Tuesday, 12 May 2020 00:00

ተቃዋሚ ፓርቲዎች “የሽግግር መንግስት” ሃሳብ ተቀባይነት የለውም አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በአገሪቱ ኮቪድ -19 መከሰቱን ተከትሎ ምርጫው በመራዘሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው መራዘምና በመንግስት ቅቡልነት ዙሪያ የተለያዩ አቋም እያንፀባረቁ ሲሆን አብዛኞቹ “የሽግግር መንግስት” መቋቋም የሚለውን ሃሳብ ተቃውመውታል፡፡
“የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ምርጫ 2012 በኢትዮጵያ ፣ ፖለቲካዊ ቅርቃርና አማራጭ  የመውጫ መንገዶች” በሚል ርዕስ ባለ 11 ገጽ የመፍትሔ ሃሳቦች ሰነድ ያቀረበው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ  በህገ መንግስቱ ማዕቀፍ ስር ያሉ አማራጮችን ይዘረዝራል፡፡
ፓርቲው ፓርላማውን መበተን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚሉት አማራጮች በህገመንግስቱ ያሉ ቢሆንም፣ እነዚህ አማራጮች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ተንትኖ የሚገልፀው የፓርቲው ሰነድ፤ “መፍትሔው ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ነው” ሲል ከእነትንታኔዎቹ ያቀርባል፡፡
በዚህ የመፍትሔ ሃሳብ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፤ “የሽግግር ወይም ባለአደራ መንግስት የሚባለው ሃሳብ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ጥልቅ መተማመንና መግባባት ሳይኖር ሊመሰረት አይችልም”  አማራጭ ሃሳቡ፤ ለሀገሪቱ የችግር መውጫ ሳይሆን ተጨማሪ ችግር መፍጠሪያ ነው ሲል ፓርቲው ያጣጥለዋል፡፡
በተመሳሳይ የተብራራና ሁሉንም አማራጮች የፈተሸ የመፍትሔ ሃሳብ ሰነድ ያቀረበው ኢዜማ በበኩሉ፤ የሚቀርቡ መፍትሔዎች ከህገመንግስቱ ማዕቀፍ ያልወጡ፣ ሀገረ መንግስቱን የሚያስቀጥሉና ወደ ተረጋጋ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚያሸጋግሩ መሆን አለባቸው ብሏል፡፡
ኢዜማ በዚህ የመፍትሔ ሃሳብ ሰነዱ፤ በህገመንግስቱ ማዕቀፍ ስር ያሉ አማራጮችን ከእነ ደካማና ጠንካራ ጐናቸው የዘረዘረ ሲሆን፤ ከሁሉም የተሻለው ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ የሚለው ሃሳብ መሆኑን አስታውቋል፡፡
“ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ አሁን ሀገሪቱ ለገባችበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፤  ቀጣዩ ምርጫም ከ1 አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሊካሄድ ይገባል” ይላል - ኢዜማ፡፡
ከህገመንግስቱ ማዕቀፍ ውጪ ያሉ የሽግግር መንግስት ምስረታ ጥያቄዎች ተቀባይነት የሌላቸው፤ ሀገርን ለባሰ ትርምስና ብጥብጥ የሚዳርጉ መሆናቸውን በመግለፁ ኢዜማ ሃሳቡን ተቃውሞታል፡፡
ኢዜማም ሆነ ነፃነትንና እኩልነት ፓርቲ፤ በህገመንግስቱ አንቀጽ 58(1) ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ነው ሃሳብ ያቀረቡት፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ባቀረበው የመፍትሔ አማራጭ፤ “አሁን ባለው መንግስት የሚመራና የህግ የበላይነት የተከበረበት የሽግግር ሂደት እንጂ የሽግግር መንግስት የሚለው አማራጭ ተቀባይነት የለውም፤ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል” ብሏል፡፡
ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሽግግር ሂደቱን መምራቱ ከህዝባችን ሰላምና ደህንነት ሲታይ፤ ካሉት አማራጮች በአንፃራዊነት የተሻለ ነው ይላል - አብን፡፡
በዚህ መንግስት በሚመራው የሽግግር ወቅትም፣ የሀገርና የህዝብን ጥቅም ማዕከል ያደረገ ድርድርና የእርቅ ሂደት ማከናወን ያስፈልጋል ያለው ንቅናቄው፤ ህገ መንግስቱን ማሻሻል፣  የህዝብና ቤት ቆጠራ ማካሄድ ይገባል ሲል ለመንግስት የቤት ሥራ ይሰጣል፡፡
ሰባት ፓርቲዎች የተሰባሰቡበት “ትብብር ለህብረ ብሔር ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም” በበኩሉ፤ አሁን ከህገመንግስቱ መፍትሔ ማፍለቅ አያስፈልግም፤ ብቸኛ መፍትሔው ፖለቲካዊ ድርድርና ውይይት ማካሄድ ነው ብሏል፡፡
ኦነግ፣ ኦፌኮ፣ ኦብነግ፣ አረና እና ሌሎች የተካተቱበት የፓርቲዎች ትብብር፤ በገለልተኛ አካል ከሚደረገው ድርድርና ውይይት ከሚፈልቅ ሃሳብ በመነሳት ሀገሪቱ ምርጫ ሊካሄድ ይገባል ይላል፡፡
የሽግግር መንግስት ማቋቋም የማይቻል መሆኑን የጠቆመው ትብብሩ፤ አሁን ያለው መንግስት መዋቅሩን እንደያዘ የፖለቲካ ድርድርና ውይይት ማድረግ ግን አስፈላጊ መሆኑን ይገልፃል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመንግስትም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዋነኛ ትኩረት ኮቪድ 19ኝን መከላከል ላይ ሊሆን እንደሚገባ የገለፀው የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት በበኩሉ፤ ሁሉም ፓርቲዎች በሰከነና ኃላፊነት በሚሰማው አካሄድ ሀገሪቱን ለበለጠ ችግር የማይዳርግ መፍትሔ ላይ እንዲስማሙና በህገመንግስቱ ማዕቀፍ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ምክር ለግሷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ የሽግግር መንግስትም ሆነ ከህገመንግስቱ ውጪ ያሉ አካሄዶች ተቀባይነት የላቸውም፤ መንግስት ህጉን በሚጥሱ ላይ ህገመንግስቱን ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡


Read 3015 times