Sunday, 10 May 2020 00:00

አይባልም

Written by  አዛኤል ሽታሁን
Rate this item
(1 Vote)

 “...የመጣው ቢመጣ ቀኑ ቢጨልም
መገዛት ነው እንጂ ሞት አያስፈራም፡፡”
(የአርበኞች ግጥም)
መቼም በመሀይምነት አፍሪቃን ከማንም ጋር የማያወዳድሯት አውሮጳውያን፤ የነሱን ጨለማነት ለማውሳት ደግሞ በ1988 ዓ.ም የሞከሩት እንዲሁም በ1928 ዓ.ም የደገሙት ሽንፍት ማስረጃ ይሆነናል፡፡ የሰው የመኖር ህልውና በሌሎች የመኖር ህልውና ውስጥ መሆኑን የረሱ የነጭ አዚመኞች፤ ጥቁርን በመልኩ ምክንያት (ምክንያት ከሆነ ማለት ነው እንግዲህ) ብቻ ባሪያ ሊያደርጉት ዘመቱ፡፡
የነጮቹ ይሄንን ማሰብ ከህሊና መዘበራረቅ የመነጨ ይመስላል፡፡ ጌታ መሆን የሚፈልገው ባሪያ የነበረ ሰው ነው:: ታላቅ መሆንም የሻተ ሰው በተቃራኒው ታናሽነቱን ለመበቀል የታገለ መሆኑ ነው፡፡ ታላቅ ከነበርክ ታላቅ መሆንን አትሻም፡፡ ስለዚህ የበታችነትህን ለመገልበጥ ታላቅነትህን በምንም ነገር ውስጥ ማሳደድህ አይቀርም፡፡
በነገራችን ላይ ህመም ነውና፡፡
መሬት ስናወርደው......
አባት አለም ፀጋዬ ገብረ መድህን፣ በአርበኛው በፃድቁ በጳጳሱ አቡነ ጴጥሮስ የምናብ አንደበት ይሄንን ይለናል፡-
“....አውሮጳ እንደሁ ትናጋዋን በፋሺስታዊ
ነቀርሳ
ታርሳ ተምሳ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን እንደኮረብታ
ተጭኗት
ቀና ብላ እውነትን እንዳታይ አንገቷን
ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት ስልጡን ብኩን
መፃጉ ናት..”
ይህ የግጥም መስመር አምስት ነው:: አምስቱን ጣልያን የወረራ አምስቱን የኢትዮጵያ የስቃይ ዘመን በአምስት መስመር ስንኝ ያመሰጠረበት ይመስለኛል፡፡ ፀጋዬ የአውሮጳን ህሊና መዘባረቅ ውጥንቅትነት ሲገልፅ በአንድ ቃል አልቋጨውም፡፡
“....በፋሽስታዊ ነቀርሳ”  ብሎ ይጀምራል:: በማይድን ደዌ መያዟን፡፡ ያውም ፋሽስታዊ በሚባል ደዌ፡፡ ከዛም በዚህ ህመም ይህችው አህጉር “..ታርሳ ተምሳ በስብሳ...” ብሎ የሚዘገንነውን ስርአት፣ በዘግናኝ ፊደላት ያስቀምጠዋል፡፡ በመጨረሻ ይህ ህማም አዲስ በሽታዋ እንዳልሆነ “በምፃጉ” ምሰላ ይነግረናል፡፡
(በታላቁ መፅሐፍ እንደተቀመጠው፡- ምፃጉ ለ38 አመት በአልጋ የነበረ፡፡ ሰው እንኳ ሊጠጋው የማይችል፡፡ የሰውነቱ ሽታ ከሰው ሁሉ ያገለለው፡፡ የከረመ የታመመ:: በመጨረሻ በክርስቶስ የዳነ፡፡ የአልጋው ተሸካሚ የሆነ፡፡ የስቃይ ሰው ነበር፡፡)
በነገራችን ላይ ፀጋዬ ትሁት ገጣሚ መሆኑን የምናየው ይህ ሁሉ ነውር የሞላባን አውሮጳ “ስልጡን” ብሎ በመጥራቱ ነው፡፡ መሰልጠኗን ከእነ ነቀርሳዋ የታቀፈች የሀገር ስብስብ መሆኗን ያመነ ያመሰጠረ ፍትሀዊ ገጣሚ ነው፡፡
ደግሞስ ፀጋዬ አይደል፡፡
(እንዲያውም የነገሩን ውስብስብነት የተረዳው ባለቅኔው ፀጋዬ በቲያትሩም በጥናቱም በትምህርቱም የነጮቹን እብደት ታጥሎታል፡፡ ፓንአፍሪካኒስት በመሆንም ጡንቸኛውን ስርአት ሞግቶታል፡፡
በዚሁ ቅኝ ግዛት በሚሉት ግራ በገባው የነጭ ጣጣ ብዙዎች አልቀዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቅዱስ አባት ጴጥሮስም የዚህ ክፉ ሰይፍ ሰለባ ሆነዋል፡፡ የሞታቸው ክብር በልቡ የሚንቀለቀለው ፀጋዬ በርሳቸው ቦታ ሆኖ  “ጴጥሮስ ያቺን ሰአት” በማለት አብሯቸው አልቅሷል፡፡ ስለ ጎልማሳው አቡነ ጴጥሮስ ወጣቱ ፀጋዬ አንድ ለሊት ሙሉ ታመመ፡፡)
ሌላ መሬት ስናወርደው......
መሬትን ከእነ ሰው መውረስን ከማን እንደተማሩ ባናውቅም፣ ብቻ ካልወረስናችሁ ብለው በ1928 ዓ.ም ከተሙ፡፡ ሀበሻ ግራ ገባው፡፡ የመጣውን ጠላት እንዴት እንሸኘው? በሚል ጭንቅ፣ የጭንቅ ቀኑን ጀመረው፡፡ ንጉሱ ለአቤቱታ ሸሹ ...ሸሹ፡፡ የገቡበት ጠፋ፡፡ የሀበሻ ዘር ላይ ቀን ከዘመን ከፋ፡፡ ሹማምንት የማዕረግ ቀሚሳቸውን እየሰበሰቡ ወደ ቤታቸው ተሰበሰቡ፡፡ የቤተ መንግስት አውራዎች ሲወጡ ተራ በተራ የሀገር ልጆች መጡ፡፡
እነ ገረሱ ዱኪ፣ እነ በላይ ዘለቀ፣ እነ ራስ አበበ አረጋይ፣ እነ ኡመር ሰመትር፣ እነ ሸዋረገድ ገድሌ፣ እነ ደጃዝማች በቀለ ወያ፣ እነ ጃጋማ ኬሎ፣ እነ ገለታ ቆርቾ፣ እነ ሻለቃ መስፍን ስለሺ፣ እነ ብዙ ብዙ እልፍ አእላፍ ወጣቶች፣ ጎልማሶች በመፅሐፍና በስም ያልተፃፉ ግን ኢትዮጵያን በልባቸው የፃፉ፣ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለመሬቷ ክብር አለፉ፡፡
ለሰማይ ለምድር የከበደ እልቂት ሆነ፡፡ በእየሱስ መወለድ 3ሺ ህፃናትን በቀጠፈው ሄሮድስ ብንገረምም፣ ኢትዮጵያውያን ግን በሶስት ቀን ውስጥ ብቻ 30,000 ልጆቿን ገበረች፡፡ ስለ ምን ቢሉ? ጥያቄው ከመልሱ ስለማይመጣጠን እንለፈው፡፡ ብቻ የደም ዝናብ በሀገረ ጦቢያ ዘነበ፡፡ ቀደምት መከራን የሚያስመሰግን መከራ ሆነባት:: አይን እንባ ጨረሰ፡፡ ደረት መምታት እስኪደክም ደረቶች ከእነ ወኔያም ልባቸው በመንገድ ወደቁ፡፡ ፍትሀት ቀረ፡፡ ቀብር ቀረ፡፡ ለቅሶ ቀረ፡፡ ጭካኔ ከገደብ ያለፈበት፣ ጭካኔ በጭካኔ ያፈረበት፣ ነጭ ሁሉ መልኩን ብርሀን፤ ልቡን ጨለማ ያደረገበት ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ሰማይና ምድር እንደ ክርስቶስ የስቅለት ቀን፣ እንደ 9 ሰአቱ በቀን የጨለመበት፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ከእነ ታቦታቸው ከእነ ካህናታቸው የነደዱበት፡፡ መስጊዶች ከእነ ኢማሞቻው የተለኮሱበት፡፡ ይህ ሁሉ ስለ ምን ቢሉ? ጥያቄው ከመልሱ ስለማይመጣጠን እንለፈው፡፡ ብቻ የተማረ ሁሉ ከሚያውቀው ቁጥር በላይ በሆነ ቁጥር እልፎች የሞቱበት የቆሰሉበት የደሙበት----የኢትዮጵያ ፀሀይ የጠለቀበት ነው፡፡ ይህ አምስት አመት፡፡ ከድንግል ማርያም አምስቱ ሀዘናት ጋር የሚመሳጠር አምስት የኢትዮጵያ ሀዘን፡፡
ሲደመደም.....መጨረሻ የሌለው ደስታም ሀዘንም የለም እና መጨረሻው ደረሰ:: አቢሲንያ የገበረችው ደም ጎርፍ ሆኖ ጣልያንን ወሰደው፡፡ ይህ ቀን ሚያዝያ 27 ነው፡፡ ደም እያፈሰስን፣ ደም እየገበርን ተዋጋነው፡፡ ሰላም የነሳንን ሰላሙን ነሳነው:: የቅኝ ግዛት ሀሳቡን ሸለትነው፡፡ ሊገዛን መጥቶ ተገዝቶ ሄደ፡፡ ስለዚህ ይህ ቀን፣ ይህ ፀሀይ፣ ይህ ንጋት፣ ይህ ዕለት፣ የድል በዓል እንጂ የነፃነት በዓል አይባልም፡፡
“...የመጣው ቢመጣ ቀኑ ቢጨልም
መገዛት ነው እንጂ ሞት አያስፈራም፡፡”  (የአርበኞች ግጥም)
እንኳን ለድል በዓል አደረሰን!!!



Read 1625 times