Monday, 04 May 2020 00:00

አይባልም

Written by  አዛኤል
Rate this item
(0 votes)

   "በመኖር ያልተገለጠ እምነት፤ እንኳን እምነት እውቀት አይባልም"
                 
"ቢስሚላሂ ብዬ እስቲ ልናገር
አለቢስሚላሂ አያምርም ነገር
ስራም ንግግሬ ጭራሹ እንዲያምር...."
(ሼህ መሀመድ አወል)
ቢስሚላህ ረሂማን ረሂም!!
የአለም የሰላም ሀይማኖት ኢስላም መሰረቱ፣ የአላህ እዝነት እንደሆነ የቅዱስ ቁርአን መጀመሪያው ይመሰክራል፡፡ ሩህሩህና አዛኝ በሆነው በአላህ ስም!! በሚል የርህራሄ ቃል የአላህን እዝነት በመለመን መፅሐፉ ትልቁን እውነት ያበክራል፡፡
ርህራሄን
እዝነትን
ራህመትን
ቸርነትን::
.... ሌሎችም ትዕዛዞች ሁሉ የሀይማኖቱ አምዶች፣ ሰውን ያስቀደሙ ከአምላክ የተቀሰሙ መገለጦች ናቸው፤ ይሉናል የተገለጠላቸው ሰሀባዎቹ፡፡
"...አንድ ሰው የተራበና የታረዘ እንግዳ ከመጣበት (ከመጣለት) ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡ ሕይወት ከአንዲት ግመሉ ውጪ ሌላ ሀብት ባይኖረው እንኳ እርሷኑ አርዶ እንግዳውን ያስተናግድ ነበር፡፡ ... የጥንት ዐረቦች የወይን ጠጅ በሚጠጡ ጊዜ ለቸርነት ባህሪ ስለሚገፋፋቸው፣ የወይንን ዛፍ "ከረም" (ቸርነት) በሚል ስያሜ ይጠሩታል፡፡ የወይን ጠጅን ደግሞ "ኢብነልከሪም " (የቸርነት ልጅ) ይሉታል፡፡ ቸርነትን በጥንታዊ ግጥሞቻቸው ሳይቀር ያነሳሱት ነበር፡፡ ......" እያለ የጥንት ዐረብ ልማድን ያወሳናል፤ ኢትዮጵያዊው የእስልምና መምህሩ ሀሰን ታጁ ፡፡
መሬት ስናወርደው.....
በአላህ ማመን በአላህ ፍቃድ ለተፈጠረ ሰው ከማዘን እንደሚቀዳ የዘመናዊው ኢስላም ዩኒቨርሲቲ መምህራን ይተነትናሉ፡፡ በተለይም የሀይማኖቱ አምድ ከሆኑት ውስጥ ታላቁ ነብዩ ሙሐመድ ህይወታቸውን መራራታቸውን የአዳም ዘር ሁሉ ሊቀዳ ይገባዋል፡፡ "እስልምናን ማወቅ የፈለገ የርሳቸውን ሕይወት ይወቅ፡፡ ቁርአንን መረዳት የሚሻ የርሳቸውን ህይወት ይረዳ፡፡" ባይ ናቸው፤ የነብዩን የሕይወት ታሪክ የከተቡ ልሂቃን፡፡ በተለይም በዚህ በረመዷን ወር ላይ የነብዩ ዋና ትዕዛዝ እዝነት ነው፡፡ ወሩም የአላህን እዝነት የምንጠይቅበት ነውና፡፡  "ረሒቀል መኽቱም" በሚል የተፃፈ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የህይወት ታሪክ  በሸኽ ሶፍዩራህማን አልሙባረክ ከፉሪ አንድ ትልቅ ሀሳብ አለው፡፡ "እድሜያቸው 40 ሲደርስ የነብይነት ምልክቶች ይታዩባቸው ጀመር፡፡ በሂራእ ዋሻ ውስጥ መገለል በጅመሩ በ3ኛው አመት በወርሃ ረመዷን አላህ ለሰው ልጆች 'እዝነቱን' ለመለገስ በመሻት በነብይነት አላቃቸው፡፡ ጅብሪል የቁርአን አንቀጾችን ይዞላቸው ወረደ::..." ፡፡
እውነቱን ለመናገር በዚህ ሀሳብ ውስጥ "እዝነቱን" የሚለው ቃል ወደ ልባችን መፍሰሱ አይቀርም፡፡ የአምላክ እዝነት መገለጫ ነው የነብዩ መመረጥ፡፡ ለሰው ልጅ ደግነት ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ አላህ አላቃቸው፡፡ እርሳቸውም 'ላ' የሚል ቃል ከአንደበታቸው የማይወጣ፣ ሁሉን እሺ የሚሉ የሺዎች መሪ የሚሊየኖች ምሳሌ የቢሊየኖች መምህር ናቸው፡፡ ነብዩ ሙሐመድ፡፡
የረመዷን ወር እና እርሳቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት መልክ ናቸው፡፡ ብዙ የእስልምና መምህራን፤ የርሳቸውም የነብይነት ብስራት ወር ነው ይሉታል፡፡ "ሂራእ ውስጥ ቆይታ ያደርጉ የነበረው በረመዷን ነበር፡፡ ጅብሪል ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኛቸውም በዚያው በረመዷን ወር ነው::" ብለው ቁርአንን ማስረጃ ያደርጋሉ፡፡
 "የረመዷን ወር .....ቁርአን የወረደበት ወር ነው፡፡"
(አል በቀራህ ፡185)
ሌላ መሬት ስናወርደው....
በክርስትናውም ቢሆን ይህ ሀሳብ የፅድቅ የመዐዘን ድንጋይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለ ሌሎች ማሰብ፡፡ ስለ ሌሎች መኖር፡፡ እንደ ክርስቶስ ስለ ሌሎች መሞት፡፡ ክርስትናው በመፅሐፍ ብቻ ሳይሆን በዜማም ሳይቀር ቀምሮ አኑሮታል፡፡ ከያሬድ ሶስት የዜማ ቀመሮች መሀል "አራራይ" አንዱ ነው፡፡ ማራራት ለሰው እንደ ሰው፣ የሰውን ህመም  መሰማት  ማሰማት እንደ ማለት ነው፡፡ ስነ-ልቦናው ደግሞ የሰውን ችግር እንደ ራስ ማየት በሚል ትርጉም ስር empathy ይለዋል፡፡
ወገን.......
እውቀት ማለት የተረጋገጠ እምነት፤ እምነት ማለት ደግሞ ያልተረጋገጠ እውቀት ነው፤ ቢሉም ዘመናዊ ፈላስፎቹ፤ የሁለቱን ትንታኔ ከማስቀመጥ ይልቅ በሀይማኖት መቀመጥ ከብዙ የእብደት ጣጣ እንደሚጠብቅ ደግሞ የሀይማኖት ተንታኞቹ ያስቀምጣሉ፡፡ ማወቅ በመኖር መገለጥ አለበት እና ነው፡፡ አለም ለሚያውቁ ቦታ ስትሰጥ ... ሀይማኖት ደግሞ ያወቁትን ለሚኖሩ ሰፊ ክብርን ትቸራለች፡፡ "ሀይማኖት እንተአልባአቲ ምግባረ ሰናይ ሙት ይእቲ" ሀይማኖት ያለ ምግባር ሙት ነው፡፡ ለዚህም ነው ስለ ቸርነት ማወቅ ቸር አያደርግም የሚሉን፡፡ ቸርነት የሚኖር እውነት ነው፡፡ እዝነት ስለ ሌሎች የሚከፈል የመክፈል አቅም ነው፡፡ ማዘን ያልቻለ አማኝ መብረር እንደማይችል ክንፍ ነው፡፡ ክንፋችን ይበር ዘንድ አብሮን ካልሆነ ሸክም ነው፡፡ ሀይማኖትም እንኖሮበት ዘንድ አብሮን ካልሆነ ሸክም ነው፡፡ እንጠየቅበታለን፡፡ የክርስትናውን ሁዳዴ ፆም ፈፅመን የእስልምናውን ረመዷን ጀምረነዋል፡፡ በመከራ የተጠጋነው ጌታ በደስታም እንዳንተወው፣ ትምህርቱ ከተአምራቱ ጋር በነፍሳችን መቀመጥ አለበት፡፡
በመኖር ያልተገለጠ እምነት እንኳን እምነት እውቀት አይባልም፡፡
እንደ ነብያችን .... በአንድ ወቅት የነብዩ ሙሐመድ ባለቤታቸው እመት አኢሻ ስለ ነብዩ ባህሪ ተጠይቀው ሲመልሱ...."የነብዩ ሙሐመድ ሰብዕና ቁርአን ነበር" እንዳሉት፡፡
ረመዷን ከሪም!!!

Read 318 times