Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Monday, 04 May 2020 00:00

እንዲህም አለ፤ እንዲያም አለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

‹‹የስፓኒሽ ፍሉ የቤተሰባችንን ታሪክ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል››

ለሂዩስተን ነዋሪዎቹ እህትማማቾች ሎሪ እና ቤት-አን፣ የኮቪድ - 19 ወረርሽኝ፣ የራሳቸውን ቤተሰብ ታሪክ የሚያስታውስ ቆጥቋጭ  ትዝታ ነው፡፡  
‹‹ነገሩ ትንሽ እውነት ዘለል ይመስላል››  የምትለው ሎሪ ክራፍት፤ ‹‹በቅርቡ፡- “ውድ እግዚአብሄር ሆይ፤ ታሪክ ራሱን እንዲደግም አትፍቀድለት”  እያልኩ ሳስብ ነበር፡፡” ብላለች፡፡
ኮቪድ- 19 ከመከሰቱ ከብዙ ዓመታት በፊት፣ የ1918ቱ የስፓኒሽ ፍሉ ወረርሽኝ አገሪቱን አሽመድምዷት ነበር፡፡ በአሜሪካ ከ650 ሺ በላይ ሰዎች በወረርሽኙ አልቀዋል:: በመላው ዓለም ደግሞ 50 ሚሊዮን ህዝብ በወረርሽኙ ሞቷል፡፡   
‹‹ወረርሽኙ  በእርግጠኝነት የቤተሰባችንን ታሪክ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል›› ትላለች፤ ቤት-አን፡፡ የሁለቱ እህትማማቾች ቅድመ አያት፣ ቻርልስ ሬይድ ክሮትስ፤ በሰሜን ካሮሊና የተሳካላቸው የቢዝነስ ሰው ነበሩ፤ ገና በ38 ዓመት ዕድሜያቸው ነበር  በስፓኒሽ ፍሉ ተይዘው ለህልፈት የተዳረጉት፡፡
‹‹ይህ የቤተሰባችን ታሪክ አካል መሆኑን አውቀን ነው ያደግነው›› ትላለች፤ ቤት - አን::
አሁን ከሌላ ወረርሽኝ ጋር በተጋፈጡበትና ከቤት ውስጥ እንዳይወጡ በተገደዱበት ወቅት ታዲያ ሁለቱ እህትማማቾች፣ በጉግልና አንሴስትሪ ዶት ኮም አጋዥነት፣ ሰነዶችን በጥልቀት መፈተሽ ያዙ፡፡  
የሞት ሰርተፊኬትና የ1918 የጋዜጣ ዘገባ፣ በቤተሰባቸው ታሪክ ላይ ብርሃን ፈንጥቋል፡፡ የክሮትስ ሞት ቤተሰቡን በሥነ ልቦናና በፋይናንስ ጭምር ያሽመደመደ ክስተት ነበር፡፡ ከዓመት በኋላ ደግሞ ታላቅ አጎታቸውም በዚሁ ወረርሽኝ ለህልፈት ተዳረጉ፡፡
 “አንዳንዶች ከድህነት ወደ ሃብት ማማ ወጥተዋል፤ ሌሎች ደግሞ ከሃብት ማማ ወደ ድህነት አዘቅት ወርደዋል፡፡” በማለት ቤት- አን ታስታውሳለች፤ የስፓኒሽ ፍሉን ወረርሽኝ፡፡  
ዛሬ ከ100 ዓመታት በኋላም፣ በርካታ ቤተሰቦች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እያለፉ ናቸው፡፡
‹‹ተመሳሳይነቱ በእጅጉ ያስደነግጣል›› የምትለው ሎሪ፤ ‹‹ለእኛ ጉዳዩ ተጨባጭ ነው፤ በእውን ተከስቷል፤ ስለዚህም  በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡›› ስትል ስጋቷን ገልጻለች፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ሎሪና ቤት-አን ተስፋ ለማድረግ በቂ ምክንያት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡ አያታቸው፤ አባታቸውንና አጎታቸውን በወረርሽኙ በተነጠቁ ወቅት ገና የ9 ዓመት ብላቴና ነበሩ፤ ነገር ግን ቤተሰቡን ወደፊት እንዲሻገር አድርገውታል፡፡
‹‹ለልጆቼ ጠንካራ ሌጋሲ ላጋራቸው እፈልጋለሁ›› የምትለው ቤት- አን፤ ‹‹ያን ጊዜ የተከሰተው አሁን መደገም የለበትም፤ እነዚህ አስከፊ ነገሮች ሲከሰቱም እንደ አገር በድል እንሻገረዋለን፡፡ እንደ ቤተሰብም አሸንፈን አናልፈዋለን፡፡  ሁልጊዜም ብሩህ ተስፋ አለ፤ ሁልጊዜም ጽኑ እምነት አለ፡፡›› ብላለች፡፡
እነዚህ ሁለት እህትማማቾች፤የየራሳቸውን ድንቅ ቤተሰቦች ያፈሩ ሲሆኑ ከወረርሽኙ በኋላ ህይወት ዳግም ወደፊት እንደምትገሰግስ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ የትኛውም በሽታ የቤተሰብን የማሸነፍና የመሻገር ውስጣዊ መሻት ሊያጠፋው አይችልም፡፡
*    *   *  
የሰራተኞቿን ደሞዝ ለመክፈል አውቶሞቢሏን የሸጠችው አሜሪካዊት
 
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ህይወትን በእጅጉ ፈታኝ አድርጐታል፤ አያሌ ኩባንያዎች ተዘግተው ብዙ ሺ ሰዎች ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በአሜሪካዋ የጆርጂያ ግዛትም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው (ከ17 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ  መያዛቸው ተረጋግጧል…)፡፡ በሰማይራ ከተማ እንዳሉ ብዙዎቹ የንግድ ተቋማት፤ አንዲት የሬስቶራንት ባለቤት፣ ምግብ ቤቷን ለመዝጋትና አብዛኞቹን ሰራተኞቿን ለመቀነስ ተገዳለች፡፡
ቪትልስ ሬስቶራንት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ደቡባዊ ምግቦችን እየከሸነ ለደንበኞቹ ሲያቀርብ የቆየ ነው፤ ነገር ግን እንደ ብዙዎቹ አነስተኛ ቢዝነሶች ሁሉ በኮቪድ - 19 ሳቢያ ለኪሳራ ተዳርጓል፡፡
እንዲያም ሆኖ የሬስቶራንቱ ባለቤት ቻሪቲ ስሌየርስ፤ ሰራተኞቿን ያለ ደሞዝ መሸኘት አልወደደችም፡፡ ከዚያ ይልቅ እጅግ ውድ የሆነውን ፎርድ ሙስታንግ አውቶሞቢሏን ለመሸጥ ወሰነች፡፡ ከሽያጩ ያገኘችውን 11 ሺ ዶላርም ለስምንት ሰራተኞቿ ደሞዝ ክፍያና ለቤት ኪራይ ወጪ ተጠቅማበታለች፡፡
ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ በተከሰተው ቀውስ፣ የሬስቶራንት ዕለታዊ ገቢዋ ከ3ሺ 500 ዶላር ወደ 300 ዶላር በማሽቆልቆሉ ነበር መኪናዋን የመሸጥ አስቸጋሪ ውሳኔ ላይ የደረሰችው፡፡  
‹‹በወቅቱ ፈጣን ውሳኔ መወሰን ነበረብኝ፤ ለጥቂት ወራት የሚያዘልቀኝ በቂ ገንዘብ ለማግኘትና ሬስቶራንቴን ላለመዝጋት ላደርገው የምችለው ብቸኛ ነገር ይሄ ብቻ ነበር›› ብላለች - ፎርድ ሙስታንግ መኪናዋን መሸጥ፡፡  
‹‹ገንዘቡ ሁለት ወራትን ለመዝለቅ በቂ ነው›› ያለችው ሳልየርስ፣ ‹‹ሁለት ወራት የኮቪድ ሥርጭት ቀንሶ ዳግም ሥራችንን ለመጀመር በቂ ጊዜ ይሰጠናል ብዬ አስባለሁ›› ስትል ተስፋዋን ገልጻለች፡፡
ሳልየርስ እጅግ ውዱን አውቶሞቢሏን የገዛችው ከጥቂት ወራት በፊት ሲሆን ያላት ብቸኛዋ መኪናም ነበር፡፡ አሁን ከቤቷ ወደ ሥራዋ የምትመላለሰው ሁለት ሰራተኞቿ ሊፍት እየሰጧት እንደሆነም ታውቋል፡፡
ኮቪድ - 19 ለገንዘብ እጥረትና ለኪሳራ ቢዳርጋትም፣ የሬስቶራንት ቢዝነሷ የጀርባ አጥንት የሆኑትን ሠራተኞቿን አልዘነጋችም:: ከሰብአዊነትም ከቢዝነስም አንፃር አትራፊ መንገድ ነው የመረጠችው፡፡
ያለጥርጣሬ ይኼ ክፉ ጊዜ ያልፋል፤ የሬስቶራንት ቢዝነሷም ዳግም ያንሰራራል፤ በፈታኝ ወቅት የወሰነችው ብልህነት የተመላበት ውሳኔ ጥግ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡


Read 566 times