Sunday, 03 May 2020 00:00

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

    ‹‹ከአሳማ ጋር ብትላፋ ሁለታችሁም ትቆሽሻላችሁ፤ አሳማው ግን ደስ ይለዋል››
                        
           ትንሽ ትንሽ ትዝ የምትለኝ የሱፊዎች ጨዋታ ነበረች፡፡ የፐርሸያ ንጉሥ የነበረው ታላቁ ነስረዲን አንድ ቀን ለሊት ሹማምንቶቹን አስከትሎ በከተማው ጎዳና ላይ ሲዘዋወር፣ አንድ ሰካራም ቤቱ ውስጥ ሆኖ ሲለፈልፍ ይሰማል፡፡ ወደ ቤቱ ይቀርብና በሩን እያንኳኳ፡-
‹‹ክፈት››
‹‹አልከፍትም›› አለ ሰውየው፡፡
ንጉሡም ተቆጥቶ መስኮቱን ሰብሮ በመግባት፡-
‹‹ለምንድነው ሰክረህ የምትጮኸው? ትቀጣለህ›› ሲለው ሰውዬአችን የመለሰው በሌላ ጥያቄ ነበር፡፡… ያለውን መጨረሻ ላይ እነግራችኋለሁ፡፡  
***
ስህተት፣ አለመግባባትና ጠብ የሚያጭሩ የአስተሳሰብ እንከኖች አጀማመር፣ ከፍጥረት ታሪክ ያልተናነሰ ዕድሜ አለው፡፡ እናታችን ሄዋንን ‹ያሳሳታት ሰይጣን› በእባብ ተመስሎ እንደነበር ይተረካል፡፡ ሰይጣን ከሰው በፊት ይኖር ከነበረ ደግሞ እነዚህ የሞራል ህጸጾች በሰው አልተጀመሩም ማለት ነው:: እንደሚተረከው ከሆነ፤ የመጀመሪያው አለመግባባት የተፈጠረው የመላዕክት አለቃ በነበረው ዲያብሎስና በፈጣሪው መሃል ሲሆን ሰውና ፈጣሪው ተቀያይመው፣ አዳም ከገነት የተባረረው ከዛ በኋላ ነው:: ሞትም የተጀመረው በሁለቱ የአዳም ልጆች አለመግባባት መሆኑ ሲነገር፣ እግዜር አጥፊውን ‹ተው› አለማለቱ አባታቸውን አሳዝኗል ይባላል፡፡
አዳም ከገነት ቢባረርም ‹‹ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሏት›› ተብሎ ተመርቋልና ትውልድ እየተበራከተ መጣ፡፡ ግጭትና አለመግባባትም የዛኑ ያህል ተስፋፋ:: ሁኔታው እግዜርን ስላሳሰበው ፍቅርና መተሳሰብን እንዲያስተምራቸው የሚወደው ልጁን ላከላቸው፡፡ አሻፈረኝ አሉ፡፡ ይባስ ብለው ሰቀሉት፡፡ አልተቀየማቸውም፡፡ እንደውም ‹‹ድናችኋል፣ ነፃ ወጥታችኋል›› አላቸው፡፡ ይህም ሆኖ ከጥፋት አልተቆጠቡም፡፡… ባሰባቸው እንጂ፡፡
እግዜር ሁለት ነገሮችን አሰበ፡፡ አንድም ዲያብሎስን ማስወገድ፣ አንድም የሰውን አዕምሮ ማሳደግ፡፡ ጥፋት የፈጣሪ ባህሪ ባለመሆኑ ዲያብሎስን ማረው፡፡ ወደ ሁለተኛው አማራጭ አደላ፡፡ ሶፊስቶችን፣ ሱፊስቶችን፣ ስቶይኮችንና ሌሎች ብዙ ሊቃውንቶችን እያከታተለ መላክ ጀመረ፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ብዙዎች አላዳመጧቸውም፡፡ ሊቃውንቱ ግን አልታከቱም፡፡ የሰው ልጅ በፍቅርና በመተሳሰብ ደስ ብሎት የሚኖረው፣ የእርስ በርስ ግንኙነቱ የተመጠነ ሲሆን፣ በማይነካካ የግል ባህርያት ላይ የተመሠረተ አንድነት ሲኖረው መሆኑን አስተማሩ፡፡ እንደ አርስቶትል ‹Golden mean › ማለት ነው፡፡ የአዕምሮ እርቀት!!
የሊቃውንቱ አስተሳሰብ በኋላ ቀርና ባልሰለጠኑ ማህበረሰቦች ውስጥ ስር አልሰደደም፡፡ ስር ቢሰድ ኖሮ ሕዝቦች በግጭት፣ በስደትና በረሃብ ባልተጎዱ ነበር፡፡ የአዕምሮ ርቀት ላልገባው ሕዝብ፣ በዚህ ዘመን ደግሞ የአካላዊ ርቀት የሞት የሽረት ጉዳይ ሆነበት፡፡ ምንም ዕውቀት የማያስፈልገው፣ ከመታጨቅና ከመገፈታተር የመቆጠብ ባህልን ለተወሰነ ጊዜ እንኳ ለመለማመድ የህመሙን ያህል ከባድ ሆነበት፡፡
ወዳጄ፡- መታጨቅና መገፈታተር የመንገኝነት መገለጫ ነው፡፡ መንገኝነት እንደ ቃሉ የእንስሳት እንጂ የሰው ባህሪ አይደለም፡፡ ሰውና እንስሳ ደስታንም ሆነ ሃዘንን የሚመለከቱበት መንገድ ጨርሶ አይመሳሰልም፡፡ ኬል ቦረፍ፤ ‹‹ከአሳማ ጋር ብትላፋ ሁለታችሁም ትቆሽሻላችሁ:: አሳማው ግን ደስ ይለዋል›› እንደሚለው ነው፡፡
ወዳጄ፡- የእንስሳትን ነገር ካነሳን አይቀር፣ አእዋፋትን ጨምሮ ብዙዎቹ ከሁለት በላይ ጫጩቶችን መፈልፈል ወይም ግልገሎችን ማፍራት ተፈጥሯቸው ነው፡፡ የሰው መንታ መውለድ ግን እንደ መካንነት ወይም ተፈጥሯዊ አካል ጉዳተኝነት አልፎ፣ አልፎ የሚያጋጥም ክስተት እንጂ ተፈጥሯዊ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡
መውለድ ካልን ዘንዳ፣ እግረ መንገዳችንን የናት ሆድ ዥንጉርጉር መሆኑን እናስታውስ:: አባባሉ የሚያሳውቀን ከአንድ ማህጸን ብንወጣ እንኳ ኑሯችንና አካባቢያችን በሚያሳድርብን ተፅዕኖ ምክንያት አስተሳሰባችን ሊለያይ ወይም ላይመሳሰል መቻሉን ነው፡፡ አቤልና ቃየል የተጋደሉት፣ የታራስ ቡልባ ልጆች በተለያየ ጎራ ተሰልፈው የተዋጉት በሃሳብ ልዩነት ነው፡፡ ሰበቡ ምንም ይሁን ምንም!!
ወዳጄ፡- በተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ሐሳባቸው ሊመሳሰል፣ አንድ ዓይነት ፍልስፍና ወይም ርዕዮተ ዓለም ደጋፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጨቋኝ ተጨቋኝ፣ ፊውዳል ሰርፍ፣ ቀጣሪ ተቀጣሪ የምንባባልበትም ምክንያት የኑሮ መደባችንን ለመግለጽ ነው፡፡ በጥቅል አስተሳሰብ ‹‹መደብ›› የሚባለው አጠራር ከኑሮ ጋር ባይቆራኝ ኖሮ፣ ጨቋኝ ተጨቋኝ፣ አሰሪና ሰራተኛ ወዘተ መባሉ ቀርቶ የአጫጭሮችና ረዣዥሞች፣ የሴቶችና የወንዶች፣ የጥቁርና የነጭ ወዘተ መደብ ይባል ነበር፡፡
ወዳጄ፡- በተለያየ አካባቢና ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ወንድማማቾች በአስተሳሰብ ቢጋጩ፣ የናትም ሆድ ዥጉርጉር ቢባል አይገርምም፡፡ ይህ ማለት ግን በማናቸውም የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ተመሳሳይ ዓላማና አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህኛዎቹ ከባለመደቦቹ የሚለዩት አስተሳሰባቸው ዕውቀትን ብቻ መሠረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ አስተሳሰብ ደግሞ ከልምድ፣ ተፈጥሮንና የሰውን ስነ ልቦና ከመረዳት፣ የዓለምን ሁኔታ ከመገንዘብና መጽሐፍትን ከመመርመር የሚገኝ ነው፡፡ በፍጥነት በሚለዋወጠው ዓለም ላይም የራስን ቦታ አውቆ ለመቆም ያስችላል፡፡ የራስን ቦታ ማወቅ ተግባብቶ ለመኖርና ከስህተት ለመራቅ መፍትሔ ነው፡፡ እዚህ ጋ የአዕምሮና የአካላዊ ቦታ ርቀት ይገናኛሉ፡፡  
“Find yourself and be yourself. Remember there is no one like you in this world”… የሚለን ታላቁ ካርኒጌ ነው፡፡
***
ወደ ሰሞነኛው ጉዳያችን ስንመጣ፣ በሮመዳን ዋዜማ፣ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች ውስጥ አንድም ህመምተኛ ያለመገኘቱ ዜና አስደሳች ነው፡፡ እነሆ፡- ዱአችን እንዲሰምር የበደሉንን ይቅር ብለን፣ የበደልናቸውን ይቅርታ ጠይቀን፣ ፆማችንን በታላቅ ተስፋ ጀምረናል፡፡
ንጉስ ነስረዲን፡- “ስለ ምን ትጾማለህ?” ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ… “አላህ ፊት ከእነ ነውሬ መቆም ስለማልችል ነው›› ብሎ ነበር አሉ፡፡ ወደ መጀመሪያው ጨዋታችን የሚመልሰንም ይኸው ታሪከኛ ንጉሥ ነው:: ነስረዲን ሰውየውን፡-
‹‹ለምንድነው ሰክረህ የምትጮኸው?›› ሲለው
“አላህ የሰውን ነውር አትመልከት አላለምን?” በማለት ነበር የመለሰለት፡፡
ንጉሡም ሰውየውን አመስግኖ ተመለሰ:: ሰውየውም መጮሁን አቆመ፡፡ ጥያቄው፡- በቀላሉ መግባባት እያለ ግጭትና መሳሳትን ምን አመጣው? የሚል ነው፡፡
ወዳጄ፡- ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፍ የንባብ ቀን ተከብሯል፡፡ ‹‹ሙሉ ሰው›› መሆን የምትሻ ከሆነ፣ ኮሮና በፈጠረልህ distance ተጠቀምበት፡፡ አንብብ!!
ሮመዳን ከሪም!
ሠላም!

Read 513 times