Tuesday, 12 May 2020 00:00

ትውልድ የሚሻገር ደማቅ ታሪክ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)

አንዳንድ መጻሕፍት እንደ ተንቀሳቃሽ ምስል (ፊልም) በምናብ ዘልቀው ስሜት የመፍጠር ኃይላቸው ብርቱ ነው፡፡ በይድረስ ይድረስ፣ በቃላት ታጭቀው ለአንባቢ የቀረቡ መናኛ ትርክቶች አይደሉም:: የብ/ጄነራል ተስፋዬ ሃብተማርያም ግለ ታሪክ  የሆነው “የጦር ሜዳ ውሎ” መጽሐፍ፣ ለአባባሉ እማኝ መሆን ይችላል:: ምንም እንኳን፤ መጽሐፉ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕትመት ብርሃን የበቃው፣ በ1997 ዓ.ም ቢሆንም፤ ሁሌም እየተገለጠ  ቢነበብ፣ እንደ አዲስ ስሜት የመፍጠር አቅሙ የማይደክም፣ የታሪክ ዝክር ነው፡፡
ድርሳኑ፣ የአንባቢን ትኩረት መሳብ የሚጀምረው ገና በልባሱ ነው፡፡ በሽፋኑ ላይ የታተመው ምስል፣ በውስጡ አዛንቆ ለያዘው ታሪክ፣ በልክ የተሰፋ ነው፡፡ ደልዳላ የወንድ ቁንጮ የመሰለ መለዮ ለባሽ፣ ከትግል አጋሩ ጋር በድል አድራጊነት ስሜት፣ ፈገግታውን ለአወድ ርዕይ አቅርቧል፡፡ ሕያው የሆነው ምስል፣ ወደ ውስጥ ዘልቀን ከታሪኩ ማጀት እንድንቋደስ ያማልለናል፡፡ ይኽንን ግብዣ ቸል ብሎ ማለፍ ሀሞትን ይጠይቃል፡፡
ድርሳኑ ለእናት ሀገር ጦቢያ ከልክ በላይ የተከፈለ መስዋአትነትን ያትታል:: በባለታሪኩ ውስጥ ጥልቅ የሀገር ፍቅር፣ ወደር የሌለው ጀግንነትንና የተራቀቀ የጦር ሜዳን ዕውቀትን በውል እንገነዘባለን፡፡ ጦቢያ ጀግና ለማፍራት ማሕጸነ ለምለም እንደሆነች፣ የባለታሪኩ አስደናቂ ገድል ምስክር ነው፡፡
ብ/ጄነራሉ ወታደራዊ ማእረጋቸውን የተጎናጸፉት፤ ልክ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በገሀድ ሲሰራበት እንደኖረው የዘውጌ መሥፈሪያ አልነበረም፤ “ላብ ደምን ያድናል” በሚል ቆፍጠን ባለ ወታደራዊ መርህ መሠረት ጋራ ቧጠው፣ አለት ተንተርሰው፣ ለእናት ሀገራቸው በከፈሉት ወደር የሌለው መስዋዕትነት ነው፡፡
እኚህ ጀግና ግን ተጋድሏቸውን የሚመጥን ቋሚ መዘክር በስማቸው አልተቀመጠም፡፡ “ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚለው ብሂል፣ አመድ አፋሹን ጀግና በትክክል ይገልጻቸዋል፡፡ ረብ ያለው ታሪክ ያልሰሩ፤ ከሰፈራቸው የተሻገረ ርዕይ የሌላቸው፤ ሀገራቸውንና ወገናቸውን ከባእድ ኃይል ጋር ሆነው ሲወጉ የነበሩ ባንዳዎች እንኳን ያልተገባ ክብር ሲሰጣቸው ታዝበናል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ ትኩረቴን ከሳቡት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ጥቂቱን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከውድቀት የመታደግ  ገድል
የሀገር ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ተቋማዊ ስኬት እስካለንበት ዘመን ድረስ እንዲዘልቅ፤ በንጉሡ ዘመን የተቋቋመው የበረራ ደህንነት መሥሪያ ቤት ድርሻው የላቀ ነበር፡፡ በዚህ መሥሪያ ቤት ውስጥ ደግሞ የባለታሪኩ  የመሪነት ሚና ትልቅ እንደነበር ከድርሳኑ እንረዳለን፡፡  
የንጉሡን አገዛዝ የሚቃወሙት ቡድኖች ኃይላቸውን አስተባብረው፣ የጥፋት በትራቸውን የሚያሳርፉት በአየር መንገዱ ላይ በመሆኑ የተነሳ ተቋሙ እየተሽመደመደ እንደሄደ፣ በገጽ 53 ላይ እንዲህ ተጠቅሷል፡-
“በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ተቃዋሚ ቡድኖች የወሰዱት እርምጃና ያደረሱት ጉዳት በዓለም ዜና ማሰራጫ በዓለም በሙሉ ተናኘ፡፡ ዜናውን የሰሙ ሁሉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ መብረር ለሕይወት አስጊ ነው የሚል ሰበብ እየፈጠሩ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ መገልገል እስከ ማቆም ደረሱ፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጠቀም ቢኖር አማራጭ ያጣ ሰው ወይም በሕይወቱ ላይ የሞት ፍርድ የፈረደ ብቻ ነበር፡፡ --”
በብ/ጄነራል ተስፋዬ ሃብተማርያም የሚመራው፣ የበራራ ደህንነት ከተቋቋመ በኋላ፤ አየር መንገዱ ላይ ይደረስ የነበረው የጠለፋ ሥጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሄደ፡፡ በዚህም ምክንያት፤ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ፣ በአየር መንገዱ ላይ ያለው እምነት  እየተጠናከረ በመምጣቱ፣ ተዳክሞ የነበረው ተቋም ዳግም ሊያንሰራራ ችሏል፡፡ ይኽንን ለሀገር ትልቅ ውለታ የሠራን ተቋም፣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ፣ ገና የሥልጣን መንበሩን በቅጡ እንኳን ሳያሟሽ ነበር ያፈረሰው፡፡
ናቅፋን ላይ የተሠራው ታሪክ
ባለ ታሪኩ ከሁሉም ግዳጅ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡት፣ ተፈጥሮ እንደ ወታደር በሚዋጋበት፣ ናቅፋ ተብሎ በሚጠራው የኤርትራ ተራራማ ሥፍራ አካባቢ ነበር:: ጊዜው 1969 ዓ.ም ሲሆን ናቅፋ ላይ በሻብእያ ቀለበት ውስጥ የገባውን 15ኛ ሻለቃን ለማዳን ብቸኛው ተስፋ፣ በብ/ጄነራሉ የሚመራው የአየር ወለድ ሠራዊት ነበር፡፡ ሠራዊቱ፣ በጠላት በተከበበው ወረዳ መሀል ከ300 እስከ 600 ሜትር ከፍታ ወሰን ውስጥ ከአውሮጵላን ላይ በመዝለል፣ ፈጣን የማጥቃት ውጊያ መክፈት ይጠበቅበታል፡፡
ግዳጁን ከምንም በላይ ከባድ ያደረገው ግን፤ ጠላት በዚህ  ከፍታ ላይ የሚበርን አውሮጵላን ከመሬት የሚደባልቅ የአየር መቃወሚያ መታጠቁ ነበር፡፡ የአየር መቃወሚያው እስከ 2500 ሜትር ድረስ ባለው ወሰን ውስጥ የስኬታማ አቅም አለው:: በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ የጦርነት ከባቢ ውስጥ፣ እንኳን ለመፈጸም፣ ለማሰብ የሚያዳግትን ሀገራዊ ግዳጅን ከግቡ ለማድረስ፣ ባለ ታሪኩ ግንባራቸውን አላጠፉም፡፡ ከዚህ ቀደም በአየር ወለድ ታሪክ ውስጥ ተሞክሮ የማያውቅን፣ ከ3000 ሜትር ከፍታ ላይ የመዝለል ገድልን፣ የሚመሩት የጀግኖች ስብስብ መፈጸም ችሏል፡፡ ይኽም ሰራዊት፣ በወረደበት ቀጠና ግዛቱን እያሰፋ፣ ከሻብእያ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ፣ 15ኛ ሻለቃን በመታደግ፣ ትንግርታዊ ድልን ለማስመዝገብ ችሏል፡፡
የደርግ መሠረታዊ ድክመት
ባለ ታሪኩ ከግለ ታሪካቸው ጎን ለጎን፣ የደርግን ተቋማዊ ድክመት፣ ጠቆም እያደረጉ ያልፋሉ፡፡ ደርግ ከጦር ሜዳ ትግል ይልቅ፤ በሌሎች ጥቃቅን እንከኖች ምክንያት እየተሰነካከለ፣ በርካታ እድሎች ከእጁ ሲያመልጡት እንደነበር ድርሳኑ ይነግረናል:: ለአብነት፣ አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ቁርጠኛ ባለመሆን የተነሳ፣ ጠላት ትንፋሽ ሰብስቦ መልሶ የተደራጀባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ በዚህም ተጠቃሽ የሚሆነው  ዘመቻ ባሕረ ነጋሽ  ነበር፡፡ ደርግ፣ በዘመቻ ባሕረ ነጋሽ፣ የሻብእያን እስትንፋስ እስከ ወዲያኛው ቀጥ የሚያደርግበት ዕድል በእጁ ቢገባም፤ ድሉ በፈጠረበት ጊዜያዊ እርካታ ምክንያት፣ ጠላት መልሶ አንገቱ ቀና ማድረግ ችሏል፡፡
ለዚህም መጽሐፉ እማኝነቱን እንዲህ ይሰጣል፡-
ውጊያው እስከ ነሐሴ 24 ቀን 1977 ዓ.ም ድረስ ቀጥሎ ሐይኮታን፣ ተስነይና አሊጊደርን፤ ስብደራትንና ጋሎጅን በአጠቃላይ የጋሽና ሰቲት አውራጃ ከተሞችና ሰፋፊ እርሻዎች በሙሉ በወገን ቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡ ሻብዕያ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ስለደረሰበት፤ ከዕዝና ቁጥጥር ውጭ ሆነ፤ የውጊያ መንፈሱ ተዳክሞ፣ እግሩ ወዳመራው አቅጣጫ እረኛ እንደሌለው መንጋ ተበታተነ፡፡ የማሳደድ ውጊያው እንደቀጠለ፤ በፍጥነት ጦር ወደ ናቅፋ ተልኮ ቢሆን ኖሮ፣ የናቅፋን ከተማ ያለ ምንም መስዋእትነት መቆጣጠር ይቻል እንደነበር በቦታው ላይ ይከላከሉ የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ እኛ ባገኘነው ድል እየተኩራራን፣ ከበሮ እየደለቅን ስንጨፍር፣ ጠላት የተበተነውን ጦሩን ሰብስቦ መልሶ እንዲቋቋም ዕድል ሰጠው፡፡   
መጽሐፉ ሌላ የሚያጋራን  ቁምነገር፣ ከወታደራዊ ዲሲፕሊን መጓደል ጋር ተያይዞ ይፈጠር ስለነበረው ምስቅልቅል ነው፡፡   ከተራው እስከ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን በመሸታ  ቤት ሞቅታ፣ እንደ ዋዛ የሚነዛው እጅግ አስፈላጊ መረጃ፣ ለጠላት ሲሳይ የተዳረጉበት አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው:: ለሻብእያ የሚሰልሉ የውስጥ አርበኞች ሥፍር ቁጥር አልነበራቸውም፡፡ እነዚህ የውስጥ አርበኞች በሚያሳልፉት ወታደራዊ መረጃ መሠረት፣ በብዙ የጦር አውድ፣ ደርግ ድል እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል፡፡
መጽሐፉ የዘነጋቸው ታሪኮች
ብ/ጄነራል ተስፋዬ ከዓመት በፊት፣ ከኢሳት ጋር ያደረጉትን ረጅም ቃለ መጠይቅ መለስ ብለን ከተመለከትን፣ መጽሐፉ ውስጥ መካተት የሚገባቸው ሌሎች የሚያጓጉ ታሪኮች እንዳሏቸው ለመገንዘብ አያዳግተንም፡፡ ኢትዮጵያ በኤርትራ በተወረረችበት ወቅት፣ የቀድሞ ሰራዊትን ብቻ ያካተተውን 10ኛ ክፍለ ጦርን እየመሩ፣ በዛላምባሳ በኩል የሻብእያን ምሽግ በመስበር ትልቅ ገድል ፈጽመዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከሱዳን ጋር በነበረው የውክልና ጦርነት፣ የሱዳን ነጻ አውጪ ግንባርን በማቋቋም ትጥቅና ሥልጠና የሚሰጥበትን ሂደት በበላይነት አስተባብረዋል፡፡ የውክልና ጦርነቱ ሱዳንን ውሎ አድሮ ሁለት ሀገር አድርጓታል:: ሱዳን አሁን ላለችበት የተገደበ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽእኖ የጄነራሉ እጅ ትልቅ ነበር፡፡ እነዚህና መሰል ታሪኮች በቀጣይ እትም ላይ መካተት ቢችሉ መጽሐፉን የበለጠ ምልኡ  ያደርጉታል፡፡
ማሰሪያ ነጥብ
መጽሐፉ በተዘዋዋሪም ቢሆን፤ የሚያጋራን ቁምነገር፣ በአስራ ሰባት ዓመታት ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ደርግ ለሕወሓት ካለው ሥር የሰደደ ንቀት  የተነሳ፣ ያለ የሌለ ኃይሉን ያከማቸው በኤርትራ ክፍለ ሀገር እንደነበረ ነው::
ምናልባትም፤ ከሻብእያ ጋር የነበረው ጦርነት፣ በሰላም ድርደር መቋጫ ቢያገኝ ኖሮ፣ ሕወሓት ለወራት የሚያሰነብት ወታደራዊ  አቅም ሊኖረው እንደማይችል፤ ከዚህ ቀደም ለሕትመት በበቁ ድርሳናት መረዳት እንችላለን፡፡ “የጦር ሜዳ ውሎም” መጽሐፍም፣ የሚያጠናክርልን ይሄንኑ ሐቅ ነው፡፡
በአጠቃላይ የጦር ሜዳን ገድል መጻሕፍት ማንበብ ፋይዳው፣ በታሪኩ ብቻ ተደምሞ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የባለ ታሪኮችን አስደናቂ መስዋእትነት ወደ ራሳችን ሕይወት በማምጣት ትልቅ የመንፈስ ከፍታን መፍጠር እንችላለን፡፡ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለማለፍ የማይበገር ሥነ ልቦናን እንድንታጠቅ ይረዳናል፡፡

Read 1493 times