Saturday, 02 May 2020 14:04

ጨለማ አይፈሬው

Written by  ከተመስገን ጌታሁን
Rate this item
(1 Vote)

 ትንሽ ልጅ ነው፡፡ በቀኝ ትከሻው ባዶ ገንቦ ተሸክሟል-ከምንጭ ውኃ እንዲቀዳ ታዞ፡፡ ቆሸሽ ያለችግራጫ ካኒቴራና አረንጓዴ ቁምጣ ሱሪ ለብሷል፡፡ ባዶ እግሩን ነው፡፡አንገቱም ላይ ክታብ አስሯል፡፡ ከቤት ሲወጣ መሽቷል፡፡ ብቻውን ነው፡፡ የከተማዋን ምሥራቃዊ አቅጣጫ ይዞ ከተማዋንወደኋላው እየተዋት በሄደ ቁጥር ጸጥታው እየጨመረ ሲሄድ ይሰማዋል፡፡ጸጥታው እየጨመረ ሲሄድና የጨለማው ግርማ ሞገስ ሲበረታ ነፍሱን ፍርሀት ፈጥርቆ ሊገድላት ደርሷል፡፡ ልቡ ፈጥና እየመታች ነው፡፡ የጆሮው ታምቡር ስልቱን እንደሳተ ከበሮ ጆሮግንዱ ስር እየጨፈረበት፣ ልቡ ላይ ፍርሀት ከነጭፍሮቹ ነግሷል፡፡ ግራም ተጋብቷል፡፡
ወላጆቹ ትንሹን ልጅ “ዓለሙ” ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ የእርሱ ብጤ ትንንሽ ልጆች ጓደኞቹ በስሙ ሳይሆን “ቦዲው’ እያሉ ነው በቅጽል ስሙ የሚጠሩት፡፡ የመንደሩን ልጆች ከጥቃት ስለሚጠብቅ ጓደኞቹ ይወዱታል፡፡ በደፋርነቱ የሌላ ሰፈር ልጆች በጣም ይፈሩታል፤ ይናደዱበታል፤ ይጠሉታልም፡፡አሁን ግን በጣም ፈርቷል፡፡
ፍርሀቱ ምን ቢበረታ ወደኋላ መመለስ ለዚህ ትንሽ ልጅ ከቶ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ጊዜው እሁድምሽት ነበር፡፡ በየሣምንቱ ሰኞ ለሚውለው ትልቅ ገበያ ለመገበያየት ከሩቅ አገር (ዶቅዓ) የመጡ ገበያተኞችበጊዜ ክትተዋል፡፡ ይህም ሆኖ መንገዱሙሉበሙሉ ጭር ዘላለም ነበር፡፡ አልፎ አልፎ የመሸባቸው ቆለኞች ከብቶቻቸውን እየነዱ ፤ ዕቃ የጫኑ ግመሎቻቸውን እየሳቡ ወደ ከተማ ይገባሉ፡፡ ባጠገቡ ገበያተኞች ሲያልፉ ፍርሀቱ መለስ ትልልታለች፡፡
ዓለሙ እነአባ አረጋዊ ቤት ጀርባ ባለው ጠባብ ሸለቆ፣ግርጌ ካለችው ምንጭ ቀድቶ፣ቶሎ ለመገላገል ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ውኃ ሊቀዳ የመሸበት ሰው እንዳለ በማሰብ፣ቁልቁል ጨለማ ወደ ዋጠው ሸለቆው እየተመለከተ ተጣራ፡፡ ጮኾ ጮኾ የሚመልስት ቢያጣልቡ ፍስስ አለችበት፡፡ ከሸለቆው ማዶ ጉብታ ላይ ፈንጠር ፈንጠር ካሉ ጎጆዎችየሚወጣ የብርሃን ጭላንጭል በሩቅ ይታያል፡፡ጆሮውን አንቅቶ ሲያዳምጥበየበረቱየተዘጋባቸው የቤት እንሰሳት ድምጽ በቀር የሰው ድምጽ ፈጽሞ አይሰማም፡፡ ጸጥታው ያስፈራል፡፡ብቻውን ቁልቁለቱን ወርዶ፤ ውኃ ከምንጯ ቀድቶ፤ ቀጥ ያለውን አቀበት መልሶ እስኪወጣ ድረስ ግፋ ቢል የሚወስድበት ጊዜ ከአስራ አምስት ደቂቃ አይበልጥም ነበር፡፡ ሆኖም ፍርሀቱ አሸንፎት አንድ እርምጃ መራመድ አልቻለም፡፡
በቀን ብርሃን ሸለቆም ማዶ ካሉት ጓደኞቹ ጋር ለመጫወት፣ ብቻውን ያንን ሸለቆ ወርዶና ወጥቶ ያለምንም ስጋት ይሻገር ነበር፡፡ ከምንጩ ግራና ቀኝ፣ትንሽ ራቅ ብሎ፣ ሰው የማይደፍራቸው በርካታ ዋሻዎችእንዳሉ ያውቃል፡፡በየዋሻዎቹ ውስጥ የነጋበት ጅብ እንደሚደበቅ ስለሰማ፣ ብቻውን ወደ ምንጯ መውረድ ፈጽሞ እንደማይችል ገብቶታል፡፡ በዚያ ላይ“ጅብ የሰደበውን ያውቃል”ሲባል ስለሚሰማ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ዋሻዎቹ አፍ ድረስ ተጠግተው፣ ጅቡን እየተሳደቡ ድንጋይ የወረወሩበትን በርካታ ጊዜያት አሰበና መላአካለቱን ፍርሀት ወረረው፡፡ አንድ ቂም የያዘበት ጅብ ሊበላው ቢመጣ ማንም እንደማያስጥለው ሲያስብ፣ጥርሶቹ በፍርሀት ተንገጫገጩ፡፡
ይህም ሆኖ ወደቤት መመለስ አይታሰብም፡፡ ብቸኛው አማራጭ ወደ ጸሀይ መውጫ አቅጣጫ፣ሁለት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኘውና “ለጋሸንበቆ”ተብሎ ወደሚጠራው ምንጭ ደፍሮ መሄድ ብቻ ነው፡፡ ጠመዝማዛ መንገዶችን ካቆራረጠ በኋላ ግማሽ ክብ ሰርቶ እንደዘንዶ ተጠቅሎ፣ወደቀኝ ከሚታጠፈው፣የመኪና መንገድ ድልድይ ራስጌ፣ሀያ ሜትር ገባ ብሎ ነው፣ምንጯን የሚያገኛት፡፡ ቁልቁል በሸለቆ መሀል መውረድ አይጠበቅበትም፡፡ ትንሹ ልጅ ለጋሸንበቆ መሄድ እንደሚሻለው ራሱን አሳመነና ጉዞውን ወደፊት ቀጠለ፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን መንገድ ላይ የሚያገኛቸው ለገበያ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ቆለኞች፣ባጠገቡ ሲያልፉ፣ፍርሀቱን እየቀነሰለት፣ራሱን እያደፋፈረ ወደፊት ቀጠለ፡፡
ተራራውን ታክኮ ወደግራ የሚታጠፈውን የመኪና መንገድ ጨርሶ ሁለቱን ተራራዎች የሚያገናኘውን ድልድይ ሲሻገር ጭርታው እየጨመረ መጣ፡፡ ፍርሀቱም ያንን ያህል ጨመረ፡፡ ሁለተኛውን ጠመዝማዛ መንገድ ሲጨርስ፣ አንድ ኪሎሜትር ተኩል ያህል እንደቀረው ገመተ፡፡ በስተግራ በኩል እላዩላይ አዚም የጣለበትን ተራራ አልፎ አልፎ አንጋጦ እያየ፣ በስተቀኝ በኩል ያለውን ጅው ያለ ገደል እየቃኘ፣እንደ እባብ ዚሃዚሃ የሚሰራውን መንገድ ተከትሎ ተዳፋቱንተያያዘው፡፡
ፍርሀቱን ለመርሳት ትኩረቱን ምንጯ ላይ ለማድረግ ሞከረ፡፡ አስፋልቱን ለቅቆ ከድልድዩ ራስጌ አግድም እንደተጓዘትልቁ ዋርካ ስር ይደርሳል፡፡ መሬት ላይ ወጥተው ለእግረኛ ደንቃራ የሆኑት ጥልፍልፎቹ የዋርካው ስሮች እንዳያደናቅፉት ተጠንቅቆ ማለፍ አለበት፡፡ ከዚያም በግራ በኩል ዋርካውን በግራ እጁ ደገፍ ብሎበዝግታ ተራምዶ፣ፊት ለፊቱ ካለው ድንጋያማተራራ ግርጌ ስር፣ ኩልል ብላ ወደምትፈሰው የምንጭ ውኃ ይደርሳል፡፡
ጓደኞቹ ዘንድ ለገተሚራ ወርዶ ሲመለስ፣ ወደ ምንጯ ጎራ ይሉና፣ በሙቀት የተቃጠለው ሰውነታቸውን ለማቀዝቀዝ በትንንሽ መዳፎቻቸው፣ ከምንጩ ውኃአፈስ አፈስ እያደረጉ ጥማቸውን ይቆርጣሉ፡፡ ውኃ ሊቀዱ የወረዱ ሴቶች ካጋጠሟቸው፣ከቅል በተሰራ ፎሌ፣ከምንጯ ቀድተው ሲሰጧቸው፣ ነፍሳቸው መለስ ትልላቸዋለች፡፡ ዓለሙእርምጃውን አፋጥኖ፣ሰውነቱ በፍርሀት እንደራደ፣ በግምት አንድ ኪሎ ሜትር ያህል እንደተጓዘ፣ ግመሎቹን እየሳበ፣ ከዶቅአ ወደ ከተማዋ የሚገባ አርብቶአደር ጋር ፊትለፊት ተገጣጠሙ፡፡ አርብቶ አደሮች በጨለማ መጓዝ ብርቃቸው አይደለም፡፡
ትንሹን ልጅ ለማደፋፈር ይሁን ለማስደንገጥ አርብቶአደሩ“ዲህዲዲዲዲ” ብሎ ሲጮኸበትለቅሶ የተቀላቀለበት ጩኸት አሰምቶ እንደ ወፍ ወደፊት በረረ፡፡ የትንሹን ልጅ የጣርጩኸት፣የገደል ማሚቶው እየተቀባበለ ሲያስተጋባ፣በጣም ሩቅ ከሆነ ቦታ “አይዞህ ማሙሽ” የሚል ድምጽ አስተጋባ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ገንቦው ከትከሻው ወድቆ እንዳይሰበር ጭምድ አድርጎ እንደያዘ ነበር፡፡
ወደኋላ ለመመለስ ቢፈልግ አሁንም አይችልም፡፡ በዚያ ላይ ዘመናቸውን በውትድርና ያሳለፉት አባቱ ፊት ባዶ ገንቦ ይዞ መቆም ለእርሱ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ በየጊዜው የሚተርኩለት ጨለማን ተገን አድርገው፣ በጠላት ላይ ያደረሱት የጥቃት ታሪክ፣በአእምሮው ውልብ አለበት፡፡እንደ አባቱ ጠላትን በደፈጣ የሚያጠቃ ወታደር ሳይሆን፣ከጠላት ጦር ጥቃት እንደሚሸሽ ፈሪ ራሱን አሰበ፡፡ብርድ ብርድ አለው፡፡ እጅ መስጠትም አልፈለገምና  የሩጫውን ፍጥነት ጨመረ፡፡
በስተግራ በኩል ያለውን ተራራ፣ ጥግጥጉን ይዞ የሚወርደውን ጠመዝማዛ መንገድ እንዳጋመሰ፣ ምንጩ ጋር ለመድረስ አንድ ኪሎሜትር ያህል ብቻ ቀርቶታል፡፡ ያንጊዜ ሩጫውን ቀንሶ ጆሮውን ቀስሮ አካባቢውን እያዳመጠ ተራመደ፡፡ በዚህ ሁኔታ ለጋሸንበቆ ለመድረስ ግማሽ ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀረው የበርካታ ልጆች ድምጽ ሲሰማ ተደናግጦ፣ ከመንገዱ ወጥቶ፣ ተራራው ስር ባለው አንዱ ቋጥኝ ልጥፍ አለ፡፡
ፍልውኃ ወርደው ሲታጠቡና አደን ሲያድኑ ውለው፣እጅብ ብለው እየተመለሱ የነበሩ የከተማዋ ወጣቶች መሆናቸውን ባለማወቁ  ነው ትንሹ ልጅ ቋጥኝ ስርየተሸሸገው፡፡እንደወትሮ ቢሆን ኖሮ ተላላፊ የጭነት መኪና ይዟቸው ወደ ከተማ ይገባ ነበር፡፡የገበያ ዋዜማ ስለነበረች፣በነጻ የሚያሳፍራቸው የጭነት መኪና አላገኙም፡፡ በእግራቸው ሲመለሱ መሽቶባቸው ስለነበረ ቤተሰቦቻቸው መጨነቅ ጀምረዋል፡፡ ለአደን የሚያስቸግሩ ሁለት ሰሳዎችን ግዳይ ጥለው በወሳንሳ ተሸክመው ስለነበር በድካም ዝለዋል፡፡
ወጣቶቹ ድካማቸው ሲበረታ የእርስ በእርስ ወሬያቸውን ትተው፣ በህብረት ሆነው የእስካውት ቦይ መዝሙር መዘመር ጀመሩ፡፡ “ዲንዲጎም ጎሎጎሊ ዋሻ፤ ዲንዲንጎም፤ ኤላ ኤላሽላ ኤላሆ…..” እንደ እንሽላሊት ቋጥኙ ስር ልጥፍ ያለው ዓለሙ፤ይህችን የግሪኮች መዝሙር ያውቃታል፡፡ በገደል ማሚቶ ታጅበው የሚዘምሩትን ዝማሬ ሲሰማ፣ከፍርሀቱ ወጥቶ በእፎይታ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡
ትንሹ ልጅ የጓደኛው ታላቅ ወንድም ከወጣቶቹ መካከል መኖሩን በድምጹ ሲለየው ፍርሀቱን እንዳያውቁበት ራሱን ለማረጋጋት ሞከረ፡፡ በረጅሙ ከተነፈሰ በኋላከተደበቀበት ቋጥኝ ስር ወጣ፡፡ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ለማሰብ እየሞከረ“ሰለሞን ሰለሞን” ብሎ ተጣራ፡፡
ድንገት ከቋጥኝ ስር ወጥቶ እየጮኸ የሚጣራውን የትንሹን ልጅ ድምጽ ወጣቶቹ ሲሰሙ፣ሁሉም ድንገት መዝሙራቸውን አቆሙ፡፡ ሰለሞን የታናሽ ወንድሙ ጓደኛ ዓለሙ እንደሆነ ነበር ወዲያው ያወቀው፡፡ ግራ በተጋባ ስሜት ውስጥ ሆኖ“ዓለሙ በዚህ ጨለማ እዚህ ምን ትሰራለህ?”በመገረም ጠየቀውና “የጎረቤቴ ልጅ  ዓለሙ ነው ተረጋጉ” አላቸው-ጓደኞቹን፡፡
ትንሹ ልጅ እንባው እንዳይፈስ እየታገለ በተሰባበረ ድምጽ፤ “ውኃ ልቀዳ መጥቼ ነው” አላቸው፡፡ ከዚህም ከዚያም “አይዞህ፤ አይዞህ፤ አትፍራ እኛ አለንልህ” ሲሉት እምባውን ዘረገፈው፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ገንቦውንከትንሹ ልጅ ትከሻ ላይ አውርዶለት፣ በቀኝ እጁ እያንጠለጠለ “ወደኋላ ከምንመለስ እነአባአረጋዊ ቤት ጀርባ ካለው ሸለቆ ወርደን ብንቀዳለት ይሻላል” ብሎ ሀሳብ አቀረበ፡፡ ሁሉም ተስማሙና ዓለሙ ፊቱን አዙሮ አብሯቸው ያቋረጡትን የእስካውት መዝሙር እየዘመረ ተመለሰ፡፡ ከብቸኝነት ወጥቶ ድንገት በበርካታ ወጣቶች ሲታጀብ፣ህጻኑ ልጅ እንደ ጠላት ሲያሳድደው የነበረው ፍርሀቱ፣በተራው ሸሽቶት ጥሎት ሲሄድ ተሰማው፡፡
ዓለሙብቻውን ሆኖ የፈራውን ሸለቆ፤ካጀቡት ወጣቶች ጋርለመውረድ ምንም አላስፈራውም፡፡ ለራሱ እስኪገርመው ድረስ ቅንጣት ታክል ፍርሀት በውስጡ አልነበረም፡፡ ከደቂቃዎች በፊት ሲያባርረው የነበረው የገዛ ፍርሀቱ፣ ደራሹ ሲጠፋ በትንሿ ልቡ ራሱን ወቀሰ፡፡ በእነዚህ ጨለማአይፈሬ ታላላቅ የሰፈሩ ልጆች ጀግንነት ተጅቦ፣ውኃውን ቀድቶ ወደቤቱ ሲመለስ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ሞከረ፡፡ በትንሹ ልጅ ፍርሀትና ለቅሶከወጣቶቹ መካከል የሳቀበትአልነበረም፡፡ የትንሹን ልጅ አባትም የወቀሰ አንድም ወጣት አልነበረም፡፡ ይልቁንም በጀግንነቱ እየተደነቁ ነበር ሲያወሩ የሰማቸው፡፡
ከዚያች ምሽት ጀምሮ ጨለማውን ቀስበቀስ ተለማመደው፡፡ ማንም ሳያዘው ገና ደንገዝገዝ እንዳለ ገንቦውን ይዞ ወደ ምንጭ መውረድ ጀመረ፡፡ እየቆየ በሄደ ቁጥር በተለይ እሁድ ምሽት፣ በገበያ ዋዜማ በመንገዱ ሰው ስለማይጠፋ፣ወደ ለጋሸንበቆ መውረድ ያስደስተዋል፡፡ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት እያመሸ፣ ምንጭ ወርዶ ውኃ መቅዳት ተለማመደ፡፡ በጊዜ ሂደት የጨለማውን ፍርሀት አሸንፎ ከጨለማው ጋር ተወዳጀ፡፡
ፍርሀቱ እየለቀቀውከጨለማው ጋር እየተወዳጀ ሲሄድ፣እርሱም በተራው ለመጀመሪያ ጊዜ ያስደነገጠውን የአርብቶ አደር ቃል ድምጽ አስመስሎ በሚያስደነግጣቸው ሰዎች መሳቅ ጀመረ፡፡ ካደፈጠበት ቦታ ድንገት ብቅ ብሎ “ዲህዲዲዲዲዲ” እያለ በጩኸት ባጠገባቸው ያልፍና ቁልቁል ወደ ለጋሸንበቆ በሩጫ ከፊታቸው እንደ ጭልፊት ይሰወራል፡፡ በሰዎች ፍርሀት አያሌ ምሽቶችን ድምጹ አጥፍቶ ብቻውን ከተከት ብሎ ስቋል፡፡ ከድንጋጤቸው መለስ ሲሉ የረገሙት ሰዎች ቁጥርም ቀላል አልነበረም፡፡ አንድ ቀን አንድ ተላላፊ መንገደኛ፣በድንጋጤ አንካሴ ወርውሮ ከሳተው ወዲህ፣ ሰዎችን በጨለማ ማስደንገጥ አቆመ፡፡ አንካሴ የወረወረውም ልጅ በድንጋጤ ዘሎ፣ወደሸለቆው ሲወርድ፣ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ወደ አቅራቢያው መንደር ተመልሶ ባለአንካሴውን ልጅ እግር መንገደኛ ከወደቀበት ገደል ቢያስነሳውም፣በዚህ ድርጊቱ ሲበዛ ነበር የተጸጸተው፡፡
ዓለሙ ጎረመሰ፡፡ የስድሳ ስድስቱ አብዮቱ ጭካኔው በርትቶ፣ ሰውን በጅምላ መብላት ሲጀመር ነበር በአራተኛው ዓመት ላይ ራሱን በቆላማውየአፋር ምድር ላይ ያገኘው፡፡ አራተኛው አብዮት በተከበረ በማግስቱ ኳስ ሊጫወት እንደወጣ በዚያው የቀረው፡፡ይህች አገር ድብልቅልቋ ሲወጣ  በአፋር ምድር ከሰው ይልቅ ከጨለማ ጋር የልቡ ወዳጅ ሆኖ፣ያንን ክፉ ዘመን በሰላም አሳለፈ፡፡ በጠራው የበረሃ ሰማይ፣በምሽት የሚፍለቀለቁትን ክዋክብት መመልከት ያስደስተዋል፡፡ ሙቀቱ ብርቱ በሆነበት ወራት የቤቱ ጣሪያ ላይ ወይም ከቤቱ ትይዩ ባለው መስክ ላይ ነበር ሌሊቱን የሚያሳልፈው፡፡እንቅልፍ እስኪወስደው የክዋክብቱን አቀማመጥናእንደ ጎርፍ የሚፈሰውን የክዋክብት ብዛት እየተመለከተ፣ በመደነቅ ነበር የሚያመሸው፡፡  
ተረኛ የምሽት የመስኖ ሰራተኛ ሲሆንበግምባሩ ላይ የሚታሰር የእጅ ባትሪ ቢሰጠውም እምብዛም ባትሪውን አይጠቀምበትም፡፡ በቦይ ተጠልፎ የሚፈሰውን የአዋሽ ወንዝ ማከፋፈያ ስርጭቱን አመጣጥኖ መዘውሩን ሲያንቀሳቅስ ባትሪ ፈጽሞ አይጠቀምም፡፡አንዳች ነገር የቦዩን ፍሰት ካገደው ውኃው ውስጥ ገብቶ ውኃው እንዳይተላለፍ ምክንያት የሆነውን ባዕድ ነገር ጎትቶ ሲያወጣ ሁሉ በጨለማ ነው፡፡በአጋጣሚ ሱፐርቫይዘሮች ተገኝተው ባትሪ ሲያበሩበት ባትሪውን እንዲያጠፉ ይጮህባቸው ነበር፡፡ በዚህ ባህሪው ሁልጊዜ እንደተገረሙ ነበር፡፡
ዓለሙ መንገድ እየሄደ ቢሆንፈጽሞ ባትሪውን አያበራም፡፡ አስፈላጊ ከሆነ አንድ ረባዳማ ቦታ ፈልጎ ቁጢጥ ይልና የብርሀን ማስተላለፊያውን መስታወት በመዳፉ ካፈነ በኋላ ነበር ባትሪውን የሚያበራው፡፡ ምንም ቢፈጠር ደፍሮ ባትሪውን አሻግሮ አያበራም፡፡ በወጋገኑ ብቻ ነው ለማየት የሚጥረው፡፡ አባቱ የነገሩትን ታሪክ እያስታወሰ፣በጉዞ ላይ እያለ ባትሪ ካበራ፣በጨለማ ውስጥ ጠመንጃ አድፍጦ የሚጠብቀው ሰውየተኩስ ዒላማ ውስጥ የሚገባ ይመስለዋል፡፡ባትሪ የሚያበሩ ሰዎችን ከሩቅ ሲያይ ሰውነቱ ሽምቅቅ ይልበታል፡፡
ዓለሙ በበጨለማ ውስጥ መጓዝ እጅግ ያስደስተዋል፡፡ ጨለማው ጥይት እንደማይበሳው ጋሻ ሆኖ ያገለግለዋል፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ጆሮዎቹ የዓይን ያህል ሲያበሩለት ይሰማዋል፡፡ ከኋላውና ከፊቱየሚንቀሳቀስ ነገር ድምጹ በነፋስ ተጉዞ አስቀድሞ ወደ ጆሮው ሲደርስ ዛፍ፤ ቅጠል፤ ሰው፤ እንሰሳ መሆኑን በቀላሉ ይለየዋል፡፡ በርከት ያለ ኮቴ ከሰማ ጆሮውን መሬት ላይ ለጥፎየሚሰማውን ነገር ምንነቱን፤ ብዛቱንና ርቀቱን ጥሩ አድርጎይገምታል፡፡አንድ ምሽት ይኸ ዓመሉ ላልተጠበቀ አደጋ ዳርጎት ነበር፡፡ ስራውን ለተረኛው አስረክቦ ወደ ካምፑ ሲመለስ፣ከምሽቱ አራት ሰዓት ሞልቶ ነበር፡፡ በጊዜያዊነት የሚኖርባት ካምፕ፤ ዕውሪቱ ካምፕ ተብላ ነው በወዛደሮቹ የምትጠራው፡፡መብራት ስለሌላት ነው ዕውሪቱ ካምፕ የተባለችው፡፡ በስራ ተጠምዶ ስለዋለ ደክሞታል፤ እርቦታልም፡፡
ወትሮ የሚሄድበት መንገድ ላይ ችግር ተፈጥሯል፡፡ መንገዱን ውኃ ሰብሮት ትልቅ ሸለቆ ስለሰራ ጭቃው በእግር ለመሻገር አያስችለውም፡፡ በእርሻው ዳርቻ የተዘረጋውን ዙሪያ ጥምጥም መንገድ ተከትሎ እንዳይሄድ በትንሹ አንድ ድፍን ሰዓት ይፈጅበታል፡፡ፊትለፊቱ ያለውን በኤሌክትሪክ ብርሃን የደመቀካምፕማቋረጥከደፈረ ደግሞ ዕውሪቱ ካምፕ ለመድረስ ግፋ ቢል ሀያ ደቂቃ ይበቃዋል፡፡
በኤሌክትሪክ የደመቀውን የቋሚ ሰራተኞች ካምፕ አቋርጦ ለመሄድ ወሰነ፡፡ ካምፑ ዙሪያው በሽቦ የታጠረ ነው፡፡ ሁለት ዋና መግቢያና መውጫ በሮች አሉት፡፡ከዋና በሮቹ በተጨማሪ ጥበቃ የሚካሄድባቸውን ቦታዎች ያውቃል፡፡ በዚያ ምሽት ደግሞ ካምፑን አቋርጦ እንዲሄድ፣ የጥበቃ ሰራተኞቹ አይፈቅዱለትም፡፡ ጨለማ የዋጠውን አካባቢ መርጦ ሽቦ አጥሩን ሾልኮ፣በመንገዶቹ ዳርና ዳር የተተከሉት ዛፎችን ከለላ አድርጎ፣ የመረብ ኳስ ሜዳውን በሰላም አለፈ፡፡ ከመረብ ኳስ ሜዳው ጎን ሰራተኞቹ ሲዝናኑ የሚያመሹበትክበብ አለ፡፡ ሠራተኞች መስኩ ላይ ሰብሰብ ብለው ሞቅ ያለ ጨዋታይዘዋል፡፡ ጨለማውን አሳብሮ የሚመጣው ሞገድ፣የሚያወሩትን ወሬ ለጆሮው ያቀብለዋል፡፡ መዝናኛ ክበቡን ወደግራ ትቶአለፈ፡፡ ከዚያም ጥግጥጉን ዛፎቹን ከለላ አድርጎ መንገዱን ተያያዘው፡፡ ይሁንና መንገዱን ለመሻገር ግራና ቀኝ በተሰቀለው ምሰሶ ላይ የሚያበራው የፍሎረሰንት መብራት፣እይታ ውስጥ እንደሚከተው ሲረዳ፣ እርምጃውን ገታ አደረገ፡፡ መንገዱን አሳብሮ ውኃ የሚፈስበትን ቦይ በዝላይ ከመሻገሩ በፊት፣ዛፍ ጥላ ስር እንደቆመ አካባቢውን ቃኘ፡፡
ጥቅጥቅ ያለው ዛፍ በስተግራ በኩል ያለውን ዕይታውን  ሸፍኖበታል፡፡ ትንሽ አመነታ፡፡ ጆሮውንም ቀስሮ ለማዳመጥ ሞከረ፡፡ ቅር እያለው ከተከለለበት ሲወጣ፣በመጠጥ ሞቅታ ውስጥ ሆነው ወደቤታቸው የሚሄዱ ሁለት ሰዎች፣ወደቀኝ ሲታጠፉ፣ፊትለፊት ተገጣጠሙ፡፡ ያልጠበቁት ነገር ነበርና ሁለቱም ወገኖች እንደተደናገጡ፣ በያሉበት ለአፍታ ተፋጥጠው ቆሙ፡፡ ዓለሙ በቀኝ ትከሻው ላይ የተሸከመው አካፋ ወደሰማይ ተወድሯል፡፡
ድንጋጤው መለስ እንዳለላቸው፣ በመጠጥ ሞቅታ ውስጥ ሆነው፤“ማነህ አንተ? እዚህ ምንትሰራለህ?”ሲሉ በጥያቄ አጣደፉት፡፡ ስራ አምሽቶ ወደ ዕውሪቱ ካምፕ እየሄደ መሆኑን በእርጋታአስረዳቸው፡፡ የነገራቸውን አላመኑትም ነበር፡፡ “ስራ ያመሸህ ብትሆን ኖሮ እዚህ አታደፍጥም ነበር፡፡ ታስታውቃለህ አንተ ጸረ አብዮተኛ ነህ፤ ቅደም!” ብለው ሲያምቧርቁበት፣ አሁንም እንደተረጋጋ “እሽ ጓዶች፤ወዴት ነው የምቀድመው?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ አቅጣጫውን እያሳዩት “ወደ አብዮት ጥበቃ ቢሮ ነዋ! ኋላ የት ኖሯል? ይልቅ ሳትበላሽ ቅደም” ሲሉት ምንም ቃል ሳይነተፍስ፣ወደ አሳዩት አቅጣጫ አንድ ሁለት እርምጃ እንደተራመደ፣አንደኛው “አካፋውን አምጣ” ብሎ አዘዘውና፣ ሊቀበለው እጁን ዘረጋ፡፡
ዓለሙየመሀል አገሩን ትንቅንቅ ክፉ ዘመን ለማለፍ አስቦ ነበር፣ ትምህርቱን አቋርጦ በረሃ የወረደው፡፡ እንዳዘዙት ቢፈጽም በራሱ አካፋ ማጅራቱን መትተው ሊጥሉት ይችላሉ፡፡ አካፋውን እንዲሰጣቸው ያዘዙት ፈርተውትም ሊሆን አንደሚችል ገመተ፡፡ ሆኖም የትኛውንም የራሱን ሀሳብ ማመን አልፈለገም፡፡ ያዘዙት ቦታ በሰላም ቢደርስ በሚያቀርቡለት አስልቺጥያቄ፤ተማሪ እንደሆነ በቀላሉ እንደሚደርሱበት ያውቃል፡፡ ያንጊዜ ደግሞ ተማሪ መሆን በራሱ በኢህአፓነት ለመፈረጅ ከበቂ በላይ ነበር፡፡
በዕድሜ ጠና ያለው ሰውዬ አሁንም፤“አካፋውን አቀብለኝ እኮ ነው የምልህ”አለው፡፡ የሰውየውን ፍርሀት የገዛ አንደበቱ እንዳሳበቀበት ተገንዝቧል፡፡ በዚያ ላይ በየቤታቸው ያሉ ሰዎች ጭቅጭቁን ሰምተው ከወጡ የባሰ ችግር ውስጥ እንደሚገባ ሲያስበው፣ ሰውነቱን አንዳች ስሜት ሲወረው ተሰማው፡፡አካፋውን ለመስጠት ዘወር እንዳለነበር፣በብርሃን ፍጥነት፣በአካፋው ጀርባ፣ተከታታይ ምት ያሳረፈባቸው፡፡ አንዳቸውም ድምጽ ሳያሰሙ አንዱ ወደጎኑ፣ አንዱ ወደኋላው፣እጥፍጥፍ ብለው ወደቁ፡፡ውኃ የሞላውን ቦይ፣እንደ ነብር ዘሎ ጨለማው ውስጥ ተሰወረ፡፡
አስቀድሞ እንዳሰበው ሰው የማይንቀሳቀስበትን አሸዋማውን መንገድ አቋርጦ፤ የውሃ ማከማቻ ታንከር የተተከለበት በአሸዋ የተሸፈነ መለስተኛ ኮረብታ በስተግራ በኩል ድምጹን አጥፍቶ በሰላም አለፈ፡፡ ኮረብታው ላይ የጥበቃ ሰራተኞች እንዳሉ ያውቃል፡፡ በነጭ ቀለም ያሸበረቀ ባለአንድ ፎቅ ግዙፍ ህንጻ ውበት፤ ልጅ ሆኖ ያየውን የህንድ ፊልም አስታወሰው፡፡ በዚህ በረሃ መሀል ምን ሊሰራ የቆመ ህንጻ እንደሆነ እየገረመው፣ ፈጠን ፈጠን ብሎ፣ ህንጻውን በቅርብ ርቀት አለፈ፡፡ ጥበቃ ሰራተኛው ሲያንኮራፋ ከሩቅ ይሰማል፡፡ ውቡን ህንጻ ወደቀኝ ትቶ፣ ማንም ዝር ወደማይልበት የሎሚ ተክል ፈጥኖ ሲገባ እፎይታ ተሰማው፡፡ የሎሚው ጠረን ልብን ያውዳል፡፡ እሾኃማው የሽቦ አጥር እንዳይወጋው ተጠንቅቆ፣በደረቱ መሬት ላይ ልጥፍ ብሎ፣ አጥሩን ሲሾልክ ፣እፎይታ ተሰማው፡፡ የጥጥ ቡቃያው መሀል ያለውን ዱጋ (ቁልል አፈር) ተከትሎ ጥቂት እንደተጓዘ፣ የተኩስና የሰው ጫጫታ ድምጽ ከኋላው ከርቀት ተሰማው ፡፡ በአካፋ የጣላቸው ሰዎች መንገደኛ እንዳገኛቸው ተስፋ አድርጎ፣ ወደፊት ገሰገሰ፡፡ በሰራው ነገር ተጸጸተ፡፡
ሊነጋጋ ሲል ለማንም ሳይነግር እውሪቱን ካምፕ ለቆ፣አንዲት ትንሽ ከተማው አቅራቢያ ወዳለው እርሻ ጣቢያ ሄዶ በጉልበት ሰራተኛነት ተቀጠረ፡፡ የአስር ቀን ጆርናታውን (ደመወዙ) ጥሎ መሄዱ ቢቆጨውም ፣ዳግም ወደ እውሪቱ ካምፕ አልተመለሰም፡፡ ዓለሙ የከተመበት አዲሱ ካምፕ አጠገብ የከተማ ወግ የያዘች ትንሽ መንደር አለች፡፡ መንደሪቱ ንግድ ቤቶች፤ ጠጅ ቤቶች፤ ቡናቤቶች አሏት፡፡ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር የቆርቆሮ ቤት በመንደሪቱ አይታይም፡፡ የቤቶቹ ጣሪያ በአፈር የተሸፈነ ነው፤ ግድግዳዎቹ  በጭቃ የተለሰኑናቸው፡፡ ጣራ በአፈር መሸፈን የበረሃ ቤቶች ወግ ነው፡፡እግር የጣለው እንግዳ ከእነሕይወቱ መቃብር የገባ ሊሰማው ይችላል፡፡ያች ሚጢጢ መንደር፣ፖሊስ ጣቢያም ሆነ ፍርድ ቤት ወይም ሌላ የመንግሥት መስሪያ ቤት የላትም፡፡
በዚያች የከተማ ወግ ባላት መንደር፣ሰው ራሱን ችሎ መኖር ይጠበቅበታል፡፡ ከቻለ በሕይወት ይኖራል፤ (survival of the fittest) ካልቻለም ወይ አንዱ ቡድን ጋ ይጠጋል፤ ካልሆነም እቤቱ በጊዜ መክተት ይኖርበታል፡፡ ዓለሙ ጠጅ መቀማመስ ወይም ቢራ መጠጣት ሲያምረው፣ የልቡ ወዳጅ የሆነውን ጨለማውን ተማምኖ ነው ከቤቱ የሚወጣው፡፡አንድ ምሽት ፋጤ ጢኒቂሎ ጠጅ ቤት፣ ጠጅ ቀማምሶ ሲወጣ፣ገና የደጁን ጉበን እንደረገጠ ነበር ዱላ ያረፈበት፡፡ ለአናቱ የተሰነዘረው የቀኝ ጆሮውን በጨረፍታ ነክቶትትከሻውላይ አረፈበት፤የፈሪ በትር ባይሆን ኖሮ ሕይወቱን ያሳጣው ነበር፡፡ ከዚያ አደጋ ከተረፈ ወዲህ ምሽት ላይ ወደ መሸታ ቤት ጎራ ሲል፣በገባበት ደጅ ተመልሶ ወጥቶ አያውቅም፡፡
መሸታ ቤቶቹ መደዳውን ሰልፍ ሰርተው የተደረደሩና ኩታ ገጠም ናቸው፡፡ ሁሉም መሸታ ቤቶች በፊት ለፊትና በጀርባ በኩል መግቢያና መውጫ አላቸው፡፡ መጠጥ ሲጠጣ ያመሸ ሰው፣በፊትለፊትም ሆነ በኋላ በር ከመውጣቱ በፊት የበሩን ጉበን እንደረገጠ፣የሚጠብቀውን አደጋ መገመት ይኖርበታል፡፡ ጨለማውን ተገን አድርጎ የጠገበ ዱላ የያዘ ሰው፣ በሩ ጥግ መኖር አለመኖሩን ሳያረጋግጥ የሚወጣ በነፍሱ የፈረደ ነው፡፡
ከዚያች ቀን ወዲህ ዓለሙ ሊቀማምስ ፣ከጓደኞቹም ሆነ ብቻውን ሲወጣ፣ የሚቀመጠው በጀርባ በኩል ካለው የቤቱ ታዛ ስር ነው፡፡ ዓይኑ ጨለማውን ስለሚለማመድ የሚገባ የሚወጣውን መቆጣጠር ያስችለዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ባርኔጣ አድርጎ ሲገባ ይታይና፣ዱላውን በቁመቱ ልክ አድርጎ ባርኔጣውን ዱላው ላይ ይሰቅልና ወደውጭ ብቅ ያደርጋታል፡፡ ዓለሙን ያገኙት መስሏቸው አንድ ሁለት ቀን ባርኔጣው ዱላ ሲያርፍባት፣ ደፍ ብላ ወድቃለች፡፡ አደጋ ያደረሰው ሰው፤ ከዚያ በኋላ ድራሹ ይጠፋል፡፡ ምን ማንን በምን ምክንያት እንደሚመታው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እንዲህ ዓይነት ብልሀት ሁልጊዜ እንደማያዋጣ ስለሚያውቅ፣ውጭ ተቀምጦ የሚወጣ የሚገባውን እየተከታተለ ነው፣ መጠጥ መቀማመስ የሚመርጠው፡፡
ዓለሙ ከአስር ዓመት በኋላ ነበር ወደ መሀል አገር የተመለሰው፡፡ ኑሮውን አዲስ አበባ ሲያደርግ   በምሽት በብርሃን መጓዝ፣ እጅግ ሲበዛ ፈተና ሆኖበት፣ለብዙ ጊዜያት ተቸግሯል፡፡ያቋረጠውን ከፍተኛ ትምህርት በማታው ክፍለጊዜ ቀጥሏል፡፡በምሽትብርሃን በሚፈስበት ጎዳና፣ከታክሲ ሲወርድ ምቾት አይሠጠውም፡፡ ወደሰፈሩ የሚወስደው ጨለማ መንገድ ውስጥ ገብቶ እስኪሰወር ድረስ አስር ጊዜ  እየተገላመጠ ነበር የሚራመደው፡፡ ልማድ አለቅ ብሎት የቻለውን ያህል ከኤሌክትሪክ መብራት ርቆ ነውይጓዝ የነበረው፡፡መብራት በመጥፋቱ ምክንያት የእኛን መብራት ኃይል የማይወቅስ ሰው ቢኖር ዓለሙ ብቻ ነው፡፡
ጨለማ አያስፈራውም፡፡ እርሱን የሚያስፈራው ትውስታ ነው፡፡ ባይሳካለትም በሕይወት የሌሉ ወላጆቹንና ዘመዶቹን ማስታወስ አይፈልግም፡፡ ትውስታ ውስጥ ሲገባ ለምን እንደሚረበሽ አያውቅም፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ብቻውን ይሰማቸው የነበሩ ሙዚቃዎች በቴሌቪዥን ጣቢያ ሲተላለፉ ካየፈጥኖ ጣቢያውን ይቀይረዋል፡፡ በዝምታ ተውጦ በልቡ ውስጥ የሚመላለስ አንዳች ነገር ሳይኖር፤ አእምሮውም ሆነ አንደበቱ አንዳችም ቃላት ሳያወጡ፣በሰማይ ላይ የፈሰሱትን ክዋክብት ሲመለከት እፎይታ ይሰማዋል፡፡ በዝምታ ውስጥ ሆኖ ለጸሎት ሲንበረከክ ከእግዚአብሔር ጋር አንዳች ቃል ሳይነጋገር፤ አንዳችም ሀሳብ በአእምሮው ሳይመላለስ፤ መቆየት እፎይታ ይሰጠዋል፡፡ ምንም ሳያስብ፤ ውስጡ ባዶ ሆኖ፤ የሚፈልገውንና የሚሻውን ሳይጠይቅ በዝምታ ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት መንበርከክ ተለማምዷል፡፡ ውስጡ ባዶ ሲሆን ትውስታው ከፊቱ ዘወር ይላል፡፡ የኋላውን ጥሎ ትውስታውን አራግፎ ወደፊት ያያል፡፡
የምንጭ ውኃ ሊቀዳ ብቻውን የወረደባትን ያችን የመጀመሪያ ምሽትማስታወስ አይፈልግም፡፡ ትውስታው ያስፈራዋል፡፡ በጨለማ ውስጥ ሆኖ ክፍሉ ውስጥ ሲተኛ በቀይሽብር ዘመን የወደቁትንአብሮ አደግ ጓደኞችን ይረሳል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት በጨለማው ውስጥ ሲንበረከክ ትናንትን ሳያስብ፤ ነገን እያለመ ሁሉን ይረሳል፡፡ በአርምሞ ድቅድቅ ጨለማ ባለበት ሱባኤ መያዣ ዋሻ ውስጥ ለቀናት፤ ለሳምንታትና ለወራት ከሰው ተለይቶ ሲቀመጥሁሉን ይረሳል፡፡ እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው ምርምሮ እንዳያገኝ፣ በሰው ልጆች ልብ ሁሉ ዘላለምነትን የሰጠው መሆኑን በልጅነቱ ከመምሬ ታረቀኝ አንደበት ሰምቷል፡፡በመምሬ ታረቀኝ ሀሳብም ልቡ ይስማማል፡፡ በጨለማው ውስጥ ሲሆን ሞቱን አያስብም፤ ዘላለማዊነት በውስጡ ይፈሳል፡፡ ትውስታውን ግን ለምን እንደሚፈራ አያውቅም፡፡  

Read 371 times