Print this page
Tuesday, 28 April 2020 00:00

ኮሮና ቫይረስና ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  - ኮሮና ከድመት ወደ ሰው፤ ከሰው ወደ ድመት ይተላለፋል
              - የከብት ግብይትና እርድ ልማዳችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው
              - የቫይረስ በሽታዎች መድሃኒታቸው በቀላሉ አይገኝም
              - በእኛ አገር በሌሎች ዓለማት የጠፉ የእንስሳት በሽታዎች አሉ

          የሰው ልጅ ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፍ ቫይረስ ሲጠቃ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ከኮሮና በፊት በተደጋጋሚ ተጠቅቷል፡፡ የኮሮናን ቫይረስ ለየት የሚያደርገው አጣዳፊና የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ ለመሆኑ ከእንስሳት ወደ ሰው ስለሚተላለፉ በሽታዎች ምን ያህል እናውቃለን? የመተላለፊያ መንገዶቹንስ? ሰዎች እንዴት ራሳቸውን ከእንስሳት ከሚተላለፉ በሽታዎች መከላከል ይችላሉ? ድመትና ውሻን የመሳሰሉ የቤት እንስሳት በኮሮና ቫይረስ ሊያዙ ይችላሉ? የአዲስ አድማሱ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ የእንስሳት ሕክምና ተመራማሪና በ “ትሮፒካል አኒማል ፓታሎጂ” ስፔሻላይዝ ያደረጉትን ዶ/ር ባንትይገኝ ታምራትን በኮሮና ቫይረስና የእንስሳት በሽታዎች ዙሪያ ሙያዊ ማብራሪያ ጠይቋቸው ሰፋ ያለ መረጃ ሰጥተውታል፡፡


       እስቲ ከእንስሳት ወደ ሰው ስለሚተላለፉ በሽታዎች በጥቅሉ ይንገሩን?
የሰው ልጅ ከእንስሳት ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስላል ብለን ወደ ኋላ ተመልሰን ታሪካዊ ዳራውን ማየት ይጠቅማል:: የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ እንስሳትን በተለያየ መንገድ ለምግብነትና ለንግድ ሥራ እንደሚያድን ይታወቃል:: በአደን ወቅት ደግሞ የተለያዩ የእንስሳት በሽታዎች ወደ ሰው ልጆችም ሲተላለፉ እንደነበርና በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ሕይወት እንደተቀጠፈ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኮሮናም ከእነዚህ አንዱ ነው:: ለምሳሌ በኛ ዕድሜ በቅርብ ጊዜ እንኳ ያየናቸውን ብንመለከት፣ ከሌሊት ወፍ መነሻ ያደረገው ኢቦላ፣ ከዝንጀሮ የመጣው ኤችአይቪ፣ ከውሻ የሚመጣው የእብድ ውሻ በሽታ እንዲሁም በስፔን በተደረገ ጥናት ፓንጉሊን የሚባል (የሸለመጥማጥ ዝርያ ያለው) እንስሳ አሁን ለተከሰተው የኮረና ቫይረስ መነሻ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ተደርሷል:: የድመት ዝርያ ያላቸው እንደ ነብር የመሳሰሉት ፓንጉሊንን ተመራጭ ምግባቸው አድርገው ስለሚወስዱ በቀጥታ በሽታው እየተላለፈባቸው መሆኑም ተረጋግጧል፡፡
አሁን እየተደረጉ ባሉ ጥናቶች፤ ይሄን እንስሳ የሚመገቡ ሌሎች እንስሳት በኮሮና ቫይረስ እየተያዙ መሆኑ ታውቋል:: ከዚህ በመለስ የኮሮና ቫይረስን ባህሪ ስንመለከተው፤ ከውሻ ወደ ውሻ፣ ከድመት ወደ ድመት፣ ከድመት ወደ ሰው፣ ከሰው ወደ ድመት… በአጠቃላይ ከእንስሳት ወደ ሰው፤ ከሰው ወደ እንስሳት የሚተላለፍ መሆኑንም ጥናቶች ያመላክታሉ:: በአጠቃላይ ግን አሁን ኮሮና ቫይረስ ወደ ሰው የተላለፈው ከእንስሳት ብቻ ነው  የሚለውን እርግጠኛ ለመሆን ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ እስካሁን የተደረጉ ጥናቶች፣ ከእንስሳት ወደ ሰው የተላለፈ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡
ቫይረሶች ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፉ በምን ዓይነት መንገዶች ነው?
በትንፋሽ፣ የእንስሳቱን ስጋ በመመገብ፣ የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር፣ እንዲሁም በንክኪ… እንደሚተላለፉ ጥናቶች ይጠቁማሉ:: ስለዚህ ከእንስሳት ጋር በሚኖር ቅርበት ላይ ገደብ ማበጀትና እንስሳትን በየጊዜው ማስተከብ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
እስቲ ዓለምን እያስጨነቀ ስላለው የኮሮና ቫይረስ ባህርይ በዝርዝር ያስረዱን? መቼ ነው በደንብ የታወቀው?
ኮሮና ቫይረስ በፊትም የሚታወቅና የነበረ ቫይረስ ነው፡፡ ቫይረሱ በቀላሉ ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፍ ነው፡፡ በእንስሳት ላይ የሚታይ የበሽታም አይነት ነው፡፡ በእንስሳት ላይ የሚፈጠሩ በሽታዎች ልክ በሰው ላይ እንደሚፈጠሩት በሽታዎች በቫይረስ፣ ባክቴሪያና ፈንገስ አማካኝነት የሚፈጠሩ ናቸው:: ኦባ ሰንጋ፣ አባ ጎርባ እያልን የምንጠራቸው የእንስሳት በሽታዎች፤ በባክቴሪያ የሚመጡ በመሆናቸው በቀላሉ መድሃኒት ተገኝቶላቸዋል:: የቫይረስ በሽታዎች ግን አስቸጋሪዎች ናቸው:: መድሃኒታቸውም በቀላሉ አይገኝም:: ኮሮናን ጨምሮ ሌሎችም ቫይረሶች ባህሪያቸው በጣም ተለዋዋጭ በመሆኑ መድሃኒታቸውን በቀላሉ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ መድሃኒት ተገኘላቸው ተብሎ ሲሞከር ቫይረሱ ወዲያው ባህሪይውን የመቀየር ተፈጥሮ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ በብዛት በቫይረስ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለማከም የሚወሰዱ መድሃኒቶች፤ በቫይረሱ ምክንያት ሊመጡ የሚችሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመቀነስ ያህል ነው እንጂ በቀጥታ ቫይረሶችን ለማጥቃት አይሆንም፡፡ ለምሳሌ ኤችአይቪ ክትባትም መድሃኒትም አልተገኘለትም:: ነገር ግን ከቫይረሱ በስተጀርባ የሚመጡ ጉዳቶችን ለመቀነስ የሚረዳ መድሃኒት ተዘጋጅቶለታል፡፡ በብዛት ከቫይረሱ በተጓዳኝ የሚመጡ ጉዳቶችን ለመቀነስ ነው ጥረት የሚደረገው እንጂ በቀጥታ ቫይረሶችን ለመዋጋት የሚደረጉ ጥረቶች አስቸጋሪ ናቸው፡፡
ኮሮና ቀድሞ የሚታወቅ ቫይረስ ከሆነ፣ እንዴት አሁን በሰው ላይ ተከሰተ?
ኮሮና የነበረ ቫይረስ ነው ይታወቃል፤ አዲስ ቫይረስ አይደለም፡፡ ዶሮዎችን ያጠቁ ከነበሩ ቫይረሶች አንዱ ነው፡፡ ከበፊት ጀምሮ ቫይረሱ እንዳለ በጥናት ይታወቅ እንጂ ሰው ላይ ጥቃት ሲፈፅም ብዙም አይታወቅም:: ይሄ የመጀመሪያው ሊሆን ይችላል፡፡ ቫይረሱ አሁን በሕዝብ ላይ በወረርሽኝ መልክ ተከሰተ እንጂ ቀድሞም የነበረ ነው፡፡ ዶሮዎችን የሚያጠቃ ቫይረስ ነበር፡፡
ከእንስሳት ወደ  ሰዎች የሚተላለፉ በሽታዎችን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ብዙ ጊዜ የተለያዩ አገሮች ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ይረዳናል በሚል ገደብ የሚያበጅ ህግን ያዘጋጃሉ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ገደቦች ውጤታማ ሲሆኑ አይታይም፡፡ በተለይ እንደ ኮረና ያሉ ወረርሽኞች ሲመጡ  ሕግ አውጥቶ ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት አለ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ የቁጥጥር አካሄዶች ብዙ ጊዜ ውጤታማ አይሆኑም:: ምክንያቱም እንስሳትና ሰው፣ በሕዝብ ቁጥር ልክ ተመሳስሎ አብሮ ነው የሚኖረው:: በየቤቱ ነው የሚኖረው፡፡ ስለዚህ ለቁጥጥር አመቺ አይደለም፡፡ ከዚህ በሻገር እንስሳትና ሰው ግንኙነታቸው የባህል ያህል የዳበረ ነው፤ በቀላሉ ሊላቀቁት የሚቻል አይደለም::  ስለዚህ በአብዛኛው ሊደረግ የሚችለው በባለሙያዎች ግንዛቤ እንዲሰጥ ማድረግ ነው፡፡ ሕብረተሰቡ የቤት እንስሳትን እንዲያስከትብ፣ እንዲያሳክም መምከር ያስፈልጋል፡፡
እንደ ባለሙያ፤ ከእንስሳት በሽታዎች ጋር ተያይዞ ለሕብረተሰቡ ምን ይመክራሉ?
በተለይ እንደ ውሻ፣ ድመትና ሌሎች የቤት እንሳስትን በየጊዜው ማስከተብ ያስፈልጋል፣ የሕመም ምልክት ሲያሳዩም ርቀትን መጠበቅና አለመንካት፣ ፈጥኖም ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል፡፡ ይሄ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም፡፡ ጤንነትን የመጠበቅ ነው:: በእንስሳው ላይ ያለው በሽታ ምንነቱ እስካልታወቀ ድረስ ቤተሰብን የሚጨርስ ገዳይ ሊሆንም ይችላል፡፡ ስለዚህ ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ሌላው በበሽታም ሆነ በድንገት የሞተን እንስሳ ቆዳ አለመግፈፍ ነው:: እንስሳው የሞተበት ምክንያት እስካልታወቀ ድረስ ቆዳውን መግፈፍ እንስሳውን ለሞት ያበቃው ቫይረስ ወይም ባክቴሪያ ወደ ውጪ እንዲወጣና አካባቢውን እንዲበክል ወይም ለብዙ አመታት አፈር ውስጥ ተደብቆ እንዲኖር ይረዳዋል፡፡ ለምሳሌ አንትራክስ የምንለው በሽታ በኦክስጅን አማካይነት ለበርካታ አመታት መኖር የሚችል ነው፡፡ በዚህ በሽታ የሞተን በሬም ሆነ ሌላ እንስሳ ቆዳ መግፈፍ፣ በሽታው ለ10 አመት በአፈር ውስጥ እንዲኖርና እንዲዛመት ይረዳዋል:: ስለዚህ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ እንስሳው መቀበር ወይም መቃጠል ነው ያለበት:: የሞተ እንስሳን በምናስወግድበት ወቅትም አፋችንን በሚገባ አፍነንና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ተከትለን መሆንም ይገባዋል፡፡
ሌላው ሕብረተሰቡ ማወቅ ያለበት ጉዳይ በማንኛውም ሁኔታ፣ ከእንስሳት ጋር ያለውን ግንኙነት መገደብ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ በየቤቱ ከውሻ ጋር የመታገል፣ ከድመት ጋር የመተሻሸት ልማድ አለ፡፡ ይሄ በጣም አደገኛ ስለሆነ ጥንቃቄ ይሻል፡፡ በተለይም ኮሮና ከድመት ወደ ሰው፣ ከሰው ወደ ድመት የሚተላለፍ መሆኑን ጥናቶች መጠቆማቸው ይታወቃል፡፡ ይሄ ማለት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከባህል አኳያም ጥሬ ስጋ መብላትና ወተት ሳያፈሉ መጠጣት፣ በተለይ አሁን በፍፁም ሊቀር ይገባዋል፤ ይሄ በእሳት እንደ መጫወት ነው፡፡ በቀጣይም ሕብረተሰቡ ከዚህ አይነቱ ልማዳዊ የአመጋገብ ሥርዓት ራሱን ማቀብ አለበት:: ኮሮና ብቻ ሳይሆን ሌሎች በሽታዎች ሊከሰቱ የሚችሉበት እድል ሰፊ ስለሆነ ሰዎች ጥሬ ስጋና ወተትን ሳያበስሉና ሳያፈሉ የመጠቀም ልማድን መተው አለባቸው:: ማንኛውንም የስጋ ውጤት ወዲያው አብስሎ መጠቀም የቀዘቀዘ ከሆነም ወዲያው አሙቆ የመጠቀም ባህል በእጅጉ መዳብር አለበት፡፡ ሌላው በሕብረተሰቡ ውስጥ ትልቅ ችግር የሚያስከትለው ደግሞ፣እንስሳትን ወደ ቄራ ወስዶ የማሳረድ ልማድ አለመኖሩ ነው፡፡ ቤት ውስጥ የማረድ ልምድ መቅረት ይገባዋል፡፡ ማንኛውም እንስሳ ከመታረዱ በፊት አስፈላጊው የጤና ምርመራዎች ተደርጎለት፣ ወደ ሚታረድባቸው ቄራዎች ወስዶ የማሳረድ ልማድ በእጅጉ መዳበር አለበት፡፡ በቤት ውስጥ የግድ የሚታረድ ከሆነም፣ አራጆቹ የማሳል፣ የተቅማጥ፣ የማስነጠስ ምልክት የማይታይባቸው መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
የእርድ እንስሳት ከገበያ በሚገዙበት ወቅት ምን አይነት ጥንቃቄ መደረግ አለበት ይላሉ?
አንዱና ወሳኙ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት፣ በእንስሳት ግብይት ወቅት ነው፡፡ የምንገዛው በግም ይሁን በሬ አሊያም ሌላ ከብት… የፈዘዘ አለመሆኑን፣  ፀጉሩ ጭብርር ያላለ፣ በአፍና አፍንጫው ፈሳሽ የማይበዛው፣ ተቅማጥ የሌለውና የማያነክስ እንዲሁም ንቁ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ እንስሳትንም በእጅ ከመነካከት መታቀብ ያስፈልጋል፡፡
መንግስት ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን በተመለከተ፣ የሕብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ  ምን አይነት እርምጃዎችን መውሰድ አለበት?
መንግስት የአለም እንስሳት ጤና ድርጅትና የአለም ንግድ ድርጅት ያወጧቸውን መስፈርቶች በአግባቡ መከተል አለበት:: እነዚህ ተቋማት ያወጧቸው በተለይ ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚገባ የተላለፉ መመሪያዎች አሉ፡፡ እነሱን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ የንግድ ሥርዓቱም በዚህ መመራት አለበት፡፡ ለምሳሌ እነሱ ካወጣቸው መስፈርቶች አንዱ፤ የትኛውም አገር ሌላውን የጎረቤት አገር ሕዝብ፣ ከእንስሳት ወደ ሰው ከሚተላለፉ በሽታዎች የመጠበቅ ግዴታ አለበት - ይላል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ጎረቤት አገራት ይሄን ጠብቀው እየሰሩ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው እስካሁን ባለው አደረጃጀት፤ የእንስሳት ጤና ዘርፋችን በጣም ደካማ ነው፡፡ ሌሎች አገራት አሉ የሚባሉ ዋና ዋና የእንስሳት በሽታዎችን አስወግደው፣ የሕብረተሰባቸውን ጤንነት አስተማማኝ እያደረጉ ነው፡፡ በኛ አገር ግን በሌሎች አገራት የጠፉ በሽታዎች አሁንም አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን በሽታዎች ልንዋጋ የምንችልበትን መንገድ በአፋጣኝ ልንዘይድ ይገባል፡፡ ይሄ ሥራ የስጋ ምርታችንንም ያበለጽጋል፡፡ የስጋ ምርት ተቀባይ አገራት አንዱ መስፈርታቸው፣ በአገሪቱ ምን በሽታዎች አሉ? የሚለው በመሆኑ፤ በሽታዎችን አጥፍቶ የስጋ ውጤቶችንና ምርቶችን አሁን ካለው የአረብ ገበያ በተጨማሪ፣ ሌሎች ከፍተኛ ክፍያ ከፍለው መሸመት ወደሚችሉ የአውሮፓ አገራት መሻገርም ይገባል፡፡ ለዚህ ሁነኛ ስትራቴጂ መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ በመንግስት በኩል፤ የእንስሳት ጤና ዘርፉን በሰው ሀይል በደንብ ማደራጀትና በቁሳቁስ ማጠናከር ያስፈልጋል::
ሌላው በመንግስት በኩል ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ፤ የሰውንም የእንስሳውንም ጤንነት አስተማማኝ ለማድረግ፣ የጤና ዘርፋችንን ተናባቢና ተመጋጋቢ ማድረግ ነው፡፡ አሁን ባለው አደረጃጀት፣ ጤና ሚኒስቴር ለብቻው፣ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ለብቻው፣ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ለብቻው ነው እየተጓዙ ያሉት:: ነገር ግን በኢትዮጵያም ይሁን በሌላው አለም አብዛኛው ወረርሽኝ በሽታ መነሻው ከእንስሳት ወደ ሰው መሆኑን እየተመለከትን ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት አንድ ሄሊዝ ፖሊሲን መሰረት አድርጎ፣ የጤና ዘርፉን አደረጃጀት እንደገና ማዋቀር ያስፈልገዋል:: እነዚህ ተበታትነው ያሉ የጤና ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት፣ አንድ ላይ ሆነው የሚመሩበት ወይም የሚናበቡበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ አሁን ከአደረጃጀታቸው ጀምሮ በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ የለም፡፡ ይሄ ትልቅ ክፍተት ይፈጥራል፤ ስለዚህ ከወዲሁ ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል፤ መንግስት የአገሪቱን የእንስሳት ግብይት ሥርዓትም ማሻሻል አለበት፡፡ በየሜዳው የሚደረጉ ግብይቶች፣ ወደ የማዕከላት ግብይት መለወጥ አለበት፡፡ በየቦታው የግብይት ማዕከላት ተገንብተው ወደ ዘመናዊ የማዕከላት ግብይት ሥርዓት በአፋጣኝ መሸጋገር ይገባል፡፡ የእንስሳት ግብይትን በማዕከል ብቻ እንዲፈፀም ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ቢያንስ በማዕከላት ግብይት የሚፈፀምባቸው እንስሳት፣ የጤና ምርመራ ሊደረግላቸው ይችላል። ከየት እንደመጡ፣ ምን አይነት ባህሪ እንዳላቸው ማወቅ ያስችላል፡፡ መገናኛ ብዙሃንም በእንስሳት ጤንነት ዙሪያ በየጊዜው ግንዛቤ መስጠት አለባቸው፡፡
የአገራችን የእንስሳት ጤና አጠባበቅ አደረጃጀት በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?
ከሁለት አመት በፊት ይመስለኛል፤ የእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት በሚል ሚኒስትር ስር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በግብርና ሚኒስቴር ስር ሆኗል፡፡ የሚመራውም በአንድ የሚኒስትር ዴታ ስር ባለ ዳይሬክቶሬት ደረጃ ነው፡፡
የእንስሳት ጤና ጥበቃ በቂ ትኩረት ተሰጥቶታል ማለት ይቻላል?
በእንስሳት ሀብታም የመሆናችንን ያህል፣ ከሃብታችንም ተጠቃሚ አይደለንም:: በሰጠነው ትኩረት ልክ ነው እያገኘን  ያለነው፡፡ መከላከልና ማስቆም የምንችላቸው የበሽታ አይነቶች አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡ በየዓመቱ ወደ አፋር አካባቢ በርካታ እንስሳት ይሞታሉ፡፡ በዚያ ላይ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያዎች አልተሰሩም፤ አሁንም ድሮ የነበሩት ናቸው ያሉት፡፡ እነሱ ደግሞ ብዙም ውጤታማ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የተሰጠው ትኩረት በእጅጉ አናሳ ነው:: አንዱ የዚህ ችግር ምንጭ ደግሞ ዘርፉ በባለሙያዎች አለመመራቱ ነው፡፡ በዘርፉ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች በቦታው ላይ የሉም፡፡ ስለዚህ ዘርፉ ተቆርቋሪ አለው ለማለት አያስደፍርም። ለአገሪቱ ከቡና ቀጥሎ የስጋ ኤክስፖርት ነው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘው፡፡ ይሄ የበለጠ በጤና አጠባበቅና አደረጃጀት ቢዳብር፣ የአውሮፓ ገበያን ሰብሮ በመግባትም ውጤታማ ለመሆን ያስችላል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት፤ በትኩረት ሊያስብበት ይገባል፡፡      



Read 1403 times