Friday, 01 May 2020 20:01

በኮሮና የተያዙ 133 ደርሰዋል ፤ተጨማሪ 2 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    አይኤምኤፍ ለኮሮና መከላከያ የ411 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ    
  ባለፉት 24 ሰዓታት ለ912 ሰዎች ምርመራ ተደርጎ፣ 2 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በፌስቡክ ገጻቸው ያስታወቁ ሲሆን ቫይረሱ የተገኘባቸው የ20 እና 25 አመት ወጣት ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለዋል።
አንደኛው ከፑንትላንድ የተመለሰና በጅግጅጋ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ ከኬንያ የተመለሰና በሞያሌ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገኝ መሆኑንም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 133 የደረሰ ሲሆን፥ 66 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ አገግመዋል ተብሏል፡፡ ከነዚህም መካከል 7ቱ አዲስ ያገገሙ መሆናቸውም ተገልጧል፡፡
በሌላ በኩል፤አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም፣ ለኢትዮጵያ የ411 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ያጸደቀ ሲሆን ድጋፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት መከታተሉን እንደቀጠለ በመግለፅም፤ እንደ አስፈላጊነቱ የፖሊሲ ምክርና የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል፡፡
 ኢትዮጵያ፤ በዚህ ቫይረስ ምክንያት ተጋላጭና ታዳጊ የሆኑ ሀገራት የብድር ክፍያ እርፍታ እንዲያገኙ ተቋሙ በፈረንጆቹ ሚያዚያ 13 ቀን 2020 ያሳለፈው ውሳኔም ተጠቃሚ እንደምትሆንም ታውቋል፡፡ የተቋሙ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ታኦ ዣንግ፣ ኢትዮጵያ  የግሉን ዘርፍ ሚና ለማሳደግ ከተቋሙ በወሰደችው የገንዘብ ድጋፍ፣ መልካም ለውጥ ማሳየቷን ተናግረዋል። የሀገሪቱ መንግስት ይህን ለውጥ ለማስቀጠል ፍላጎቱ ቢኖረውም፣ ኮቪድ-19 ግን በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትርጉም ያለው ተፅእኖ ማሳረፉን ጠቁመው፤በዚሁ መሰረትም አስቸኳይ የፋይናንስ ድጋፉ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡  
 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና የተቋሙን ማኔጂንግ ዳይሬክተር  ብቃት ለተሞላበት አመራራቸውና የኮቪድ-19ን ቀውስ ለመመከት በምናደርገው ጥረት፣ ከጎናችን በመቆማቸው ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል፤ በፌስቡክ ገጻቸው ባሳፈሩት መልዕክት። ድጋፉ ኢትዮጵያ በዘርፉ የሚያስፈልጋትን የገንዘብ መጠን መቶ በመቶ የሚሸፍን መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የማርና የበግ ስጦታ ለጤና ባለሙያዎች

የኮሮናቫይረስን በማከም ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሐኪሞችና የጤና ባለሞያዎች፣ ከከፋ ዞን የአገር ሽማግሌዎች፣ የማርና በግ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ የከፋ ዞን አስተዳደርና የአገር ሽማግሌዎች፣ በአዲስ አበባ ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ተገኝተው፣ የኮሮናቫይረስን በማከም ሥራ ለተጠመዱ ባለሞያዎች፣ ከ100 ሺ ብር በላይ የሚገመት የማርና በግ ስጦታ በዛሬው ዕለት ማበርከታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
የከፋ ዞን የአገር ሽማግሌዎች ተወካይ አቶ አድማሱ አቱሞ፣ ስጦታውን ሲያበረክቱ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ሐኪሞችና ባለሞያዎች ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ጊዜያቸውን ሳይሳሱ፣ ለህብረሰተባቸው እያዋሉ ነው ብለዋል። “በዚህ አበርክቷቸውም ፈጣሪ ከጎናቸው እንዲሆን እንመኛለን፤ ለሞራል እንዲሆናቸው የበረከት ምሳሌ የሆኑትን የማርና በግ ስጦታ አበርክተናል” ብለዋል። አቶ አድማሱ፡፡ ሐኪሞችና ባለሞያዎች ጥረታቸው ለፍሬ በቅቶ፣ ታማሚዎች አገግመው ለቤታቸው እንዲበቁም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ አግደው፣ ከከፋ ዞን አባቶች፣ ወጣቶችና የዞኑ አስተዳደር ስለተበረከተላቸው ስጦታና መልካም ምኞት አመስግነው፤ “ለእኛ ያላችሁን ፍቅርና አክብሮት፣ ራሳችሁን ከወረርሽኙ በመጠበቅ ልታሳዩን ይገባል” ብለዋል፡፡  
 

Read 1652 times