Saturday, 09 May 2020 12:29

ኮሮና በማህበረሰቡ ውስጥ ተሰራጭቷል የሚል ስጋት አለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  - በሽታው በአጭር ጊዜ ውስጥ የመዛመት ዕድል አለው ተብሏል
     - ሰሞኑን በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠባቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ከማህበረሰቡ ውስጥ የተገኙ ናቸው
    - ለበሽታው ስርጭት ከፍተኛ ተጋላጭነት እንዳላቸው የሚጠረጠሩ ተቋማት ላይ አሰሳ እየተካሄደ ነው
          
             የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በማህበረሰቡ ውስጥ ተሰራጭቷል የሚል ስጋት እንዳለ የገለፁት የጤና ባለሙያዎች፤ ይህም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ እንደሚያደርገው አስታወቁ፡፡
ባለፉት 3 ቀናት ብቻ 49 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ያወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሚኒስትሮች የፀረ ኮቪድ -19 ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን፤ ይህም በሽታው በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት የመዛመት ዕድል እንዳለው በግልጽ ያመላክታል ብለዋል፡፡ አያይዘውም፤ የወረርሽኙ አዝማሚያ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት በወቅታዊ ጉዳዮች ሳንዘናጋ የጥንቃቄ መመሪያዎችን አጥብቀን ተግባራዊ እንድናደርግ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የማህበረሰብ ጤና ባለሙያው ዶ/ር ቴዎድሮስ ታመነ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ሰሞኑን የበሽታውን ስርጭት አስመልክቶ ከሚቀርቡት ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጠባቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያልነበሩና በማህበረሰቡ ውስጥ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይህ ሁኔታም በሽታው ወደ ማህበረሰቡ ዘልቆ ገብቷል የሚለውን ሥጋት ያጠናክረዋል ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፡፡ በበሽታው  መያዛቸው ይፋ ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል በድንገተኛ የናሙና ጥናት የተገኙ መኖራቸው ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በአገራችን የኮቪድ 19 ቅድመ ዝግጅትና ምላሽ ዋና አስተባባሪ አቶ ዘውዱ አሰፋ እንደገለፁት፤ በቅርቡ ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጠባቸው ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ምንም አይነት የውጪ ጉዞ ያልነበራቸው፣ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ግንኙነትና ንኪኪ የሌላቸው መሆኑና አብዛኛዎቹም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያልነበሩ መሆናቸው የበሽታው ስርጭት ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ ገብቶ ይሆናል የሚለውን ጥርጣሬ ማስነሳቱን ጠቁመው፤ ይህንን ሁኔታ ለማረጋገጥ ግን ተጨማሪ ምርመራዎች ሊደረጉ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ከለይቶ ማቆያ ውጪ ሆነው ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ በቫይረሱ ተጠርጥረው ተጨማሪ ምርመራ ከተደረገላቸው፣ በጤና ተቋማት ውስጥ ተኝተው ከሚታከሙ ህሙማንና፣ ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው ተብለው በሚታሰቡ ቦታዎች ላይ በተደረጉ ምርመራዎች፣ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች መገኘታቸውን ያመለከቱት አቶ ዘውዱ፤ ይህም ሁኔታ በሽታው በማህበረሰቡ ውስጥ መግባቱን የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም፤ ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭነት አላቸው ተብለው በሚታሰቡ እንደ አረጋውያን መንከባከቢያ፣ ሕጻናት ማሳደጊያ፣ ማረሚያ ቤቶችና መሰል ተቋማት ላይ የአሰሳ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የህብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች በኮቪድ 19 በሽታ መከላከል ኮሚቴ ውስጥ የሚሰሩት ዶ/ር ሰለሞን ወርቁ በበኩላቸው፤ “በለይቶ ማቆያ ውስጥ ከነበሩ ሰዎች ውጪ የሆኑና በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡ የበሽታው ስርጭት ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ ለመግባቱ አመላካች ነው፤ ይህ ደግሞ ጥሩ ዜና አይደለም::
ምክንያቱም በሽታው ወደ ማህበረሰቡ ውስጥ ከገባ ለመቆጣጠርና ስርጭቱን ለመከላከል አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ::”
በሽታው ኖሮባቸው እንዳለባቸው የማያውቁ ወይም ምልክት የማያሳዩ ሰዎች ደግሞ በሽታውን በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ለማስተላለፍ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል ብለዋል - ዶ/ር ሰለሞን፡፡
የበሽታው ስርጭት ፍጥነትና የመሰራጫ መንገዱ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሻ መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር ሰለሞን፤ ጤናማ መስለው በሽታውን የሚያሰራጩ በርካታ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግና ራሱን ከቫይረሱ ሊከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕና ሐሙስ በተደረገው ምርመራ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በሻይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በተለይ ከትናንት በስቲያ ቫይረሱ ከተገኘባቸው 29 ግለሰቦች መካከል 19ኙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እንዲሁም በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያልነበራቸው መሆናቸው ትልቅ ስጋት ፈጥሯል፡፡
ትናንት አርብ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠውን 3 ሰዎች ጨምሮ፣ እስካሁን 194 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ለ30ሺ 306 ሰዎች ምርመራ መደረጉም ተገልጿል፡፡  



Read 12744 times