰላም ከሌለ ሀገር የለም። አንተ የሶማሊያ ዜጋ ነበርክ። ሀገሪቷ ሰላሟ ስለተረበሸ ነው በስደት እንግሊዝ የገባኸው አይደል? የአንድ ሰው መነሳትን ከሀገር ሰላም ጋር ማወዳደር አያስፈልግም።
እሱን የተካው ሰው ሰላም እንደሚያሰፍን በምን አረጋገጡ?
መቼ አረጋግጫለሁ አልኩ?
ማለቴ የተነሳው ሰው ያላሳካውን ያሳካልኛል ብለው እንዴት አመኑ?
በልምዱ፣ በትምህርቱና አጠቃላይ ባለው ምልከታ አመዛዝኜ ነው ለቦታው ይሆናል ያልኩት። ከዚህ ቀደም የሀገር መሪን የማማከር የስራ ልምድ አለው፤ በትምህርትም እስከ ፒኤችዲ ዘልቋል፡፡ በህብረተሰብ ጤና እና በግጭት አወጋገድ፣ conflict resolution ላይ ልምድ አለው። የአለም ፖለቲካ አካሄድ፣ የሀገራችንን ፖለቲካና የክልላችንን ተጨባጭ ሁኔታ በደንብ የሚያውቅ ሰው ነው።
ከዚህ ቀደም የፀጥታ ዘርፍ፣ ከአማፂ ጋር ለመዋጋት አይነት፣ የፀጥታ ስራ እንዲሁ ትምህርት የሚያስፈልገው በማይመስል አይነት ነው የሚፈረጀው። የፀጥታ ስራ ትምህርትና ልምድ ይፈልጋል። ከዚህ ቀደም ታማኝነትና ዝምድና ነበር የሚታየው፤ ለዚያ ነው በችግር የምንታመሰው። እኔ ሰው ነኝ ልቦናን አልመረምርም። አላውቅም። የቀድሞም ሰው ይረዳኛል ብዬ አምኜ ነበር። ስራው እየወረደብኝ መጣ። የሙስናም አዝማሚያ አየሁበት። ቀየርኩት። አሁን የምሾመውም ሰው ለግል ፍላጎቴ አይደለም የምሾመው። ህዝብን እንዲያገለግል ነው። ባመንኩት ደረጃ ካላገለገለ ሊነሳም ይችላል። የሚመራን መርህና መርህ ብቻ ነው። ይህ መርህ አድሎና ኢ-ፍትሃዊነት አለበት ብሎ መጠየቅ አንድ ነገር ነው። እንዴት ሰው አንስተህ ተካህ ይባላል? መጠየቅ ካለብን መንግስታዊ አሰራር ካበላሸን ነው። አሰራር ነው መጠየቅ ያለበት እንጂ እከሌን አንስተህ ለምን እከሌን አደረግህ መባል የለበትም።
አሁንም እስቲ ወደ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ልመልስዎት። እርስዎ የሆስፒታል ስራው እየተቀላጠፈ ነው ሲሉ፣ ፕሮጀክቱ ገና አልተጀመረም ብለዋል የጤና ሚኒስትሩ:: ከሁለታችሁ ማነው ትክክል? ማነው የተሳሳተው?
ሆስፒታል አይደለም፤ የደም ባንክ ነው፡፡  
ይቅርታ ልክ ነዎት፤ የደም ባንክ ነው።
ጉዳዩ ከአዘጋገብ ስህተት የተፈጠረ ነው። የደም ባንኩ አሁን አልቆ ስራው የፊኒሺንግ እና የውስጥ አስፈላጊ ግዢዎች አልቀው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ነው። ሲዘግቡት ስራ ጀምሯል አሉ በስህተት። ሚኒስትሩ ስራው አልቆ አልተጀመረም አሉ። እውነታው ስራው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መሆኑ ነው።
ሚኒስትሩ፣ የደም ባንኩ ስራ አልጀመረም ሲሉ፤ እርስዎ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ነው ይላሉ፡፡ አብራችሁ እየሰራችሁ፣ እንዴት እንዲህ አይነት ልዩነት ይኖራል?
እኔ እና ሚኒስትሩ እኮ ሰዎች ነን። Miss Communication ነው የተፈጠረው። ሰዎች ነን። በበርካታ ጉዳዮች ላይ የመረጃ መዛነፍ ሊኖር ይችላል። This is normal. ስራው ማለቂያው ላይ ነው። ገንዘቡ አልተበላም።
ልክ ነዎት ክቡር ፕሬዚዳንት፤ የሰው ልጅ ነዎት፤ ሚስኮምኒኬሽን ሊፈጠር ይችላል። ተናብባችሁ ብትሰሩ ኖሮ “ተጀምሯል፣ አልተጀመረም፣ አልቋል አላለቀም” አይነት ውዝግብ አይመጣም ነበር። የደም ባንክን የመሰለ ትልቅ ጉዳይ አልቆ ስራ ጀመረ፣ ኧረ አልጀመረም፣ እርስዎ ደግሞ አሁን በመልካም ደረጃ ነው ያለው ይሉኛል። ይህን ጉዳይ ከረሳችሁት ሌላ ምን የረሳችሁትን ነገር አስታውሰው ለተመልካቾቻችን ሊነግሩ ይችላሉ?
(በግርምት ግንባራቸውን ቋጠር አድርገው) የረሳችሁት ካለ ንገረኝ ምን ማለት ነው? የረሳነውን አንተ የምታስታውሰው ነገር ካለ ንገረኝ እንጂ። ስንት ጉዳይ አብራርቼ፣ ስንት ጉዳይ ተናገሬ ሳበቃ፣ የረሳኸው ካለ -- ምን ማለት ነው? (መገረማቸው በውስጣቸው “ሆ! ይህ ሰውዬ አብዷል እንዴ!” የሚል ይመስላል)
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ማለቴ የደም ባንክን የመሰለ የሰው ህይወትን ለማትረፍ ትልቅ ስራ ከረሳችሁ፣ ምናልባት የውሃ ችግር ቅድም የነገሩኝን ረስታችሁትስ ቢሆን፣ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ እንዲሁ የፀጥታ ጉዳይን እንደማትረሱት፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ፣ የልማት ጉዳይን እንደማትረሱት ምን ዋስትና አለን ለማለት ነው?
(የታከታቸው መሰሉ፤ አየር ስበው አስወጡ፤ በቅሬታ በለዘበ፣ የትዝብት ቃና ባለው ድምፀት) እባክህ አብዱልሀፊዝ፤ እባክህ እባክህ፣ ተመልካቾች ቁምነገር እየጠበቁ፣ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ መጠየቅ ስትችል…
(አቋርጦ ገባ) እጠይቃለሁ ---- ገና ብዙ የማነሳው ነገር አለ…
(ቆጣ ባለና ከፍ ባለ ድምፅ) የደም ባንኩን እኮ አልረሳነውም፣ አልተረሳም፡፡ ብሩም አልተበላም። ሚኒስትሩ ሄደው ስራውን አዩ፤ መጀመር በሚያስችል ደረጃ ነው አሉኝ። እኔ የእሳቸውን ተቀብዬ አስተላለፍኩ። ጥያቄው ወደ ዞን ሀላፊ ሲመጣ፣ ገና አልተጀመረም አለ። ከዚያ ሚኒስትሩ መልሰው አልተጀመረም አሉ። በቃ absolutely it’s a minor miscommunication. ምንም የረባ፣ ለክርክር የሚበቃ ጉዳይ አይደለም።
እሺ የሚጀመርበትን ጊዜ በትክክል ሊነግሩኝ ይችላሉ? ክቡር ፕሬዚዳንት፤ የደም ባንክ ጉዳይ አጣዳፊ ስለሆነ ነው ደጋግሜ የጠየክዎት፡፡ ስለዚህ መቼ ለአገልግሎት ይደርሳል?
(ፕሬዚዳንቱ አቀርቅረው ጭንቅላታቸውን ወዘወዙ። የደም ባንኩ ተራ ጥያቄ ደማቸውን ያፈላው ይመስላል) በቅርቡ ይደርሳል። ይህ ደርሷል አልደረሰም ንትርክ፣ ከሳምንታት በፊት የነበረ ነው። አሁን ላይ እንደውም ለአገልግሎት ዝግጁ ሳይሆን አይቀርም። በነገርህ ላይ በአብዲ እና ከአብዲ በፊት በነበረው አስተዳደር፤ ትምህርት ቤት ተሰራ ተብሎ ሪፖርት ይደረጋል። ብሩ ተበልቶ ትምህርት ቤቱ አይሰራም። ህንፃ ተሰራ ተብሎ ህንፃውን ልትፈልገው ብትመጣ እዚህ ነበረ፣ ማን አነሳው? ይሉሃል። በእኔ ጊዜ ንትርኩ፤ አልቋል አላለቀም መሆኑ በራሱ ለውጥ ነው።
መልካም። በእርስዎና በክልሉ የፓርላማ አባላት መካከል ግጭት መኖሩ ይነገራል፡፡ ምንድነው የግጭቱ መንስዔ?
ምንም ግጭት የለም መሃላችን። የመንግስትን ስራ በአግባቡ ይቆጣጠራሉ። የደም ባንኩ ንትርክ ምንጩ፣ እኔ ለፓርላማው ባቀረብኩት ሪፖርት ላይ አባላት እኮ ናቸው “ያላለቀ ስራ ሪፖርት አድርገሃል” ብለው ያፋጠጡኝ። ይህ የዴሞክራሲያዊነት መገለጫ ነው። ስራቸውን ያለ ምንም እቀባ በነፃነት ነው የሚሰሩት።
ክቡር ፕሬዝዳንት፤ ሌላ የማነሳልዎት ጉዳይ በእርስዎ ቀጥተኛ ትእዛዝ፣ እርስዎ ስላሳሰሩት ኢርሻድ የተባለ ሰው ነው። ለመሆኑ እርስዎ ከእስሩ ጀርባ አሉ እንዴ? ማለቴ ማዕከላዊ መንግስት አዲሳባ ስለታሰረ፣ እርስዎ እንዳሳሰሩት መረጃ ደርሶኛል። ለምን አሳሰሩት?
ህግ ከጣሰ ይታሰራላ!
ለምን ታሰረ?
ሰው ሲታሰር መብቱ ተገፈፈ ወይስ አልተገፈፈም? ማሰቃየት ደርሶበታል ወይ አልደረሰበት? ተብሎ ይጠየቃል እንጂ እንዴት ሰው ለምን ታሰረ ይባላል? ሰው የማይታሰርበት ሀገር አይተህ ታውቃለህ? ሰውን የማያስር መንግስት አይተህ ታውቃለህ-- አንተ?
አላውቅም፣ ግን በህጉ መሰረት ነው የሚታሰረው። ይህ ሰው ግን “እኔ ሳላጠፋ ከህግ ውጪ ፕሬዚዳንቱ ነው ያሳሰሩኝ” እያለ ነው። እርስዎ አሳስረውታል አላሳሰሩትም?
እኔ እንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት አልፈልግም ነበር። ግን ላንተ ልስጥህ። ሰው ሲታሰር “ሙስጠፋ ነው ያሳሰረው፤ የሙስጠፋ ወንድም ነው ያሳሰረው፤ አጎቱ ነው ያሳሰረው--” እየተባለ አሉባልታ ይነዛል። ሁሉም “ሙስጠፋ እንዲህ አደረገኝ፣ ይህን ፈፀመብኝ” እያለ ቢያወራ፣ እኔ እየተከታተልኩ መልስ መስጠት የለብኝም። በዚህ ጥያቄህ ተመልካቾች እንዳይሳሳቱ ስል ጉዳዩን ልንገርህ። አሁን የጠቀስከው  ሰው፤ በአብዲ ኢሌ ጊዜ ከፍተኛ ወንጀሎችን አብሮ ሲሰራ የነበረ፣ የአብዲ ኢሌ ቀኝ እጅ ከሚባሉት አንዱ ነው። በክልሉ በደረሰው የሀምሌ 28 ከባድ አደጋና የማይታመን ውድመት ውስጥ እጁ አለበት ተብሎ ነው የታሰረው። መንግስት አሰረው። አለቀ። ኋላ ለፖለቲካው መረጋጋት፣ ለለውጡና ሽግግሩ ሲባል እሱ ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰዎች ይቅርታ በተደረገላቸው መሰረት፣ ይቅርታ ተደርጎለት ተፈታ። ክልሉ ውስጥ የደረሰው ያ መዓት፤ በመንግስት ደረጃ የተፈፀመ ስለሆነ ሁሉም በህግ የሚጠየቁበትን አሰራር ብንከተል፣ ማንም ላይተርፍ ይችል ይሆናል። ሁሉንም አስረን ደግሞ ሀገር ማረጋጋትና ሰላም መፍጠር አንችልም። ለዚያ ብለን በሆደ ሰፊነት ከተለቀቁት ውስጥ ይህ አንተ ስሙን የጠቀስከው ሰው ይገኝበታል።
ከዚያም ወደ ክልሉ ሲመጣ ዳግመኛ ታሰረ። እርስዎ መለቀቁን አልደገፉትም ማለት ነው?
አይ እንደዚያ አይደለም። ወደ ሌላ ወንጀል ሊሸጋገር ሲል ህግ ማስከበር ስላለብን አሰርነው። ጉዳዩን በህግ ይዘነው። ኋላ ክሱን አቋርጠን ለቀነዋል። እሱ ፕሬዚዳንቱ አሳሰረኝ ይላል። የታሰረው ግን የክልሉ የሀይማኖት አሊሞች ላይ በቀሰቀሰው ከባድ ውንጀላ ነው። በእምነታቸው ጠንከር ብለው በደንብ የእስልምና ስርዓትን የሚያከብሩ ትላልቅ ሰዎች ላይ “አልሸባብ ስለሆኑ ሊወገዱ ይገባል” እያለ አደገኛ ቅስቀሳ ውስጥ ገባ። የከፋ ነገር ሳይደርስ ከህግ በታች መሆኑን ልናሳውቀው አሰርነው። እንደ አብዲ ኢሌ መንግስት፣ የሚቦርቅበት ዘመን ማለፉን ልናስገነዝበው በህግ ጠይቀነዋል። አሁን ግን አልታሰረም። በነፃነት እየተንቀሳቀሰ ነው። ከእስሩ ጀርባ ሌላ የፖለቲካ ጨዋታ ሊጫወት ይፈልጋል። በሶማሌ ህዝብ ስቃይና መከራ ሀብት እንዳካበተ ማንም ያውቃል። ይህን በሆደ ሰፊነት አልፈነዋል። ግን ህግ ከጣሰ ዛሬም ይታሰራል፤ ነገም ሊታሰር ይችላል። ማንም ከህግ በላይ መሆን አይችልም።
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ስለ ሃይማኖት ጉዳይ ካነሳን አይቀር፣ እርስዎ እራስዎ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ “ሶማሌና ሙስሊም ያልሆኑ ሌሎች ብሔሮችና የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችን የእምነት በዓላት፣ ጅጅጋ ላይ በድምቀት እንዲያከብሩ፣ የተለየ መብት ሰጥተዋል” በሚል ይተቻሉ፡፡ ስለዚህ ትችት ምን ይላሉ?
አዎ! ህገ መንግስቱ ያጎናፀፋቸውን መብት ሰጥተናል፤ አንነፍጋቸውም። ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ብዙ የተለያዩ ብሔርና እምነት በሰላም ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር ናት። እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ጤነኛ አስተሳሰብ የሌላቸውና ከእነርሱ በስተቀር የሌላ እምነት ተከታይ መኖር የለበትም ከሚሉ ፅንፈኛ አክራሪ ቡድኖች እንጂ ከአንተ ዓይነት በተለይ የእምነት እኩልነትና ነፃነት በተከበረበት በሰለጠነ፣ በእንግሊዝ ሀገር ውስጥ ከሚኖር ሰው አልጠበቅሁም ነበር፤ በጣምም ገርሞኛል! እኔ በማስተዳድርበት ክልል ህገ መንግስትም ሆነ በሀገሪቱ ህገ መንግስት፣ የእምነት ነፃነት ተረጋግጧል። የፈለገህን ሃይማኖት ማምለክና ማራመድ በሚቻልበት ሀገር ውስጥ ነው ያለነው። የእኔ ህጋዊ ኃላፊነት፣ ለሁሉም እምነት ህጋዊ ከለላ መስጠት ነው። በነገርህ ላይ የሶማሌ ህዝብ፣ ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር አብሮ የመኖር አንዳችም  ችግር የሌለበት፣ ተከባብሮ የሚኖር ህዝብ ነው። በክልሉ ከዚህ ቀደምም በይፋ ሰው የፈለገውን እምነት በነፃነት ያመልካል። እኔ ያደረግኩት፣ ሙስሊምንና ክርስቲያንን ለማጋጨት፣ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የጥፋት ሀይሎች ሀይማኖታዊ በዓላት ላይ አደጋ እንዳይጥሉ ነው፣ ደህንነታቸውን በሚገባ ያስጠበቅኩት።
አንተ አብዱልሀፊዝ ግን ለንደን ነው የምትኖረው። ሙስሊም በቁጥር የሚያንስበት ሀገር መብትህ ተከብሮ እየኖርክ፣ እንደፈለክ በአደባባይ እያመለክ፣ የሰብአዊ መብትን የሚገነዘብ ጋዜጠኛ ሆነህ በኢትዮጵያ ሀገራቸው ላይ ሀይማኖታቸውን ለሚያከብሩ የተለያዩ ዜጎች ከለላ ሰጥቼ፣ ደህንነታቸውን በማስጠበቄ እንዴት እንዲህ አይነት ጥያቄን ትጠይቃለህ? በጣም አስገርሞኛል። መታረም ያለበት አመለካከት ነው። (ጋዜጠኛው ተሸማቀቀ፣ ልክ ነዎት በሚል አይነት ራሱን ነቀነቀ፤ ፕሬዚዳንቱን ነጥብ ለማስጣል የተሰጠው መረጃ፣ እራሱን ነጥብ ስላስጣለው ሳያፍር አልቀረም)
መልካም። እርስዎ ወደዚህ ስልጣን ከመምጣትዎ በፊት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከመሰራትዎ ባሻገር የሰብአዊ መብትን ማዕከል ያደረገ አክቲቪስትም ነበሩ። የእርስዎን የፖለቲካ አካሄድና የአስተዳደር ሁኔታ የሚነቅፉ ወገኖች፤ “አቶ ሙስጠፋ አሁንም አክቲቪስት ናቸው። ሀገር የማስተዳደር ችሎታ የላቸውም። መሪነት እና አክቲቪስትነት እየተቀላቀለባቸውና እየተምታታባቸው ነው” ይላሉ። በርካታ ኮፍያዎችን ደራርበው ለብሰዋል። መቼ ነው እነዚህን ኮፍያዎች የሚያወልቁት?
(ፕሬዚዳንቱ በስጨት ያሉ ይመስላሉ፤ ቃላቶችን ረገጥ፣ ሻከር እያደረጉ) ይላሉ!-- ይላሉ!-+ ይላሉ። ይበሉዋ!
እና?
(ፕሬዚዳንቱ ለአፍታ ዝም አሉና) እየውልህ፤ ትችታቸው ይህን ተግባር ፈጽመሃል፤ ተግባሩ ከአክቲቪስትነት የመጣ ነው። ይህን  አድርገሃል፤ ይህ ደግሞ ከፖለቲከኝነት አልያም ከሌላ ማንነትህ የመጣ ነው --- በማለት ዘርዘር አድርገው ሲተቹ ምላሽ ልሰጥ እችላለሁ። ለእያንዳንዱ የማይረባ ትችት መልስ እየሰጠሁ ጊዜ አልፈጅም። በጣም አሳሳቢ ችግሮችን የምንፈታበትን ውድ ጊዜ፣ ለምን በማይረባ ንትርክ  አባክናለሁ። እኔ እሰራለሁ። እነሱም ይተቹ።
ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ጥያቄዎቼን አጠናቅቄያለሁ፡፡ አመስግኜዎት ፕሮግራሙን ከመዝጋቴ በፊት የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት--
አብዱልሀፊዝ፤ በርካታ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን አንስተሃል፡፡ የክልሉን ጉዳይ እንዳብራራ እድሉን ሰጥተኸኛል። ያነሳሃቸው ጥያቄዎች ጠቃሚና ብዙ የክልሉ ጉዳዮችን የሸፈኑ ናቸው፡፡ ለዚህም አመሰግናለሁ። በመጨረሻም፣ ይህን ፕሮግራም እየተከታተለ ያለ የሶማሌ ህዝብ፣ በኢትዮጵያም በአፍሪካ ቀንድ ያሉ፣ በመላው አለም የሚገኙ ሁሉ፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያለውን የተሻሻለ ለውጥ በንቃት እየተከታተሉ እንዲደግፉን አደራ እላለሁ። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን በሙሉ ልብ እንዲደግፉት ከልብ እጠይቃለሁ፡፡
የዶ/ር ዐቢይ ራዕይ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የሚበጅ፣ የትብብርና የመደጋገፍ ራዕይ ነው። ይህ ደግሞ ለህዝባችን እጅግ ጠቃሚ ራዕይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን በስራቸውና በተግባራቸው ለመመዘን ክፍት በሆነ ልብ፣ ነፃ በሆነ አዕምሮ፣ ባልተጣሩ ወሬዎች ላይ ሳይሆን በእርግጥም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ድጋፍም ሆነ ነቀፋ እንዲሰጡ በማክበር እጠይቃለሁ። ለመላው ሙስሊም ህዝብ፤ መልካም የረመዳን ፆም፣ የተባረከ ፆም በተለይም ከዚህ ኮሮና ወረርሺኝ ህዝባችንን አላህ እንዲጠብቅልን፣ የምንፀልየውን ፀሎት አላህ የሚቀበልበት የረመዳን ፆም እንዲሆን ከልብ እመኛለሁ። አንተም ለሰጠኸኝ እድል አመሰግንሃለው።
(ፈገግ በማለት) ክቡር ፕሬዚዳንት፤ ሌላ ጊዜ ያሉበት ከተማ መጥቼ፣ የሚባለውን ለውጥና የጎደለውን በማየት ሌላ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ይፈቅዱልኛል?
በሚገባ እፈቅድልሃለሁ።
በነገራችን ላይ የሶማሌ ህዝብ፣ እንደ እርስዎ ያለ አዋቂና በሳል መሪ በማግኘቱ ዕድለኛ ነው። ለቃለ ምልልሱ አመሰግናለሁ::
ከተርጓሚው (- እኔም ሙክታር ዑስማን ባለቤቴ ኢፍራህ አህመድ ከጊዜዋ ተሻምቼ ይህን ረጅም ቃለ መጠየቅ እንድተረጉም በሞራል ስለረዳቺኝ ከልብ አመሰግናለሁ። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!)


Read 8232 times
Administrator

Latest from Administrator