Print this page
Tuesday, 28 April 2020 00:00

‹‹ካልታዘልኩ አላምን አለች ሙሽራ›!›

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

      ኮሮና እብድ አይደል ዘሎ ሰው አያንቅም
ሰነፍ ሰው ካገኘ አያነቃንቅም
ይህ ለኮሮና ሲባል የተደረሰ ግጥም አይደለም፤ ለኮሮና ሲባል የተሻሻለ እንጂ:: ነባሩ ግጥም ‹‹ድህነት እብድ አይደል ዘሎ ሰው አያንቅም/ ሰነፍ ሰው ካገኘ አያነቃንቅም›› ሲል፤ ድሃ ሆኖ በረሃብ አለንጋ የሚገረፍና በድንቁርና ጨለማ ውስጥ የሚማስን ሰነፍ ሰው ብቻ ነው ማለቱ ነው፡፡
ኮሮናና ድህነት በጋራ የሚፈልጉት፣ በጣም የሚወዱትና የሚስማማቸው የሰው ልጅ ጠባይ አለ፡፡ እሱም ስንፍናና ዝንጉነት ነው:: አድርግ የተባለውን በትክክል የሚያደርግ፤ አታድርግ የተባለውን ደግሞ እርም ብሎ የሚተውን ሰው ኮሮና ፈጽሞ አይደፍርም፡፡ እሱ የሚንቀውና የሚያጠቃው፣ እየመረጠም አፈር ከድሜ የሚያስግጠው፣ የእጁን ንጽህና የማይጠብቀውን፤ በሳሙና የማይታጠበውን ነው፡፡ ብምረው አይማረኝ ብሎ የተነሳው በሳሙና ባልታጠበ፣ ንጽህናውን ባልጠበቀ እጅ አይኑን የሚያሸውን፣ አፍንጫውን የሚጠርገውንና አፉን የሚያብሰውን ነው፡፡ እነዚህ አይነት ሰዎችን ኮሮና ይወዳቸዋል፡፡
ኮሮና ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ መሆኑን እናውቃለን፡፡ እኔ ጥቂት ላብራራው፡፡ ሐኪሞች ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው ነው የሚተላለፈው ሲሉ፤ ያ ሰው ከሰማይ ይወርዳል ወይም እንደ ተምች ከመሬት ይፈላል አላሉም፡፡ እርስዎ ነጋዴ ከሆኑ፣ ያ ሰው ደንበኛዎ ነው፡፡ ቀጥረው የሚያሰሩ ከሆነ፣ ሰራተኛዎ ነው፡፡ ትዳር መሥርተው ከወለዱ ልጅዎ፣ ባለቤትዎ ወይም የእርስዎ ወንድም፣ እህትና አባት ወይም የቅርብ ዘመድ ነው፡፡ ሰውየው የመሥሪያ ቤትዎ ባልደረባ ወይም የትምህርት ቤትዎ ጓደኛ፣አሊያም  በአንድ ምክንያት ከእርስዎ ጋር የቅርብ ግንኙነት የመሰረተ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ይኸ ሰው ወደ እርስዎ ሲመጣ ሌላ ጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ሰላምታ ሊያቀርብልዎት ወይም አንድ ጉዳይ ለመፈፀም አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በአንድ በማያውቀው አጋጣሚ በቫይረሱ ተጠቅቶ፣ ሳያውቀውም፣ ቫይረሱን ወደ እርስዎ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡
በዚህ መንገድ ማለትም በዝምድና፣ በጓደኝነት ወደ እኛ የሚመጡ ሰዎችን ደፍረን “ርቀታችሁን ጠብቁ፣ አፋችሁንና አፍንጫችሁን ሸፍኑ” ብሎ መናገር፣ ከዚህም ባሻገር፣ የእኛ የሆነን ዕቃ እንዳይነኩ መከልከል የግድ ነው፡፡ ነገሩን ቸል ማለት ወይም በይሉኝታ ዝምታን መምረጥ ግን ሞትን እንደ መምረጥ ነው፡፡  በእኛ ብቻ ቢበቃ ደግሞ ደግ ነበር፡፡ ከእኛ ጋር ቅርበት ላላቸው ሰዎች ሁሉ የተቀበልነውን ይዘንላቸው ነው የምንሄደው፡፡
ስለዚህም የእራስዎንና በእርስዎ ዙሪያ ያሉትን ሰዎች ደህንነት ለመጠበቅ የመጀመሪያው ሰው እርስዎ ራስዎ መሆንዎን ከልብ መቀበል ይኖርብዎታል፡፡ ርቀትዎን መጠበቅም ወሳኝ መሆኑን ለአፍታም እንኳን ሊዘነጉት አይገባም፡፡ የእርስዎ ደህንነት መረጋገጥ፣ የሌላውም ደህንነት መረጋገጥ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ሁልጊዜ ያለ መታከት መጠንቀቅ አስፈላጊና የማይታለፍ የሚሆነው፣ የራስ ልጅ እንኳ ቢሆን፣ የእያንዳንዱ ሰው ውሎ አዳሩ በሌላው ሰው ቁጥጥርና ጥበቃ ስር ስላልሆነ፣ያ ሰው በደረሰበት አካባቢ የገጠመው አይታወቅም፡፡ እንዲህ እያስጨነቀን እያሳሰበን፣ የሚያደርሰው ጉዳት እስከ ምን ድረስ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት እያዳገተን ያለው የኮሮና ቫይረስ፤ ወደ አገራችን ከገባ 44 ቀናትን አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ 11ሺ662 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው፣ 117  ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሦስት ሰዎች በቫይረሱ ሲሞቱ፣ ከ25 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል፡፡
የሞቱት ሰዎችን ማንነትና የቀብር አፈጻጸማቸውን ግን መንግሥት አልነገረንም:: ምናልባት የደበቀን በሁኔታው እንዳንሸበር ፈልጎ ይሆናል፡፡ እሱ ይደብቀን እንጂ የኮሮናን ክፋት በኢኳዶር አይተነዋል፤ሬሳ የመቅበሪያ ቦታና ጊዜ ጠፍቶ፣ እንደ ዕቃ በኮንቴይነር ሲከማች፣ ቤተሰብ መቅበር አልቻልኩም ብሎ መንገድ ላይ ጥሎ፣ ከፖሊስ ለማምለጥ ሲሸሽና ሴቶች የባሎቻቸውን ሬሳ የሚያነሳላቸው አጥተው፣ ለአራት ቀን ተራ ሲጠብቁ፣ በሃዘን ተሞልተን ታዝበናል፡፡
በእኛም አገር ሁለት ነገሮች በአሳሳቢነታቸው ሳይጠቀሱ መታለፍ የለባቸውም፤ አንደኛው የዱከም ነዋሪ የነበሩት ወይዘሮ ጉዳይ ነው፡፡ እሳቸው ወይም ቤተሰባቸው ነገሩን ደብቀው፣ አስር የሚሆኑ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሐኪሞች፣ ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆነዋል:: ሁለተኛው፤ ጅማ ዞን ሊሙ ኩሳ ወረዳ፣ መንደራ ቀበሌ ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ወይዘሮ ናቸው፡፡ አንድ ወር ለሚሆን ጊዜ ወይዘሮዋ ፀበል እያሉ ከቦታ ቦታ ይዘዋወሩ እንደነበር፣ የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገልጠዋል፡፡ የሁለቱ ሰዎች ሥራ ዝቅ ሲል አላዋቂነት፣ ከፍ ሲልም ክፋት ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡
መንግሥት ሕዝቡን ለማሳወቅና ለማስጠንቀቅ እያደረገ ያለው ጥረት የተጋነነ ለሚመስላቸው ወገኖች፤ አሁን የጠቀስኳቸው አብነቶች ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው - አፋቸውን እንዲይዙ፡፡
ለኮሮና ጥንቃቄ ለማድረግ ብዙ ሰዎች በበሽታው እስኪሞቱ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎች፤ቀጣዩ ተረኛ እነሱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ አይከፋም፡፡  
‹‹ካልታዘልኩ አላምን አለች ሙሽራ› የሚለው ብሂል ግን ለኮሮና  አይሰራም!

Read 7008 times