Saturday, 09 May 2020 12:45

ኮሮና ተኮር ዘፈን፣ መዝሙር እና “ዘፈ-መዝሙሮች!”

Written by  በተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(0 votes)

  ጥያቄ፡- በአሁን ሰዓት በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በዩ-ቲዩብና በመሳሰሉት ሚዲያ በመሰማት ላይ የሚገኙት ኮሮና-ተኮር የሙዚቃ ስራዎች (በተለይም ዘፈኖች) ቫይረሱን ከመዋጋት አንጻር የመንግሥትን ሰዋዊ/ሳይንሳዊ ምላሽ የሚያግዙ ናቸው ወይስ የሚያዳክሙ? እየተደመጡ የሚገኙት ግጥሞች ዜጎችን በ”እንችላለን” ስሜት የሚያጀግኑ ናቸው ወይንስ አቅመ-ቢስነትን የሚያሰርጹ? አገራችን በእጇ ውስጥ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን በፍጥነት እንድትጠቀምና የቫይረሱን ስርጭት ትገታ ዘንድ ዜጎቿ ራሳቸውን የማዳን ሀላፊነት እንዲወስዱ የሚያበረታቱ ናቸው ወይስ (በሌሎች ዓለማት፣ በተለይም በኃያላን አገሮች፣ የታዩ እልቂቶችን ዜና አጉልቶ በማውጣት) “እኛማ አንችለውም” የሚል የማቃት ስሜትን የሚኮተኩቱ? ሳልረሳው፡- ልብ አድርጉልኝ፤ አሁን የምነግራችሁ ትልቅ ዕውቀትን የሚጠይቅ “ትንቢት” አይደለም:: የሰለጠኑ አገሮች ቅርብ ሊባል በሚችል ጊዜ ውስጥ ወረርሽኙን ይቆጣጠሩታል፡፡ ያኔ ኮቪድ 19 “መድሃኒት የሌለው በሽታ” መባሉ ያቆማል፡፡ ያኔ፤ በአሁን አይነት የፈዘዘ አካሄዳችን ከቀጠልን፤ ሕዝቡን ማለቴ ነው፤ ምናልባት “እነዚህ ሀያላን አገራት እንድናልቅ ስለሚፈልጉ መድሃኒትና ምግብ እየረዱን አይደለም” እያልን ማላዘን እንጀምር ይሆናል፡፡ ያኔ ... “ኮሮና ሀብታምና ደሀን እኩል አደረገ” የሚለው ትርክት ላይመለስ ይቀለበሳል፡፡ በመሀከላችን ያለው ርቀት በጣም፣ እጅግ በጣም ሰፊ ነው’ኮ - ጎበዝ:: የሰው ሞት ብዛት እንደሆነ እኛም አገር ከየአቅጣጫው መረጃ የሚሰበሰብ ቢሆን ኖሮ፣ በመኪና አደጋ፣ በወባ፣ ወዘተ በየቀኑ የሚረግፈው ሰው ብዛት አስደንጋጭ መሆኑን እንረዳ ነበር፡፡
ወደ ጥያቄዬ ልመለስ፤ ለመሆኑ፡- ገጣሚዎች ኮሮና-ተኮር ግጥሞችን ሲጽፉ፣ የመገናኛ ብዙኃን ጣጣቸውን የጨረሱ የሙዚቃ ሥራዎች ጣቢያቸው ድረስ ሲቀርቡላቸው ይዘቶቻቸውን ያጤናሉ፣ ወይስ “ኮሮና” የሚባል ቃል እስከገባበት ድረስ እንደ ወረደ ወደ ህዝብ ጆሮና አይን ያደርሳሉ? አስተምራለሁ ብሎ ማደናገርምኮ አለ፤ ይህን ያስቡታል? “እንበርታ፣ ቫይረሱን ለማሸነፍ እንችላለን!” የሚልን የሆነ ድርጅት አጭር መልዕክት ተከትሎ “ምን ጉድ ነው ይሄ!? ማለቃችን ነው - ! ለካስ የሰው አቅም እስከዚህ ድረስ ነው!” የሚል - ተብረክርኮ የሚያብረከርክ ዘፈ-መዝሙር በምስል ተደግፎ ሲለቀቅ፣ አዘጋጆቹ ምን ይሰማቸው ይሆን?
የበለጠ እየተግባባን እንሂድ፡- በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ፣ ኮሮና-ነክ የዘፈን ግጥሞች እንዲያስተላልፉ የሚጠበቀው ስለ ቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶች፣ ቫይረሱ ስለሚያስከትላቸው የጤና ችግሮችና ሰዎች ሊወስዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ወይም የመከላከያ ዘዴዎች ወዘተ ነው፡፡ ዘፈኖች በአቀራረባቸውም የሰዎችን ስሜት የሚያነቃቁና የሚያጀግኑ መሆን ነው ያለባቸው፡፡ በተጨማሪም፤  ጊዜው ቢዘገይም ሰዎች (ሳይንቲስቶች) ለበሽታው መፍትሔ፤ ክትባት ከተቻለም መድሃኒት፤ ሊያዘጋጁ እንደሚችሉ፤ ከዚህ በፊት በወረርሽኝ መልክ ተከስተው ዓለምን አሸብረው እንደነበሩት እንደ ቂጢኝ፣ ኩፍኝና የሥጋ ደዌ በሽታ ሁሉ ኮሮና ቫይረስንም በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንደሚቻል ተስፋ መስጠት ነው ድርሻቸው:: የዘፈኖች መልዕክት ተቀባዮች፣ እንዲሁም መልዕክቶችን ወደ ስራ ተርጓሚዎች ሰዎች መሆናቸውን ማስታወስ ነው፤ ዘፈኖች ለዘመቻው ሊጨምሩት የሚችሉት እሴት፡፡
ለማንኛውም፣ ይህ የማንቂያ ጽሁፍ ነው - የሚያተኩረውም ዘፈኖች የመንግሥትን ሰዋዊ/ሳይንሳዊ ምላሽ የሚደግፉ ሆነው እንዲቀርቡ ማሳሰብ ላይ ነው:: በሀይማኖታዊ ተቋማት በኩል፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለማስቆም፣ ጭብጣቸውን ፀሎት (ምልጃ/ልመና) ያደረጉ በርካታ መዝሙሮች በዘማሪያን መቅረባቸው አይቀርም:: ከድሮውም በመዝሙርና መሰል ሥራዎች “ለሰው እንተርፋለን እንኳን ለራሳችን” ሊያስብሏቸው የሚችሉ” ዜማና ግጥሞችን ታጥቀዋል፡፡  ያ ሌላ መስመር፣ ሌላ ምላሽ  ነው::  እነዚህ ሀይማኖታዊ የሙዚቃ ስራዎቻቸው፣ የሰዎችን እርስበርስ የመረዳዳትን አስፈላጊነት በማስተማር፣ ሰዎች ለፀረ ኮሮና ዘመቻው አዎንታዊ የሆኑ ምላሾችን እንዲሰጡ አስተዋፅዖ እያደረጉም ነው፡፡ አሁን ሳስቶ የሚታየው የዘፈኑ ጎራ ነው:: የሳሳው ደግሞ - ራሱን የቻለው ሀይማኖታዊ ምላሽ ላይ ተደራቢ በመሆኑ ነው፡፡ ዘፈ-መዝሙሮች የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ እንደ ተቋም፤ ለሚያራምደው አቋም ቀጥተኛ የሆነ ገንቢ ሚና አይኖራቸውም፡፡
እኔ የምለው፡- “ማሳሰቢያ ለዘፈን ግጥም ደራሲዎች-! ... አምላኬ ሆይ ማረን...! ... በቃችሁ በለን! ... አንተ ካላገዝከን እኛ ደካሞች ነንና ይህን ፈተና ልንቋቋም አንችልም....! ... ሀጢዓታችን በመብዛቱ የተነሳ የሰደድክብንን የቅጣት ናዳ ከጫንቃችን ላይ አንሳልን! ... ይቅርታ ... አጥፍተናል ... ማረን! ... ኮሮና ሊያስተምረን መጣ!” አይነት ግጥሞችን እየጻፋችሁ ከሆነ፣ ለሰዋዊው/ሳይንሳዊው የመንግሥት ፀረ-ኮሮና ዘመቻ ተፈላጊ ስንቅና ትጥቅ እያዘጋጃችሁ ያለመሆናችሁን እወቁት፡፡” ብሎ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ለማስነገር ምን ያህል ገንዘብ ይጠይቅ ይሆን?
በነገራችን ላይ፡- “ዘፈ-መዝሙር” የሚለውን ቃል ፈጥሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአንባቢያን ያስተላለፍኩት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ልሳን በሆነችው “ብሌን” መጽሄት አማካይነት ነው፤ ጊዜው ደግሞ ሰኔ 2003፡፡ “ርዕሰ-ጉዳዩ”፣ ማኅበሩ ለ50ኛ ዓመት (1950 - 2002) የምስረታ በዓሉ ፍጆታ ያሳተመው “ልዩ የሥነ-ጽሁፍ መጽሄት - ቁጥር 7” ላይ ነው ከምርጥ “ሀሳቦች” አንዱ ሆኖ የታተመው፡፡ ጽሁፉ፣ ከይዘት አንጻር የኢትዮጵያን “ሙዚቃ” ከሶስት ከፍዬ ያቀረብኩበት ነው - ዘፈን፣ መዝሙር እና ዘፈ-መዝሙር በሚል፡፡ ዋና ጭብጡ፣ ዘፋኞች ሰዋዊ የችግር አፈታት መንገዶችን ከህዝቡ አንድ እርምጃ ቀደም ብለው “ማሳየት” ሲገባቸው ከህዝቡ እኩል፣ አንዳንዴም ከህዝቡ አንድ እርምጃ ከኋላ ቀርተው ሳይንሳዊ ያልሆኑ፤ አንዳንዴም አሳሳችና አዘናጊ የሆኑ፤ መፍትሄዎችን በዜማ ከሽነው ማቅረባቸውን ያቁሙ የሚል ነው:: ከጥላሁን ገሠሠ “ዋይ ዋይ ሲሉ” ጀምሮ በተለያዩ ዘፋኞች የተቀነቀኑ ዘፈ-መዝሙሮች ከጥሩ ወግ ጋር ቀርበዋል በጽሁፉ ውስጥ ተካተው፡፡ ዘፈ-መዝሙሮች በሌላውም ዓለም አሉ፡፡ ይኑሩ፤ ችግር የለም:: እንዲህ ያለ ትኩረት የሚሻ ዘመቻ ሲኖር ግን ባይኖሩ ነው የሚሻለው፡፡
እነሆ አንድ የዘፈ-መዝሙር ምሳሌ:: ታስታውሱ እንደሆነ፣ ከአንድ አስር አመት በፊት የህፃናት መብቶች እንዲከበሩ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት የተቀናጀ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ እኔም እንደ ማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያነቴ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዱ የነበሩ ንቅናቄዎችን በከፍተኛ ባለሙያነት ከሚያግዙ ሰዎች መካከል ነበርኩ፡፡ በግል ጥረቴም፣ የህፃናት “መዝሙሮችን” የያዘ ካሴት በማውጣት ንቅናቄውን የሚደግፉ ሰዋዊ መልዕክቶች በስፋት እንዲሰራጩ አድርጌያለሁ፡፡ ከስራዎቼ አንዱ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስን የሚመለከት “አዋጅ!” - ዘፈን ነበር፡፡ “በዚህ ከቀጠለ የሰዉ አኳኋን ... ተናግረናል እኛ ያንሳል የእድር ድንኳን!” የሚል  ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ማስጠንቀቂያ ነበረው በህፃነት የተቀነቀነው “ዘፈን”፡፡ ቀደም ወዳለው ወግ ልመለስና፡- ማህበራዊ ሃላፊነትን ስለመወጣት እያስተማርንና፣ አገር ህግን በማስከበር ድባብ ውስጥ በነበረችበት ወቅት - ፀሐዬ ዮሐንስ የጎዳና ተዳዳሪዎችን አስመልክቶ አንድ ዘፈን አወጣ፡፡ “አምላኬ ሆይ የጎዳና ሰብሎችህን ሰብስባቸው ... በቃህ በለን (ም)” አለበት መሰለኝ ... እንደዚያ ነገር ነው ግጥሙ፡፡ ደነገጥኩ፡፡ እኛ ባለድርሻ አካላትን እያሳደድን፣ የህግ አንቀጾችን እየጠቀስን በምናፋጥጥበት ወቅት ዘፋኙ፣ በምወደው ተስረቅራቂ ድምጹ፣ ተጠያቂነትን ከሰዎች ትከሻ ላይ አንስቶ ወደ አምላኩ ሲያሸጋግር በመስማቴ ነው የደነገጥኩት፡፡ እንዴ፤ ወዴት ወዴት? ያን ጊዜ ነው መዝሙር ያልሆኑ ዘፈኖችን ወይም ዘፈን ያልሆኑ መዝሙሮችን “ዘፈ-መዝሙር” ያልኳቸው፡፡
እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት፣ ማንኛውም ዜጋ እንደየ ሀይማኖቱ/እምነቱ የፈለገውን ተግባር በተገቢው ቦታና መስመር ሊያከናውን ይችላል፡፡ ይሁንና፣ ዘፈ-መዝሙሮችና በዘፋኞች የሚቀርቡ መዝሙሮች መብዛት በሰዋዊ ዘመቻው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ መውሰድ ይገባል፡፡ ሌላም ልበል፡- የተፈጥሮ ሳይንስንና ማህበራዊ ሳይንስን የማይንተራሱ የሙዚቃ ስራዎች (ዘፈ-መዝሙሮች) እየበዙ ከመጡ - ዘፋኞች ወደ ዘማሪነት መኮብለላቸው ብሎም ዘፈን እየተዳከመ መምጣቱ አይቀርም:: ሌሎችን አይቶ መሆን ይኖራል፡፡ አንዲት ዚምባቡዌያዊ የማህበረሰብ ጤና አስተማሪ አንድ ስልጠና ላይ የነገረችን ታሪክ ትዝ አለኝ:: “በርካታ እናቶችን ከአንድ ዛፍ ስር ሰብስቤ ስለ ጡት ማጥባት አስፈላጊነት፣ ስለ ድህረ ወሊድ ክትትል ሳስተምራቸው” አለች፤ ሴትየዋ “ሴቶቹ ያዳምጡኝ የነበሩት ጀርባቸው ላይ ያዘሏቸው ህፃናት እንዳያለቅሱ ወይም ከእንቅልፋቸው እንዳይነቁባቸው እሹሹሩሩ እንደ ማለት እየተወዛወዙ ነበር፡፡ ብዙዎቹ አንድ እጃቸውን ወደ ጀርባቸው ጣል አድርገውም ነበር፡፡ እና፤ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ሌጣዋ ሴትዮ ራሴን ቁጭ ያልኩበት ኩርሲ ላይ እንደነሱ እየተወዛወዝኩ አገኘሁት - ሌላ ቀርቶ አንድ እጄም ወደ ጀርባዬ ዞሮ ነበር፡፡” ለማለት የፈለኩትን አስተላለፌ ይሆን?  ከሙዚቃ አንጻር፣ የሳይንሱና የሀይማኖቱ ጎራ ድብልቅልቁ ወጥቷል፡፡ እንዲያውም ብዙ ደራሲያን የሚቀላቸው፣ ተጨባጭ የሆኑ ምክንያትና ውጤቶችን ማገናኘት ሳይሆን ከሀይማኖት መጽሐፍት የሆኑ ጥቅሶችን በመውሰድ ሀይማኖታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ለማስተማር መሞከር ነው፡፡ ይህ አካሄድ የሀይማኖት መሪዎችንም እንደማያስደስት ደርሼበታለሁ፡፡ “ዘፋኝ አርፎ ይዝፈን እንጂ ለምን ይዘምራል?” የሚል አስተያየት ያላቸው ይመስለኛል:: ስገምት - መተላለፊያ መንገዶቹ በግልጽ ስለሚታወቀው  ስለ ትራኮማ (የአይን ህመም) ግጥምና ዜማ አምጡ ቢባሉ የተወሰኑ ደራሲያን ዘፈመዝሙር ይዘው ብቅ ማለታቸው አይቀርም፡፡
ትንሽ ልጨምር፡- ድምዳሜዬ በጥናት የተደገፈ ባይሆንም፣ በአለፍ አገደም እንደሰማሁትና እንዳስተዋልኩት፣  አብዛኛው ለማለት ባልደፍር፣ እጅግ ብዙ ዜጎቻችን (አዲስ አበባም ሆነ በክልሎች የሚገኙት) ሰዋዊ/ሳይንሳዊውን ምላሽ እየተከተሉ የሚገኙት በሙሉ ልባቸው አይደለም፡፡ ጥናት ቢደረግ፣ በራሳቸው ጥረት ከቫይረሱ ለመዳን እንደሚችሉ ከሚያስቡ ሰዎች ቁጥር፣ በፈጣሪ ቸርነት እንተርፋለን ብለው “የሚያምኑ” ዜጎች ቁጥር ይበልጣል፡፡ በዚያ ላይ፣ “ኢትዮጵያችን ልዩ አገር ናት፣ ፈጣሪ ልዩ ጥበቃ ያደርግልናል ...” ብለው ሀሳባቸውን ጥለው የሚኖሩ፣ የመንግሥትን ምክር በአንድ ጆሯቸው ሰምተው በሌላው የሚያፈሱ፣ ሰዎች ብዛት የትየለሌ ነው:: ቀኑን ሙሉ፣ በመገናኛ ብዙሃን ሲሰሙ የዋሉትን ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ በአንድ “ከወደ እንትን ተሰማ ... እነ እገሌ አሉት” በሚባል ተስፋ ሰጪ የስሚ ስሚ ዜና ውድቅ ለማድረግ ዝግጁ የሆኑ ዜጎች በበዙበት አገር፣ ዘፋኞች መዝሙሩን ለዘማሪዎች ቢተዉ፣ ዘፈንና መዝሙርን በመደባለቅም መልዕክታቸውን ተጣራሽ እንዳያደርጉት ነው ማሳሰቢያዬ፡፡ ዘፋኝ መሆን ሀይማኖተኛ መሆንን ይከለክላል፤ አላልኩም አይደል?
ትናንትና ያጋጠመኝን ልንገራችሁና ልሰናበታችሁ፡፡ ሰፈሬ ውስጥ ከዝናም ተጠልዬ ከአንድ በሲባጎ ከተከለለች ሱቅ ታዛ ስር ቆሜ ሳለሁ፣ አንድ የሰፈሬ ሰው ወደኔ ሲመጣ አየሁትና “እዚያው በሩቁ - ርቀትህን ጠብቅ፤ ሰውዬ!” አልኩት፤ እጄን ወደሱ ዘርግቼ፡፡ “አንተ ደግሞ፣ ሞኝ የነገሩትን አይረሳም፤ እግዚአብሔር አገራችንን ምሯታል፤ ... ዜና አትከታተልም እንዴ? ... ምን አለ በለኝ፣ ከአሁን በኋላ ከኮሮና ጋር ብንቆይ፣ ብንቆይ ሁለት ወር ነው” አለኝ:: ለማንኛውም ራቅ እንዲለኝ እየተከላከልኩ፤ ቢሆንም ተፈላጊውን ጥንቃቄ ውሰድ አልኩት፡፡ እሱ ግን “አትጨናነቅ፤ ምናለ በለኝ፤ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የገባውን ቃል አይሽርም” አለኝ፤ በድጋሚ፡፡ በዚህ ሰዓት ከበሽተኞች ጋር ደፋ ቀና የሚሉ የህክምና ባለሙያዎች፣ የቫይረሱ መዘዝ የአገርን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ሳይጎዳ እንዲያልፍ በየሙያ ዘርፋቸው የሚባትሉ ባለሙያዎች .... ወታደሮች፣ ፖሊሶች ... በምናቤ ታዩኝ፡፡ ሰውየውን ማነጋገር አቁሜ ጫማዬ ላይ የሚያርፈውን የዝናብ እንጥፍጣፊ አጎንብሼ ሳስተውል፣ ከአንድ ሀያ አመት በፊት የሥራ ባልደረባዬ የነበረው አቶ አሰፋ በየነ የነገረኝ ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡ እንግዲህ ወደ ወለጋ ውስጥ የሆነ ነገር ነው፡፡ አንድ ተማሪ፣ ለአስራ ሁለተኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ዝግጅት እያደረገ እያለ ከአማርኛ መምህሩ ጋር ይጣላል፡፡ ሰውየው ናቸው ጥፋተኛ፤ “ስማ እንትና፣ አንተ የአማርኛ ውጤትህ ኤፍ (ዜሮ ማለት ነው) ነው የሚሆነው፤ ምን አለ በለኝ፤ ከምላሴ ላይ ፀጉር ይነቀል!” ብለው ያንኳስሱታል - ያውም በጓደኞቹ ፊት:: ልጁ፣ አስተማሪው ሊያበረታቱት ሲገባ ሞራል ሊሰብር የሚችል ነገር ስለተናገሩት ተበሳጨ:: ወራት አለፉና ማትሪክን ተፈተነ፡፡ የፈተናው ውጤትም ከእጁ ገባ፡፡ አስተማሪው እንደዚያ ሲያንኳስሱት የሰሙ ተማሪዎች ውጤቱን እንዲያሳያቸው ጠየቁት፡፡ ፈቃደኛ አልሆነም:: የውጤት ካርዱን ይዞ አስተማሪው ወዳሉበት ገሰገሰ፡፡ ይሄ ልጅ እኒህን ሰውዬ ጭንቅላታቸውን በድንጋይ በርቅሶ ወደ ገጠር ሊገባ ሳያስብ አይቀርም ብለው ሰጉ፤ ጓደኞቹ፡፡ “መምህር እገሌን አይታችኋል ...?” እያለ ብዙ ተማሪዎችንና አስተማሪዎች ሲጠይቅ፣ ሲያፈላልጋቸው ቆይቶ ሰውየውን አገኛቸው፤ “እ ... መምህር እገሌ ...” አላቸው፤ ካርዱን ገልጦ አይናቸው ስር እያስገባ:: “ይታይዎታል? እኔ ነኝ ኤፍ የማመጣው? እኔ የእንትና ልጅ ...? ህ?” እያለ ተውረገረገባቸው:: ሰውየው እጃቸውን ዘርግተው የጎረምሳውን እጅ ወደ ታች ካወረዱ በኋላ ካርዱን ተቀብለው ውጤቱን ተመልክተው ሲያበቁ፣ ራሳቸውን በአድናቆት ነቀነቁ፡፡ በዙሪያው ያሉ ተማሪዎች የሁለቱን ታሪክ ስለሚያውቁ፤ ሰውየው ራሳቸውን የነቀነቁት ወይ ሲ፣ ወይ ዲ አግኝቶ ቢሆን ነው ብለው እየገመቱ፣ ጎረምሳውንና አስተማሪያቸውን ከበቧቸው:: ጎረምሳው ቀጠለ፡ “ ... እ! ይታይዎታል - ኤ?” አላቸው:: ጓደኞቹ እንዲሰሙት ነው ጮክ ያለው፡፡ እሳቸውም መለሱ፤ “እኮ ... እኔ ኤፍ ታገኛለህ ባልልህ ኖሮ ኤፍ ማምጣትህ አይቀርም ነበር፤ እድሜ ለኔ በል!” አሉትና ከቅድሙ የበለጠ በንዴት አጦፉት፡፡ ወጣቱ የተናደደው በሁለቱም አቅጣጫ አሸናፊ ሊያደርጋቸው የሚያስችላቸውን መንገድ በመከተላቸው ነው፡፡ ኤፍ ቢያመጣ ኖሮ “እኮ! ብዬህ ነበር” ይሉታል፡፡ ኤ ሲያመጣ ሲያዩ ደግሞ “እኮ! እንደዚያ ባልልህ ኖሮ ወዳቂ ነበርክ!” ይሉታል፡፡ እና ... ቁና ተንፍሼ ካጎነበስኩበት ቀና ስል ሰውየው አጠገቤ የለም፡፡ ዝናሙም አባርቷል፡፡ ይህን እያሰብኩ ወደ ቤቴ አቀናሁ፡- እነዚህ አሁን እየተደረጉ ያሉ ሰዋዊ/ሳይንሳዊ ጥረቶችን የማያደንቁ፣ የማያግዙ ሰዎች በሆነ አጋጣሚ ወረርሽኙ ብዙ ጉዳት ሳያደርስ ቢያልፍ ምን ሊሉ እንደሚችሉ አዳጋች አይደለም፡፡ እነሱ ምንም ይበሉ ጥረቱና ጥንቃቄው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ አሁንም የጤና ባለሙያዎችን ምክርና መመሪያ በመተግበር የራሳችንንና የሌሎችን ህይወት እንታደግ፡፡


Read 2575 times