Print this page
Monday, 11 May 2020 00:00

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

 ከልጅነት ተረቶቻችን አንዱን እናስታውስ፡-
‹‹አያ አንበሶ፤ ጤና ይስጥልኝ››… አለ… አያ ጅቦ፡፡
‹‹አብሮ ይስጥልን፡፡… ምን እግር ጣለህ?››
‹‹ዘጠኝ ልጆች አሉኝ፡፡ ሰፈር ለሰፈር ከሚያውደለድሉ አንዳንዴ እንኳ ካንተ ጋር አደን ውለው ቢመለሱ ብዬ ልለምንህ ነው››
‹‹ችግር የለም ላካቸው››  አለ አጅሬው… ነገር ለማሳጠር፡፡
‹‹ማለቴ… እ…››
‹‹አያ ጅቦ፤ ጨረሰን’ኮ››
አያ ጅቦ አመስግኖ ወደ ሰፈሩ ተመለሰ:: በማግስቱ ጎረምሶቹ ጅቦች መጥተው ከአያ አንበሶ ጋር አደን ወጡ፡፡ ዕድል ሆኖ ቀናቸውና አስር ከብቶች ማረኩ፡፡ አያ አንበሶም ዘጠኙን ለራሱ አስቀርቶ አንዷን ለነሱ ሰጣቸው። ሰፈራቸው ሲደርሱ አባታቸው ተደስቶ፡-  
‹‹ብራቮ! ቀናችሁ አይደል?›› አላቸውና ስለ ውሏቸው የሚያወሩትን ያዳምጥ ጀመር:: እነሱም እንዴት አያ አንበሶ፤ አስሩን ከብቶች ከእረኛ ላይ እንደነጠቀ ሲተርኩለት… አያ ጅቦ የሰማውን ለማረጋገጥ፡-
‹‹ስንት አላችሁ?›› በማለት ጠየቀ፡፡
‹‹አስር››
‹‹ሌሎቹ ምን ሆኑ? በላችኋቸው?››
‹‹አይ… አያ አንበሶ ወሰዳቸው››
‹‹ዘጠኙንም!››
‹‹አዎ፡፡… አባታቸውም ከተቀመጠበት ተነስቶ በንዴት እየጦፈ፤
‹‹እናንተ ጅሎች! እኩል መካፈል ነበረባችሁ፡፡ ይኸ ጥጋበኛ! እሱ ማን ስለሆነ ነው?›› በማለት እየፎከረ፣ ልጆቹንና ኮሳሳዋን ከብት ይዞ ወደ አያ አንበሶ ጎሬ ገሰገሰ፡፡ እንደደረሰም፡-
‹‹አያ አንበሶ›› ሲል ተጣራ - ጮክ ብሎ፡፡
ዝም፡፡
‹‹አያ አንበሶ አንተን’ኮ ነው፡፡… እኔ እምለው…›› ብሎ ሲጀምር፤ አያ አንበሶ ብቅ ብሎ ዓይኑን እያጉረጠረጠ…
‹‹አንተ ምትለው ምንድነው… ተናገር›› በማለት አፈጠጠ፡፡
አያ ጅቦም አይቶ በማያውቀው ባህሪ ደነገጠ፡፡ የአንበሳው ፊት ሲለዋወጥ በቆመበት ብርክ ያዘው፡፡
‹‹በል እንጂ ተናገር!››…. አያ ጅቦ ምላሱ ተሳስሮ፣ እየተንተባተበ እንዲህ አለ “…. ምን ይሆን?”
*   *   *   
‹‹አርባ ቢወለድ አርባ ነው ጉዱ
 የተባረከው ይበቃል አንዱ
ደጋ ወጥታችሁ ቆላ ውረዱ
 እሽ ካላችሁ ይለመን ወንዱ!!››
ወዳጄ፡- ያለፈው ማክሰኞ የአገራችን አርበኞች፣ ፋሽስት ኢጣሊያንን ከእናት ምድራቸው ያባረሩበትን፣ ባንዲራችን ተመልሶ የተውለበለበበትን 79ኛ ዓመት የነፃነት ቀን በዓል በያለንበት ርቀታችንን ጠብቀን ያከበርንበት ዕለት ነው፡፡… ሚያዝያ ሃያ ሰባት!!
ወዳጄ፡- ነፃነት የሌለው ሕዝብ በሌሎች ፈቃድ የሚያድር፣ በሌሎች ሳንባ የሚተነፍስ፣ ጥርጣሬና ፍርሃት የወረሰው፣ መንፈሱ የታሰረና አካሉ የተሽመደመደ ነው:: ነፃነት የሌለው ሕዝብ እንደ ዕቃ የሚሸጥና የሚለወጥ፣ ብርቱዎችን ለማገልገል ጎንበስ ቀና የሚል፣ ፍትህ የተነፈገ፣ ሰብዓዊ ክብሩን የተገፈፈ፣ በሕግና ሥርዓት የመተዳደር መብቱን ተነጥቆ በገዛ አገሩ ስደተኛ እንዲሆን የተፈረደበት ነው፡፡
ወዳጄ፡- ነፃነት ከሌለ ሰላም፣ ነፃነት ከሌለ ሳቅ፣ ነፃነት ከሌለ ዕውነት አይታሰብም:: ነፃነት ከሌለ ህሊና ይፈተናል፡፡ በዳኝነት ወንበር ተቀምጠህ እንኳ ለበደለኞች እንድታደላ ትገደዳለህ፡፡ ወገኖችህ እየተራቡ ወራሪዎች ሲያንዛርጡ፣ አገርህ እየመነመነች አገራቸው ከፍ ስትል እያየህ… ዝም አትልም:: አርበኞቻችን ‹እንቢ ላገሬ፣ እንቢ ለክብሬ!›› ብለው የዘመቱት፣ ‹ጥራኝ ዱሩ› ብለው ጫካ የገቡት ለዚህ ነው፡፡ ከነፃነት በላይ ምን አለ?
ወዳጄ፡- የነፃነት በዓል በመጣ ቁጥር፣ በስሙ የተሰየመውን የት/ቤቴንም ትዝታዎች አስታውሳለሁ፡፡ ጅማ ሚያዝያ ሃያ ሰባት ት/ቤትን!! ሚያዝያ ሃያ ሰባት ት/ቤት በጊዜው በብዙ ነገሮች የታወቀ ነበር፡፡ የእግር ኳስ ቡድን፣ የቴአትር ሙዚቃ ክበብ፣ እኔ የነበርኩበት የቦይ ስካውት ክለብ… ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ት/ቤቱ ታላላቅ የጠፈር ሳይንቲስቶችን፣ የህክምና ዶክተሮችን፣ አርቲስቶችን፣ የሕግ፣ የፋይናንስና ኢኮኖሚክስ፣ የግብርና ባለሙያዎችንና ኢንዱስትሪያሊቶችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ታዋቂ የአስተዳደር ሰዎችንና የጦር መኮንኖችን አፍርቷል… የአገር መሪዎችንም ጭምር!! በየዓመቱ የነፃነት ቀን በዓል ሲከበር በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች መካከል የመዝሙር ውድድር ይደረግ ነበር፡፡ የህንድ፣ የጣሊያንና የዓረብ ክልሶች ከሆኑት አብሮ አደግ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ሆነን፡-
‹‹ሚያዝያ ሃያ ሰባት ብርሃናችን ነሽ
ነፃነት በግርማ የተጎናፀፍሽ…››
እያልን ዘምረናል… ከነፃነት በላይ ምን አለ?
ሚያዝያ ሃያ ሰባትንና የነፃነትን ነገር የማስታውስበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ወዳጄ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ነው፡፡ ስብሃት የተወለደው ሚያዝያ 27/1928 ዓ.ም ሲሆን በሕይወት ቢቆይ ኖሮ ዘንድሮ የሰማንያ አራት ዓመት ልደቱን ያከብር ነበር:: አንዳንዴ፡-
‹‹የኔ ልደት የነፃነት በዓል ስለሆነ፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያከብሩታል›› እያለ ሲኩራራ ‹‹አቦ ‹አንጀባ› አታድርግብን!›› እያልን እንቀልድ ነበር - አፈሩ ይቅለለውና!!
ከስብሃት ጋር የነበረን ወዳጅነት… ከጓደኝነት የዘለለ ነው - ቤተሰባዊነት:: ሚስት ባገባሁበት ጊዜ በከተማው አስተዳደር የክብር መዝገብ ላይ የፈረሙት እሱና ዘነበ ወላ ናቸው። በሁለታችን መሃል ከሞላ ጎደል የአንድ ትውልድ ያህል የዕድሜ ልዩነት ቢኖርም፣ ጓደኝነታችን የነፍስ ነው፡፡ ስብሃት ከማን ጋር ምን እንደሚያወራ፣ ከማን ጋር ምን እንደሚያደርግ ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር፡፡ በንባብ ያዳበረው ጥልቅ ምሁራዊ ግንዛቤው፣ ቀልድ አዋቂነቱና አራዳነቱ አቻ አይገኝለትም፡፡ ጋሼ ስብሃት… እኔ እስከማውቀው ድረስ በባህሪው ፍጹም ደግና ርህሩህ ሰው ሲሆን አስገራሚ የማስታወስ ችሎታም ነበረው፡፡ በሕይወት እስካለሁ ልረሳቸው የማልችላቸውን ብዙ ድንቅ ነገሮች አጫውቶኛል፡፡ ጋሸ ስብሃት… እምጳ!!
ወዳጄ፡-  የድሮዎቹን ሊቃውንት እነከበደ ሚካኤልና ሃዲስ አለማየሁን ጨምሮ በበዓሉ፣ በፀጋዬና በሌሎችም ታላላቅ ሰዎች ደርሶ እንደ ታዘብነው፣ ከእኛ በእጅጉ የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች የምናነሳው፣ በበጎነታቸውና በላቀ ችሎታቸው ሳይሆን እንደኛው ‹ሰው› መሆናቸውን በምንዘነጋው ደካማ ጎናቸው (dark side) ወይም ተቀናቃኞችና ቅናተኞች በሚያወሩት ትርኪምርኪ ወሬ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ የዛሬ ሳምንት በሸገር ሬዲዮ የጨዋታ ፕሮግራም ስለ ደበበ ሰይፉ ማንነት ሲዘከር የሰማነው ልብ የሚሰብር እውነት “እንኳንም ያ ጊዜ አለፈ” ያሰኛል። ስብሃትም የወሬ አሯሯጨች ሰለባ ነበር - አልተሰበረም እንጂ፡፡
ወዳጄ፡- ሚያዝያ ሃያ ሰባትንና አርበኞቻችንን ስናስብ፣ ትምህርት ቤታችንንም ጓደኞቻችንንም ለማስታወስ አጋጣሚ አገኘን፡። በአንድ ድንጋይ ሶስት ወፍ፡፡…. የነፃነት ቀን ነዋ!!... ከነፃነት በላይ ምን አለ?
 *   *   *
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- አባት ጅብ ተበሳጭቶ ልጆቹንና ያመጧትን ከብት ይዞ እየፎከረ ወደ አያ አንበሶ ዘንድ ደረሰ ብለናል:: “እንዴት እንዲህ ይደረጋል” ብሎ እምቧ ከረዩ ለማለት፡፡
‹‹አያ አንበሶ፣ አያ አንበሶ!›› እያለ ተጣራ፡፡
ዝም፡፡
‹‹አያ አንበሶ፤ ምን ይዘጋሃል? እኔ እምለው…››
አያ አንበሶ አላስጨረሰውም፡፡ ከጐሬው ብቅ ብሎ…
‹‹ምን አባክነው ምትለው?›› በማለት እንዳፈጠጠበትም ተጨዋውተናል፡፡ የሚገባበት የጨነቀው ጅብም፡-
‹‹ተናገር እንጂ›› ሲባል
‹‹ማለት የፈለኩት…›› አለ እየተንቀጠቀጠ:: ‹‹…ማለቴ የመጣሁት ልጆቼ የማይገባቸውን ተቀብለው መምጣታቸው ስህተት በመሆኑ ይቅርታ ለመጠየቅና ያመጡትን ለመመለስ ነው›› አለ - አያ ጅቦ፡፡ አያ አንበሶ መልስ ሳይሰጠው ከብቲቱን ይዞ ወደ ጐሬው:: መንገኛውም ወደ ሰፈሩ ተግተለተለ ይባላል:: ፉከራ ሌላ መጋፈጥ ሌላ!
ወዳጄ፡- The man who does not wish to be merely one of the masses needs to cease to be easy on himself” በማለት የፃፈልንን ታስታውሳለህ?... ነፃነት በዋዛ አይገኝም፡፡ ሌላው ቢቀር አንተነትህን ትከፍላለህ፡፡
ሠላም!


Read 1316 times