Saturday, 09 May 2020 12:28

የአገሪቱ መግቢያ በሮች ለኮሮና ስርጭት መባባስ ምክንያት እየሆኑ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

   - የሰላምና የጤና ሚኒስቴር ዴኤታዎችን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት አፋር ከትመዋል
      - የሰመራ ሎጊያ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በቫይረሱ ተይዘዋል መባሉን የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አስተባብለዋል
       - ጫት ፍለጋ ድንበር ተሻግረው የሚገቡ የሱማሌና የጅቡቲ ዜጎች ተበራክተዋል
                 
              የሶማሊያ፣ የጅቡቲና ኬኒያ አገራትን የሚያዋስኑት የአፋርና የሶማሌ ክልሎች በኮሮና ቫይረስ ስርጭት መባባስ ከፍተኛ ሥጋት ላይ መውደቃቸውንና ስርጭቱን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡ ክልሎቹ ሕገወጥ የድንበር መግቢያ በሮችን መዝጋት፣ ድንበር ተሻግረው የሚገቡ ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያዎች ውስጥ ማስገባትና በየኬላዎቹ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ መጀመራቸው ታውቋል፡፡
የአፋር ክልል መንግሥት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ካሎይታ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር አስራ አንድ መድረሱን ጠቁመው፤ እነዚህም ከጅቡቲ የገቡና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው ብለዋል:: ክል ከሰላምና ጤና ሚኒስቴርና ከክልሉ ፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር፤ በድንበር አካባቢ ያለውን ጉዳይ ለመቆጣጠር የሚስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ያስታወቁት ኃላፊው፤ ሰሞኑን 14 ሕገ ወጥ መግቢያ በሮች እንዲዘጉና በሕጋዊ መግቢያ በሮች ላይም ቁጥጥር እንዲጠናከር የማድረግ ሥራ ሰርተናል ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ዴኤታና የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ለዚሁ ሥራ በአፋር ክልል እንደሚገኙ የገለፁት አቶ አህመድ፤ ክልሉ አለም አቀፍ ድንበርና በሽታው በብዛት ከተሰራጨባት ጅቡቲ ጋር የሚዋሰን እንዲሁም ጅቡቲና ኢትዮጵያን የሚያገናኘው ዋና መንገድም በመሆኑ፤ የበሽታው ስርጭት ሊባባስ ይችላል ብለዋል፡፡ ክልሉ ህብረተሰቡ ስለ በሽታው ያለውን ግንዛቤ ማስፋት፣ ህገ ወጥ መግቢያ በሮችን ከመዝጋት የዘለለ ሥራ መስራት እንደማይችልና በሽታው በከፍተኛ መንገድ ሊሰራጭ የሚችልበት የጅቡቲ አፋር ዋና መንገድ እንዲዘጋ ወይም ሾፌሮችና መኪኖች እንዳይገቡ ለማድረግ የሚያስችል ስልጣን እንደሌለው ጠቁመዋል። በፌደራል መንግሥቱ የተሰጠውንና ሾፌሮቹ ከተማው ውስጥ ሳይቆሙ ወይም ቆይታ ሳያደርጉ እንዲያልፉ የሚያዘውን መመሪያ በማስተባበሩ በኩልም ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ከጅቡቲ ጋር በስፋት የሚዋሰን ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያ ለገቢና ወጪ ንግዱ በዋነኝነት የምትጠቀመው በጅቡቲ ወደብ ሲሆን ሁለቱን አገራት የሚያገናኘው ዋና መንገድም በዚሁ በአፋር ክልል ውስጥ የሚገኘው በመሆኑ ለበሽታው ስርጭት መባባስ ከፍተኛ ስጋት ሆኗል፡፡
“በክልሉ የሰመራ ሎጊያ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በቫይረሱ ተይዘው ለህክምና ወደ አዲስ አበባ  መጥተዋል” በሚል የተሰራጨው መረጃ ሀሰት ነው ሲሉም የክልሉ ኮሚኒኬሽን ኃላፊው አቶ አህመድ አስተባብለዋል:: በክልሉ ከአፋር ዩኒቨርሲቲና ከጤና ተቋማት በተጨማሪ በ14ቱ ህገወጥ መግቢያ በሮች፣ 14 ለይቶ ማቆያ ሥፍራዎች ተዘጋጅተው፣ በሕገወጥ መንገድ ወደ ክልሉ የሚገባ ማንኛውም ሰው ለአስራ አራት ቀናት በለይቶ ማቆያዎች ውስጥ እንዲቆይ እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በሶማሌ ክልልም በተመሳሳይ መንገድ በመግቢያ ድንበሮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ የተጀመረ ሲሆን ከልሉ ከሶማሊያ ከኬኒያና ከጅቡቲ ጋር የሚዋሰን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከትናንት በስቲያ ከሶማሊያ ጋር የሚያገናኘው ድንበር በክልሉ ሰላምና ደህንነት ኃላፊ ዶ/ር ሁሴን ቃሲም በሚመራ ቡድን ተጎብኝቷል፡፡ በውጨሌ፣ ጎሪያ አውል፣ ቶጎ ጫሌና አውበሬ በተባሉ መግቢያ ድንበሮች ላይ በተደረገው ጉብኝትም፣ በሮቹ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አመቺ በመሆናቸው ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ መመሪያ መተላለፉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የሶማሊያ መንግሥት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ወደ ክልሉ የሚገቡ መኪኖች ላይ እገዳ መጣሉን ተከትሎ፣ በርካታ ሶማሊያውያን ጫት ለመግዛት በሕገወጥ የመግቢያ በሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አልፈው እየገቡ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ ይህም ለበሽታው ስርጭት መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡  

Read 11361 times