Wednesday, 29 April 2020 00:00

አይባልም

Written by  አዛኤል
Rate this item
(1 Vote)

   ግላዊነት አብሮ መሆንን በእጅጉ የሚቃወም ሀሳብ ነው ቢሉም አንዳንዶች፣ ሌሎች ደግሞ የትኛውም አብሮነት ምንጩ ጤነኛ ግላዊነት ነው ባይ ናቸው፡፡ አብዝተን ስለ ሁለቱ መከራከራችን የተለመደ ነው፡፡ አለም በየትኛው ትመራ? ሀገር በየትኛው ትዘወር? ቤተሰብ በየትኛው ይቀየስ? ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ አሳሳቢ የአኗኗር ስልተ ምት ሙግት ነው፡፡  ግላዊነት ሀይልን መፍጠር ነው፡፡ ሀይል፤ የመኖር ዋስትና ነው፡፡ የገንዘብ ሀይል (Economic power) የሚሉት (የሚያበላህ ይገዛሀል ነውና!) ሌላኛው የፖለቲካ ሀይል በመጨረሻም በምድር ላይ ከየትኛውም ጠላት የሚታደግ ሀይልን ማበጀት ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ሌሎች ከተባባሩ እሰየው፣ ካልሆነም ግን ሀይሉን በራስ አቅም መፍጠር የግድ ይሆናል፡፡  
በጦርነት፣ በእርዳታ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሀይማኖት፣ በታሪክ ሊሆን ይችላል ውድድሩ:: ብቻ አብረን መሆን ስለማንችል፣ ለየብቻችን እንሞካከር የሚል ጉንጭ አልፋ ፉክክር ነው፡፡ እነ ሂትለር የዚህ ፉክክር ጠንሳሽ ነበሩ፡፡   
ይህ ሁሉ ለምን ቢሉ? ዘርን፣ ሉአላዊነትን፣ የባህል የበላይነትን አስጠብቆ ህይወትን በልቶ ብቻ ሳይሆን ኮርቶም የመኖር መብት እናት መሆኗን ለታችኞቹ ማስቀናት ነው፡፡ እኛም እስከ ተወሰነ አመት ድረስ እየቀናን ነበር አይደል?
ወደ መሬት ስናወርደው.......
መሬት፤ በየዘመኑ፣ በየድንበሩ፣ በየሀገሩ የተማዘዘችው አፈ-ሙዝ፣ የፈበረከችው ንፍገት የተባለ ሰውን የማስራብ ፕሮጀክት እንዲሁም እርዳታ በሚል የተጫወተችው ብልጠት አስተዛዝቦ አወዛግቦ በጎሪጥ እያስተያያት ነው፡፡ የአሁኑም ፉክክር ገና ወደፊት ያስተዛዝባታል፡፡
Existentialism በሚለው መፅሐፍ ላይ የሰው ልጅ ህልው ሆኖ የመዝለቁ ጉዳይ፣ ዋስትና አልባ የሆነ ያበቃ፣ የተከተተ መሆኑን ያበክራል፡፡ ከዚህም በኋላ ሰው ሰውን ሆኖ ለመዝለቁ እንጃለት ተባለ፡፡ በተለይም የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ተመልክተው፣ የዚያን ሁሉ ሚሊዮን ሰዎች መሞትን፣ አያሌ ህፃናት ስደትን፣ አእላፍ እናቶች መደፈርን፣ ሌላው ቢቀር ሚሊዮኖች ገብተው ያልወጡበት የጀርመኑ “የአሽዊትዝ” ማጎሪያ ቤት ትልቅ መቃብር መሆንን--በጠቅላላው የሰው ልጅ ሰብዕና ዝቅጠትን የታዘቡቱ እውን ህይወት ይህ ነው? ይጠብቀናል የተባባልነው ፍቅራችን የት ገባ? መላእክቱስ ስራቸውን አቆሙ ይሆን? ፈጣሪስ ይህ ሁሉ ሲሆን ዝም ያለው ምን ብንበድለው ነው? የሚል ለምድር ለሰማይ የከበደ ጥያቄ አነሱ:: እነ ዣን ፖል ሳርተር  ወገባቸውን ይዘው ሞገቱ፡፡
የዚሁ ፍልስፍና መሪ ተደርጎ የሚታሰበው ዣን ፖል ሳርተር፤እ.ኤ.አ. በ1943 ለንባብ ያበቃው being and nothingness የተሰኘ ሥራው የኖቤል አሸናፊ መሆኑ ቢነገረውም፣ “ቀቅላችሁ ብሉት” በማለት ሽልማቱን ሳይቀበል ቀርቷል፡፡ የፈረንሳይ የፖለቲካ ፍልስፍና ቀያሹ ሳርት፣ ህይወቱ ባለፈች ጊዜ የዓለም ጋዜጦች “ፈረንሳይ ማስተዋሏን አጣች” (France has lost its conscience) የሚል ርዕሰ አንቀፅ አስነብበዋል፡፡ ሳርተርና የእድሜ ዘመን ወዳጁ de beauvior ከፈረንሳይ ነፃ መውጣትና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ የተነሱ ሊቀ ፈረንሳይ ናቸው፡፡ የዚህ አይነት ዳግም ውርደት፣ ዳግም ዝቅጠት፣ ዳግም ቅጥፈት፣ ዳግም ልሽቀት ተመልሶ እንዳይከሰት ለፈረንሳይ የደከሙ-- የቆዘሙ-- የደሙ-- የታመሙ ናቸው፡፡
በጦርነቱ አሸናፊ እስኪጠፋው ሁሉ ባዶ ነበር፡፡ የሞቱም ሞቱ፣ የገደሉትም ሞቱ:: ሁሉም እኩል ነበር፡፡ አለም ተባብሮ ያበደበት ጊዜ!!
ወደ መሬት ስናወርደው.....
የዚህ ሁሉ ከንቱነት መነሻው ‘ግላዊነት’ የሚባል ክብደት አልባ እብደት ነው:: ታላቁ ደራሲ ካምዩ በእናቱ እስፓኝ፣ በአባቱ ፈረንሳይ፣ የትውልድ ሀገሩ ደግሞ አልጄሪያ ነበር፡፡ ካምዩ በአልጄሪያ ሳለ የአልጀሪያ ነፃ አውጪዎች “ከዘራችን ውጪ ወደ ውጪ” የሚል ፈሊጥን አነሱ፡፡ “የሌሎች ዘሮች አብረውን መሆን ስጋታችን ነው” አሉ፡፡ የፈረንሳይ ዜግነት ያለውን ካምዩ ሂድልን ብለው ገፉት፡፡ ካምዩ ላለመውጣት ቢታገልም የሚወዱት ወዳጆቹ ግን ገንዘብ ሰጥተው ህይወቱን አተረፉት፡፡ ካምዩ ምን አለ “ምንም እንኳ እዚህ ተወልደን ብናድግና አልጄሪያን እንደ እናት ሀገር ብንወዳት ዳሩ አልጄሪያኑ በበኩላቸው አምርረው ዘርህ ፈረንሳይ ከሆነ ከሀገራችን ውጣልን ካሉ ህሊናችን እንድንወጣ ያስገድደናል?” ሲል አወዛጋቢ ጥያቄ በጋዜጣ ላይ ፃፈ፡፡ ክፋቱ ፈረንሳይም በናዚ ጦር ተከብባ ነበር፡፡ ያውም በሁለት ሳምንት ውስጥ፡፡ እነ ጀነራል ደጎል ለፈረንሳይ በጦሩ በኩል ተፈጠሩ፡፡ እነ ካምዩ ደግሞ በተውኔቱ በኩል ተወለዱ:: ያውም አብዘርድን (absurd) ይዘው ብቅ አሉ፡፡ የጦርነቱ ውጤትም መነሻም ግላዊነትን አይተው በሰው ህይወት ተስፋ የቆረጠ ዘውግ ፈጠሩ፡፡ “ለእውር ሰው ደማቅ ፋኖስን እንደ መስጠት” ነው ይሉታል፤ የህይወትን ትርጉም አልባነት ሲያስቀምጡ:: እብደትም ከበድ ሲል በጎ ነው፡፡ ቀላል እብደት ያገኘውን መፍጀት ነውና ወጉ:: ቀላሎች በቀላሉ ባበዱ ቁጥር የሞት ቀን ያረዝማሉ እና “ዓለም ከዚህ ጦርነት ያተረፈችው አለማትረፍን ነው” ተባለላት:: ይህ ግላዊነት ገና መዐት እንደሚያመጣ ብንገምትም፣ ይሄም የኛ ዘመን በበሽታው በኩል ደርሶታል፡፡
አሁንም ግን አሸናፊ የለውም፡፡ የዋሽንግተኑ አዛዥ ናዛዥ፣ ለዓለም የጤና ድርጅት፣ ብሬን አልሰጥም ብለው ግላዊነትን በይፋ አሳይተውናል፡፡ የጤና ድርጅቱ መሪም በየአቅጣጫው በነገር ተወጥረዋል፡፡ እሳቸውም፤
“ስንቱን መጠጥ ችዬ ዝናዬ ሲነገር
ከእንክርዳድም ብሶ አሰከረኝ ነገር፡፡”
--እያሉ ይመስላሉ፡፡ ብቻ ደጋፊም ተቃዋሚም በማያሻው በሰው ሞት ላይ መደገፍና መቃወም  በሚል መከፋፈል መጃጃል ነው እላለሁ፡፡
ስንጠቀልለው........
“ምድርና ሰማይ ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” እንዳለው ታላቁ መምህር፤ ቃላቸው ያላላፈ የታላላቅ ፈላስፎቻችን ሀሳብ ሊሞግተን ሊጎተጉተን የግድ ነው:: “ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል” እየተባልን አድገናል፤ ግላዊነት ልክ ካልሰጠነው ‘ግደላዊነትን’ ያመጣል:: አንድ ጣራ አለን፡፡ ሰማይ፡፡ አንድ ወለል አለን፡፡ ምድር፡፡
የኔ ሰማይ ብቻውን ይደምን አይባልም፡፡


Read 330 times