Print this page
Saturday, 25 April 2020 13:36

የመስቀሉ ድንበር!

Written by  ደሬ
Rate this item
(4 votes)


            ፍልቅልቅ ብለው እንደሳት የሚነድዱ ዐይኖች፣ እንባ የገረፋቸው ጉንጮች፣ ሰቀቀን ያረገባቸው ተስፋዎች ጋራው ላይ ተቀይጠዋል፡፡ ቆነጃጅት፣ ፈርጣማ ወጣቶች፣ እንደ አበባ የፈኩ ልምጭ የመሰሉ እመቤቶች፣ የገረጡ ፊቶች፣ የነደዱ ቀለሞች፣ ሁሉም በያይነቱ ፊታቸው ተዘርግቷል፡፡
ሶስቱ ሰዎች ከሁሉም ከፍ ብለው ሰማዩን የደገፉ ምሰሶ የሆኑ ይመስል በየመስቀሎቻቸው ላይ ተንጠልጥለዋል፡፡ ደማቸው ቁልቁል ቢንዠቀዠቅም፣ ምድረ ዐለሙ ላይ የተነጠፈው ትዕይንት፣ ልባቸውን እየሰረቀ ወደፊትና ወ ደኋላ ይወስደዋል፡፡
ኃይለኛ የተባለው አንዱ ወንበዴም ጠንካራ ጡንቻው ዝሏል፤ ጀርባው፣ ግንባሩ፣ ሁለንተናው እንደ ቅጠል ረግፏል፡፡ በተለይ የህዝቡ ድምጽ በህብር ሲባርቅ እንደ ፈሪ ልቡን ያርደዋል፡፡ በዚያ ላይ
የጥላቻ ቃላት፣ የመረሩ ስላቆች፣ እሳት የሚረጩ ክፉ ዐይኖች ከጅራፍ የበለጠ ያምማሉ፡፡ አጠገቡ ያለው ደምጽ ስሜት አልሰጠውም፡፡ ይልቁኑ በዚያ ጥላቻ፣ በዚያ ሰቀቀናዊ ሁካታ መካከል የሚታዩት ሃብቶች አስጎምዥተውታል፡፡ ብዙ እጆች በተዘረጉ ቁጥር እጆቻቸው ላይ ያለው የወርቅ አምባር ፣ጣቶቻቸው ላይ የሚፍለቀለቀው አልማዝ ቀለበት ልቡን ይነሳዋል፡፡
በሌላ በኩል አካሉ ላይ የሚሰማው ጥዝጣዜ ይነዘንዘዋል፡፡ ቢሆንም ዱላ ለእርሱ አዲስ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ከሰው ተጣልቶ፣ ተደባድቦ፣ ወግቶ ተወግቶ ቤት ገብቷል፡፡ ጥዝጣዜ ብርቁ አይደለም፤ በጩቤ ተወግቶ አንጀቱ ተዘርግፎ፣ በገዛ እጁ በጨርቅ አስሮ ወደ ቤቱ ገብቶ፣ ራሱን አክሟል፡፡
በግራ በኩል የተንጠለጠለው ጓደኛውም ቢሆን ያው ነው፡፡ ብዙ ወንጀል፣ ብዙ የግፍ ታሪኮች፣ የጸጸት መዝገቦች በልቡ አሉ፤ብዙ የክስ ፋይሎች መጠጥ በጠጣ ቁጥር ይገርፉታል፡፡ ተመሳሳይ ሕይወታቸውን አስታውሶ ሊጠራው አሰበና መልሶ ተወው፡፡ የዛሬው መከራቸው ከሌላው ጊዜ የሚለየው ከሞት ጋር አፍንጫ ለአፍንጫ መሻተቱና በአደባባይ ላይ በሕዝብ የሚነድድድ ፍርድ ፊት መቆማቸው ነው:: በርግጥም ዛሬ ሞት ፍጥነቱን ጨምሮ፣ ሮጦ ኮቴያቸውን ጠልፎታል፡፡ በቃ!
አንድ ቀን አሁን አጠገቡ ያለው ሰውዬ ሲያስተምር፣ ጉባዔ ውስጥ ገብቶ የሰረቀው ነገር ትዝ አለውና ሳቀ፡፡ አንዱ ፈሪሳዊ በንዴት ጦፎ፣ ፊትለፊት እየተወረወረ፣ አሁን አጠገቡ የተሰቀለውን መምህር  ሲሳደብ፣ ቀስስ ብሎ፣ እጁን ኪሱ ውስጥ ከተተ፤ ፈሪሳዊው ‹‹የእጁን ስጡት! ዋጋውን ስጡት! አስወግዱት!›› እያለ በቁጣ ሲጋልብ የተነጠቀውን አላወቀም ነበር:: ወደ ፊት መጋለቡን ቀጠለ፡፡ ጨካኙ ወንበዴ የወሰደውን ዕቃ ሲያየው ቁጥር የሌለው ወርቅ ነበር የያዘው፡፡ የደስታው ትዝታ የሚጠዘጥዘውን አካሉን እንዳዲስ ነዘረው፡፡ የአንገት ሃብል፣ የአፍንጫ፣ የጆሮ ጌጥ---- ብዙ ወርቅ ነበር፡፡ ሳያውቀው ፈገግ ብሎ ጓደኛውን ለወሬ ፈለገው:: ጎኑ የተሰቀለው መምህር በሁለቱ መካከል ድንበር ሆኗል፡፡
አሻግሮ ‹‹አስታወስከው?››
‹‹ምኑን?›› አለ በተጨነቀ ስሜት፡፡
‹‹ወርቁን የሰጠችውን ሴትዮ››
‹‹ከፈሪሳዊው ነው የሰረቅሁት አላልከኝም እንዴ?››
‹‹አዎ፤የሴትየዋን ታሪክ ረሳኸው እንዴ?››
‹‹አላስታውስም!›› አለና በመሰላቸት ፊቱን አዞረ፡፡
ይህ ወንበዴ ግን አልረሳውም፡፡ በወርቁ ምክንያት አንዲት ለጋሽ ሴትና ፈሪሳዊው ተጣልተው ነበር፡፡
አይኑን መለስ ሲያደርግ የሰዎቹ እንደ እሳት የሚንቀለቀል ቁጣ፣ ከርሱ ይልቅ ጎኑ በተሰቀለው መምህር ላይ ብሷል፡፡ በዚህ ምድር ደግ መሆንና ያለመሆን ልዩነት እንደሌለው ማሳያው ያ ቀን መሰለው፡፡
ድንገት አጠገቡ የተሰቀለው ሰው ሲያቃስት ሰማውና ሃሳቡን የረበሸው ሲመስለው ‹‹መካከላችን ገባህኮ ሰውዬው›› አለው፤ኢየሱስ አንድ አፍታ ገረመመውና፣ ስቃዩንና ሕዝቡን ማሰላሰል ቐጠለ፡፡ ያ ሕዝብ ሳምንት ዘንባባና ልብስ ያነጠፈለት ነበረ፤አሁን ደግሞ መስቀል ላይ አንጠልጥሎት በደስታ ይጨፍራል፤ይስቃል፡፡ እርሱ ደግሞ የዚህኑ ጨካኝ ሕዝብ ዕዳ ለመክፈል መራራ እየጠጣ ነው፡፡ ደሙን እያፈሰሰ ነው፡፡
ይህ አሽሟጣጭ ወንበዴ በወዲያኛው በኩል የተሰቀለውን የዕድሜ ልክ ጓደኛ ቢያገኘው ደስታውን ባልቻለው፡፡ የዛሬ ሐዘኑ ምክንያት መስቀል ላይ በምስማር መንጠልጠሉ ብቻ አይደለም፤ ይህንን ጽዋ አንድ ቀን እንደሚጨልጠው ያውቅ ነበር፡፡ የዘራው ዘር ፍጻሜ ይህ እንደሚሆን ያውቃል፡፡ አሁን ግን አጠገቡ ጓደኛው አለመሰቀሉ ይብስ አበሳጭቶታል፤ ዋዘኛ ፌዘኛ ነው፡፡ እየሞተ ለመሳቅ አይመለስም፤እየጠዘጠዘው እንኳ ማላገጥ እያማረው ነው፡፡ ይህ መሲህ ነኝ ባይ መካከላቸው ገባ፤ድንበር አበጀ፤በሞታቸው መካከል ጣልቃ ገባ፡፡ ጨዋታቸውን ሰረቃቸው::
ፊቱን ወደ አደባባዩ፣ ወደ ኮረብታው ሕዝብ ሲመልስ፣ ከሚያለቅሱት ጥቂት ሰዎች በቀር ሁሉም በፈንጠዝያ የተሞሉ ይመስላሉ:: ሌባው ጨዋ፣ ዘማዊው ቅዱስ፣ በሌሎች ላይ ጦሩን ይሰብቃል፡፡ ምራቁን ይተፋል፤ ይረግማል፣ያጣጥላል፡፡ የፈጣሪ ልብ ምን ያስብ ይሆን ብሎ የሚያስብ ይመስል፣ ዐይኖቹን ወደ ሰማይ ላካቸው፡፡ ማንንም አላየም፤እንኳን እነርሱ አጠገባቸው የተሰቀለው መሲህ ነኝ ባይ እንኳ አይዞህ ባይ አልነበረውም፡፡ ደንገት ፊቱን ወደ ሕዝቡ ሲመልስ፣ ልጅ እያለ ጎረቤቱ የነበሩትን ሰውዬ አያቸውና የቆነጠጡት ቁንጥጫ ትዝ አለው፡፡ የሰው ጓሮ ገብቶ ፍራፍሬ ሲሰርቅ አግኝተው ነበር የቆነጠጡት፡፡ ከዚያ ለእናቱ ሄዶ ሲነግራቸው፣ እሳት ጎርሰው ሄደው፣ ሰውዬውን ከፍ ዝቅ አደረጉት፡፡ ይሄኔ የልብ ልብ ተሰማው፡፡ የጎረቤቱ ሰውዬ ዐይናቸውን ብድግ ሲያደርጉ፣ ዐይን ለዐይን ተገጣጠሙ፡፡ ሰውዬው በሸማ ፊታቸውን ሸፍነው አለቀሱ፡፡ እርሱም አንዳች ስሜት የተሰማው ይመስል ዐይኖቹን የሚደብቅበት ጠፋው፡፡
ለምንና ለማን እንዳለቀሱ አልገባውም፤ ምናልባት መምህራቸው የሆነው ኢየሱስ መሰቀሉ አሳዝኗቸው ይሆናል፤አይታወቅም፡፡
‹‹ልጄ ያኔ የቆነጠጥኩህ እዚህ እንዳላይህ ብዬ ነበር፡፡››
ደነገጠ፡፡
ሰውዬው ሄዱ፡፡ ትዝታቸው ግን ቶሎ ከልቡ አልጠፋም፡፡
አጠገቡ የተሰቀለው ኢየሱስ የሚባል ሰው፣ ብዙ ሰዎችን በትምህርቱና በታምራቱ ማርኳል እንደሚባል ያውቃል፡፡ ታዲያ ይህ ሰውዬ ታምራት መስራት ከቻለ ለምን አያድነንም! ብሎ ለመቀለድ አሰበና፣ ደሙ ሲዘንብ ዐይቶ ተወው:: ታምራት ቢጠቅም ኖሮ ይህ ሁሉ ሊሰቅለው የተንጋጋ ሕዝብ ይድን ነበረ፡፡ አሁን ተዐምር ቢያሳይ አሁን ይረሳል፡፡ አባቶቻችን ስንት ተዐምራት አይተው አይደል ምድረበዳ የቀሩት:: የትናንቱን ዛሬ እየረሱ፣የዛሬውን ለነገ ማሳደር አቅቷቸው!! የራሱን ሕይወት አሰበና ነፍሱ ከዚህ በሽቃጣ አለም የምትሰናበትን ጊዜ ናፈቀ:: ይህንን ሃሳቡን መልሶ ሊተወው ይችላል::
እንደጠረጠረው ድንገት ቁልቁል ወደ ሕዝቡ ሲያይ፤ የቁጣ ዐይኞች እንደ እሳት ሲንቦገቦጉ፣ እጃቸው ሲውለበለብ፣ በወርቅ ጌጦች የተንቆጠቆቱን ዐይቶ ጎመዠ፡፡ የሚያብረቀርቀውን ጌጣጌጥ ዱብ ብሎ ወርዶ እየነጠቀ እብስ ቢል ደስታውን አይችለውም ነበር፡፡ ግን እጅና እግሩ መስቀል ላይ በምስማር ተሰፍቷል፡፡
ድምጹን ከፍ አድርጎ ‹‹አየኸው ያንን ሰውዬ? አንገቱ ላይ ያለው ወርቅ ስንት ወቄት ይሆናል?››
ባልንጀራው ተቆጣ ‹‹ሞት ጉሮሮ ውስጥ ሆነህ እንደዚህ ያለ ሃሳብ ታስባለህ?››
‹‹ጎንህ ያለውን አዳኝ ነኝ ባይ፣ ሆዱን ልታባባ ነው?››
‹‹በመጨረሻው ሰዐት እንኳ ቀና ሁን!!››
‹‹ምንም ወደ ማይጠቅምህና ወደ ማይረባህ ነገር አትጸልይ፤ይልቅ የልብህን ተናግረህ ሙት::››
‹‹እንደ ኢዮብ ሚስት አታስብ፤ ያ ምክር የሰነፍ ምክር ነበር፡፡ ኢዮብ የተቃወማት እንደማያዋጣ ስላወቀ ነበር፡፡››
ድንገት ከሕዝቡ መካከል ‹‹እናንት መርዘኞች፤ ዛሬ ዋጋችሁን አገኛቸሁ፤ የልጆቼን ቀለብ ነጥቃችሁኝ አልቀራችሁም፣ዋጋችሁን ተቀበላችሁ!!›› ብሎ ጥርሱን ነከሰባቸውና ጦር ይዞ ሊወጋቸው መጣ፡፡
ተሳዳቢውን ሊወጋው ሲል መሃል የተሰቀለው ‹‹እኔን ውጋኝ›› አለው ፡፡
ከዚያ አንዲት ሴት እየበረረች መጥታ በጩኸት ‹‹አንተን ወጊ ያደረገህ ማነው? አጋጣሚ ሆኖ እንጂ አንተስ ሌባ አይደለህ? እኔ ለእግዚአብሄር ቤት የሰጠሁትን ስጦታ ስለሰረቀህ፣ በኋላም እኔ አግንቼው ካንተ መውሰዱን ስለነገረኝ ልትበቀለው ነው? በጦር ልትወጋው ነው? ከርሱ ይልቅ መሰቀል የነበረብህ አንተ ነበርክ፡፡ እርሱ የሰረቀው ካንተ ነው፤አንተ የሰረቅኸው ከጌታ ላይ ነው፡፡›› ሰውዬው ጦሩን ወርውሮ ሸሸ፡፡
ከዚያ መሃል የተሰቀለው ‹‹ጌታ ምህረቱ ብዙ ነው፡፡ የሰረቁትን መች ገደለ! እንዲመለሱ ይታገሳል፡፡››
‹‹ጌታዬ፤አንዱን ልጄን ከሞትያዳንክልኝ የናይን ከተማዋ ሴት ነኝ፡፡››
‹‹ልጄ የመጣሁት እናንተን ለማዳን ነው፤አሁን መስቀል ላይ ያለሁትም ለዚያ ነው::››
‹‹የኔ ጌታ እኔ ልሰቀል! እኔ ልወጋ!!››
‹‹ልጄ አንቺ እንዳትወጊ ነው የተወጋሁት!››
ድንገት አንድ ወጣት ጦርና ጎራዴ ይዞ ‹፣ማን አባቱ ነው ጌታዬን የሰቀለው!..እነዚህ ወታደሮች ናቸው!...ለጌታዬ እሞታለሁ፡፡›› ሲል እናቱ ጥምጥም ብላበት ‹‹ልጄ ጌታ ለጦርነት አልመጣም!››
‹‹ልጄ በሰይፍ ለማሸነፍ አልመጣሁም፤ ለጴጥሮስ የነገርኩትን ልንገርህ፣አብ የሰጠኝን ጽዋ እጠጣ ዘንድ ይገባኛል፡፡››
ልጁ አለቀሰ ‹‹ጌታ ሆይ፤ እኛን በማዳንህ ትሰቀላለህ?››
‹‹አዎ ልጄ፣ ሰይፍህን ወደ ሰገባው ክተተው!››
‹‹ማዳን ከቻለ ራሱን አያድንም?››
‹‹እኛንም ሊያድነን ይችላል፡፡››
‹፣ካበቃ በኋላ?››
‹መንግስቱ የዘላለም ነው፤የሰማዩ መንግስት ይቀጥላል፤ጌታ ሆይ በመንግስትህ አስበኝ፡፡››
‹‹ዛሬ በገነት ከኔ ጋር ትሆናለህ፡፡››
የመስቀሉ ግራና ቀኝ ሲኦልና መንግስ ተሰማይ ሆነ፡፡ ድንበሩ ተሰመረ፡፡ ፍርድና ይቅርታው ተጠናቀቀ….
ጌታም ጎኑን በጦር ሲወጉት ‹‹ተ…ፈ…ጸ…መ›› አለ፡፡
ጸሐይ ወዲያው ፈገግታዋ ጠፋ፡፡ የምድር ሳቆች ተነጠቁ፡፡ ጎልጎታ ጋራ ላይ ቀንበጦች ጠወለጉ፤ …በማይታየው የትንሳኤ ቀን፣ አዳዲስ የብርሃን ጨረሮች ከየአድማሱ ጉያ የሚፈለቀቁበት፣ የዋዜማ መዝሙር ተዘመረ፤ በሰው ልጆች ደጅ የተስፋ አድማሳት ፈገግ አሉ::…

Read 2333 times