Print this page
Saturday, 02 May 2020 12:20

የኮሮና ወረርሽኝ፣ የህግ ተጠያቂነትና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

• በሽታን መደበቅና ሆን ብሎ ወደ ሌሎች ማስተላለፍ እስከ 20 ዓመት  እስር ሊያስቀጣ ይችላል
  • ከለይቶ ማቆያ ማምለጥና እንዲያመልጡ መተባበርስ?
  • ደረጃቸውን ያልጠበቁ ሳኒታይዘሮች ያቀረቡ በህግ መጠየቅ ነበረባቸው
  • ያለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወሰዱ እርምጃዎች ትክክል አይደሉም

በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ይህን ወረርሽኝ ከሌሎች በሽታዎች የሚለየው የስርጭት ፍጥነቱና መድሃኒትም ሆነ ክትባት ያልተገኘለት መሆኑ ነው፡፡ ሌላው መለያው ደግሞ የግለሰብ ሳይሆን የማህበረሰብ በሽታ መሆኑ ነው፡፡ የአንድ ግለሰብ በቫይረሱ መያዝ ቤተሰብን ጨምሮ ለሌሎች ይተርፋል፡፡ ለዚህ ነው መላው ዓለም በህግ እንዲሁም በፖሊስና ወታደር ጭምር የወረርሽኙን ሥርጭት ለመግታት እየሞከረ ያለው፡፡ ለመሆኑ በሽታውን ሆን ብሎ ወደ ሌሎች ማስተላለፍ የህግ ተጠያቂነቱ ምን ያህል ነው? በሽታን ከሀኪም መደበቅስ ያስጠይቅ ይሆን? ከለይቶ ማቆያ ማምለጥ እንደ ወንጀል ይቆጠራልን? የወረርሽኙን ሥርጭት ለመቆጣጠር የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምን አግባብ ነው መተርጐም የሚገባው? የአዲስ አድማሱ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ አንጋፋውን የህግ ባለሙያ አቶ ደበበ ሃብተ ገብርኤልን በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡


    በሽታን መደበቅን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ምን ይላል?
በኛ የወንጀል ህግ ውስጥ ይሄን በተመለከተ የተቀመጡ ግልጽ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በተለይ የወንጀል ህግ ቁጥር 514፣ ተላላፊ በሽታ ማሰራጨትን አስመልክቶ ግልጽ ድንጋጌ ያስቀምጣል፡፡ ማንም ሰው አስቦ፣ ሆን ብሎ በሰው ላይ ተላላፊ በሽታ ያሠራጨ እንደሆነ፣ ከ10 አመት እስከ ሞት ድረስ እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል፡፡ በሽታው እንዳለበት እያወቀ ለሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርግ ቀርቶ በሽታውን ያስተላለፈ ከሆነ፣ እስከ 10 አመት እስር ሊያስቀጣው ይችላል፡፡  በሽታውን በጥላቻ በቂም በቀል፣ በክፋት ሆን ብሎ የሚያሠራጭ ከሆነ ወይም ይሄ ሃሳብ ባይኖረው እንኳ ከባድ ጉዳትና ሞት የሚያስከትል በሽታ ከሆነና ይሄን እያወቀ ያሠራጨ ከሆነ፣ ከ20 አመት እስከ እድሜ ልክ እስር ወይም በሞት ሊቀጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ተላላፊ ተብሎ የተሰየመን በሽታ ማስተላለፍ በራሱ እስከ 20 አመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም ሁኔታው ከባድ ከሆነ እድሜ ልክ እንዲሁም በሞት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡ በሽታውን ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርግ በቸልታ ያስተላለፈ ከሆነ ደግሞ እስከ 5 አመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡ ከዚህ በተረፈ ደግሞ በህግ የተቀመጡ በሽታን የመከላከል እርምጃዎችን ስለ መጣስ ይደነግጋል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስኪታወጅ ድረስ በራሱ የበሽታው መተላለፊያ መንገዶችና መከላከያው በግልጽ እየታወቀ፣ ያንን ጥሶ የሚገኝ ሰው እስከ 3 እና 5 አመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡ ይህ በቸልተኝነት ከተደረገ እስከ 3 አመት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡
ለህክምና ባለሙያዎች የተሳሳተ መረጃ መስጠትስ?
ይሄን በሚመለከት ሌላ ህግ አለ፡፡ የመድሃኒት፣ የምግብና የጤና እንክብካቤ አዋጅ አለ፡፡ እዚያ አዋጅ ላይ ለይቶ ስለ ማቆየት የተቀመጡ ህጐች አሉ፡፡ አሁን ማንኛውም ውጭ ሀገር የሄደ ሰው በለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባት እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ ይሄን አለማድረግ ለጤና አጠባበቅ የተቀመጡ ህጐችን መጣስ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ ከኮሮና ጋር በተያያዘ አሁን መንግስት ያወጣቸው የጥንቃቄ ህጐች አሉ፡፡ ይሄን መጣስ የህግ ተጠያቂነት ያስከትላል፡፡ ከለይቶ ማቆያ የወጣ፣ እንዲወጣ ያመቻቹ ወይም ተገቢውን ጥበቃ ያላደረጉ በህግ ይጠየቃሉ፡፡ ሰውየው በሽታው ባይኖርበትም ለጥንቃቄ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ባለመፈፀሙ የህግ ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ ለሃኪሞች የተሳሳተ መረጃ መስጠትም ከዚሁ የሚመነጭ የህግ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ በሽታው ያለበት ሆኖ ከደበቀና የተሳሳተ መረጃ የሰጠ ከሆነ ደግሞ ተጠያቂነቱ ይብሳል፡፡ ከ10 አመት እስከ ሞት በሚያስቀጡ አንቀፆች ሊከሰስ ይችላል፡፡  
ማነው እንደዚህ አይነት ተጠያቂዎችን ለህግ የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት?
 በዚህ የወንጀል ህግ መሠረት፣ ተጠርጣሪን የማሳወቅ ግዴታ፣ ጉዳዩን በሚያውቁት ላይ ያስቀምጣል፡፡ አንድ ሰው ህመም ያለበት መሆኑን እያወቁ ከአጠገቡ ያሉ ሰዎች ወይም የቤተሰብ አባላት ዝም ካሉ፣ እነሱም የወንጀል ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ጉዳዩ እንደ ሌሎች ወንጀሎች በቸልታ የሚታይ አይሆንም፡፡
ከተላላፊ በሽታ ጋር ተያይዞ አንድ ሰው በሽታው እንዳለበት እያወቁ፣ ለህግ አለማመልከት በራሱ በእስራት ያስቀጣል፡፡ ለምሣሌ ትራንስፖርት ላይ በሽታው ያለበትን ሰው ደብቆ ይዞ መሄድ ወይም በግልጽ የተቀመጡ የበሽታው ምልክቶች ያለበትን ሰው ለምሣሌ የኮሮና ምልክቶች፡- ማሳል፣ ትኩሳት፣ ማስነጠስ የመሳሰሉት እየታዩ፣ በቸልታ ዝም ብሎ ይዞ መሄድ የህግ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ እንደውም ህጉ የሚለው፤ ቀጣይ ፌርማታ ላይ አውርዶ ለፖሊስ ወስዶ ማስረከብ አለበት ነው የሚለው፡፡ ህጉ ከገንዘብ እስከ እስራት በየደረጃው ቅጣቶችን ያስቀምጣል፡፡
የወረርሽኞች መከሰትን ተከትሎ የሸቀጦችን ዋጋ ማናርን በተመለከተስ ህጉ ምን ይላል?
በእንዲህ ያለ ወቅት ንግድን ዝም ብሎ ማቆም፣ ዋጋ በድንገት መጨመር የህግ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው አፈጻጸም ህጉ በሚገባ እየተተገበረ አለመሆኑን እያስተዋልን ነው፡፡ እንዲሁ “ይሄን ያህል ነጋዴዎች ሱቃቸው ታሸገ” ሲባል ነው እንጂ በፍ/ቤት ተቀጡ የሚለውን እየሰማን አይደለም፡፡
ለምሣሌ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ሳኒታይዘሮች ናቸው ተብለው የተወሰኑ ምርቶችን ህብረተሰቡ እንዳይጠቀም በሚዲያ ተነግሮ ነበር፡፡ እነዚህ ሳኒታይዘሮችን ግን ህዝቡ አስቀድሞ በሽታ ይከላከሉልኛል በሚል እምነት ሲጠቀምባቸው ነበር፡፡ ህዝቡ ከተጠቀመባቸውና ከተጭበረበረ በኋላ ነው ትክክለኛ አይደለም የተባሉት፡፡ ነገር ግን ይሄን ወንጀል የፈፀሙ አካላት ለህግ አልቀረቡም፡፡ እንዲያውም የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች አሟልተው ስራቸውን መቀጠል እንደሚችሉ ነው የተነገረው፡፡ ይሄ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ አስቀድሞ ተጭበርብሮ በሽታውን ይከላከሉልኛል በሚል ምርቶቹን ገዝቶ የከሠረው፣ ራሱን ከበሽታው መከላከል ያልቻለውስ ፍትህ የቱ ጋ ነው የሚያገኘው ታዲያ? ድርጊቱ ወንጀል መሆኑ በወንጀለኛ ህጉ ተቀምጧል፡፡ በጽኑ እስራትም የሚያስቀጣ ነው፡፡ ስለዚህ ምርቶቹ ስህተቶች ናቸው፤ ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም ያለው አካል በመግለጫ ብቻ ማቆም አልነበረበትም፤ ጉዳዩን ወደ ህግ አካልም መውሰድ ነበረበት፡፡
በሌላ በኩል ፖሊስ እንደ ማንኛውም ዜጋ ወሬውን ሠምቷል፡፡ ፖሊስም ጠቅላይ አቃቤ ህግም ሰምተዋል፡፡ የግድ እነሱ ጋ ክስ እስኪመጣ መጠበቅ አይገባቸውም፡፡ በራሳቸው ጉዳዩን መርምረው ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው፡፡ ሰዎች ገንዘባቸውን አውጥተው ገዝተው፣ ከበሽታ ይጠብቀናል ብለው ሲጠቀሙበት የነበረ ነገር፣ ከበሽታው እንዳልጠበቃቸው በግልጽ ይታወቃል፡፡ ታዲያ ይሄ እንዴት ዝም ይባላል?  የህግ አስፈፃሚው አካል እነዚህን ተከታትሎ ህግ የማስፈፀም ድርሻውን መወጣት አለበት፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደ ህግ ባለሙያ እንዴት ይገመግሙታል?
ይሄኛው አዋጅ ከበሽታው ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል “እንዲህ አድርጉ አታደርጉ” ይል የነበረውን መንግስት የህግ መሠረት ያስያዘበት ነው፡፡ ለምሳሌ በፊት እንቅስቃሴ ላይ ተራርቃችሁ ቁሙ ወይም እጃችሁን ታጠቡ ይላል እንጂ አስገዳጅ አያደርገውም፤ አሁን አስገዳጅ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ ሌላው ለምሳሌ አንዳንድ ክልሎች እንቅስቃሴን የሚገድቡ እርምጃዎችን ያለ አስቸኳይ አዋጅ ወስደዋል፡፡ ትራንስፖርት አግደዋል፡፡ ይሄ መሰረታዊ ስህተት ነው፡፡ አሁን ነው የሕግ መሰረት ያገኙት እንጂ አስቀድሞ በነበረው ሂደት ግን ትክክል አልነበረም፡፡
እንቅስቃሴዎችን ያለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገድበው የነበሩ ክልሎች ስህተት ሰርተዋል ማለት ነው?
ትክክል አልነበሩም፡፡ በሕጉ መሰረት በመሄድ በኩል የትግራይ ክልል የተሻለ ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ ክልሎችም የራሳቸውን አስቸኳይ አዋጅ በክልላቸው ማወጅ ስለሚችሉ ከዚያ ተነስቶ አውጆ ነው ገደቦችን ያበጀው። የፌዴራል መንግሥቱ ግን ሳያውጅ ነበር አንዳንድ ክልከላዎችን ያስቀመጠው፡፡ አንዳንድ ክልሎችም ማለትም ደቡብ፣ አማራና ኦሮሚያ መብትን የሚገድቡ እርምጃዎችን ያለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲወስዱ ነበር፡፡ እርግጥ በሽታው ከፈጠረው ስጋት አንፃርና የአገሪቱ ሕግ ከሚፈቅደው ነገር አኳያ፣ እርምጃዎች በመወሰዱ የሚነሱ የሕጋዊነት ጥያቄዎች እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡ ያለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲወሰዱ የነበሩ እርምጃዎች ግን የሕግ ጥሰት የነበረባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ የትራንስፖርት ገደብ፣ ትራንስፖርት ሰጪዎች ከጭነታቸው ግማሽ ብቻ እንዲጭኑ ማስገደድ የመሳሰሉት ያለ ሕግ መሰረት ነበር ሲፈፀሙ የነበሩት፡፡ በወቅቱ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምንድን ነው የሕግ መሰረቱ ተብሎ ቢጠየቅ መልስ አይኖረውም፡፡ አሁን ግን አዋጁ እነዚህን ሕጋዊ ያደርጋቸዋል፡፡
የትግራይ ክልል የራሱን ለ3 ወር የሚቆይ አዋጅ አውጇል፡፡ የፌዴራሉ መንግስትም ለ5 ወር የሚቆይ አዋጅ አውጇል፡፡ ገዥው አዋጅ የቱ ነው? እንዴትስ ነው ሊጣጣም የሚችለው?
እንግዲህ እኛ የፌዴራል ሥርዓትን ነው የምንከተለው። ክልሎችም ሕግ የማውጣት ስልጣን አላቸው። ነገር ግን ክልሎች የሚያወጧቸው ሕጎች የፌዴራል መንግሥት ከሚያወጣው ጋር ተቃራኒ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ተቃርኖ ከተገኘ ተፈፃሚ የሚሆነው የፌደራሉ ህግ ነው፡፡ ነገር ግን ተቃርኖ ኖሮ የተሻለ መብት የሚሰጥ ካለ የተሻለው ሊወሰድ ይችላል፡፡ ዋናው ለዜጎች የተሻለ መብት መስጠት ሊሆን ይችላል መነፃፀሪያው፡፡ በእርግጥ ይሄ ጉዳይ የሕግ ትርጉም ይጠይቃል። ከሁለቱ የተሻለ የትኛው ነው የሚለው በፍ/ቤት ይተረጎማል፡፡ ለምሳሌ በትግራይ የወጣውና በፌደራል የወጣው ለንጽጽር ቀርቦ የሕግ ትርጉም ይሰጥበታል ማለት ነው፡፡ ሲጀመር ግን በትግራይ ክልል የወጣው ሕግ፣ የፌደራሉን አይቃረንም፡፡  በመደበኛው አካሄድ ግን ያው የፌደራል መንግሥቱ የሚያወጣው ሕግ የበላይ ነው፡፡
ይህ አዋጅ ሲፈፀም ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል የሚሏቸው ጉዳዮች ካሉ ቢነግሩን?
እንዲህ አይነት ገደቦች በሚቀመጡበት ወቅት በአለማቀፍ የሰብዓዊ መብት መርሆዎች መሰረት መንግሥት ሊከተላቸው የሚገቡ መመሪያዎች አሉ፡፡ አንደኛው ገደቡ በሕግ መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው የሚጣለው ገደብ ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ማለት ገደብ በሚቀመጥበት ወቅት የተቀመጠው ገደብ ሊከላከል ካሰበው አደጋ ስፋት ጋር የሚመጣጠን መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ይሄ ቫይረስ ከ3 ወር ባልበለጠ ጊዜ በቁጥጥር ስር ቢውልና ምንም ስጋት ባይኖር ገደቡ ፈጥኖ መነሳት አለበት ወይም ደግሞ አዋጁ ከታለመለት አላማ ውጭ ወጥቶ የሌላ አላማ ማስፈፀሚያ መሆን የለበትም፡፡ በሽታውን ለመከላከል በሚል ሰዎች ሙሉ ለሙሉ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጎ እንደገና ደግሞ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ምግብ አለማቅረብ የሚፈቀድ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በበሽታ ሞቱ በረሃብ ሞቱ ያው ነው፤ ለውጥ የለውም፡፡ ስለዚህ የሚወሰደው እርምጃ መመጣጠን አለበት፡፡ የሰው ልጅ በየትኛውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ቢሆን እንኳ በሕይወት የመኖር መብት አለው፡፡ በየትኛውም መንገድ ሊገደብ የማይችል መብት ቢኖር፣ በሕይወት የመኖር መብት ነው፡፡ በእርግጥ ይሄ በኛ ሕገ መንግሥት ላይ አከራካሪ ነገር አለው፡፡ ይሁን እንጂ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰው የመኖር መብት አይገደብም። ስለዚህ የተመጣጣኝነት ጉዳይ ነው ዋናው ነገር፡፡ ሌላው ደግሞ አዋጁ ተቀባይነት ያለው መሆን መቻል አለበት፡፡ አደጋውን ለመከላከል በሚል ሽፋን ሌሎች የማይገናኙ መብቶችን መገደብ የለበትም፡፡ ለምሳሌ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከዚህ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ላይታገድ ይችላል። አዋጁን ፈጽሞ ለፖለቲካ አላማ ማዋል አይቻልም፡፡ ስለዚህ ይሄ አዋጅ ሲፈፀምም እነዚህን ታሳቢ አድርጎ መሆን አለበት፡፡  

Read 3360 times