Print this page
Monday, 04 May 2020 00:00

የደቡብ ክልል የሰላም አምባሳደሮች ቡድን ምን እየሰራ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

   “ህዝቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ በጉጉት እየጠበቀ ነው” - የሰላም አምባሳደሮች ቡድን

        56 ያህል ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፎ የያዘው የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል፤ ከ13 በላይ ዞኖች ክልል እንሁን የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ፣ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ በተከሰተ ሁከትና ብጥብጥ የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ የግልና የመንግስት ሀብት ወድሟል፡፡
ብዙዎችን ከቀዬአቸው አፈናቅሏል፡፡ የደቡብ ክልል መንግስትና ነባሩ ደህዴን ባስጠኑት ጥናት መሰረት፤ የሲዳማ ክልልነት ፀድቆ የ14ቱ ዞኖች የክልልነት ጥያቄ በእንጥልጥል እንዳለ ነው፡፡ ነገር ግን የደቡብ የተለያዩ አካባቢ ተወላጅ ምሁራን፣ ባለሀብቶችና ጉዳዩ ይመለከተናል የሚሉ ግለሰቦች፤ በክልሉ ያለውን ሁከትና ብጥብጥ ለማርገብ 80 አባላት ያሉት የሰላም አምባሳደሮች ቡድን በማቋቋምና ይህ ቡድን በየዞኑና በየወረዳው እየተንቀሳቀሰ፣ ህብረተሰቡን በማወያየት፣ ፍላጐቱን አድምጠው የዳሰሳ ጥናት ካቀረቡ በኋላ ከክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ የየማህበረሰቡን ተወካዮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ማወያየታቸው ይታወሳል፡፡
የሰላም አምባሳደሮች ቡድን ምን ሥራዎችን አከናወነ? ምንስ ውጤት አስገኘ?  በቀጣይስ ምን አስቧል? የደቡብ ክልል መንግስትና የቀድሞው ደህኢዴን ያስጠናውን ጥናት በተመለከተ ቡድኑ ምን ይላል? በሚሉና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሰላም አምባሳደሮች ቡድን አባል የሆኑትን አቶ ወንድሙ ሀይሌን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ አነጋግራቸዋለች፡፡

        እርስዎ እንዴትና በምን አጋጣሚ ነበር የሰላም አምባሳደሮች ቡድን አባል የሆኑት?
አብዛኛው ህዝብ እንደሚያውቀው፤ በደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ከ13  የሚበልጡ ዞኖች የየራሳቸው ክልል እንዲሰጣቸው ለክልሉ ምክር ቤት ጥያቄ አስገብተዋል፡፡ ሆኖም የክልሉ መንግስት ከአንድ ዓመት በላይ ምላሽ ሳይሰጥ በመቅረቱ፣ እነዚህ ከ13 በላይ ዞኖች በህጉ ቅደም ተከተል መሰረት ጥያቄያቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቀረቡ፡፡ ለዚህ ጥያቄ እልባት ለመስጠት የደቡብ ክልል መንግስትና የነባሩ ደህኢዴን ስራ አስፈፃሚ ጥናት አስጠንቶ ነበር፡፡ በጥናቱ የተገኘው ግኝትና አጥኚው ቡድን ያቀረበው የመፍትሔ ሃሳብ የህዝብን ጥያቄ የሚመልስ ሆኖ አልተገኘም፡፡
እንዴት? እስኪ በግልጽ ያብራሩልኝ?
አንደኛ፤ ከጥናትም አንፃር ስንመለከተው፣ አንድ ዞን ብቻ ወደ ከልልነት ተሻግሮ፣ ቀሪው 55 ብሔር ብሔረሰብ አብሮ ይቀጥል የሚል ውሳኔ ላይ መደረሱ እንዴት እንደታየ አልገባንም፡፡
የሲዳማን ክልልነት ነው የሚሉኝ?
አዎ እንደዛ ማለቴ ነው፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ ሲደርስ በየደረጃው ያሉ አመራሮችንና ህዝቡንም ለማወያየት ተሞክሯል:: ነገር ግን ህዝቡም ይሁን አመራሩ አልተቀበለውም:: በተለይም የታችኛው የአመራር ክፍል አልተቀበለውም፡፡ በዚህ የተነሳ ከ13 የሚበልጡት ዞኖች ጥያቄያቸው አልተመለሰም፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 47/1 ላይ የሰፈረውም፣ እስካሁን የነበሩትን ዘጠኝ ክልሎች ይዘረዝርና፣ ከእነዘህ ክልሎች ውስጥ በክልልነት ለመውጣት የሚፈልጉ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ ይላል፡፡ ብሔር ግን አይልም፤ ለአንድ ብሔር አልፈቀደም ማለት ነው፡፡ ከአንድ በላይ የሆኑ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፈለጉበት ጊዜ ክልል ለመመስረት ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ ጥናቱም ይህን መሰረት ያደረገ አልነበረም፡፡ 1ለ 55 ሲወሰን ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጐ የተጠና ጥናት አልነበረም፡፡ አንድ ዞን ክልል ሆኖ ሌላው 55ቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድ ላይ ይሁኑ የሚል ግኝትም በጥናቱ የለም፡፡
ግን የክልሉ መንግስትና ነባሩ ዴህኢዴን ባስጠኑት ጥናት፤ ምን ያህል ሰው ተሳትፏል? በጥናቱ 1 ለ55 ውሳኔም በጥናቱ አልተካተተም ካሉ፣ በጥናቱ ውስጥ በትክክል የነበረው ውጤት ምንድን ነው? ስላልገባኝ ነው?
እነሱ ባስጠኑት ጥናት ላይ ወደ 17ሺህ ህዝብ ተጠይቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 56.37 በመቶው ‹‹አንድ ላይ በመሆናችን ተጐድተናል›› የሚል ምላሽ ነው የሰጠው፤ 56 ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ደቡብ በሚል ብቻ ተጨፍልቀን መቀመጣችን ጐድቶናል ያሉ ናቸው፡፡ ጉዳቱም በመልካም አስተዳደር፣ በልማት፣ በፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ችግር የሚገለጽ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ‹‹ጉዳቱ ቢኖርም አንድም ዞን ክልል ሆኖ ሳይወጣ ሁላችንም እንደ ቀድሞው ደቡብ ክልል ሆነን እንቀጥል›› የሚሉት ደግሞ 43.17 በመቶዎቹ ናቸው፡፡ ስለዚህ በጥናቱ መሰረት 1ለ55 የሚል ግኝት የለም፡፡
የክልሉ መንግስትና ነባሩ ዴህኢዴን ያቀረቡት 1ለ55፤ ከጥናቱ ግኝት ውጭ ነው የምለው በዚህ እውነታ ላይ ተመስርቼ ነው:: ይሄ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ቁጣ ቀሰቀሰ፡፡ 1 ለ55 ከተወሰነ ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ተነሳ፡፡ ቀድሞ ከነበረው ቀውስ በባሰ ሁኔታ የሰላምና የፀጥታ እጦት ተፈጠረ፡፡ ከዚህ በኋላ እንዴት የሠላም አምባሳደሮቹ ቡድን አባል ሆንክ ወደሚለው ጥያቄሽ እመለሳለሁ፡፡
እሺ ይቀጥሉ….
ይህ አለመረጋጋትና ቀውስ ሲፈጠር መንግስት፣ ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ሆኖ በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር አደረገ:: በዚህ መሃል ላይ ግን በርካታ ንብረት ወድሟል፣ ብዙዎች ከቤት ንብረታቸው ተነቅለው ተፈናቅለዋል፡፡ ህይወታቸውን ያጡም አሉ፡፡ የግልና የመንግስት በርካታ ንብረትም ወድሟል፡፡ የመንግስት መኪኖች፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎችም ንብረቶች ተቃጥለዋል፡፡ ይሄ እንግዲህ 1ለ55 ጥያቄ ህዝቡ አልተቀበለውም ማለት ነው፡፡ ህዝቡ ቁጣውን የሀይል እርምጃ በመውሰድ፣ መንገድ በመዝጋት፣ መንገድ ላይ የመኪና ጐማ በማቃጠል መግለጽ ጀመረ፡፡ በተለያዩ ዞኖች ላይም በተለያዩ ጊዜያትና ቀናት ይህ ክስተት ሲፈፀም ቆየ:: ስለዚህ የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ዴህዴን ያስጠኑትን ጥናት አልተቀበለውም:: ህዝቡም ‹‹ራሴን ችዬ ክልል ልሁን›› ብሎ ለክልሉ ምክር ቤት ያቀረበው ጥያቄም መልስ አላገኘም፡፡ በዚህ ምክንያት ህዝብና መንግስት ተለያዩ፡፡
ዞኖች በህጉ መሰረት የክልሎች ብሔረሰብ ምክር ቤት በአንድ አመት ውስጥ የክልልነት ወይም የማንነት ጥያቄን ካልመለሰ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መጥተው ማመልከት ወይም በክስ መልክ ማቅረብ እንደሚችሉ ይደነግጋል፤ ዞኖችም ይህን ተከትለው ጥያቄያቸውን ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት አቅርበዋል፡፡ ምን ምላሽ አገኙ?
ጉዳዩን በክስ መልክ ዞኖች ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አምጥተውት እያለ ከክልሉ ከሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ምሁራንና ይመለከተናል የሚሉ ግለሰቦች ተሰባሰቡና ክልሉ በዚህ መልኩ ከሚታመስ፣ በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ከሚደርስ፣ ለምን ጠቅላይ ሚኒስትሩን አግኝተን በማነጋገርና የመፍትሔ ሃሳብ አቅርበን፣ ሃሳቡን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀበሉን ከሆነ፣ ወደተሻለ የመፍትሔ አቅጣጫ አይሻገርም? የሚል ነገር ላይ ተደረሰ፡፡
ከዚያም ሁሉም በየአካባቢው፣ በየዞኑ፣ በየብሔሩ እየተመካከረ፤ ሃሳቦችን እያቀረበና እየተወያየ ቆየና በጣም ጥሩ የሆነ የሰላም አምባሳደሮች ቡድን ተቋቋመ፡፡
በዚህም ሂደት የሰላም አምባሳደር ቡድን ሆኜ ከአካባቢዬ ተመረጥኩ እያሉኝ ነው?
አዎ፤ አባልና የአንድ ንዑስ ቡድን አስተባባሪም ነኝ፡፡
ከየትኛው አካባቢ ነው የተወከሉት
እኔ ከሀዲያ ነው ቡድኑን የተቀላቀልኩት::
ከዚያስ ምን ሆነ?
ከዚያ ያ ቡድን ግንባር ፈጠረና፣ ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀረበ፡፡      
ይሄ መቼ ነበር የሆነው?
ባለፈው ጥር ወር መግቢያ ላይ ነው ጥያቄ የቀረበው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄውን ተቀበሉ፡፡ ጥያቄውን ከተቀበሉ በኋላ የሰላም አምባሳደር የኮሚቴ አባላትን ጥር 13 ቀን ይመስለኛል  አወያዩ፡፡ እንግዲህ የክልሉ መንግስትና መሪ ድርጅቱ ዴህዴን ያስወሰኑት ውሳኔ በጥናት ያልተገኘ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የአንዱ ዞን ጥያቄ ከተመለሰ በህገ - መንግስቱ መሰረት የሌሎቹም መመለስ ነበረበት፡፡ ስለዚህ ይህንን ሃሳብ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዘን ስንቀርብ፣ እርሳቸውም ከእኛ ጋር ሲወያዩ፣ ለ56 ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለሁሉም ክልል መስጠት አይቻልም፡፡ 56ቱም በአንድ ላይ ተጨፍልቀው መኖራቸውም አግባብ አይደለም ተባለ፡፡
ይሄንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ ወይስ እናንተ ያቀረባችሁት ሃሳብ ነው?
እኛ ሀሳቡን አቀረብን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንኑ ደገሙት፡፡ ስለዚህ ለ56ቱም ክልል መስጠት አይቻልም፤ ሁሉንም እንደ ድሮው በአንድ ክልል ጨፍልቆ ማስኬድ አይቻልም፡፡ የ1 ለ55 ውሳኔም አይሰራም በሚል ላይ ተስማማን:: በዚህ ከተስማማን በኋላ ከክልሉ ከተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በዚያው ጥር ወር አጋማሽ ላይ ሰብስበው አወያዩ፡፡ በውይይቱ ላይም ‹‹ከክልሉ በየአቅጣጫው እየተነሳ ያለውን ጥያቄ በህዝብ ውይይት ህዝቡ የሚፈልገው ምን እንደሆነ ትክክለኛ የህዝቡን ስሜት ታች ድረስ ወርደውና ህዝቡን አወያይተው የሚያመጡ የሰላም አምባሳደር ኮሚቴዎችን አቋቁመናል እነዚህ ኮሚቴዎች ታች ድረስ ሄደው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ተወያይተው 56 ክልል መስጠት ስለማይቻል፣ ማን ከማን ጋር ስነ-ምህዳራዊ፣ ስነልቦናዊና ባህላዊ ተግባቦትና ቅርርብ ሊኖረው እንደሚችል እያወያዩና ተቀራራቢዎቹን በየፍላጐታቸው አንድ ክልል እያደረጉ፣ የህዝቡ ፍላጐት አደረጃጀት ይሰራል›› - አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ እኛም በዚህ መሰረት የእቅድ ዝርዝር አውጥተን፣ የእቅዱን ማስፈፀሚያ ፕሮግራም አዘጋጅተን ቅድመ ውይይት መርሃ ግብሮችን በዞኖችና በልዩ ወረዳዎች ተዘዋውረን አስይዘን በዚያ ውይይት ላይ የሚሳተፉ የተለያዩ የብሔረሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌ፣ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የአርሶአደር፣ የአርብቶ አደር፣ የምሁራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮችና ሌሎች ይመለከታቸዋል የተባሉ ወገኖች የተውጣጡበት በየዞኑና በልዩ ወረዳዎች ከቀበሌ ጀምሮ ጥሪ ተደርጐ ህዝባዊ ውይይት ተካሄደ፡፡ ይህ ውይይት በክልሉ፣ በ15 ዞኖችና በ5 ልዩ ወረዳዎች ላይ ተደርጓል፡፡ በ15ቱ ዞኖችና በ5ቱም ልዩ ወረዳዎች በተካሄዱ የውይይት መድረኮች ላይ ህዝቡ በአጠቃላይ ደርሶብኛል ያለውን ብሶት በደልና ችግር አንስቷል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ክልሉና የደህዴን ስራ አስፈፃሚ ያሳለፈውን የ1 ለ55 ውሳኔ የተቀበለ አንድም ሰው አልተገኘም፡፡ እንደውም እኔ በነበርኩበት አካባቢ ላይ ቃል በቃል በተላለፈው ሀሳብ የተባለው፤ “ለዚያ ጥናት የወጣው ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት በከንቱ ኪሳራ የጠፋ ነው፡፡ በጀቱን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ከምንወድቅ ለፀጥታ ስራ ብንጠቀምበት ይሻል ነበር፤ ኪሳራውን ደግሞ የክልሉ መንግስትና የደህዴን ሥራ አስፈፃሚ መመለስ አለበት” የሚል ነበር፡፡
ለጥናቱ የወጣው የገንዘብ መጠን ታውቋል እንዴ?
በእርግጥ የበጀቱን መጠን አናውቅም፡፡ ያው ግን ምንም ያህል ይሁን በጀት በጀት ነው፤ የህዝብ ገንዘብ ነው፡፡
ከዚያስ ከህዝባዊ ውይይቱ በኋላ ምን አደረጋችሁ?
በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት ሺህ የማህበረሰብ ተወካዮችን ባወያዩበት ወቅት፤ የሰላም አምባሳደር ኮሚቴ ማቋቋማቸውን ሲገልፁ፤ ይህንን የሰማ በየአካባቢው ያለው ሰው በማህበራዊ ሚዲያ ሁሉ ተሰራጨ፡፡ እናም ‹‹ክልል እንሆናለን›› ሲል የነበረው ሁሉ ረገብ አለና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና ማቅረብ ጀመረ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእውነቱ በዚህ ላይ የሰሩት ስራ እጅግ የሚደነቅና የተለየ ነው:: ምክንያቱም ደቡብ ክልል ነባር ክልል ነው፤ ማደራጀትም ሆነ ከተፈለገ ማፍረስ ከተፈለገ፣ ፖለቲካዊ ውሳኔ መስጠት ይቻላል፡፡ ይሄ ይሄ ዞን አንድ ላይ፣ ያ ያ ዞን ደግሞ አንድ ላይ ብሎ ህዝቡን ማወያየትና አቅጣጫ መስጠት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እርሳቸው እስኪ ህዝቡ ምን ይላል? አመራሩ 1 ለ55ቱን ህዝብ ተቀብሎታል እያለ ነው፤ ህዝቡ ደግሞ ፍላጐቱ ምንድን ነው? ብለው ህዝቡን በግንባር አግኝተው ሲያወያዩ፣ ህዝቡ 1ለ 55 ውሳኔን እንኳን ሊቀበል አያውቀውም፡፡ እንኳን ህዝቡ የታች አመራሩም ራሱ አያውቀውም፡፡ የተወሰኑ የነባሩ የደህኢዴን ጥቂት ሥራ አስፈፃሚዎች፣ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሰሩት ሥራ ነው፡፡
‹‹የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሰሩት ሥራ ነው›› ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? ሊያብራሩት ይችላሉ?
ጥቅማቸው ምንድን ነው የሚለውን ስንመለከት፣ አንደኛ ደቡብ ክልል ትልቅ ከሚባሉ ክልሎች አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ትልቅ ክልል ስም ስልጣን ላይ መቆየትና የፖለቲካ የፊት መሪ ሆኖ የመቆየት ጥቅም አለ፡፡ ሁለተኛው የሀብት ቅርምት ጥቅም አላቸው፤ ስለዚህ ይሄ ጥቅም እንዳይቋረጥና ጥቅም ለማስከበር ህዝቡና የታች አመራሩ ሳይወያይበት፣ 1ለ55ቱ ፀድቋል፤ ህዝቡ ተቀብሎታል ብለው አስፈጽመዋል፡፡ ይህን የተቃወሙ አመራሮች፣ በየቦታው ከስራቸው ተባርረዋል፡፡ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎችና ሌሎች አመራሮች ከስራ ተባርረዋል፡፡ ‹‹ይህንን 1 ለ55 የተሰኘ ውሳኔ የኔ ህዝብ አይቀበለውም›› በማለታቸው ከስራቸው የተባረሩ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ የስራ ምደባ ሳያገኙ ያለ ስራ ስምንትና ዘጠኝ ወር ዝም ብለው የተቀመጡ አሉ፡፡
በመጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእኛን የውይይት ጥሪ ተቀብለው ከ2ሺህ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ እንደዛ ክልል እየተባለ ሲጮህ የነበረው ነገር ቆሟል፣ የሰው ሞት ተገትቷል፤ የንብረት ዘረፋና የሰው መፈናቀልን ለማስቀረት ተችሏል፡፡ የሀብት ውድመትና የመንገድ መዘጋት ቆሟል፡፡ ለምን ካልሺኝ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ ‹‹የሰላም አምባደር ኮሚቴዎች ወደ ታች ወርደው ህዝበ ያወያያሉ›› እናንተ በምትሰጡት መልስና ሃሳብ መሰረት አዳዲስ ክልል ይፈጠራል በማለታቸው እኛ ለማወያየት ታች ድረስ በወረድንበት ጊዜ የህዝቡን ደስታና እፎይታ አይተናል፡፡ እንደውም አንዳንዶች እርጥብ ሳር እያነሱ ‹‹ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሰዱልን›› ይሉ ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ ህዝቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ እፎይታ ማግኘቱን የሚያሳይ ነው፡፡
እርስዎ የተወከሉበት ሃዲያ በዋናነት ጥያቄው ግን ምንድን ነው ለመሆኑ የህዝቡ ብዛት ምን ያህል ነው?
ሃዲያ ትልቅ ባህልና ታሪክ ያለው ህዝብ ነው:: የህዝቡ ብዛት ወደ 3ሚ ይጠጋል:: ህዝቡ በዋናነት ጥያቄው የልማት ጉዳይ ነው፡፡ እያነሳ ያለው ስለ ፍትሃዊ የህብት ክፍፍል ነው፡፡ እርግጥ ሃዲያ ክልል ለመሆን የሚያንሰው ነገር የለም፤ ነገር ግን ክልል ሲሆን መዋቅር ይበዛል:: ከስር መዓት ዞኖችና ወረዳዎች ይፈጠሩና ይበዛሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ህዝቡ ከሚመደብለት በጀት አብላጫው ለአስተዳደራዊ ወጪ ይውልና የሚናፍቀው ልማትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እየናፈቀው ይቀራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ 56 ክልል ከመሆን ቅድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደየ መልክአ ምድራዊ፣ ስነልቦናዊና ባህላዊ ቅርርቡ ሰብስብ ሰብሰብ እያለ ክልል ቢሆን፤ በአገሪቱም ላይ ትርጉም ያለው ልማት ይሰራል፤ ሰላምና መረጋጋትም ይመጣል፤ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱም ይበዛል፡፡ የሰላም አምባሳደሮቹም ከየዞኑና ከየወረዳው ተውጣጥቶ ተመካክሮ ነው እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደረሰው፡፡
የኮሚቴ አባላቱ ምን ያህል ናችሁ?
በመጀመሪያ 80 ያህል ነበርን፤ በከፍተኛ ተሳትፎ እስከ መጨረሻ የዘለቅነው ግን 45 ያህሉ ነን፡፡ ወደ በኋላ ላይ ለምስጋናም እጠቅሳቸዋለሁ ብዬ ነበር ካነሳሽ አይቀር ከምሁራንና ታዋቂ ሰዎች መካከል ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስና ክቡር አባዱላ ገመዳ ይገኙበታል፡፡ በተለይ ዶ/ር አሸብር በበላይነት ከማስተባበርም ባለፈ በግላቸው በጀት በመመደብ፣ ጊዜያቸውን በመሰዋት ከፍተኛ ጥረት አድርገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ እንዲቀርብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ህዝባዊ ውይይቱም ውጤታማ እንዲሆንና በታሰበው መልኩ እንዲሳካ፣ ህዝቡ የጠየቀውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲያገኝ በማድረጋቸው፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ታድገዋል፡፡ ምክንያቱም ቅድም እንዳልኩሽ፤ ብዙ ዘረፋ ነበር፤ ብዙ የሃብት መውደምና ብዙ የሰው መፈናቀል ነበር፡፡ ያ ሁሉ ሲቀር የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጥሩ ይሆናል፤ አንድ የመንግስት መኪና ሲቃጠል 3 እና 4 ሚ ብር ነው የሚቃጠለው፤ ሲሰራ ግን ብዙ ልማት ያመጣል፡፡ ለሰላማዊ ሰልፍና ለብጥብጥ ሲወጣ የነበረ ገንዘብ ተርፏል ማለት ነው፡፡ ወጣቱ ጊዜውን አላስፈላጊ ለሆነ ብጥብጥ ሲያውል ነበር፤ አሁን ወደ ስራ ገብቷል ማለት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሚናው ቀላል አይደለም፡፡ የተሳካ ህዝባዊ ውይይት እንዲደረግ የሰላም አምባሳደር ኮሚቴውን በማስተባበር፣ በጀት በመመደብ ከፍተኛ ድርሻ አድርገዋል፡፡ እውነት ለመናገር፤ እነዚህ ሰዎች የአገር ሸክም ነው ያቀለሉት:: ህዝቡ ጥያቄው ለሚመለከተው የአገር መሪ መድረሱን አረጋግጦ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረጉ ነው ይሄ ሁሉ መረጋጋት የመጣው፡፡ ስለዚህ ዶ/ር አሸብርንና ክቡር አባዱላን እንዲሁም የህዝብ ጉዳይ ያገባኛል ይመለከተኛል ብለው በግል ተነሳሽነት የግል ስራቸውንና ጥቅማቸውን እየተው እየሰሩ ያሉትን የሰላም አምባሳደር ቡድን አባላትንም ማመስገን እፈልጋለሁ:: ምክንያቱም አንድ የተለየ ሃሳብ ሲመጣ፣ በዚያው ልክ ተግዳሮችም አሉ፤ እነ ዶ/ር አሸብር ይህንን ነገር ሲያስተባብሩና የህዝብ ድምጽ እንዲሰማ ሲያደርጉ ብዙ ችግሮችን ተጋፍጠዋል፡፡
ምን አይነት ችግሮች?
ህዝቡን ለማወያየት ታች ዞንና ልዩ ወረዳዎች ስንቀሳቀስ፣ ሁሉም አልጋ ባልጋ አይደለም የነበረው፡፡ እነ ዶ/ር አሸብር ላይ ከዛቻና ማስፈራሪያ ባለፈም ብዙ ሰብዕናን የሚነኩ ዘለፋዎች ደርሰውባቸውና ነበር ስንት ጫና ተቋቁመው ነው እዚህ የተደረሰው፡፡ መድረኮች እንዳይሳኩ ሃሳቡን ለመቀልበስ እነክቡር አባዱላና ዶ/ር አሸብር ላይ ዘመቻ ተከፍቶ ነበር ሌሎች ሚዲያዎች ላይም ዘመቻ ተከፍቶ ነበር፡፡ እንኳን ዋና አስተባባሪዎቹ ላይ እኛም ላይ ብዙ አላስፈላጊ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲሰነዘር ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ የህዝብ ድምጽ በአግባቡ ስለተደመጠና ግቡን ስለመታ የተከፈቱብን ዘመቻዎች ካሳካነው ግብ አንፃር ሲታዩ ኢምንት ናቸው፡፡
በሰላም አምባሳደሮች ኮሚቴ አባልነትዎ በቀጣይ ክልሉ ምን ቅርጽ ይዞ ቢቀጥል ዘላቂ ሰላምና ልማት ያመጣል ይላሉ፡፡ ሌላው ከህዝባዊ ውይይቱና ከዳሰሳ ጥናታችሁ ያገኛችሁትን ውጤት ምን አደረጋችሁት?      
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እኛ አላማችን ህዝባዊ ውይይት አድርገን፤ የህዝቡን ትክክለኛ ስሜትና ድምጽ ማዳመጥ ነበር:: ያንን በተሳካ ሁኔታ ከውነን መጥተናል፡፡ ሪፖርትም ጨርሰናል፡፡ ‹‹አሁን ክልሉ ምን ቅርጽ ቢይዝ ነው ዘላቂ ሰላም ወንድማማችነትና እርስ በእርስ መተማመን የሚመጣው?›› ብለሽ ላነሳሺው ጥያቄ ህዝቡ ራሱ ማን ከማን ጋር አንድ ላይ ሆኖ ክልል ቢሆን ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጣ አውቆ ጨርሶ ተቀምጧል:: የትኛው ዞን ከየትኛው ዞን፣ የትኛው ልዩ ወረዳ ከየትኛው ዞን ጋር ቢሆን የሚፈልገውን ልማት እንደሚያገኝ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሩ እንደሚቀረፍ አውቆታል:: የሚገርምሽ ‹‹ከዚህኛው ዞን ጋር ባልሆን እንኳን ከዚህኛው ወረዳ ጋር እሆናለሁ›› እያለ እስከ ሶስተኛ አማራጭ ድረስ አስቀምጧል፡፡ አሁን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብን ውይይት መነሻ በማድረግ፣ ሃሳብ ይሰጣሉ ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡ ይህንን ስንጠብቅ ህዝቡ እንደ ስጋት ያነሳቸው ነገሮች አሉ:: በመጀመሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አክብሮታቸውን ገልፀው፤ ይቅርታ ወደ ኋላ ለመመለሴ ይሄ ክልል ቀደም ሲል አምስት ክልል ነበር፤ ወደ አንድ ክልልነት ሲመጣ ህዝቡ አያውቅም፤ በማን ውሳኔ አንድ እንደሆነ አይታወቅም ሰነድም የለም:: ይሄን እኛም ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለው ያስጠኑት ክልሉና የደህዴን ስራ አስፈፃሚዎችም አላገኙትም፡፡ ከዚህ አንፃር እንዲህ እየሆነ የመጣ ክልል አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጡት አቅጣጫ እንዳይቀለበስና ከምርጫ በፊት ይፋ እንዲሆን የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰን ነበር፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ምርጫውም ተራዝሟል፡፡
ሁለተኛው፤ አሁን በስኬት የተጠናቀቀው ህዝባዊ ውይይት እንዳይሳካ የሚተጉ ሀይሎች ስላሉ ይህ በሰላም አምባሳደሮቹ በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደርሶ ሳይሳካ እንዳይቀር አደራ እያለ ነው ህዝቡ፡፡ ስለዚህ በአስቸኳይ እንዲመለስልን እንፈልጋለን የሚል ግፊት አለ፡፡ ምክንያቱም እኛንም ጠቅላይ ሚኒስትሩንም በማመን፣ ህዝቡ ትግሉንና ረብሻውን አቁሞ በሰላማዊ መንገድ እየጠበቀ ነው፡፡ እንደውም የኮሮና ወረርሽኝ ገብቶ የሁሉንም ነገር ትኩረት ሳበው እንጂ ህዝቡ የዚህን ጉዳይ ምላሽ የሚጠብቀው ከመጋቢት 30 በፊት ነበር፡፡ ይሄ ነገር ተገልፆ፣ ሌላው ህጋዊ ሂደቱ ግን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር የሚከወን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ በጉጉት እየጠበቀ ነው፡፡ እኛም ሪፖርቱንና ምክረ ሃሳቡን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማቅረብ ዝግጁ ነን:: አሁን ዓለም ከገባበት የኮሮና ወረርሽኝ ውጥረት እኛም እንደ ሀገር ትልቅ ትኩረት ለወረርሽኙ እንደ መስጠታችን ከዚህ መለስ ሲሉ፣ ጉዳዩን በትኩረት አይተው ምላሽ እንዲሰጡ ህዝቡ ጥሪ እያቀረበ ነው፡፡ እኛም በቅርቡ ምላሽ ይሰጣሉ ብለን እናምናለን፡፡ አሁን ስጋት ስላለን ነው፡፡ እንዳልኩሽ ይሄ እንዳይሳካ የሚንቀሳቀሱ አካላት ሩጫቸውን አጠናክረው ስለቀጠሉ፣ ልፋትና ድካማችን የህዝቡም ጉጉት ገደል እንዳይገባ በማሰብ ነው እኛም ወደ እናንተ መጥተን ሃሳባችንንና የህዝቡን ፍላጐት ለመግለጽ የሞከርነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Read 2914 times