Saturday, 02 May 2020 12:45

የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ

Written by 
Rate this item
(12 votes)

     ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሽማግሌ ከልጃቸው ጋር መንገድ ሲሄዱ ብዙ አውሬዎች ካሉበት ጫካ ይደርሳሉ፡፡ ሽማግሌው በጣም ደንግጠው በአቅራቢያው ከምትገኝ ትንሽ ጐጆ ልጃቸውን ይዘው ይገቡና ይደበቃሉ፡፡
አውሬዎቹ ድምፃቸው ይሰማል፡፡
ልጅ - “አባዬ፤ ይሄ ጅብ ነው” ይላል፡፡
አባት - “ምንም ይሁን ልጄ አውሬ አውሬ ነው ዝም ብለን በራችንን ዘግተን እንቀመጥ” ይሉታል፡፡
ልጅ ሌላ ጩኸት ይሰማና፤
“አባዬ ይሄኛው ነብር ነው?” ይላል
አባት - “የኔ ልጅ፤ ምንም ይሁን ምን ዝም ብትል ነው የሚበጀን፡፡ አንዳንድ አውሬ እንኳን ድምጽ ሰምቶ፣ ጠረን አሽትቶም አይለቅም፡፡”
ልጅ፤ ልጅ ነውና ሌላ ድምጽ ሲሰማ፤
“አባዬ ይሄ ግን ያለ ጥርጥር አንበሳ ነው፡፡ አንበሳ ደግሞ አንዴ ከጮኸ የጫካው እንስሳት በሙሉ በርግገው ይሸሻሉ፡፡”
አባት - “ልጄ አውሬዎቹ ሲሸሹ እኛ ወደተደበቅንባት ጐጆ ከመጡ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ለዚያ ነው ትንፍሽ ማለት የለብንም የምልህ፡፡ እንዲያውም ጐጆይቱን ቆይ በደንብ ልቀርቅራት”
አለና ተነስቶ ወደ በሩ ሄዶ ሙቀጫም፣ ወፍጮም፣ ሠንዱቅም አስጠግቶ ጥብቅ አድርጐ ዘጋው፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አካባቢው ሁሉ ፀጥ፣ እረጭ አለ፡፡
አባት - “በል አሁን ኮሽ ሳታረግ ተኛ፡፡”
ልጅ - “እሺ፤ ግን አባዬ እንደ እኛ ሠፈር መስሎህ እንዳታንኮራፋ፡፡ ካንኮራፋህ አውሬዎቹን ትጠራቸዋለህ፡፡”
አባት - “ማንኮራፋቴን ደግሞ እንዴት አድርገህ ሰማህ?”
ልጅ - “እኔ አንተ ስታንኮራፋ ለመስማት ብዬ’ኮ አይደለም ስታንኮራፋ የሰማሁት፡፡”
አባት - “ታዲያ እንዴት ሰማህ?”
ልጅ - “እያንኮራፋህ እየቀሰቀስከኝ ነዋ!”
አባት - በልጁ መልስ እየተገረመ፤ “በል እንተኛ” ብሎ ፀጉሩን እያሻሸው ይተኛሉ፡፡ ጠዋት ገና ንጋት ላይ፤
“አባዬ፤ ነግቷል እኮ በጊዜ መንገድ እንጀምር”
አባት - “ቆይ ትንሽ እንተኛ” ይልና ጋደም ይላል፡፡ ልጅ እንደገና ይቀሰቅሰዋል፡፡
“ኧረ አባዬ ፀሐይ ይከርርብናል በጊዜ እንነሳ!!”
አባት -  “የእኔ ልጅ ክፍቱን ላደረ መንገድ ምን አስጨነቀህ፤ ትርፉ መጋኛ ነው!” ብሎ እንቅልፉን መለጠጡን ቀጠለ፡፡
*   *   *
አባት ልጅን መቀስቀስ ሲገባው ተቀስቃሽ ሲሆን ደግ አይደለም፡፡ ማናቸውንም አዲስ ነገር ለይቶ ማወቅ ትላንት የነበረውን ለማመዛዘን፣ ዛሬን ለማጣጣምና ነገ የሚሆነውን ለመገንዘብ አባት የተሻለ ልምድ አለው፡፡ ያም ሆኖ አንዳንድ ዘመን ንቃቱ የልጅ፣ እንቅልፉ የአባት እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ገጣሚው እንዳለው፤
“ትላንትን አትርሳው
ዛሬን በጣም ያዘው
ብርታቱን ስታገኝ
 ነገን ዛሬ ኑረው
ትውልድ የሚቆየው፣
አንዱን እንዲያ ሲባል ነው
በዕቅድ አለመኖር የቸልተኝነት ውጤት ነው፡፡ ቸል አንበል፤ መንገድ ካልሄዱት ረዥም ነው፡፡
“አስቤ ጨረስኩት የፈረሴን ጉልበት
አንድ ቀን ደስ ብሎኝ ሳልቀመጥበት”
…እንዳንል ለተግባር መዘጋጀቱ ዋና ነገር ነው፡፡ በተግባር ለመኖር ተግባራዊ እይታ ያሻናል፡፡ በትንሽ በትልቁ አለመበርገግ አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ አለመበርገግ ማለት ግን አለመጠንቀቅ ማለት አይደለም፡፡
ዛሬ ሁሉ ነገር ጥንቃቄን ይፈልጋል፡፡
“ሳይደግስ አይጣላም” ይላል አበሻ፡፡ A Blessing in disguise ይለዋል ፈረንጅ:: ትላንት ቸል እንለው የነበረውን ጥቃቅን ነገር ዛሬ እንድናስበው ሆነናል፡፡ ስናውቀው የሚያስደነግጥ አያሌ ነገር አለ፡፡ ያ ማለት ግን ማወቅ ደግ አይደለም ማለት አይደለም:: ማወቅን ብልሃትና ብስለት ጨምረን መኖሪያ ስናደርገው፣ የህይወት ትርጉም በትክክል እጃችን ይገባል፡፡
ዋና ዋና ነገር ነግረውን እኛ መውጫ መግቢያውን ስናሰላስል፣ ሁሉን ለእኛ ትተውልን የሚቀሩ ወይም የሚሄዱ አያሌ ናቸው፡፡ ችግሩን የነገሩን ሰዎች አብረን መፍትሔውን እንሻ ማለት አለባቸው፡፡ ሐኪሙም መምህሩም ህዝቡም በጋራ ማሰብ ያለባቸው ጊዜ ላይ ነን፡፡ ዛሬ የዓለምን ጣጣ መጋፈጥ የምንችለው በጋራ በማሰብ ነው፡፡ አለበለዚያ፤
“የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ” የሚለው ተረት ይመጣል፡፡
አብረን እናስብ!
አብረን እንጨነቅ!
አብረን እናሸንፍ!!
ለሁሉም የነገ ሰው ይበለን!

Read 13941 times