Print this page
Wednesday, 29 April 2020 00:00

“ሕዝቡ” ለዛሬ እንዲደርስ መላ፣ መላ ይባል!

Written by  በተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ሴትየዋ፣ በእንግድነት ቤትዋ ከመጣች ሴት ጋር ቁምነገር እያወራች ነው፡፡ የእንግዳ ተቀባይዋ ሴትዮ ልጅ፤ እድሜው ሶስት አመት ተኩል ገደማ ይሆናል፤ የእናቱን ፊት ጠምዝዞና አፉን ጆሮዋ ላይ ለጥፎ፣ በሹክሹክታ የሆነ ነገር ይጠይቀታል፡፡ ልጁ የሚጠይቃት፣ ቀደም ሲል ጠይቋት “አይሆንም” ብላ የከለከለችውን ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡ እናት፣ እሷም በሹክሹክታና በልምምጥ ቃና ለልጁ የሆነ ነገር ትነግረዋለች፤ አንገቷ ስር ወሽቃ፡፡  ልጁ፣ እንዳኮረፈ ቢሆንም በእናቱ ሀሳብ የተሰማማ መስሎ ወደ ጓዳ ያቀናል:: ወዲያው፣ እናቱና እንግዳዋ ሴት ወሬያቸውን ከቆሙበት ይቀጥላሉ፡፡
ልጁ፣ የእንግዳዋን መምጣት በጥሩ አጋጣሚነት ስለወሰደውና አጋጣሚውም እንዲያመልጠው ስላልፈለገ፣ ሌላ ሙከራ ለማድረግ ይወስናል፡፡ እናም፣ ሮጦ ወደ እናቱ በመምጣት ፈንታ የጓዳውን በር ገርበብ አድርጎና ጉንጩን የበሩ ጉበን ላይ አጣብቆ፤ ድምጽ ሳያወጣ፣ ከናፍሩን ብቻ እያነቃነቀ፤ የቅድሙን ጥያቄ በምልክት ያቀርብላት ጀመር፡፡ አጅሬ፣ ሚስጢር የሚያወራ መስሎ የጥያቄውን ቅጂ በግልባጭ ለእንግዳዋም እየላከ መሆኑ ነው - በአየር ለይ፡፡
እናት በከፊል ልቧ ከሴትየዋ ጋር እያወራች፣ በአይንዋም በግንባርዋም ልጁን “ወጊድልኝ!” እንደ ማለት ስትለው ትቆያለች:: የድሮ ልጅ የወላጆቹን ግንባር ያነባል ይባል የለ? እሷ የጠበቀችው የግንባር ንባቡን ወደ ተግባር እንዲለውጥላት ነው:: እሱ ግን እቴ! “አንዴ ብቻ እሺ በዪኝ!” እንደማለት አይነት አንገቱን እያቅለሰለሰና ሚጢጢ እጁን እያራገበ ልመናውን ይቀጥላል፡፡ ይህን ያደረገው፣ እንግዳዋ ጣልቃ ገብታ፣ “አቦ፣ የሚፈልገውን ነገር ወዲያ ስጪውና በአንድ ልብ ወሬያችንን እንቀጥል” እንድትልለት ነው፡፡ እናቱ ግን የልጇ እንደዚያ አይን አውጣ መሆን ብግን፣ ድብን አድርጓታል፤ አሳፍሯትማልና፣  ከወንበሯ ላይ ፍንጥር ብላ ትነሳና፣ ጓዳ ገብታ፤ “እንግዳ ሲሄድ እንነጋገራለን፣ በቃ ዝም በል እሺ! ረበሽከንኮ!” ትለዋለች - በቁጣ እንዳልጀመረች ሁሉ አጎንብሳ እየሳመችው - በፍቅር እየተደራደረችው፡፡
ልጁ ይህን ሁኔታ ሲያይ እምቢ ባይነቱ ጭራሽ ባሰበት፡፡ እናቱ የተሸነፈችለት ስለመሰለውም፣ “ምናለበት እሺ ብትዪኝ ...? ህ? ሕ? እማ፣ እሺ በዪኝ በቃ፤ ኅ? - ለዛሬ ብቻ...” እያለ ይማፀናት ገባ፤ በለቅሶ ዜማ የሻከረ ድምጹን ከፍ አድርጎ፡፡
እናት ትዕግስቷ አለቀ፡፡ ምናባቱ-! ካዋረደኝ አይቀር፣ በደንብ ቀጥቼው ለምን ዝም አላሰኘውም? ብላ መሆን አለበት ጭኑ ውስጥ ገብታ በቁንጥጫ ልምዝግ ታደርገው ጀመር፡፡ ከቁንጥጫ ጋር አባሪ አድርጋ፣ “እስቲ አባህ...! ከአሁን በኋላ ትንፍሽ ትልና!” የሚል ማስጠንቀቂያም ታጉተመትም ነበር::
አሁንም ልጁ ከአቋሙ ዝንፍ አላለም:: እንባውንና ንፍጡን አዝረክርኮ ከጣሪያ በላይ ይቀበንን ጀመር፡፡ እናትና ልጅ እልህ ተያያዙ:: እሷ ትገርፈዋለች፣ እሱ እየተንፈራፈረ፣ አንዳንዴም አውቆ ግድግዳውን በቁንጮአም ጭንቅላቱ እየገጨ፣ ይጮኻል:: አመፀኛ ልጆች እንደዚያ ናቸው አይደል? ሲመች አንገት ጠምዝዘው በሹክሹክታ ይለማመጣሉ፤ ያ ካልሰራ፣ ፈቀቅ ብለው እየተቅለሰለሱ በምልክት ይለምናሉ፡፡ ይህም አልሆን ሲል፣ ያለቅሳሉ፣ እንዲታዘንላቸውም ራሳቸውን ከመሬትና ካገኙት እቃ ጋር እያጋጩ ጥያቄያቸውን ያቀርባሉ፡፡ ሰው ሲኖርማ ይብስባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በዚህ ስልት ውጤት አግኝተው ከነበረ ደግሞ በምንም ተዓምር አመፃቸውንና ራሳቸውን መጉዳታቸውን አያቆሙም፡፡
ወደ እንግዳዋ እንመለስ፡፡ የእናትና ልጅን ትዕይንት በመታዘብ ሰዓቷ ባከነ፡፡ ስለዚህ፣ እናቲቱን “ማነሽ? ወ/ሮ እገሌ፤ አንዴ ትመጪ? የመጣሁበትን ልንገርሽና ወደ ጉዳዬ ልሂድ፣ ልጅሽ ለዛሬ አልደረሰልሽም” ትላታለች - የቅጣትሽን ውጤት ለማየት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልግሻል ማለቷ ነው:: እናትም፣ አማራጭ ስላልነበራት፣ ንዴት ጉሮሮዋን እንዳነቀው፣ ልጁ ላይ የጓዳውን በር ቆልፋ፣ የጀመረችውን ወሬ ለመጨረስ ወደ እንግዳዋ ተመለሰች፡፡  ይህ ሁሉ ሲሆን - የልጁ የለቅሶ ድምጽ / “ሳውንድ ትራክ - በሉት” አልተቋረጠም ነበር፡፡
ይህን፣ ጭብጡን ሳልለቅ፣ ክሽን አድርጌ ያቀረብኩላችሁን፣ ተረት ይሁን የሆነ ሰው ገጠመኝ ያልለየሁትን ጣፋጭ “ታሪክ” የነገሩኝ ወግ አዋቂዋ ወ/ሮ አስናቀች አስታከል ናቸው - አማቴ፡፡ በወቅቱ ተርተውብኝ ይሁን ተርተውልኝ ትዝ አላለኝም፡፡ ቢመክሩኝ ቢመክሩኝ፣ እንደማይደርስላቸው አውቀው የተውኝ ነገር ይኖር ይሆን እንዴ! ወይ ጉዴ!
አሁን በምን አስታወስከው? በሉኛ! እነሆ መልሴ፡- የኮሮና ቫይረስ መምጣትን ተከትሎ፣ “ህዝባችን ተራራቅ፣ አትቀራረብ፣ አትተቃቀፍ፣ አትሳሳም፣ ለዓለምም ሆነ ለመከራ ደግሰህ አትጠራራ፣ የባሰ ነገር ኬሌለብህ በስተቀር ከቤትህ አትውጣ፣ ራስህን ነጥል!” ተብሎ በተደጋጋሚ ቢመከርም፤ የሚጠበቅበትን ያህል አዎንታዊ ምላሽ ሳይሰጥ መቅረቱን፤ ይባስ ብሎ መንግሥትም ሆነ ቤተ እምነቶች እየመከሩትና እያስጠነቀቁት ሁሉ ጤንነቱን እንዲጠብቅ ቢነገረውም  “ሞት” ምንም  አልመስልህ ብሎት በየመንገዱ ሲንገላወድ ሳይ ነው (የመጣልኝ)፡፡
እውነት ነው፡- ከ”ሕዝባችን” የኑሮ ሁኔታ፣ “የስነልቡና ውቅር”፣ ወዘተ አንጻር ለዛሬ የማይደርሱ ብዙ ነገሮች አሉ - እጅግ ብዙ:: ይሁንና፣ ልናተኩር የሚገባን የማይደርሱቱ ላይ ሳይሆን የሚደርሱት ላይ ነው፡፡ አዎ፤ በርካታ ሕዝባችን ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ የተማረም አይደለም፤ በመሆኑም፣ ቫይረሱን የሚመለከቱ መረጃዎችን ወደ ራሱ የመውሰድ የአቅም ውስንነት ሊኖረው ይችላል፡፡ መረጃው የዘለቀው ሰው ደግሞ፣ በ”እምነቱ” ምክንያት፣ “እችላለሁ” ብሎ ራሱን ለማዳን ኃላፊነት አይወስድ ይሆናል:: የኖረው “አልችልም”ን፣ “አቅም የለኝም”ን - የትህትና ምልክት አድርጎ ነው፡፡ “ባህሉ” ለብቻ መቆምን፣ በራስ መተማመን የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ስለሆነም፤ ሁሉም ሰው በእኩል ደረጃ፣ በአንዴ (ሰልፍ ይዞ - ሆ ብሎ) የመንግሥትን ትዕዛዝ ይተገብራል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው:: ማጋነን አይሁንና፣  ልመናው በዕንባ የታጀበ ቢሆን እንኳ “ሕዝቡ” በመረጃ ብዛት፣ በግጥምና በዜማ ወዘተ “ጥራት” (ብቻ) ፈጣን የባህሪ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም:: ለማስታወስ ያህል፣ ከላይ የተዋወቅነው ህፃን ራሱን ከግድግዳ ጋር እያጋጨ እናቱን ለማስፈራራት እንደሞከረው ሁሉ “እምቢ - እንዲያውም ኮሮና በሰው ተመስሎ ቢመጣ እቅፍ አድርግን እንስመዋለን” አይነት በማለት መንግሥትን ለማስፈራራት የሚሞክሩ፤ ወቅት አይተው የሆነ ትኩረት የሚፈልጉ፤ ዜጎች (ቡድኖች) ይኖራሉ፡፡ “ሕዝቡ” ግን ምን ነካው? በጣሊያን፣ በስፔን፣ በአሜሪካ የሆነውን እየሰማ፣ በቴሌቪዥን እያየ እንዴት አይጠነቀቅም? “...ብልህ ከሌሎች ተሞክሮ መማር አለበት” እያሉ መንጨርጨር የትም አያደርስም፡፡
ግን ... ግን፤ “...እምቢ አልሰማም አለ፤ እንኳን አካላዊ ፈቀቅታውን ሊጠብቅ ቀርቶ፣ መተቃቀፍና መላፋቱን እንኳ አልተወም” ምናምን የምንለው ...፤ ወረፋ ባለበት ቦታ ሁሉ የፊተኛው ሰልፈኛ ትከሻ ላይ ነው የኋለኛው አገልግሎት ፈላጊ አገጭ የሚያርፈው ... እያልን የምናማርረው “ሕዝብ” (አብላጫው) ነባር የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው? ወይስ “በቅርብ” ከገጠር ፈልሰው አዲስ አበባ የገቡ ዜጎች ናቸው? ከመደበኛ ትምህርትስ አኳያ - “የተማሩ ናቸው ያልተማሩ?”  ደግሞስ፣ ብዙ ሰዎች፤ ጋዜጠኞችን ጨምሮ፣ በግምት እንደሚናገሩት፤ የእለት ምግብ ፈላጊዎች ብቻ ናቸው ጎዳናውን ያጣበቡት? መለየት አለበት፡፡
እነሆ አንድ ሀሳብ፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ - የሶሽዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ በዚህ ጉዳይ ላይ ቅልብጭ ያለች የዳሰሳ ጥናት ቢያካሂድ፣ ለግርምታችን የሆነች መልስ ሊሰጠን ይችል ይሆናል፡፡ የትምህርት ዘርፉን ስለማውቀው ነው - ከተግባሮቹ አንዱ የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን ምክንያትና ውጤት እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ አባላት (ለምሳሌ የመርካቶ ሰፈር ነዋሪዎችና የመገናኛ አካባቢ ነዋሪዎች) ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የሚኖራቸውን ምላሽ ማጥናት ነው - ግኝቱ ለውሳኔ ሰጪዎች ግብዓት ይሆን ዘንድ፡፡  
እና፣ “ሕዝቡ” ለሚለው በተን ያለ መልስ ከተገኘ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ እና በሌሎችም መንገዶች የሚተላለፉ የ”ኮሮና ቫይረስ ተጠንቀቁ” ትምህርቶች (መረጃዎች/መልዕክቶች) ተመጥነው ሊዘጋጁ ይችላሉ - ልክ ሀኪሞች መድሃኒት ሲያዙ የታማሚን እድሜና የታማሚ የቀደመ ታሪክን እንደሚያጤኑት:: ይህ ደግሞ የተግባቦት ጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ የሚያውቁት ነገር ነው - ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ነው መረጃ ተከሽኖ መቅረብ ያለበት፡፡ በዚያ ላይ፣ ብዙ ሰዎችን የሚጎዳ የጤና ችግር በወረርሽኝ ደረጃ ሲስፋፋ የማህበረሰብ ጤና አስተማሪዎች፣ ሀኪሞች ወዘተ ወደ ፊት የመምጣታቸውን ያህል የሶሻል ሳይንስ ባለሙያዎችም (የሙያ ማህበሮቻቸውን ጨምሮ) ወደ ፊት መምጣት ነው ያለባቸው - “ሕዝቡ” ለምን እንዲህ እንደሆነ ያልገባው አካል የመፍትሔ ጥይቱን የሚተኩሰው በጨለማ እንዳይሆን ማለት ነው፡፡
ይህም የማህበራዊ ሳይንስ እውነታ ነው፡- ህዝብ መረጃ ስለደረሰው ብቻ የባህሪ ለውጥ አያመጣም፡፡ ሰውም ብቻውን ከሚለወጥ ይልቅ አጠገቡ ያሉ ሰዎች በብዛት ሲለወጡ ለመለወጥ፣ ቢያንስ ለመመሳሰል፣ ይቀለዋል:: አንዳንዴም ለመለወጥ “ቁንጥጫ” ይፈልጋል:: ምቾቱን እያሰላ እንደ ቀበጥ ልጅ አጉል ባህሪ ሊያሳይም ይችላል፡፡ ብቻ በዚህም አለ በዚያ፣ በሚገባው መንገድ ሊነገረው ይገባል - ከሁሉ በፊት፡፡
እዚህ ላይ የቀደመ ተሞክሯችንን እንቃኝ:: ትዝ ይላችኋል መቼም፤ የፀረ ኤድስ ዘመቻዎች፤ አገር በቀል መፍትሔዎችን ሲያፈላላልጉ “እድሮች” ጋ የደረሱት ብዙ ሰዎች ከሞቱ፣ በሽታው በስፋት ከተሰራጨ በኋላ ነው - በጣም ዘግይቶ:: ይህ እስኪሆን ድረስ በኤችአይቪ ኤድስ ዙሪያ የህዝብን ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሚል - ብዙ ወርክሾፖች (ስማቸው እንኳ አማርኛ ወይም አገርኛ አልነበረም)፣ ሴሚናሮች (መጀመሪ በፕሮጀክተር / በፓወር ፖይንት)፣ ስልጠናዎች፣ የሰርከስ ዝግጅቶች፣ ሰላማዊ ሰልፎች፣ ባርኔጣዎችና ቲ - ሸርቶች፣ መፈክር አዘል ጨርቆች፣ በራሪ ፅሁፎች፣ ወዘተ ወዘተ ተሞክረዋል፡፡  “ሕዝቡ” ንቅንቅ አልል ሲል ... “እንዴ! ሕዝቡ ምን ነካው?” በሚል በጥልቀት ታስቦ ነው “አድነን ዕድር!” ማለት የተጀመረው:: ዕድሮች ጥሩምባ ይዘው አዋጅ ማሰማት የጀመሩት፣ አባሎቻቸውን በግንባር ያነቁት፣ ሲቆይም ሊቃነመናብርቱ ፓስፖርት አውጥተው ተሞክሯቸውን ለሌሎች አገር ሕዝቦች ለማካፈል የበቁት ቆይቶ ነው፡፡ አሁንም፤ በአያሌው ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ላይ ተወስኖ የቆየው መረጃ የማሰራጨት ሥራ በእድሮችም ይሁን በፖሊሶች ወይም በሌላ ተገቢ አካላት መሬት መንካት ይኖርበታል:: ዕድሮች አጭርና ግልጽ መልእክቶች ተዘጋጅተውላቸው ንጋት ላይ “ሕዝቡ” በተኛበት ትምህርት ቢሰጡ - ሀሳብ ነው፡፡ “ሕዝቡ” ምን ማሰብ እንጂ “እንዴት” ማሰብ እንዳለበት በበቂ ደረጃ አልተነገረውም፡፡
ቅጣትም ሌላው ለውጥን እውን ማድረጊያ መንገድ ሊሆን ይችላል - ማን ይቀጣ? እንዴት ይቀጣ? መልሱ ለአዝማቾች ይተው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ ትምህርት መስጫ መንገዶች ብቻ ሳይሆኑ የተለመዱ አሰራሮችም ሊቀየሩ ቢችሉ ጥሩ ነው፤ ለምሳሌ፤ የትራፊክ ፖሊሶች የቅጣት ካርኒ መቁረጥ ብቻ ሳይሆን እዚያው ቀጥተው፣ ደረሰኝ ቆርጠው የሚሄዱበት መንገድ ቢኖር (ካናዳ ይህ ተሞክሮ አለ - በቅጣቱ ያላመነ ብቻ ነው ጣቢያ/ፍ.ቤት መሄድ የሚጠበቅበት)፡፡ ፖሊሶችም ይህን መሰል ሀላፊነት ሊሰጣቸው ቢችል - ተደብቆ ህግ የሚጥሰውን - ለምሳሌ ልደት የሚያከብረውን፣ ቢቀጡ - ካርኒ ቢቆርጡ:: የሐይማኖት ተቋማትም እምቢ ባይ ማህበሮች ሊቀጡ ይችላሉ፡፡  ይህን አሰራር ለማሳለጥ - የጥቆማ ማዕከላት ቢከፈቱ - ስልክ መደወል የፈራ በአካል ቀርቦ መረጃ ይሰጥ ዘንድ::
ለማጠቃለያ - ቀልድ መሰል ቁም ነገር እነሆ:: የሆነ አገር ውስጥ፣ የሆነ የገጠር አካባቢ፣ ከብቶችን እየነደፈ (ገንዲ የሚባለውን በሽታ እያስተላለፈ መሰለኝ) የሚገድል ዝንብ ላይ ዘመቻ ይከፍታሉ - የሆኑ ድርጅቶች፡፡ የህዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ “ለከብቶቻችሁ ማለቅ ምክንያት የሆነው፣ ዋናው በሽታ አስተላላፊ ይህ የምታዩት ዝንብ ነው” ለማለት - ፀ-ፀ የሚባለውን ዝንብ ምስል በትልቅ ፖስተር (ዝርግ ወረቀት/ጨርቅ) ላይ አትመው አላፊ አግዳሚው በሚያየው ቦታ ይሰቅላሉ፡፡ ባላገሩ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስብሰባ ይጠራና ወደ ከተማ ብቅ ሲል፣ ይህን ትልቅ የዝንብ ምስል አይቶ - “ምንድን ነው ደሞ ይሄ?” ብሎ ይጠይቃል:: ይኼ ከብቶቻችሁን እየጨረሰ ያለው ዝንብ ነው” ብለው ያብራራሉ፤ የዘመቻው አባላት - የድርጅቱ ሰራተኞች፡፡
ስለ ምስሉ የተነገረው አንድ ባላገር፣ እጁን አፉ ላይ ጭኖ ሲመለከት ቆይቶ ምን ቢል ጥሩ ነው? “ዑራ! እኛ ጋ ይህን የሚያህል ዝንብ የለም:: ይሄኮ አሞራ ነው የሚያኽለው፡፡ በሉ፣ በሉ ወደ እርሻችን እንሂድ፤ ይሄ ስብሰባ አይመለከተንም:: ሌሎቹም ተከተሉት፤ በሉና ታሪኩን ጨርሱ፡፡
እህ! ከዚህ የምንወስደው ትምህርት አጭርና ግልጽ ነው - ምስሎችን በሚመለከት በመደበኛ ት/ቤት ውስጥ ያለፉ ሰዎች የሚኖራቸው ግንዛቤ “ያልተማሩ” ሰዎች አይኖራቸውም:: አይን ፊደልን ብቻ ሳይሆን ምስልንም ነው የሚማረው:: ጆሮም እንደዚያው ነው፤ በነገራችና ላይ፡፡ እኔ ራሴ ስንትና ስንት የተማርኩት ሰውዬ ከልጆቼ ጋር ቁጭ ብዬ የአሜሪካን የኮሜዲ (የእንግሊዝኛ) ፊልሞችን ስመለከት - እነሱ ሲንከተከቱ እኔ ፍጥጥ ነው የምለው:: እንግሊዝኛው አይጨበጥልኝ! ቀልዱ አይጥመኝ፡፡ ለምን ይመስላችኋል? እነሱ ብዙ ፊልሞችን እያዩ ያደጉ በመሆናቸው - ከበስተኋላ ይዘው የመጧቸው ብዙ ታሪኮች አሏቸው፡፡ ይሔኛውን ፊልም እያዩ ብዙ የሚመጡባቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንዴ ወይ ዝም ስል፣ አሊያም በከፊል ግጥጥ ስል - ያዝኑልኝና ፊልሙን አቁመው ሊያስረዱኝ ይሞክራሉ፡፡ “እኔን ተውኝ፤ ለዛሬ አልደርስላችሁም” እላቸዋለሁ::  ኮሮናን የሚመለከቱ የኮሜዲ ፊልሞችን ጨርሶ ለመረዳት የሚቸገሩ ሰዎች መኖራቸውም ይስተዋል፡፡  ትምህርት .... ለሁሉም እንደየ ችሎታው! ቅጣትም አይረሳ! - ካጠፋሁ ልቆንደድ!Read 5991 times