Saturday, 02 May 2020 11:52

“1ሺህ ያህል ዜጐች ቤታቸው ህገ-ወጥ ነው በሚል ፈርሷል” - አምነስቲ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  ኢሰመኮ የመስተዳድሩን እርምጃ ኮንኗል

              የአዲስ አበባ አስተዳደር ህገ ወጥ ናቸው ያላቸውን ቤቶች ማፍረሱን ተከትሎ፣ 1ሺህ ያህል ዜጐች መጠለያ አልባ እንደሆኑና ለኮሮና ቫይረስ ስጋት መጋለጣቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያስታወቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፤ የመስተዳድሩን እርምጃ በጽኑ ኮንኗል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጉዳዩን አጣርቻለሁ ብሎ ባወጣው ሪፖርት፤ በሳተላይት መረጃ ባደረገው ምልከታ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ “ህገ ወጥ ናቸው” በሚል መጋቢት 28 ቀን 2012 ዓ.ም 40 ያህል ቤቶች መፍረሳቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ቤት የፈረሰባቸው አብዛኞቹ ዜጐች በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የተሠማሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጐች እንደሆኑ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያትም ስራ ቆሞ ገቢያቸው የተቋረጠባቸውና በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት ሜዳ ላይ መውደቃቸው የበለጠ ለወረርሽኙ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል የሚል ስጋት እንዳለው ጠቁሟል፡፡
መንግስት በዚህ ወቅት ቤቶችን ማፍረሱ ተገቢ አይደለም ዜጐችን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ነው ያለው አምነስቲ፤ ህፃናትም በከፍተኛ ደረጃ የጉዳቱ ሠለባ እንደሆኑ አስታውቋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ፤ ቤቶቹ ከገበሬ መሬት ገዛን ባሉ ህገ ወጥ ሰዎች ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ የተሠሩ እንደሆኑና ከየካቲት መጀመሪያ አንስቶ ማፍረስ መጀመሩን መግለፁን አምነስቲ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
መደበኛ ያልሆነ የመሬት አያያዝና የቤት ግንባታ መስፋፋት አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙ ከተሞች ትልቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እየሆነ መምጣቱን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፤ ይሁን እንጂ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ቤተሰቦችን በሃይል ማስወጣትና መኖሪያቸውን አፍርሶ ሴቶችንና ህፃናትን ለአደጋ ማጋለጥ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲል ድርጊቱን ኮንኗል፡፡
መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሰዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው አስወጥቶ ቤት ከማፍረስ ድርጊቱ እንዲታቀብም አሳስቧል ተቋሙ፡፡  


Read 11161 times