Saturday, 25 April 2020 13:39

የእቴጌ ወልድ ሠዓላ በጐ ሥራና የተጋፈጡት ፈተና

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(1 Vote)


             እቴጌ ወልድ ሠዓላ የዓፄ ሱስንዮስ  ባለቤት ሲሆኑ የተጋቡት በ1595 ነው፡፡ ዓፄ  ፋሲለደስንና አቤቶ ገላውዴዎስን ጨምሮ በርካታ ልጆችን ወልደዋል፡፡ ከወለቃና ከመርሐ ቤቴ የባላባት ዘር የተወለዱት  እቴጌ ወልድ ሠዓላ፤ ሃይማኖተኛና ጸሎተኛ ስለነበሩ በደቡብ ጎንደር ዞን ከእስቴ ወረዳ ከተማ ከመካነ ሥላሴ 52 ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኝ ገጠራማ ቀበሌ ላይ ገዳሙን መስርተዋል:: ደብሩም በ318 ሊቃውንት እንዲገለገል አድርገዋል፡፡ ገዳሙ በራሳቸው ርስትና ጉልት ላይ ከመመሥረቱ ባሻገር የሚተዳደረውም እቴጌይቱ በለገሡትና በገዳሙ ዙሪያ በሚገኘው መሬት ነው፡፡ ይህ እቴጌ ወልድ ሠዓላ ለቆማ ፋሲለደስ ገዳም የለገሱት ሰፊ ጋሻ መሬት በልጃቸው በዓፄ ፋሲለደስ ትእዛዝ እንዲፀና ተደርጓል፡፡ በቆማ ፋሲለደስ ከሚገኘውና ስለ ንግሥቲቱ ከሚያትተው ታሪክ ለመረዳት እንደሚቻለው፤ እቴጌ ወልድ ሠዓላ ቤተ መንግሥቱን ትተው ወደ ቆማ ፋሲለደስ በ1618 የገቡት  ባለቤታቸው ዓፄ ሱስንዮስ ባልተለመደ ሁኔታ  የካቶሊክ እምነት አማኝ ስለሆኑባቸው ተቀይመውና አዝነው ነው፡፡
እቴጌ ወልድ ሠዓላ በራሳቸው ርስትና ጉልት ላይ በመሠረቱትና፤ በ318 ሊቃውንት እንዲወደስ፤ እንዲቀደስ፤ እንዲሠለስና ለደብሩ መተዳደሪያ እንዲሆን የሰጡት ርስትና ጉልት በልጃቸው በዓፄ ፋሲለደስ አዋጅ (በብራና የተጻፈ) ጭምር እንዲጸና በተደረገው የቆማ ፋሲለደስ ገዳም ውስጥ ጥንታዊነትና ታሪካዊነት ያላቸው በርካታ መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በእቴጌ ወልድ ሠዓላ የተበረከቱ ሦስት የብራና መጻሕፍት ማለት አንድ በጣም ትልቅ፤ ሌላው ደግሞ ትንሽ መጻሕፍተ ተአምረ ማርያም፤ አንድ መጽሐፈ ሊቅ፤ እንደዚሁም ከዐረቡ ዓለም የተበረከቱና በዐረብኛ የተጻፉ የተአምረ ማርያም መጻሕፍት እንደሚገኙ ጎንደርና ቆማ ፋሲለደስ የኖረችው ፈረንሳዊቷ አናይስ ገልጻ፤ መጻሕፍቱን በፎቶግራፍ ጭምር በማስደገፍ የምርምር ውጤቷን  ለንባብ አብቅታለች፡፡
 ቆማ ፋሲለደስ የጎንደሩ ዝነኛው ንጉሥ የዓፄ ፋሲለደስ ታሪክ የሚጀምርበት ቦታም ነው፡፡ የቆማ ፋሲለደስ ቤተ ክርስትያን ከተሠራ በኋላ ንግሥት ወልድ ሠዓላ (ወልድ አስጊጦ የሣላቸው፤ አሳምሮ የፈጠራቸው ለማለት ነው) የልጃቸውን ስም ፋሲለደስ ብለው ሰይመውታል፡፡ ሀሳባቸውም ልጃቸው ልክ እንደ ሰማዕቱ ቅዱስ ፋሲለደስ የቅድስና ሥራ እንዲሠሩ በመመኘት ነው፡፡ እንደተመኙትም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት የኢትዮጵያና የመንግሥት  ሃይማኖት ሆኖ እንዲቀጥል በአዋጅ ጭምር አጽንተው ሕዝቡን ከጭንቅና ከመከራ መልሰውታል፡፡ በቆማ ፋሲለደስ ቤተ ክርስቲያን አናት ላይ የዘውድ፤ የጦርና የጠመንጃ  ምልክት መደረጉ  የንጉሥ ፋሲለደስን የንግሥና ሥርዓት ያመለክታል፡፡
ስለ ዓፄ ፋሲለደስ የሕይወት ታሪክና ስለ ቆማ ፋሲለደስ ገዳም ተመራማሪ የሆነችው ፈረንሳዊቷ አናይስ ዊዎን፤ “ዓፄ ፋሲለደስ ወንድሙን አቤቶ ገላውዴዎስን ለምን ገደለው”? ከሚል መሪ ሐሳብ ተነሥታና ከድርጊቱ ጋር ተያያዥነት ስለነበረባቸው ጉዳዮች አሰናድታ እ.ኤ.አ ሰኔ 21 ቀን 2010 በጁርናል ኦፍ ኧርሊ ሞደርን ሒስትሪ (250-293) እንደጻፈችው፤ የእቴጌ ወልድ ሠዓላና የዓፄ ሱስንዮስ ልጅ የሆኑት ዓፄ ፋሲለደስ (ስመ መንግሥታቸው ዓለም ሰገድ) ከ1632 እስከ 1667 ኢትዮጵያን የገዙ ስመ ገናና ንጉሥ ናቸው፡፡ አባታቸው ዓፄ ሱስንዮስ (ስመ መንግሥት ሥልጣን ሰገድ) ሲሆን  እናታቸው እቴጌ ወልድ ሠዓላ (ሥልጣን ሞገሳ) ናቸው፡፡ ዓፄ ሱስንዮስ ኢትዮጵያን ከ1607 እስከ 1632 በገዙበት ወቅት የሀገሪቱ ብሔራዊ ሃይማኖት የካቶሊክ እምነት መሆን አለበት ብለው ለፓፓው ሥልጣን ተገዥነታቸውን በግልጽ ስላሳወቁ በመላ ሀገሪቱ ጦርነት ተቀስቅሶ ብዙ ሰው አለቀ፡፡ በተወሰነ ቀን ውጊያ ብቻ በጎንደርና በደብረ መዊዕ (ምዕራብ ጎጃም) ከ8000 ሺህ ሕዝብ  በላይ ለኅልፈተ ሕይወት ተዳርጓል፡፡ በወቅቱ በሃይማኖት ሰበብ በሀገሪቱ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት ዓፄ ሱስንዮስና እቴጌ ወልድ ሠዓላ የወለዷቸው ልጆች ልዑል ማርቆስና ልዕልት መለኮታዊት በጦርነቱ ተገድለውባቸዋል፡፡
ኑሯቸውን በቆማ ፋሲለደስ ገዳም አድርገው የነበሩት ንግሥት ወልድ ሠዓላ፤ በ1661 ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም ዐፅማቸው ያረፈው ቆማ ገዳም ውስጥ ነው፡፡ የገዳሙ ግንባታ የተጀመረው በ1618፤ የተጠናቀቀው ደግሞ በ1640 ነበር፡፡ በእቴጌ ወልድ ሠዓላ በታነጸው ቆማ ፋሲለደስ ገዳም ውስጥ አቤቶ ገላውዴዎስ ከወንድማቸው ከዓፄ ፋሲለደስ ጋር ተጣልተው በችግር ላይ በነበሩበት ጊዜ ተደብቀውበት ነበር፡፡ የየገዳሙ መነኮሳት ዓፄ ሱስንዮስን “ውጉዝ ከመ አርዮስ” ብለው የፖለቲካ ክስረት በአደረሱባቸው ወቅት ሕዝቡ “ፋሲል ይንገሥ፤ ሃይማኖት ይመለስ” እያለ ድምጹን ማሰማት ጀመረ፡፡ ምክንያቱም በዚያ ወቅት ልጃቸው ልዑል  ፋሲለደስ የፀረ ጀስዊትስ አቋም ስለነበራቸው ነው፡፡ እቴጌ ወልድ ሠዓላ በመጨረሻ በእምነታቸው የተጽናኑትና የተደሰቱት ልጃቸው  ፋሲለደስ የኦርቶዶክስን እምነት መንግሥታዊ ሃይማኖት ባደረጉበት ጊዜ ነው፡፡
 ነገር ግን ደስታቸው ብዙም ሳይቆይ ወደ ኀዘን ተቀየረ፡፡ ምክንያቱም በሁለቱም ልጆቻቸው መኻከል የነበረው ቅራኔ እያደገ በመሔዱ ነው፡፡ ዓፄ ሱስንዮስ በሕይወት እያሉ ወራሴ መንግሥቴ ታናሹ ልጅ አቤቶ ገላውዴዎስ ነው ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን ‘ታላቁ ልጅ እያለ እንዴት ታናሹ ይነግሣል’ በሚልና በወንድማቸው ላይ በመነሣሣት ፋሲለደስ ራሳቸው  ነገሡ፡፡ ሕዝቡም ከባህላዊ የአነጋገሥ ሥርዓት ተነሥቶ ንግሥና (መንግሥት) የሚገባው ለታላቁና ለመጀመሪያው ልጅ ለፋሲለደስ እንጂ ለታናሹ ለገላውዴዎስ አይደለም እያለ ፋሲለደስን በመደገፍ የራሱን ፍርድ ሰጠ፡፡ ዓፄ ፋሲለደስ በ1632 ሲነግሡ፣ አቤቶ ገላውዴዎስ የጦሩ የበላይ አዛዥ ኾነው ተሾሙ፡፡ ዓፄ ፋሲለደስ በነገሡበት ወቅት የሁለቱ ወንድማማቾች ግንኙነት አንጻራዊ በሆነ መልክ ደኅና ነበር፡፡ ነገር ግን ነገሥታት ሲነግሡ፣ በዘልማድ የሥጋ ዘመዶቻቸው ሥልጣን ይቀሙናል የሚል ሥጋት ስለሚያድርባቸው ዓፄ ፋሲለደስም ከካቶሊኮች ሳይቀር ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል ብለው የጠረጠሯቸውን ወንድማቸውን በዓይነ ቁራኛ ይመለከቷቸው ጀመር፡፡
በዘመኑ (ከ1648-49) የየመን አምባሳደር ሆኖ ጎንደር ውስጥ ይገኝ የነበረው ሚስተር አል ሃይሚ የዓይን ምስክር ሆኖ እንደዘገበው፤ ዓፄ ፋሲለደስ በነገሡበት ወቅት ልዑል ገላውዴዎስ የንጉሡ ጦር ጠቅላይ አዛዥና የቤጌምድር ደጃዝማች ስለነበሩ የበላይነት ስሜት አድሮባቸው ነበር፡፡ ከጠባያቸው ኃይለኛነት የተነሣም ሥልጣን ሊቀሙ ይችላሉ በሚል ንጉሡን ስለ አሠጋቸውና ኑፋቄ ውስጥ ስለጣላቸው ከፋሲለደስ ለገላውዴዎስ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላም አቤቶ ገላውዴዎስ ተያዙና ታሠሩ፡፡ እናታቸው ወልድ ሠዓላ  ልጃቸው ልጃቸውን እንዳይገድልባቸው በእጅጉ ስለተጨነቁ፣ ከእግራቸው ሥር ወድቀው ዓፄ ፋሲለደስን ተማጸኗቸው፡፡ ፋሲልም የእናታቸውን ጭንቀት ተመልክተው ወንድማቸውን  እንደማይገድሉ ቃል ቢገቡላቸውም፣ በመጨረሻ ቃላቸውን ሽረው ወንድማቸውን አቤቶ ገለውዴዎስን ገደሏቸው፡፡ ይህ የፋሲለደስ ድርጊት እናታቸውን እቴጌ ወልድ ሠዓላን በእጅጉ አሳዘናቸውና የገዳዩን የፋሲለደስን ዓይን ዳግመኛ ላለማየት ማለሉ፡፡
 አናይስ አል ሃይሚን ጠቅሳ እንደዘገበችው፤ ዓፄ ፋሲለደስ ወንድማቸውን አቤቶ ገላውዴዎስን ከገደሏቸው በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩትን ግብጻዊ ጳጳስ አባ ማርቆስንም በሞት አስወግደዋቸዋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁለት ሰዎች  ለመንግሥቴ መሰናክሎች እንደሆኑ ስለገመቱ ነው፡፡ ነገር ግን በአቤቶ ገላውዴዎስና በጳጳሱ  አባ ማርቆስ መኻከል የተለየ ቅርበትና የፖለቲካ ግንኙነት አልነበረም፡፡ ነገር ግን የሁለቱ የአወጋገድ ታሪክ በዓፄ ፋሲለደስ ዜና መዋእል ላይ ተጽፎ አለመገኘቱ ያስደንቃል ይላል - አል ሃይሚ፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ በዘመኑ የዳጋ እስጢፋኖስና የክብራን ገብርኤል ገዳማት የዓፄ ፋሲለደስ ደጋፊዎች፤ የአቤቶ ገላውዴዎስ ደግሞ ተጻራሪዎች ነበሩ፡፡ የቆማ ፋሲለደስ ገዳም ግን የዓፄ ሱስንዎስ ዙፋን ወራሽ መሆን ያለበት አቤቶ ገላውዴዎስ እንጂ ዓፄ ፋሲለደስ አይደለም ብለው ይሟገቱና አቤቶ ገላውዴዎስን ይደግፉ ነበር፡፡ ይህም ድጋፍ እቴጌ ወልድ ሠዓላ መንነው ራሳቸው በሠሩት ቆማ ፋሲለደስ ገዳም ውስጥ ይኖሩና ለገዳሙም የተሟላ ድጋፍ  ያደርጉ ስለነበር፤ ወይም በሽሽታቸው ወቅት አብረዋቸው ገዳም ውስጥ ተቀምጠዋል ተብሎ የሚታሰቡትን አቤቶ ገላውዴዎስን ከልባቸው ስለሚያፈቅሯቸውና ገዳማውያኑም ለታናሹ ልጅ የማድላት አዝማሚያ ስለነበራቸው ነው ብሎ ለመገመት ይቻላል፡፡ ከዚህም የተነሣ ቆማዎች እስካሁን ድረስ የፋሲለደስን አልጋ ወራሽነት አይቀበሉትም፡፡ በ1638 ላይ አቤቶ ገላውዴዎስ በወንድማቸው ላይ ለሚያካኺዱት ዐመፅ ርዳታ ለማሰባሰብ ፈልገው ወደ ላስታ ተጉዘው ነበር፡፡ ላስታ በዘመኑ የማዕከላዊው መንግሥት ሥልጣን ይገባኛል የሚልና በሰሎሞናዊው ሥርዎ መንግሥት ሥልጣን የተወሰደበት የዛጉየ ነገሥታት መቀመጫ ነበር: ኅዳር 23 ቀን 1646 ዓፄ ፋሲለደስ እርዳታ ለማግኘት ሲሯሯጡ የነበሩትን ወንድማቸውን አቤቶ ገላውዴዎስን አሥረው ለግዞት ዳረጓቸው፡፡ ሬኔ ባሲጥ በበኩሉ እንደጻፈውም፤ ስለ ወጣቱ ልዑል አሟሟት በቤተ መንግሥቱ ዜና መዋዕል ላይ አልሰፈረም፡፡ በሌላ በኩል፤ አቤቶ ገላውዴዎስ በወንድማቸው በዓፄ ፋሲለደስ እጅ የተገደሉ መሆኑን የሚጠቁም ማስረጃ የተገኘው ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ውስጥ ከተቀመጠ የብራና መጽሐፍ ነው፡፡ የአቤቶ ገላውዴዎስ ሞት ለዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ማኅበረ መነኮሳት አስደሳች ዜና ነበር፡፡ ምክንያቱም ገዳማውያኑ ልዑሉን በካቶሊክነት (በወተሊክነት) ይጠረጥሩዋቸው  ነበርና ነው፡፡
አል ሃይሚ እንደሚያትተው፤ አቤቶ ገላውዴዎስ መንግሥት ይገባኛል ብለው በዐመጹበት፤ በተያዙበትና በተገደሉበት በ1649 እና በ1650 ላይ ሁለት የኦርቶዶክስ እምነት አባቶች ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ እነርሱም በዓፄ ፋሲለደስ ጠያቂነት ከእስክንድርያ መንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ የተላኩት አቡነ ሚካኤልና በአቤቶ ገላውዴዎስ አሳሳቢነት ከዚያው ከእስክንድርያ የመጡት አባ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ይሁንና ዓፄ ፋሲለደስ የአባ ዮሐንስን አመጣጥ እንደማይቀበሉት ገልጸው ሲቃወሙ፤ በእርሳቸው ጠያቂነት የመጡትን አቡነ ሚካኤልን ግን ስለተቀበሏቸው  እስከ1664 ድረስ በአቡንነት አገልግለዋል፡፡ ይህ ያልተለመደው ድርጊት (ጳጳስን ያለመቀበል) በታሪክ ተመራማሪዎች እንዳልተጠና አል ሃይሚ ይናገራል፡፡ አቤቶ ገላውዴዎስ ወንድማቸውን ተከትለው ከእስክንድርያ ጳጳስ ለማስመጣት ደብዳቤ መጻፋቸው በቤተ መንግሥቱ ውስጥ የማይገሠሥ ሥልጣን ባለቤት ነኝ ከሚል ስሜት የመጣ እንደነበር ይገለፃል፡፡
እናም ለሞታቸው ምክንያት የሆነውም በሌላው ሥልጣን አብዝተው ይጠቀሙ ስለነበር ነው፡፡ በአል ሃይሚ እምነት አቡነ ማርቆስ በንጉሡ የተወገዱት በእጨጌነት ሥልጣናቸው እየተጠቀሙ ከፍተኛ የሆነ ሀብት ሲያካብቱ በመገኘታቸው ነው፡፡ ይህ ድርጊታቸው በዐረብኛ ጭምር ተጽፎ ለእስክንድርያው ፓትርያርክ ተገልጾላቸዋል: እናም አቡነ ማርቆስና አቤቶ ገላውዴዎስ የጎንደርን ቤተ መንግሥት ያስቸገሩ ሰዎች በመሆናቸው እንዲወገዱ ተደርገዋል: በኢየሱሳውያን (ጀስዊትስ) ረገድ የአቤቶ ገላውዴዎስ ታሪክ ሲመረመር ሌላ መልክ ይዞ ይገኛል፡፡ ዓፄ ፋሲለደስ በነገሡ ጊዜ ከኢትዮጵያ የተባረሩት ኢየሱሳውያን ስለ ኢትዮጵያ  ሁኔታ በርካታ ደብዳቤዎችን ጽፈዋል፡፡ በተለይ አገር ውስጥ ቀርተው የነበሩት ጥቂት የካቶሊክ ካህናት ስለ ወቅቱ ሁኔታ የተሟላ ማስረጃ እያሰባሰቡ ለዶ አልሜዳና ለሜንዴዝ ይልኩ ነበር፡፡ ኢየሱሳውያን ወደ ፖርቱጋልና ወደ እስፓኝ በጻፉት የመጀመሪያ ደብዳቤ እቴጌ ወልድ ሠዓላና አቤቶ ገላውዴዎስ የካቶሊክ እምነት ተጻራሪዎች እንደሆኑ አስረድተዋል: በኋላ ደግሞ አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ከጻፉት ጽሑፍ ለመረዳት እንደሚቻለው፤ ዶ አልሜዳ የተባለውና ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የጻፈው (“ሒስቶሪያ ዶ ኢትዮጵያ” 1641) ግለሰብ  ሲያትት፤ “ወልድ ሠዓላና አቤቶ ገላውዴዎስ ድንገት ተነሣሥተው የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ሆነዋል” ብሏል፡፡
ኢየሱሳውያን ይህንን ወሬ የነዙት በሕዝቡ ዘንድ ተጻራሪ ነገሮችን ለመፍጠርና እርስ በርስ ለማጋጨት በማሰብ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሜንዴዝ ቤርናርዶ ኖውጉሪያና ቶርጋቶ ፓሪሲያኒ እርስ በርስ የሚቃረኑ ሁለት ደብዳቤዎችን (ሪፖርቶችን) ጽፈው ወደ ጎኣ ልከዋል፡፡ የመጀመሪያው ደብዳቤ ጎኣ የደረሰው መጋቢት 16 ቀን 1847 ነው፡፡ የመጀመሪያው ደብዳቤ የሚያትተው ስለ አቤቶ ገላውዴዎስ ሞት ሲሆን ሁለተኛው ደብዳቤ ደግሞ የካቶሊክ እምነት በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ህልውና አግኝቶ የቀጠለ መሆኑን  ይገልጻል፡፡ ቶርጋቶ ፓሪሲያኒ ግን ይህንን ሲጽፍ በመኻል  አገር ውስጥ  ተቀምጦ ሳይሆን በቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ጠረፍ  አካባቢ ሆኖ ነው፡፡ ከ1645-1647 የኖረውም በዚያው በቀይ ባሕር ጠረፍ ነው፡፡
ይሁንና ቶርጋቶ ስለ አቤቶ ገላውዴዎስ ዐመፅና ስለ አቡነ ማርቆስ ሁኔታ የተሟላ ጽሑፍ ጽፏል ተብሎ በታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ተደንቋል፡፡ በቶርጋቶ እምነት፤ አቤቶ ገላውዴዎስ የተገደሉት የካቶሊክ እምነት ስለተቀበሉና ይህም በንጉሡ ዘንድ የማይፈለግ ስለነበረ ነው፡፡
ኖውጉሪያና ቶርጋቶ ፓሪሲያኒ እንደ ጻፉት፤ የካቶሊክን እምነት የተቀበሉት አቤቶ ገላውዴዎስ፤ በወንድማቸው በፋሲለደስ ላይ ዐመፅ ለማስነሣት የቻሉት በርካታ ልዑላንና መሳፍንት ይደግፏቸውና የመንግሥት ጦርም ጠቅላይ አዛዥ ስለ ነበሩ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አቤቶ ገላውዴዎስን ይደግፉ የነበሩ ልዑላን፤ መሳፍንትና የጦር ሠራዊት አባላት በኋላ በንጉሡ እየታደኑ እንደ ተገደሉ እነ ቶርጋቶ ዘግበዋል፡፡ በእነ ቶርጋቶ ሪፖርት መሠረት፤ አቤቶ ገላውዴዎስ በ1646 የተገደሉት እንደ ሰማዕታት አንገታቸው ተቆርጦ ነው፡፡
ዐፅማቸውም በጎንደር ገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚገኘው በአባታቸው በዓፄ ሱስንዮስ መቃብር ቤት ዐርፏል፡፡ ዓፄ ፋሲለደስ ለጎንደር ሥልጣኔ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ፤ እስከ ዛሬ ድረስ በስማቸው የሚጠራውን  የፋሲል ግንብ የገነቡ፤ ከተማዋን ያስፋፉ፤ ለንግድ ልውውጥ ሕጋዊ መሠረት የጣሉ፤ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችና በካቶሊኮች መኻከል ይካኼድ በነበረ ጦርነት ሲፈስ የቆየውን ደም ያስቆሙና የሀገራችንን ዳር ድንበር አስከብረው የኖሩ ታላቅ ንጉሥ የነበሩ መሆናቸው በታሪክ  ሲወሳ ይኖራል፡፡

Read 1610 times