Saturday, 02 May 2020 11:55

በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጡት 131 ሰዎች፣ 42ቱ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያልነበሩ ናቸው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(9 votes)

    • ቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታት የወረርሽኙን የስርጭት መጠን ይወስናሉ ተብሏል
       • በማህበረሰቡ ውስጥ የበሽታው ስርጭት መኖሩን ለማረጋገጥ ጥናት እየተደረገ ነው
       • ስለ በሽታው ስርጭት የወደፊት ሁኔታ ለማወቅ የሚደረግ ጥናት አለመኖሩ ተገልጿል
             
          እስካሁን በአገራችን የኮረና ቫይረስ ምርመራ ተደርጐላቸው ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጠው 131 ሰዎች ውስጥ 42ቱ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያልነበሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የዓለም ጤና ድርጅት ደንብ ተወካይ ዶ/ር ፈይሳ ረጋሳ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ እስከ አለፈው ሐሙስ ድረስ ለ17824 ሰዎች የኮቪድ - 19 ምርመራ መደረጉን ጠቁመው፤ ከእነዚህም መካከል 131 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ ከውጪ አገር የሚገቡ ሰዎች የግዴታ ማቆያ (ማንዳቶሪ ኳራንታይን) ውስጥ እንዲገቡ የሚያስገደድው መመሪያ ከመጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም አንስቶ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን አስታውሰው መንገደኞቹ የቆይታ ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ህብረተሰቡ ከመቀላቀላቸው በፊት ምርመራ እንደሚደረግላቸውና አብዛኛዎቹ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙትም በዚህ የመጨረሻ ምርመራ ወቅት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከውጪ አገር ገብተው በግዴታ ማቆያ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል እስካለፈው ረቡዕ 5577 ሰዎች የቆይታ ጊዜያቸውን አጠናቀውና ምርመራ ተደርጐላቸው ወደ ህብረተሰቡ የተቀላቀሉ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በዓለማቀፍ ሆቴሎች 450 ሰዎች እንዲሁም መንግስት ባዘጋጃቸው የለይቶ ማቆያ ቦታዎች 2539 በድምሩ 2989 ሰዎች በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ላይ እንደሚገኙ ዶ/ር ፈይሳ ተናግረዋል:: ከውጪ አገር ከመጡ ሰዎች ጋር ንክኪ አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን ከማህበረሰቡ ለይቶ በማቆየት ምርመራ በማካሄዱ ሥራም እስከ አሁን 1219 የሚሆኑ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ክትትላቸውን ጨርሰውና ምርመራ ተደርጐላቸው፣ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለዋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም 590 የሚሆኑት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ዶ/ር ፈይሳ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች፣ በመንግስት ሙሉ ወጪ የሚቆዩ በመሆናቸው ሁኔታውን ከባድ ያደርገዋል ያሉት ዶ/ር ፈይሳ፤ ሆኖም የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠርና በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች በሽታውን ለሌሎች እንዳያሰራጩ ብቸኛ መንገድ በመሆኑ እየተገበርነው እንገኛለን ብለዋል፡፡
የበሽታው የስርጭት መጠን አነስተኛ ነው ብሎ መደምደም እንደማይቻል የገለፁት ዶ/ር ፈይሳ፤ ወደዚህ ዓይነቱ ድምዳሜ ለመድረስ የምርመራ መጠናችንን ማስፋትና በርከት ያለ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች መርምሮ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መጪዎቹ ጊዜያትም የህብረተሰቡን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቁ ናቸው ያሉት ዶ/ር ፈይሳ፤ ቫይረሱ በባህርይው ሞቃት የአየር ሁኔታ የማይስማማውና በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ የበለጠ የስርጭት መጠኑ የሚጨምር በመሆኑ በመጪዎቹ ጊዜያት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የህብረተሰብ ጤና ባለሙያውና የኮቪድ 19 በሽታ መከላከል ኮሚቴ ውስጥ በመስራት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ በበኩላቸው፤ የኮረና ቫይረስ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ባህርይው ገና በቅጡ ያልታወቀና የተወሳሰበ መሆኑ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡
ቫይረሱ በአገራችን ከተከሰተ በኋላ ባሉት 67 ቀናት ውስጥ የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል ቅድመ - ግምት ተቀምጦ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ያለው የስርጭት መጠን ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት ዶ/ር ሰለሞን፤ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ፈጽሞ ሊያዘናጋን አይገባም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡
 ምክንያቱም ሲገልፁ፤ የመረመርናቸው ሰዎች ቁጥር ሲጨምር በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥርም በዛው መጠን ሊጨምር ይችላል፡፡ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ማነስ የሚያመለክተው የመመርመር አቅማችን አነስተኛ መሆኑን ነው፤ ስለዚህም የምርመራ መጠናችንን መጨመር፣ ጥንቃቄያችንን የበለጠ ማጠናከርና በአለም ጤና ድርጅት የሚወጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ የበሽታውን የስርጭት መጠን ለመቆጣጠር ብቸኞቹ መንገዶች ናቸው ብለዋል፡፡
ቀጣዮቹ አራት ሳምንታት እጅግ ወሳኝ ጊዜያት መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ሰለሞን፤ የምርመራ መጠናችንን ከጨመርን፣ ጥንቃቄያችንን የበለጠ ካጠናከርንና የሚሰጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ካደረግንና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ቀደመው ሰላማዊ ህይወታችን እንመለሳለን የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ጥንቃቄያችንን የበለጠ ከጨመርንና ራሳችንን ለበሽታው ተጋላጭ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች ከተከላከልን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
በቫይረሱ ተያዙ እየተባለ የሚገለፁት ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው በሚል መዘናጋት ውስጥ መግባት ከፍተኛ ዋጋ  ሊያስከፍል እንደሚችልም ዶ/ር ሰለሞን አስጠንቅቀዋል:: በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ የሚታሰበው ቀደም ሲሉ በቫይረሱ ተይዞ መዳን አለመዳናችን የሚታወቅበት ምርመራ (አንቲ ቦዲ) ምርመራና በማህበረሰቡ ውስጥ በሽታው መግባት አለመግባቱን ለማረጋገጥ የሚያስችለው ኮሙዩኒቲ ሳምፕል ምርመራ የተሻለ መረጃ ይሰጣል ተብሎ እንደሚታሰብም ዶ/ር ሰለሞን አስረድተዋል::
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመው፤ መጪውን ሁኔታ የሚጠቁሙ የትንበያ ጥናቶች ግን አለመሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ 1408 ሰዎች ተመርምረው አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው የተገኘ ሲሆን ይህም እስካሁን ከተደረጉት ምርመራም ከፍተኛው ቁጥር እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡  


Read 11057 times