Print this page
Saturday, 02 May 2020 12:00

በኮሮና ወረርሽኝ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

  • ከ23ሺ በላይ የስፖርት ውድድሮች ተሰርዘዋል
      • 32ኛውን ኦሎምፒያድ በድጋሚ ማሸጋሸግ አይቻልም፤ መሰረዝ እንጅ
      • ከውድድሮች የሚገኝ ከ62 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታጥቷል
      • ትልልቅ የስፖርትሐ ውድድሮች ለመንፈቅና ለዓመት ተሸጋሽገዋል
      • የአውሮፓ ሊጎች መጨረሻቸውን ለመወሰን 25 ቀናት ይቀራቸዋል
      • የዓለም አትሌቲክስ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በአዲስ መዋቅር ውስጥ ይገባል
      • ጆስ ሄርማንስ ማራቶኖች ከተሞችን በማዘጋት እንዲካሄዱ ጠይቀዋል
      • ኪፕቾጌና ቀነኒሳ የቡድን ልምምድና ውድድር ናፍቋቸዋል
      • በአፍሪካ ስፖርት ላይ አደጋ ተጋርጧል፤ በተለይ በሴቶች እግር ኳስ
      • አሜሪካ የስፖርት ውድድሮችን ያለተመልካች ለመቀጠል አስባለች
                

            ከ23ሺ በላይ የስፖርት ውድድሮች ተሰርዘዋል
ዓለምአቀፍ ተቋም በሰራው ጥናታዊ ትንታኔ በኮሮና ወረርሽኝ  ምክንያት በመላው ዓለም ከ23ሺ በላይ የስፖርት ውድድሮች ተሰርዘዋል፡፡ ውድድሮቹ የተሰረዙት በተመደበላቸው መርሃ ግብር ሊካሄዱ ባለመቻላቸው፤ የውድድር ስፍራዎች በመዘጋታቸው፤ በውድድር ስፍራዎች ተመልካቾች እንዳይገቡ በመከልከላቸውና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በዓለም ዙርያ በተለያዩ አገራትና በተለያዩ ስፖርቶች ታቅደው ከነበሩ የስፖርት ውድድሮች 53% ያህሉን (ከ24,424  በላይ) የውድድር ዘመኑ ከማለቁ በፊት ማካሄድ እንደሚቻል በሪፖርቱ ተገምቷል፡፡  ከ23,379 በላይ ውድድሮችና ሌሎች መርሃ ግብሮች (47% ) ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸው አይቀርም፡፡
ከ62 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታጥቷል
በ2020 እኤአ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚካሄዱ የስፖርት ውድድሮች ከ135 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ይጠበቅ ነበር፡፡ ያለፉትን 3 ወራት ዓለምን ባመሰው የኮሮና ወረረሽኝ ግን ውድድሮች  ላልተወሰነ ጊዜ በመተላለፋቸው፤ ሙሉ በሙሉ  በመሠረዛቸው  ከ62 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታጥቷል፡፡ ስለሆነም በ2020 እ.ኤ.አ በዓለም ዙርያ በተለያዩ ስፖርቶች ከሚካሄዱ ውድድሮች የሚገኘው ገቢ ከ71.17 ቢሊዮን ዶላር በታች ይሆናል፡፡ በ2019 እ.ኤ.አ  ላይ የስፖርት ውድድሮች በመላው ዓለም ከ129 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝተዋል፡፡
32ኛውን ኦሎምፒያድ በድጋሚ ማሸጋሸግ አይቻልም፤ መሰረዝ እንጅ
የኮሮናን ወረርሽኝ በሚቀጥሉት 6 ወራት በመላው ዓለም ለመቆጣጠር ካልተቻለ በ12 ወራት የተሸጋሸገውን 32ኛው ኦሎምፒያድን ሊያሰርዘው እንደሚችል የጃፓን ኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት  ሰሞኑን ተናግረዋል:: 32ኛውን ኦሎምፒያድ በድጋሚ ማሸጋሸግ አይቻልም፤ መሰረዝ እንጅ የሚሉት  የቶኪዮ 2020 አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዮሺሮ ሞሪ፤ በ1 ዓመት የተራዘመውን 32ኛው ኦሎምፒያድ እንደታሰበው ማካሄድ ከተቻለ ዓለም የኮሮና ወረርሽኝን በመወጋት ስኬታማ መሆኗን የሚያረጋግጥ ብለዋል፡፡
በተያያዘ ቶኪዮ የምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ በ1 ዓመት መሸጋሸጉ  ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራትን ወደ በጀት እጥረት እና ኪሳራ ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ በኦሎምፒኩ ላይ የሚካሄዱ ስፖርቶችን የሚወክሉ 28 ዓለም አቀፍ የስፖርት ፌደሬሽኖች እና ማህበራት ከዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ ስለማይለቀቅ ነው፡፡ በተለይ በ32ኛው ኦሎምፒያድ እንደአዲስ ይጀመራሉ የተባሉ የኦሎምፒክ ስፖርቶች ተጎጂዎች ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሪዮ ዲጄኔሮ ባካሄደችው 31ኛው ኦሎምፒያድ ለዓለም አቀፍ የስፖርት ፌደሬሽኖች ከ520 ሚሊዮን ዶላር በላይ አካፋፍሎ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ ኦሎምፒክ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ፌደሬሽኖች እና ማህበራት መካከል አትሌቲክስ፤ ውሃ ዋና እና ጅምናስቲክ እያንዳንዳቸው እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር፤ ብስክሌት፤ ቅርጫት ኳስ መረብ ኳስ፤ እግር ኳስ እና ቴኒስ እያንዳንዳቸው 25 ሚሊዮን ዶላር፤ ቦክስ፤ ጀልባ ቀዘፋ፤ ቀስት፤ ጁዶ፤ ጠረጴዛ ቴኒስ እያንዳንዳቸው 17 ሚሊዮን ዶላር፤ ሴይሊንግ፤ ኢላማ ተኩስ እና ሻሞላ እያንዳንዳቸው 12 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ራግቢ፤ ጎልፍና ፔንታቴሎን እያንዳንዳቸው 7 ሚሊዮን ዶላር  ከዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በድጎማ ያገኙ ነበር፡፡
ትልልቅ የስፖርት ውድድሮች ለመንፈቅና ለዓመት  ተሸጋሽገዋል
የኮሮና  ወረርሽኝ የዓለም ስፖርትን ካቃወሰ 60 ቀናት አልፈዋል፡፡ ብዙዎቹ የዓለማችን ትልልቅ የስፖርት ውድድሮች መርሃግብራቸውን  ከ8 እስከ 18 ወራት አሸጋሽገዋል፡፡  
ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴና ከጃፓን መንግስት ጋር በትብብር የሚያዘጋጀው 32ኛው ኦሎምፒያድ፤ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሚካሄደው የ2020 አውሮፓ ዋንጫና በደቡብ አሜሪካ አገራት መካከል የሚደረገው ኮፓ አሜሪካ በ12 ወራት ተራዝመዋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ በተለያዩ አገራት የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ከ4 እስከ 6 ወራት እንዲራዘሙ ያደረገ ሲሆን፤ የኦሎምፒክ ሚኒማን ለማሟላት የሚካሄዱ   ውድድሮችን ቢያንስ ለ8 ወራት አዘግይቷቸዋል፡፡
ከተቋረጡ 2 ወራት ያለፋቸው የአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጐች በሚቀጥሉት 25 ቀናት ካልተጀመሩ ደግሞ የጊዜ መሸጋሸግ ሳይሆን ጭራሽኑ የመሰረዝ ዕጣ ይገጥማቸዋል፡፡
የአውሮፓ ሊጎች መጨረሻቸውን ለመወሰን 25 ቀናት ይቀራቸዋል
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ባወጣው ማሳሰቢያ በየአገራቱ የሚካሄዱ የእግር ኳስ ሊጎች እስከ ሜይ 25 ድረስ የውድድር ዘመናቸውን ለመጨረስ ወይንም ለማቋረጥ ውሳኔያቸውን እንዲያሳውቁ ጠይቋል::
የማህበሩ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሴፈሪን ለአባል አገራቱ 55 ፌደሬሽኖች በፃፉት ደብዳቤ ሊጋቸውን ለማቋረጥ ለመሰረዝ የሚወስኑት በቂ ምክንያት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከአሳማኝ የውጤት ምዘና ጋር በቀጣይ የውድድር ዘመን በአህጉራዊ ውድድሮች የሚያሳትፏቸውን ክለቦች እንዲገልፁም ተጠይቀዋል፡፡  
የአውሮፓ ሊጎች የውድድር ዘመናቸውን አጨራረስ በተመለከተ ውሳኔያቸውን ለማሳወቅ በተሰጠው  የግዜ ገደብ 25 ቀናት ቀርተዋል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በአዲስ መዋቅር ውስጥ ይገባል
በዓለም አትሌቲክስ በ2020 እኤአ ለማካሄድ ታስበው ኮሮና ወረርሽኝ በተለይ ያስተጓጎላቸው ዋና ውድድሮች  በቻይና ሊካሄድ የነበረው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በታላላቅ የዓለማችን ከተሞች ተዟዙሮ የሚካሄደው ዳይመንድ ሊግ ናቸው፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ 20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በ2021 እኤአ ላይ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው የአሜሪካዋ ዩጂን ከተማ መስተንግዶዋን ወደ 2022 እኤአ አሸጋሽጋዋለች:: ዋንኛው ምክያት የሆነው የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክና ሌሎች ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ከመተላለፋቸው ጋር ተያይዞ ነው:: የዓለም አትሌቲክስ ጃፓን የምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ እንዲሸጋሸግ በጠንካራ አቋም ይዞ ተፅእኖ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ሴባስቲያን ኮው  የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በ6 ሳምንታት ውስጥ ሲካሄድ የስታድዮም ተመልካቾችና የተሟላ ስርጭት ስለሚያስፈልገው የግዜ ሽግሽጉ የሚጠበቅ ነው ብለዋል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ  የቆዩት ሴባስቲያን ኮው የአትሌቲስ ስፖርት ህልውና ከውድድሮች ጋር የተያያዘ መሆኑ አሳስቧቸዋል፡፡ ራነርስ ወርልድ ለተባለ መፅሄት ሴባስቲያ ኮው እንደተናገሩት ዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚቀጥሉት 4 ወራት ተጀምረው አትሌቶች ወደ መደበኛ የዝግጅት ምዕራፋቸው መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ በተፈጠሩ የውድድር መርሃግበሮች መሸጋሸግ እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በሚቀጥሉት 5 የውድድር ዘመናት በአዲስ መዋቅር ውስጥ መግባቱ ግድ ይሆናል:: በ2021 እኤአ በጃፓን 32ኛው ኦሎምፒያድና ፓራሎምፒክ፤ በ2022 እኤአ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዩጂን አሜሪካ ፤ በ2023 እኤአ 21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በቡዳፔስት ሃንጋሪ፤ በ2024 እኤአ 33ኛው ኦሎምፒያድ በፓሪስ ፈረንሳይ በተከታታይ ለማካሄድ አዲስ መዋቅር የዓለም ስፖርት ባለሙያዎች መቀየስ ይኖርባቸዋል፡፡
በዓለም አትሌቲክስ  ባለፉት ጥቂት ወራት ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ የሚያስገኙ ውድድሮች በመቋረጣቸው በአትሌቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ተቋም በውድድሮች መሰረዝ ችግር ላይ የወደቁ አትሌቶችን በፋይናንስ ድጋፍ ሞራላቸውን ለመጠበቅ መወሱንም አስታውቋል፡፡  በተለይ በዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ የሚገኝባቸው ትልልቅ ማራቶኖች እና የጎዳና ላይ ሩጫዎች አለማካሄዳቸው በአትሌቶች ብቻ ሳይሆን በውድድር አዘጋጆቹም ላይ ኪሣራ ያስከትላሉ፡፡
የለንደን፣ ቶኪዮ፣ ቺካጐ፣ ቦስተን ማራቶኖች ከማይካሄዱት ይጠቀሳሉ፡፡ በዓለም ትልልቅ የትራክ፣ የጐዳና ላይ እና የአገር አቋራጭ ውድድሮች በአንድ የውድድር ዘመን እስከ 25 ሚሊዮን ደላር የሽልማት ገንዘብ ይቀርባል፣ በማራቶን፣ የጐዳና ላይ ሩጫዎች ከ21.8 ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ በትራክ ውድድሮች ከ1.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲሁም በአገር አቋራጭ ውድድሮች እስከ 71ሺ ዶላር ነው፡፡
ጆስ ሄርማንስ ማራቶኖችን ከተሞችን በማዘጋት እንዲካሄድ ጠይቀዋል
የዓለምን አትሌቲክስ በተለይ በማራቶንና ጎዳና ሩጫዎች ዓመታዊ ወቅቱን ጠብቆ ውድድሮችን ለመመለስ ከውድድር አዘጋጆች ማናጀሮች፤ አትሌቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት አዳዲስ ፈጠራዎች ይጠበቃል በማለት እውቁ የስፖርት ማናጀር ጆስ ሄርማንስ ተናግረዋል፡፡ በየውድድር ዓመቱ በመስከረም ተጀምረው ለ3 እና ለ4 ወራት በመላው ዓለም የሚካሄዱ ማራቶኖች፤ ግማሽ ማራቶኖች እና ሌሎች የጎዳና ሩጫዎች ያሉ ሲሆን በተስተካከለ ሁኔታ በ2020 እኤአ የውድድር ዘመን መቀጠል የሚቻለው በሚቀጥሉት 4 ወራት ወረርሽኙን መቆጣጠር ከተቻለ ነው፡፡
በጎዳና ላይ ሩጫዎች ከ10ሺ እስከ 40ሺ ተሳታፊዎች መኖራቸውን የጠቀሱት የአትሌቲክስ ባለሙያው፤ ውድድሮቹን መልሶ ለመቀጠል አዳዲስ ፈጠራዎች ወሳኝ ናቸው፡፡ የማራቶን ውድድሮችን አሁን ባለው ሁኔታ በየአገራቱ አትሌቶች ለማካሄድ ይቻላል የሚሉት ሆላንዳዊው ጆስ ሄርማንስ፤ ከመላው ዓለም እውቅ አትሌቶችን በመጋበዝ መስራቱ እንደሚያስፈልግና ትልልቅ የማራቶን ውድድሮችን ለማድመቅ አዘጋጆቻቸው ሙሉ ከተሞቻቸውን በማዘጋት መስራትን እንዲያስቡ ጠይቀዋል፡፡
ጆስ ሄርማንስ በተጨማሪ ምክራቸው አትሌቶች በያሉበት ሆነው ወቅታዊ የአካል ብቃታቸው እና ዝግጅታቸው እንዳይዛባ ቀለል ያሉ ልምምዶችን በየቤቶቻቸው እንዲሰሩም መክረዋል፡፡
ኪፕቾጌና ቀነኒሳ የቡድን ልምምድና ውድድር ናፍቋቸዋል
በዓለም አትሌቲክስ በኮሮና ወረርሽኝ  ከተሰረዙ የማራቶን ውድድሮች ዋንኛው ከሳምንት በፊት ሊካሄድ እቅድ የነበረው የለንደን ማራቶን ነው፡፡
ዘንድሮ በለንደን  የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኪፕቾጌና ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት የያዘው አትሌት ቀነኒሳ መገናኘታቸው ከፍተኛ ትኩረት የሳበ ነበር:: የለንደን ማራቶን አዘጋጆች ውድድራቸውን በ6 ወራት ማሸጋሸጋቸውን ሰሞኑን ያስታወቁ ሲሆን  ቀነኒሳ እና ኪፕቾጌ የቡድን ልምምድና ውድድር ቢናፍቃቸውም መደበኛ የልምምድ መርሃ ግብሮቻቸውን ለየብቻቸው በመስራት መቀጠላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
‹‹የስፖርት ልምምድን ለብቻ መስራት ጠንካራ አያደርግም፡፡ ከአጋር አትሌቶችና ከመላው ቡድን ጋር መስራት ሙሉ አቅምን ለማወቅ ያስችላል፡፡
ለ15 ዓመታት የለመድኩትን የቡድን ልምምድ ማጣት ቀላል አይደለም፡፡›› በማለት የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኪፕቾጌ የልምምድ መርሃግብሩን መቀየር አማርሮታል::  አትሌት ቀነኒሳ በበኩሉ ‹‹በወቅታዊው ሁኔታ  በቡድን መሮጥ ስለማይቻል እንጅ ብቻህን መሮጥ ብዙም ደስ የሚል ነገር አይደለም::
ያለኝን ወቅታዊ ብቃት ለመለካት ከማንም ሳልወዳድር የሚቀል አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ቤት ቁጭ ብዬ ነው የማሳልፈው፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡
በአፍሪካ ስፖርት ላይ አደጋ ተጋርጧል፤ በተለይ በሴቶች እግር ኳስ
የኮሮና  ወረርሽኝ ባለፉት 2 ወራት በአፍሪካ ስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ መፍጠሩ ቢስተዋልም አህጉሪቱ ወደ ስፖርት ውድድሮች ለመመለስ በይፋ ግልፅ የማይደረግባት ሆኗል፡፡  
በየአገራቱ የሚካሄዱ የሊግ ውድድሮች ከመቋረጣቸው ባሻገር በርካታዎቹ የሊጉን አስተዳደር ወደ ቀውስ፤ ክለቦችን ወደ መፍረስ አደጋ ውስጥ እየከተቱ መሆናቸውን አንዳንድ ዘገባዎች እያወሱ ናቸው:: በአህጉራዊ ደረጃ ከሚካሄዱት ከፍተኛ አደጋ የተጋረጠበት የሴቶች እግር ኳስ ነው፡፡  
የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ አለማካሄዱ የመጀመርያው ሲሆን፤ ሀ-12 እ ሀ-20 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች መዘጋታቸውም በአፍሪካ በደካማ በጀት የሚንቀሳቀሰውን የሴቶች እግር ኳስ ቀውስ ውስጥ ይከተዋል፡፡ በተጨማሪ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን  የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ እንዲሁም የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎችን እንዳቆማቸው ሲሆን መልሰው ስለሚቀጥሉበት ሁኔታ ምንም መረጃ እየወጣ አይደለም፡፡
አሜሪካ የስፖርት ውድድሮችን ያለተመልካች ለመቀጠል አስባለች
በአሜሪካ የስፖርት ኢንዱስትሪ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚንቀሳቀስባቸው እና ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙት የቅርጫት ኳስ፤ የአሜሪካ ፉትቦል፤ የእግር ኳስ እና ሌሎች ውድድሮችን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ያለተመልካች በማካሄድ የውድድር ዘመኑን ለመጨረስ እየታቀደ ነው፡፡ በአሜሪካ ሁሉም አይነት የስፖርት ውድድሮች ያለፉትን ሁለት ወራት እንደተቋረጡ ናቸው፡፡


Read 10906 times