Print this page
Saturday, 25 April 2020 13:20

እንዲህም አለ…እንዲያም አለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ከቤት መውጣት 17 ሺ ብር ያስቆነድዳል! “ምነው እግሬን በሰበረው?”

           በአገረ ጣልያን፤ አንዲት ጣልያናዊት እንስት፣የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚል የወጣውን በቤት ውስጥ የመቀመጥ ጥብቅ መመሪያ ጥሰው፣ ከኤሊያቸው ጋር የእግር ጉዞ ሲያደርጉ በፖሊስ ተይዘው፣ 400 ዩሮ (17ሺ 600 ብር ገደማ)  ቅጣት እንደከፈሉ የፈረንሳዩ ዜና ወኪል፣ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ከጥር ወር አጋማሽ ወዲህ ከ20ሺ በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የኮሮና ወረርሽኝ በስፋት በተሰራጨባት የሮም አውራ ጎዳና ላይ ለመውጣት ፖሊስ ቅቡል የሆነ  ምክንያት ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ውሻን ለማናፈስ ከቤት ይዞ መውጣት ቅቡል  ምክንያት ተደርጎ  የሚቆጠር ሲሆን በሌላ በኩል፤ ከኤሊ ጋር የእግር ጉዞ ማድረግ ግን መመሪያን መጣስ ነው፡፡  
“የ60 ዓመቷ አረጋዊት፣ ያለ ቅቡል ምክንያት ከቤት ወጥተው፣ በጎዳና ላይ በመገኘታቸው፣ የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ተደርገዋል” ብሏል፤ የሮማ ፖሊስ፡፡
ፖሊስ ያወጣው መግለጫ እንደሚለው፤ ሴትየዋ ከቤታቸው ወጥተው፣ በጎዳና ላይ ከኤሊያቸው ጋር በእግራቸው ሲጓዙ ነው የተገኙት፡፡ የሮማ ፖሊስ ቃል አቀባይ ኑንዝዮ ካርቦኔ፣ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት፤ እንስቷ ቅቡል ባልሆነ ምክንያት ከቤታቸው ወጥተው በመገኘታቸው፣ 400 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት  ተቀጥተዋል፡፡ (ተቆንድደዋል ቢባል ሳይሻል አይቀርም!)
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ፣ ከቤት ውስጥ ያለመውጣት ጥብቅ መመሪያ የወጣ ሲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ የቅጣት መጠን የተመዘገበው ባለፈው የፋሲካ በዓል ማግስት ሰኞ ዕለት ነበር፡፡ የጣልያን ባለሥልጣናት እንደገለጹት፤ በዚህ ዕለት 16.545 ግለሰቦች፣ ከቤት ያለመውጣት ጥብቅ መመሪያን በመጣስ፣ 400 ዮሮአቸውን ተቆንደደዋል፤ በነፍስ ወከፍ፡፡ ያለ ምንም ጥርጥር “ምነው እግሬን በሰበረው?” የሚያስብል ቅጣት ነው፡፡ ያውም በኮሮና ሳቢያ ኪስ በተራቆተበት የፋሲካ ማግስት!
ለሳኒታይዘር እጥረት አዲስ መላ!  
በጃፓን ሆስፒታሎች፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋትን ተከትሎ፣ ለተከሰተው የሳኒታይዘር እጥረት አንድ መላ የተዘየደለት ይመስላል፡፡ ይኸውም ጠንካራ የአልኮል ይዘት ያላቸውን የአልኮል መጠጦች (SPIRITS) በሳኒታይዘርነት መጠቀም ነው፡፡ “ፍጹም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ”፣ ከፍተኛ የአልኮል ይዘት ያላቸውን መጠጦች በሳኒታይዘርነት ተክቶ መጠቀም ይቻላል ብለዋል፤የአገሪቱ ባለሥልጣናት፡፡   
ባለፈው ማክሰኞ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አገኘሁት ባለው የጤና ሚኒስቴር ሰነድ፣ አዲስ መመሪያ መሰረት፤ ከ70-83 በመቶ የአልኮል ይዘት ያላቸውን መጠጦች፣ በሳኒታይዘር ምትክ፣ ጀርምን ለማጽዳት ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል፡፡  
አንዳንድ ቮድካዎች ለዚህ ጥቅም እንደሚውሉ ያመለከተው ዘገባው፤የትኞቹ እንደሆኑ ግን በስም አልጠቀሰም፡፡ በሌላ በኩል፤ ሳኪ እና ሾቹን የመሳሰሉ የጃፓን ባህላዊ መጠጦች ግን መስፈርቱን አያሟሉም ብሏል- -ከፍተኛ የአልኮል ይዘታቸው 22% እና 45% ገደማ መሆኑን በመጥቀስ፡፡  
አንዳንድ የሳኪ አምራቾች ግን የሳኒታይዘርን ፍላጐት ለማሟላት ከፍተኛ መጠን ያላቸው የአልኮል ምርቶችን መሥራት እንደጀመሩ ተጠቁሟል፡፡  ሱንቶሪ የተባለው ግዙፉ የጃፓን የመጠጥ ኩባንያ፤ በወረርሽኙ ክፉኛ በተጠቃችው አሜሪካ፣ ሳኒታይዘሮችን እያመረተ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡  
ጃፓን እስካሁን በአውሮፓና በአሜሪካ ከተከሰተው አስከፊ የኮሮና ወረርሽኝ ማምለጧን የጠቆመው ኤኤፍፒ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በቶክዮ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣት ግን ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል፡፡
በአገሪቱ በአጠቃላይ ከ7.600 በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 መጠቃታቸው የተረጋገጠ ሲሆን 109 በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡  



Read 1947 times
Administrator

Latest from Administrator