Saturday, 09 May 2020 13:45

የአውስትራሊያው ኢትዮ-ጃዝ ባንድ ከዶ/ር ሙላቱ ጋር ሁለተኛውን አልበም አወጡ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ታዋቂው የኢትዮ-ጃዝ ባንድ ‹‹ዘ ብላክ ጂሰስ ኤክስፒሪያንስ›› ከዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ ጋር የሰሩትን ሁለተኛ እና አዲስ አልበም “To Know without knowing” ለዓለም ገበያ አስተዋውቀዋል፡፡ በ2016 እኤአ ላይ ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ እና “ዘ ብላክ ጂሰስ ኤክስፒራያንስ The Cradle of humanity የሚለውን የመጀመርያ አልበማቸውን አቅርበዋል፡፡
“To Know without knowing” ከ1 ዓመት በፊት በአውስትራሊያ ገበያ ሲቀርብ ከ3 ሳምንት በፊት ደግሞ በይፋ የተዋወቀው በጀርመን አገር ነው፡፡ የአልበሙ ቅጂዎች በሜልቦርንና በአዲስ አበባ መከናወናቸው ሲታወቅ፤ በዓለም ገበያ  ለማስተዋወወቅ የተሰራጨው ነጠላ ዜማ ‹‹ኩሉን ማንኳለሽ› ነው፡፡ “To Know without knowing”ን በዓለም ገበያ በስፋት  ለማሰራጨት የነበረውን እቅድ የኮሮና ወረርሽኝ  እንዳስተጓጎለው፤ በኒውዝላንድ እና በኢትዮጵያ የነበሯቸውንም ኮንሰርቶች እንዳሰረዛቸው የተናገረው የባንዱ አባል ኢያን ዲክሰን ከአውስትራሊያ ነው፡፡ በኢትዮ ጃዝ ባንዱ ትራምፔት የሚጫወተው፤ የሙዚቃ ፕሮዲውሰር እና ማናጀር የሆነው ኢያን ዲክሰን  ዶክተር ሙላቱ እና ዘ ብላክ ጄሱስ ኤክስፕሪያንስ የፈጠሩት ጥምረት የአፍሪካ እና የኦሽኒያ የባህል ትስስርን አጠናክሮታል፡፡  ከ2009 እኤአ አንስቶ የኢትዮ ጃዝ ባንዱ እና ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ የሰሩ ሲሆን በመላው አውስትራሊያ እና በተለያዩየዓለም ክፍሎች  ኮንሰርቶችን ሰርተዋል፡፡
‹‹ዘ ብላክ ጂሰስ ኤክስፒሪያንስ›› The Black Jesus Experience BJX በሚል ምህፃረ ቃል የሚታወቅ ሲሆን ተቀማጭነቱን በሜልቦርን፣ ቪክቶሪያ አውስትራሊያ ውስጥ ያደረገ  ነው፡፡ የ15 ዓመታት ልምድ ያለው የኢትዮ ጃዝ ባንዱ ከ5 የተለያየ አገራት ዜግነት ያላቸው 8 ድምፃዊያንና የሙዚቃ መሣሪያ ተጨዋቾች ተሰባስበውበታል፡፡  የኢትዮጵያን ባህላዊ የዜማ ቅኝቶች ከሂፕሆፕ፤ ከፋንክ ጋር በማዋሃድ የሚሰሩ ሲሆን በጃዝ እና አዝማሪ ስልቶችም ይጫወታሉ፡፡
በአውስትራሊያ ተመስርቶ በኢትዮ ጃዝ ባንድነት ያለፉትን 15 ዓመታት የሰራው ባንዱ  በሂፕሆፕ/ጃዝ፣ አዝማሪ እና ፋንክ የሙዚቃ ስልቶች ይታወቃል፡፡  ብላክ ጄሱስ ኤክስፒሪያንስ በኢትዮ ጃዝ ከክቡር ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ ጋር ያለፉትን 11 ዓመታት በመስራት ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ሲሆን የኢትዮ ጃዝ አባት በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓ፤ በኢትዮጰያና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ባቀረባቸው በሚያቀርባቸው ኮንሰርቶች የሚያጅቡት ናቸው፡፡
ብላክ ጂሰስ ኤክስፒሪያንስ ከክቡር ዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ ጋር ሁለተኛውን አልበም መስራታቸው ሲሆን የመጀመርያው በ2016 እ.ኤ.አ ላይ ለዓለም ገበያ የቀረበው “Cradle of Humanity”  ነው፡፡ በኢትዮ ጃዝ ባንዱ በመሪ ድምፃዊነት የምትታወቀው ኢትዮጵያዊቷ እንሹ ታዬ ናት፡፡ ሌላው ድምፃዊና መድረክ መሪ ሚር ሞንክ ይባላል፡፡ ሌሎች የባንዱ አባላት ቦብ ቬደርፔን (ፒያኖና ኪቦርድ)፣ ፒተር ሃርፐር (ቴነስ ሳክስፎን)፣ ጀምስ ዴሲስ (ይአም) አያን ዲክሰን (ትራምፔት)፣ ሃክሊስተር (ጊታር) እንዲሁም ሪቻርድ ኖህ (በኤሌክትሪክ ሌዝ ጊታር) ናቸው፡፡  


Read 1498 times