Saturday, 09 May 2020 12:38

የፅዮን አመፀኞች ‹‹ንቃት›› ተወዳጅ ሆኗል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

  በኢትዮጵያውያን የሬጌ ሙዚቀኞች ቡድን Zion rebels /ፅዮን አመፀኞች/ የተሰራው ‹‹ንቃት›› የተሰኘ አዲስ የሩት ሬጌ አልበም ተወዳጅነት እያገኘ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ  በገባበት ሰሞን በተወሰኑ የሲዲ ህትመቶችና በተለያዩ ዲጂታል የገበያ አውታሮች የቀረበው አልበሙ በዜማ እና ግጥም ድርሰቶቹ እንዲሁም በምርጥ ቅንብሩ በመጠቀስ ላይ ነው፡፡
የፅዮን አመፀኞች Zion rebels  በኢትዮጵያ የሬጌ እንቅስቃሴ ከ15 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበተ ሲሆን፤ በሙዚቃ ቡድኑ የዜማ ግጥም ደራሲዎች እንዲሁም ድምጻውያኑ ውቅያኖስ ፍቅሩ እና ይስሓቅ ኤልያስ ናቸው፡፡
ንቃት የተሰኘው የሩት ሬጌ አልበም 11 ዘፈኖች ሲገኙበት፤ ግጥሞቹን ውቅያኖስ እና ይስሐቅ በጋራ የፃፉት ሲሆን በአንዳንዶቹ ላይ የሙዚቃ አቀናባሪው ራስ አሉላና ድምፃዊቷ ኢቦኒ ጄ ተሳትፈውበታል፡፡ በሁለት የአልበሞቹ ዘፈኖች ላይ በሳክስፎን ተጫዋችነት ለታሪክ ጥላሁን የሰራ ሲሆን፤ በ6 ዘፈኖች ላይ በሊድ ጊታር ፍፁም ጥላዬ እንዲሁም ሚካኤል በሪሁንና ራስ አሉላ ሰርተዋል፡፡ የድራም ጨዋታዎቹን ኤርምያስ ወልዴ ሲሸፍን ሄኖክ ሰብስቤ ደግሞ በቤዝ ጊታር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡  የአልበሙን የሙዚቃ ቅንብርና ሚክስ ስራዎች በዛይላ ሪከርድስ ስቱድዮው ራስ አሉላ የሰራው ሲሆን ኬኒ አለን ደግሞ በኢርስ ስቱድዮው ማስተሪንጉን አከናውኗል፡፡
‹‹ንቃት›› ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን የሬጌ ሙያተኞች የተሰራ የሩት ሬጌ አልበም መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡  የፅዮን አመፀኞች ባለፉት 10 ዓመታት በድሬዳዋ፤ በሃዋሳ እና በአዲስ አበባ በተዘጋጁ ኮንሰርቶች እንዲሁም በተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶች ልምድ አካብተዋል፡፡ ከመጀመርያው አልበማቸው በፊት  በተለያዩ ነጠላ ዜማዎች እውቅና ያገኙ ሲሆን አዲስ አመት፤ መልክሽ እና ክሩዚንግ የተባሉት ሙዚቃዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡


Read 2954 times