Saturday, 02 May 2020 11:30

በኮሮና እና በበረሃ አንበጣ ምክንያት የቀጣይ አመት የግብርና ምርት በ8 በመቶ ይቀንሳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   በበረሃ አንበጣ እና በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት የቀጣይ አመት አጠቃላይ የግብርና ምርት በ8 በመቶ እንደሚቀንስ የግብርና ሚኒስቴር ያስታወቀ ሲሆን የበረሃ አንበጣ መንጋ እስካሁን ከ3.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርና ምርት አውድሟል፡፡
በአጠቃላይ በ6 የሀገሪቱ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ስር በሚገኙ 170  ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ በ198ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተዘራ የገብስ፣ በቆሎ እና ስንዴ ምርት ማውደሙን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
እስካሁንም በአጠቃላይ ከ3.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት መውደሙንና መንግስት ጉዳቱን ለመቀነስ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር የገለፀ ሲሆን፤ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው ሀገሪቱ አሁን ከገጠሙአት ከባድ ፈተናዎች አንደኛው የበረሃ አንበጣ ነው ብለዋል፡፡
የበረሃ አንበጣው በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ለምግብ እጥረት ሊያጋልጥ እንደሚችል ቀደም ባለው ሣምንት የአለም የእርሻ ድርጅት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት በፈጠረው የአለም የግብይት ስርአት መቀዛቀዝ እና የእንቅስቃሴዎች መገታት የግብርና  ግብአቶችን ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተገለፀ ሲሆን በኮረና እና በአጠቃላይ በአንበጣ መንጋ ወረራ የ2013. ዓ.ም የኢትዮጵያ የግብርና ምርት በ8 በመቶ ሊቀንስ ይችላል ተብሏል፡፡
በአፋር፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና ድሬደዋ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባለው የበልግ አዝመራ በአንበጣ መንጋ በእጅጉ ይቸገራሉ ተብሏል::  

Read 11566 times